ታላቅ መልዕክት! አላህ ሆይ፤ ተበድለናል እርዳን! ተበድለናል እርዳን! አላሁ አክበር!››

የጁምዓ  ጦማር ታላቅ መልዕክት!

‹‹አላህ ሆይ፤ ለ አንተ ዲን እስከመጨረሻው ለመታገል ቃል እንገባለን፡፡ መብታችንን ሰላማዊ፣ ህገ-መንግስታዊ በሆነ መልኩ ብቻ ወደፊት ትግላችንን እንቀጥላለን፡፡ አላህ ሆይ፤ ተበድለናል እርዳን! ተበድለናል እርዳን! አላሁ አክበር!››

ይህ፤ ቃል በቃል የሰፈረው ሃምሌ 8 ከኮሚቴዎቻችን ጋር የተጋባነው ቃል ኪዳን ነው፡፡ያን እለት ወደ አንዋር መስጂድ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ከሌሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ውይይት ላይ ነበሩ፡፡ በዕለቱ አብዛኛዎቹ ኮሚቴዎቻችን ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል፡፡ ይህን በደል ያንገሸገሸውን ህዝብ፤ ልጆቹን ሌሊት አስደብድቦ ጠዋት ወደመስጂድ የከተተን ህዝብ ምን እንደሚሉት ተጨንቀዋል፡፡ ህዝቡ ሲመርጣቸው ምሩን እንጂ በዝምታ አስደብድቡን ብሎ አልነበረም፡፡ በሚደንቅ ሁኔታ ግን በሁሉም አባላት ላይ አንድም የሃሳብ ልዩነት አልነበረም፡፡ እናም ከላይ ያለውን የቃልኪዳን ንግግር ቃል በቃል ተስማምተው ተናጋሪ ወክለው ወደ አንዋር ተጓዙ፡፡ አንዋር ለመድረስ የገጠማቸውን ሁሉም ያውቃል፡፡ ደርሰውም የሆነውን እንደዛው፡፡

ያ ቃልኪዳን ንግግሩ ብቻ ሳይሆን መልእክቱም የጠለቀ ነበር፡፡ ለመፅናት ቃል መግባት፣ ለሰላማዊነት ቃል መግባት፣ መበደላችንን ደጋግሞ በማንሳት ግን ደግሞ ወደ አላህ ለማስጠጋት ቃል መግባት፣ በስተመጨረሻም የአላህን ታላቅነት ማውሳት፡፡ ወላሂ ላስተነተነው ታላቅ መልእክት አለው፡፡ ይህንን መልእክት ብቻውን መፅሃፍ ልናዘጋጅበት እንችላለን፡፡

መመለሻችን የሆነው የአላህን መፅሃፍ ገልፀን አንድ አንቀፅ እንጥቀስ ‹‹ከችግርም ጋር ምቾት አልለ፡፡ ከችግር ጋር በእርግጥ ምቾት አልለ፡፡ በጨረስክም ጊዜ ልፋ (ቀጥል)፡፡ ወደ ጌታህም ብቻ ከጅል፡፡›› (ቁርኣን 94/5-8 )፡፡ ኮሚቴዎቻችንም ይህን የቁርአን አንቀፅን ተንተርሰው ቃል እንዳስገቡን እንጠረጥራለን፡፡ ከችግር በኋላ ምቾት አለ ብንባል ኖሮ ምቾቱ በጣም ይርቅብን ነበር፡፡ ግና በችግር ውስጥ ነው ምቾት አለ የተባልነው፡፡ በመበደል ውስጥ የሚወለድ ራዕይ፣የሚነጥር ስብእና፣ የሚፈጠር መሰባሰብ እና መብሰል እንዲሁም ለዲን ተቆርቋሪነት ብቻ ሳይሆን ለዲን ሲሉ መበደልን የሚችል አቅም ማጎልበትም ከችግር ጋር ያሉ ምቾቶች ናቸው፡፡ አማራጮችን ሁሉ ተጠቅመን ጨርሰናል ብለን ባሰብንበት አጋጣሚ ሁሉ ይህ አንቀፅ ‹‹በጨረስክም ጊዜ ልፋ (ቀጥል)›› ይለናል፡፡ ድልንም ማግኘትም ሆነ በደለን ማሰማት ባሰብን ግዜ ‹‹ወደ ጌታህም ብቻ ከጅል›› ይለናል፡፡

ሙስሊሙ “ለመንግስት የድምፄን ስማልኝ ”ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረበት ሰኣት ጀምሮ መልካሙንም መጥፎውንም አጋጣሚ በአላህ ፈቃድና እርዳታ እያለፈ እዚህ ደርሷል :: አብዛኛውን ጊዜ በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ አደባባይ የሚያስወጣ ችግር ሲያጋጥም ሁከት የሚጋብዝ አካሄድ ውስጥ መግባት የተለመደ ነው፡፡ የተሻለው አማራጭ ግጭትን የማይጋብዙ ሰላማዊ መንገዶችን መከተል ሆኖ ሳለ፡፡ ሰላማዊ ትግል ከድርጊት አልባነትም ሆነ ኢ-ፍታሀዊነትን ካለመቃወም ጋር የሚወዳደር አይደለም፡፡ ምናልባትም ከአመፅ እንቅስቃሴ ይልቅ ተግባር ሊባል የሚችው የሰላማዊ ትግል እንቅስቃሴ ነው፡፡ የተግባራትም ሂደት ሆኖ በበርካታ ተግባራት ሊከተል የሚችል ነው፡፡ ትክክለኛ ለውጥ ሊመጣ የሚችለውም ቀጣይነት ያለውና ጠቃሚ ለውጦችን በጉዞ ላይ እያካሄዱ መጓዝ ሲቻል ነው፡፡

ዲንን መጠበቅ የሚባለው ፅንሰ ሃሳብም ቀጣይነት ያለውና በረጅም ግዜ የሚፈፀም እንጂ በአንድ ጀንበር የሚሆን አይደለም፡፡ በተለይ በኛ ላይ የተጀመረው ዘመቻ በአላህ እገዛ እና በኛ ፅናት በአደባባይ እንዲፈፀም ሆነ እንጂ በረጅሙ የተጎነጎነ ነው፡፡ ይህን መመከት ሊሳካ የሚችለው ደግሞ ጊዜ እየወሰዱ በሚታገሉበት በሰላማዊ የትግል አካሄድ ነው፡፡ በሰላማዊ የትግል አማራጭ የሚባክን ጊዜ አይኖርም፡፡ ይልቁንም በማንኛውም ጊዜ የሚገኙ መልካም አጋጣሚዎችን በሙሉ አቅማቸው ለመጠቀም እድል ይሰጣል፡፡

ሰላማዊ መንገድ ፈርጀ ብዙ በመሆኑ የትኛውን መንገድ መጠቀም እንዳለብን የሚወስነው የምንቃወመው ጉዳይ ይሆናል፡፡ እኛም የትኛውን ሰላማዊ መንገድ እንጠቀም በሚል ከመወያየት አንቆጠብም፡፡ ዛሬ ላይ የመብት ጥሰትን መቃወምን መርህ ያደረገ ሰላማዊ መንገድ ብቻ ነው እየተከተልን ያለነው፡፡ ጠንካራ ተቃውሞ እና ሌሎች ጫና ማሳደሪያ ሰላማዊ ስልቶች በርካታ ናቸው፡፡ ሁሉም በግዜው ይሆናል፡፡ እዚህ የደረስነው በኛ ብልሃት ሳይሆን በአላህ እገዛ በመሆኑ የነገ ጉዟችንም በአላህ ፈቃድ የተሳካ እንደሚሆን ተስፋ እናረጋለን፡፡