ትግል የነጻነት ብቻ ሳይሆን የመስዋእትነት አውድማም ጭምር ነው-አላሁ አክበር!

መስዋእትነት!

ለአለማት ሁሉ እዝነት የሆነው ዘላለማዊው ሐይማኖታችን እስልምና ከሚያስተምረን ታላላቅ እሴቶች አንዱና ዋነኛው መስዋእትነት ነው፡፡ አዎን! መስዋእትነት! ክፉ አሳቢዎችና ጨቋኞች በአለማችን እስካሉ ድረስ ትግል የግድ ይኖር ዘንድ የሰው ልጅ ሰብአዊ የህሊና ሚዛን ያስገድዳል፡፡ ትግል ደግሞ የነጻነት ብቻ ሳይሆን የመስዋእትነት አውድማም ጭምር ነው - የጊዜ፣ የጤና፣ የህይወት፣ የገንዘብና የሌሎችም ውድ ነገሮች መስዋእትነት አውድማ!

ከነቢዩላህ አደም ጀምሮ እስከ ታላቁ የነቢያት መደምደሚያ ሙሐመድ (ሰላም በሁሉም ላይ ይውረድና) የኢስላምን ታሪክ ብንመለከት ከመስዋእትነት ነጻ የሆነበት ወቅት በጭራሽ እንዳልነበረ እንረዳለን፡፡ በሁሉም ወቅቶችና ዘመናቶች የእስልምና ልጆች ህይወታቸውን ገብረዋል፡፡ ከበደለኞች ጋር ባደረጉት ትንቅንቅ የሚከፈለውን ሁሉ ከፍለዋል፡፡ ታላቁ ነቢይ ምን ያህል ችግር ደረሰባቸው? ታሪካቸውን ብናየውስ በምን ያህል መስዋእትነት የታጨቀ ነው? ሌላው ሌላው ችግር ቀርቶ ከቤተ ዘመዳቸው እንኳ ህይወታቸውን ለኢስላም አሳልፈው የተጡት ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡ ሁለት አጎቶቻቸውንና ሶስት የአጎት ልጆቻቸውን ጨምሮ ከስምንት ያላነሱ ዘመዶቻቸውን አጥተዋል፡፡ በቁጥር የበዙ ድንቅ ባልደረቦቻቸውን ለሞት ገብረዋል፡፡ ከነቢይነታቸው በኋላ በመካ ያሳለፏት እያንዳንዷ ቀን በመስዋእትነት የተሞላች ነበረች፡፡ ቁረይሾች እስልምናን በተቀበሉ ተከታዮቻቸው ላይ ያሳርፉት የነበረው የግፍ በትር ሲበረታ፣ ባልደረቦቻቸው ሲጨነቁ ‹‹ኧረ ያረሱለላህ! ዱኣ ያድጉና ይገላግሉን!›› ሲሉ ይወተውቷቸው ነበር፡፡ በዚያ ሁሉም ሙስሊሞችን በሚያሰቃይበት ወቅት ያ ታላቅ ነቢይ የአላህ ፈቃድ ይፈፀም ዘንድ ለተከታዮቻቸው ትእግስት እንዲያደርጉ ከመምከር ያለፈ አቅም አልነበራቸውም፡፡ አዎን! የአላህ ጥበብ የረቀቀ ነውና መስዋእትነቱ ራሱ ሶሐቦች ነጥረው የሚወጡበት የእሳት ፈተና ሆነ፤ ‹‹ወርቅ በእሳት ይፈተናል›› እንዲሉ፡፡

ሶብር እንደቃሉ ባለሶስት ፊደል አይደለም፡፡ ችግር ሲከሰት ስብእናን ይፈታተናል፡፡ ቅስምን ሊሰብር፣ ወሽመጥን ሊቆርጥ ይደርሳል፡፡ ያኔ የጥበቡ ነቢይ የተከታዮቻቸውን ጥንካሬ የሚያለመልሙት በተስፋ፣ የሚያደነድኑት ደግሞ የባሰውን ፈተና በማስታወስ ነበር፡፡ ‹‹ከናንተ በፊት ከነበሩት ህዝቦች አንዱ ከአንገቱ በታች ተቀብሮ ራሱ በመጋዝ ለሁለት ይከፈል ነበር፤ አልያም ቆዳው እና አጥንቱ እስኪለያይ በብረት ሙሽጥ ይሞሸጥ ነበር፤ ይህም ቢሆን ከእስልምናው ፍንክች አያደርገውም›› ሲሉ የቀደመውን ፈተና ያስታውሳሉ፡፡ በዚህም አያበቁም፤ ተስፋ ጣል ሳያደርጉበት አይቀሩም፡፡ አሸናፊነት የማይቀር መሆኑን፣ ከችግር በኋላ ምቾት አይቀሬ መሆኑን፣ ከትግል ኋላ ድል ተከታይ መሆኑን ይነግሯቸዋል፡፡ ‹‹አንድ መንገደኛ ከአላህ አልያም በጎቹን ከሚያጠቃበት ተኩላ ሌላ አንዳችም ሳይሰጋ ከሰንአ እስከ ሀድረመውት እስከሚሄድ ድረስ አላህ ጉዳያችንን ሙሉ ያደርገዋል፤ እናንተ ግን ትቸኩላላችሁ!››

አዎን! የሰው ልጆች ስንባል እንቸኩላለን! ድልን እናቻኩላለን! መስዋእትነት ድንቅ ስብእናዎች የሚሞረዱበት ሜዳ መሆኑን እንዘነጋለን! ድልንም እንዘነጋለን - ስቃይ ሲውጠን! ያኔ የአላህን ቃል ኪዳን ማስታወስ ነው ደጉ፡፡ ታላቁ ነቢይ ከአረቢያ ምድር በተውጣጣው አስር ሺህ የሙሽሪኮች እና አጋሮቻቸው ጦር መዲና በተከበበችበት ወቅት እንኳ ድልን አልዘነጉም፡፡ ወደፊት የሚጠብቃቸውን ድል እየነገሩ ተከታዮቻቸውን ያጸኑ ነበር፡፡

እኛም የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ዛሬ ላይ ጊዜው የሚጠይቀውን መስዋእትነት እየከፈልን እንገኛለን፡፡ የሃይማኖት ነጻነታችን እና ያንንም ያረጋገጠልንን ህገ መንግስታችንን የጣሱ ተግባሮች እንዲቆሙልን ጠይቀናል፡፡ የተሰጠን መልስ ደግሞ ፍጹም ተቃራኒ ሆኖብናል፡፡ እየተፈተንን ነው - ለኛ ከባድ ፈተና ነው! ነገር ግን ምን ፈተናችን ቢከብድ ቀደምቶቻችን ከደረሰባቸው አንጻር እዚህ ግባ ሊባል የሚችል መስዋእትነት አይደለም፡፡ ይህንን አጥብቀን መረዳቱ ፈተናችን እንዲቀለን ያደርጋል፤ ለተጨማሪ ትግልም ያዘጋጀናል፡፡ ገና ብዙ ትግልና መስዋእትነት እንደሚጠብቀን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡ እስካሁን በግልም ሆነ በጋራ የከፈልነው መስዋእትነት ዋጋ አልባ የሚሆነው የከፈልንበትን ምክንያት ስንዘነጋና ሳናሳካው ስንቀር አይደለምን?

በዚህ ለኛ ሲሉ መስዋእትነት የከፈሉ ባለውለታዎቻችንን በምንዘክርበት ሳምንታችን በግልም ሆነ በጋራ እስካሁን የከፈልነውን መስዋእትነት ዘወር ብለን እንቃኘው፤ ከቀደሙት ጋር እናስተያየው፤ ካደረሰብን ጉዳት በበለጠ ያነጠረውን ስብእናችንን፣ የገነባውን አቅማችንን እናስላው፡፡ ከዚያስ…? ከዚያማ… የሆነው ሁሉ የአላህ ውሳኔ ነውና አጅራችንን አስበን በወደደ ልብ እንቀበለው - ያኔ ከቁስሉ መፈወሻችን ይሆናል!
መስዋእትነትን በወደደ ልብ መቀበል ለመክበዱ ጥርጥር የለውም፡፡ እስቲ ሶሐባውን እናስተውል፡፡ ከጨቋኞቹ ባንዱ እልፍኝ በፈላ ዘይት የተሞላ በርሜል ከፊቱ አቅርበው ጓደኞቹን ከቀቀሏቸው በኋላ ሶሐባውን አይን አይኑን ያዩታል፡፡ ጥንካሬው ሲፈረካከስ፣ ወኔው ሲማሽሽ እያዩ ለመደሰት አሰፍስፈዋል፡፡ ሰሐባው አለቀሰ፤ እነሱም ጉጉታቸው ጨመረ፡፡ ‹‹ምነው አለቀስክ?›› አሉት በሽንፈቱ ሊሳለቁ፣ እልክ የተጋባች ነፍስያቸውን ሊያስደስቱ! እሱ ደግሞ ያለው መስዋእትነት በሚጣፍጥበት አለም ውስጥ ነበር፤ እንዲህም አላቸው፡- ‹‹ያለቀስኩት አንድ ነፍስ ብቻ ስላለኝ ነው! ብዙ ሺህ ነፍሶች ኖረውኝ የፈላ ዘይት ውስጥ ደጋግሜ እየገባሁ ብዙ ግዜ ለአላህ ዲን ስል መሞት አለመቻሌ አስለቀሰኝ!››

ታላቁ ነቢይ ደግሞ በሌላ ጥበብ የተሞላ ንግግራቸው ይህንን ማለታቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹የሙእሚን ነገር ሁሌ ይገርመኛል! ሁሉ ነገሩ ለሱ ጥሩ ነው፡፡ ጥሩ ነገር በገጠመው ጊዜ አላህን ያመሰግናል፤ ይህም ጥሩ ይሆንለታል፡፡ መጥፎ በገጠመው ጊዜ ደግሞ ትእግስት ያደርጋል፤ ይህም ለሱ ጥሩ ይሆንለታል፡፡›› (ነቢዩ ሰ.ዐ.ወ)

አላሁ አክበር!