ኢትዮጵያዊነትና ወግ ለጥቅም የሰገደበት ጊዜየድህነት ደግ ባይኖረውም የከፋ ድህነት ደግሞ በየቀኑ እኛነታችንን እያኘከ፡ እያመነዠከ ይተፋዋል፡፡ መሽቶ በነጋ ቁጥር “ባህላችን ነው” “ኩራታችን ነው” የምንለውን ሁሉ ከአፈር ይደባልቀዋል፡፡

ድህነትን ለማምለጥ፡ ጥቅምን ለመሳብ ወላጆች ሴት ልጆቻቸውን ለ’ደህና’ ተከራይ “ሂጂና ቡና አፍይለት” እያሉ በስጦታ የሚያቀርቡበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ ዶላርን ፍለጋ ወላጅ አንጀት ልጁን ከፈረንጅ ለመዳር ባጭር ጠብቆ የተሳረበት ዘመን ላይ ነው ያለነው፡፡
ወቅታችን ነዋይ የነውርን እጅ ጠምዝዞ የጣለበት ወቅት ነው፡፡ ማንነት ለገንዘብ ያጎበደደበት፡ ኢትዮጵያዊነትና ወግ ለጥቅም የሰገደበት ጊዜ ነው፡፡

በዛ ሰሞን "የኪራይ ቤቶችን ለንግድ ስራ ተከራይቶ ለሌላ ያከራየ ሁሉ ወዮለት! ቤቱን ተቀምቶ ለተከራዩ ይሰጣል" ሲባል ስንቱን ሰማን…ስንቱን አየን!
የተከራዩትን ንግድ ቤታቸውን ቢያከራዩም እንኳን ምንም አይደርስባቸውም ከተባሉት የህብረተሰብ አይነቶች ከኤች አይ ቪ ጋር የሚኖሩ ሰዎች፡ ወላጆቻቸውን ያጡ ልጆችና ጧሪ የሌላቸው ሰዎች አሉበት ተብሎ ሲነገር ነበር፡፡ ታዲያ በዚያ ሰሞን የተወሰኑ ሰዎች ቤታችውን ላለመቀማት ራሳቸውን ከነዚህ መመዘኛዎች ጋር ሲያጠጋጉ ሰነበቱ፡፡

አንዱ የ69 አመት አዛውንት ቤታቸውን እንዳይቀሙ ሲከራከሩ ቆይተው
“ምንም እንኳን ኤች አይ ቪ ባይኖርብኝም ከባድ የስኳር ህመም አለብኝ፡፡ ካልተንከባከቡት እኮ ስኳር ከኤች አይ ቪ ቢብስ እንጂ በምንም አያንስም” እንዳሉ ሰማሁ፡፡ 
በተመሳሳይ ቤትን የመነጠቅ ስጋት ላይ የነበሩ ለስልሳ 1 አመት የቀራቸው የድርጅቱ ደንበኛም “እናትና አባቴ በሕይወት የሉም፡፡ የሙት ልጅ ነኝ” ብለው ወላጆቻቸውን ያጡ መሆናቸውን በማስመስከር ቤታቸውን ላለማጣት ሲሯሯጡ ነበር፡፡ በጧሪ አልባነት ሰበብ ጥቅምን ለማስከበር የሚጥሩ ጥቂት ወላጆችም ውጪ ሃገር የሚኖሩ ልጆቻቸውን ክደው ሰንብተዋል፡፡

ከባድ ሕመምን “አንኳንም አመመኝ” የሚያሰኝ፡ በስልሳ አመት የሙት ልጅ የሚያደርግና ፡ የገዛ ልጅን የሚያስክድና በስተርጅና ቀጣፊ የሚያደርግ ድህነትና የገንዘብ ፍቅር እንዴት ያለ ነው እናንተ?!

የዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለሁ አንድ ትልቅ የእርዳታ ድርጅት በሚያካሂደው የድህነት ደረጃን ለማወቅ የተካሄደ ሰፊ ጥናት አካል ነበርኩ፡፡  ጥናቱ መርካቶና አሁን በፈረሰው ልደታ ሰፈር ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ የኔ ስራ ከቤት ቤት እየሄዱ ሰዎች ምን ያህል ድሃ እንደሆኑ መጠየቅና መመዝገብ ነበር፡፡ መርካቶ ጭድ ተራ አካባቢ ባለ አንድ ሰፈር ውስጥ ይህንኑ ስሰራ አንድ የጎስቋላ ቤት ጎስቋላ እመቤትን የተሰጠኝን መጠይቅ ይዤ በሰለጠንኩት መሰረት እነዘንዛለሁ፡፡

ስጨርስ ወደሚቀጥለው ቤት ለመሄድ ተነሳሁ፡፡ ጠይቄያት የጨረስኩት ሴት
“አሁን የትኛው ቤት ልትሄጂ ነው?”  ብላ ጠየቀችኝ፡፡
“እዚኛው!” ብዬ ቤቱን በሌባ ጣቴ አሳየኋት፡፡
“አይ እዛ አትሂጂ!” አለችኝ ጫን አድርጋ
“ለምን ?”
“እሷ ደሃ አይደለችም የኔ እናት! ኤች አይ ቪ አለብኝ ብላ ከኤን ጂ ኦ እርዳታ ታገኛለች፡፡ በዛ ነው ምትኖረው፡፡ እናን ድሃዎቹን ቁጠሪን”

እኔም “ኤች አይ ቪ እንኳን ከድህነት ማምለጫ መንገድ ሆኖ ሲቀናበት ምሰማበት ጊዜ ላይ ደረስኩ” ብዬ ሽምቅቅ ስብር አልኩና መንገዴን ቀጠልኩኝ፡፡  
ማንነታችንን እያኘከ የተፋው ድህነታችን