የአዲስ አበባ ልሂቃን ፓርቲ አንድነት ለመድረክ የስጋት ምንጭ ??


የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ(በግሌ የማከብራቸው ፓለቲከኛ) ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በወጣው አዲስ 
ታይምስ መጽሄት ላይ አንድ ምክር አዘል ጽሁፍ አስነብበው ነበር፡፡” በቅን ልቦና ለአንድነትና ለመድረክ” በላኩት በዚህ መልእክታቸው (እኔም በቅን ልቦና እንደሆነ አምናለሁ) ያቀረቡዋቸው ዋና ዋና ቅሬታዎች የሚከተሉት ሲሆኑ ገና ንባቡን ሳልጨርስ ውዝግብ እንደሚያስነሳ ታውቆኝ(ምናልባትም የአቶ አስራት ጣሴ የሰላ ምላሽ) ነበር፡፡

1. አንድነት መድረክ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ከፍ ብሎ ለመታየት የሚፈልግ ይመስላል፡፡ ይህ ለመድረክ ህልውና ጥሩ አይደለም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የአንድነት “ፍኖተ ነጻነት” ህትመት የመድረክ ትሁን ብዬ ነበር አልሆነም፣ አንድነት የሚጠራቸውንም አንዳንድ ህዝባዊ ስብሰባዎች በመድረክ ስም ይሁኑ ተብሎ ነበር አልተሳካም፡፡
2. አንድነት ዶ/ር ነጋሶን በመሪነት ቢመርጥም” የአማራ ፓርቲ ወይም የአዲስ አበባ ልሂቃን ፓርቲ “መሆኑን መካድ አያስፈልግም፡፡አዝማሚያው ግን መድረክ ውስጥ ባሉት በደቡቦች በአማራና በኦሮሞ ላይ የበላይነትን ማሳየት ነው፡፡
3.ከውጪ የሚመጣው የፓርቲዎች ማጠናከሪያ ገንዘብ መሰረቱ የከተማ ልሂቃን ላይ በመሆኑ አንድነት የተሻለ የደጋፊዎች ገቢ አለው፡፡ ነገር ግን ገንዘቡ ለዋናው ድርጅት መድረክ ነው መላክ ያለበት

በወቅቱ እነዚህን ክሶች ሳነብ አቶ ቡልቻን መጠየቅ የምፈልጋቸው እና ለጠቀሱት ችግር መፍትሄ ይሆናል ብዬ የማስባቸው ነገሮች ነበሩኝ፡፡

አንድነት ከመድረክ ፓርቲዎች ይልቅ በንጽጽር ጠንካራ ነው፡፡ ይህ ጥንካሬው የመድረክ የስጋት ምንጭ ሊሆን አይገባም፡፡ ይልቅስ ሌሎች ፓርቲዎች ራሳቸውን ለማጠናከርና አቅማቸውን ለመጨመር ጥረት ማረጋቸው መድረክን ያግዘዋል፡፡ የአነድነትን ወደላይ መውጣት ከመተቸት ይልቅ ሌሎች ፓርዎች ከፍ የሚሉበትን መፍትሄ መፈለግ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡(አቶ ቡልቻ ህወሃትንና ሌሎች ፓርቲዎችን ግንኙነት እንደምሳሌ ቢያነሱም የኢህአዴግንና የመድረክን አፈጣጠር ልዩነት የዘነጉት ይመስለኛል፡፡ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ምስረታ ከህውሃት በጦርነት ማሸነፍና ህብረብሄራዊነት አስገዳጅነት ተከትሎ ሲሆን ህወሃት የፓርቲዎቹ ፈጣሪ ነበር ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ይህም የፓርቲውን የበላይ የመሆን እድል አስፍቶታል፡፡ በመድረክ ጉዳይ ግን አባል ፓርቲዎቹ(የተለየ ጥረት ያደረጉ ሊኖሩ ቢችሉም) የየራሳቸውን ማንነት ይዘው ለረጅም ጊዜ የቆዬ በመሆናቸው የህወሃት አይነት የበላይነት ሊፈጠር ይችላል የሚለውን ስጋት አልጋራም፡፡ ከልምድም እንደምናውቀው ቢያንስ ቢያንስ ራስን በመገንጠል ወይም በማፍረስ ይገላገላሉ እንጂ!)

አንድነትን የህትመት ውጤትና ገቢን በተመለከተ ፓርቲዎች መድረክ ውስጥ ተነጋግረው በጋራ የደረሱበት ነገር ከሌለ በስተቀር መድረክ ተመሳሳይ ስራዎችን(የህትመት ውጤቶች እንዲኖረው ና ገቢ ማሰባሰቡ ላይ እንዲጠነክር )እንዲሰራ ማድረግ ነው እንጂ በአንድነትን ስራዎች ወደመድረክ አለመምጣት ቅር መሰኘት የዋህነት መስሎኝም ነበር፡፡ ከሁሉ በላይ ግን የአማራ ፓርቲነቱ ጠንካራ ክስ የአንድነት ሰዎችን ቢያስቆጣ አልገረምም፡፡ ብርቱካን ሚደቅሳን የመሰረተችውን፣ ዶ/ር ነጋሶ የሚመሩትን አቶ ዘለቀ ረዲና አቶ ሃይሉ አርአያ …..አመራር የሆኑበት ፓርቲ ላይ ይህንን አይነት ጠንካራ ክስ ማቅረባቸው አስደንግጦኛል፡፡እውነቱን ለመናገር አቶ ቡልቻ አንዲህ አይነት ማስረጃ ለማቅረብ የሚያስቸግሩ አስተያየቶችንም ባይሰጡም ደስ ይለኝ ነበር፡፡

ጽሁፋቸውን ተከትሎ የሚመጣውን ቁጣ ስጠባበቅ አቶ ዘለቀ ረዲ ከፍተኛ የአንድነት አመራር በእሮብ የሰንደቅ እትም “የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ምክር መሰል ለአንድነት የተጻፈ ደብዳቤ የኢህአዴግ የአፍራሽነት ተልእኮ ወይስ………”(በአንዴ አቶ ቡልቻን የኢህአዴግ ተላላኪ አድርገዋቸው እርፍ) የሚል እንደተለመደው የተቃዋሚዎች የውይይት ባህልን የሚያስተዛዝብ ጽሁፍ ይዘው ቀረቡ፡፡ አቶ ዘለቀ በጽሁፋው ሁለት ጉዳዮች ላይ(ፍኖተ ነጻነት ጋዜጣ እና የአንድነት ፓርቲ ማንነት) መልስ ለመስጠት ቢሞክም አቶ ቡልቻን በቅንነት ለማረም ከመሞከር ይልቅ የግል ዘለፋ የተሞላበት ጽሁፍ መጻፍ መርጠዋል፡፡
(ከነዚህም ዘለፋዎች መካከል “አንድነት በተለያዩ የህትመት ውጤቶች ህዝቡን ለማግኘት ሲሞክር እርሶ ግን ያቋቋሙት ለትርፎ የሚሆን ባንክ ነው” “የአንድነት አባላትና አመራሮች ለትርፋቸው የሚሆን ዳጎስ ያለ ሼር የሚያስገኝ ባንክ ከማቋቋም ይልቅ ህዝባቸው የሚተነፍስበት ጋዜጣ ነው ያቋቋሙ”፣”ግለኝነት ስለሚያጠቃዎት”፣ “አንድነትን በተንሸዋረረ አይን ያዩ ስለነበር”፣”ከመጠምጠም መማር ይቅደም” ፣ “ኦሮሞ ለመሆን እርሶ የተወለዱበት ቦታ መወለድ ግድ ነው ወይ”፣ “እርሶ ባይኖሩ ኖሮ ለዚህች ሃገር ማን ያስብላት ነበር”)

የአቶ ዘለቀ መልስ(የግሌ ብቻ ነው ብለው በማሳወቃቸው እግዜር ይስጣቸውና) የአንድነትን የአማራ ፓርቲ አለመሆን ለማሳየት የፓርቲውን ስራ አስፈጻሚ አወቃቀር(2 ኦሮሞ፣2 ትግሬ፣2 አማራ፣ 4 ደቡብ) እና የፓርቲውን የክልል አወቃቀር በመልካም መረጃ አስደግፈው ቢያቀርቡም (በተጨማሪም የአንድነትን የህትመት አይነቶችን የማብዛት ጥረት ጠቅሰዋል) ጽሁፋቸው ከዘለፋ ጋር መቀላቀሉ የተለመደውን የበሰለ ቅንነት ያለበት እና መማማር ላይ መሰረት ያደረገ ንግግር ማጣት እንድንናፍቅ ያደርገናል፡፡የጽሁፉ ርእስ ራሱ የተለመደውን የፍረጃ ባህል ያሳየ ነው፡፡

ሰዎች በአንድም ሆነ በሌላ መረጃ ስህተት ስለእኛ አስተያየት ሲሰጡ ሊሳሳቱ ይችላሉ፡፡ በተለይ በተለያየ መልኩ የፓለቲካና የስራ ልምድ ያላቸው ሰዎች ሲሆኑ ለጋራ አላማ የሚጥሩ ሲሆን ደሞ ይበልጥ መደማመጥና በጥንቃቄ መነጋገርን ይጠይቃል፡፡አቶ ዘለቀ መልስ ለመስጠት መሞከራቸውና ኦፌዴንንና አቶ ቡልቻን ራሳቸውንና አንድነትን አለመቀላቀላቸው ጥሩ ቢሆንም የመልሳቸው ትህትና ማጣትና(arrogancy) ከዘለፋ ጋር መቀላቀል ዛሬም ውይይትን በሃሳብ ደረጃ እንኳን ለመጀመር አለመሞከራችንን አሳይቶኛል፡፡

እስቲ ንገሩኝ ወዳጆች ቅንነትን፣ ውይይትንና መከባበርን ወደ ፓለቲካችን የሚያመጣ መድሃኒት ከየት እናግኝ?

Soliyana