የኢህአዴግ ሃይማኖታዊ ክንፍ - አህባሽ - በአገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ

ድምፃችን ይሰማ
መንግስት መንግስታዊ ሙስሊሞችን ማደራጀቱን እንደቀጠለ ነው፡፡

መንግስት በወንፊት ውሀ ቅዱልኝ እያላቸው ነው፡፡

የአህበሽ አማኞች 

እስላማዊ እንቅስቃሴዎችን እንዲያሰናክል እና እንዲያስመታ ታስቦ ከሊባኖስ በነፍጥ አጀብ ወደአገራችን የገባው አህባሽ በሁለት እግሩ ለመቆም የሚያደርገውን ስኬት አልባ እንቅስቃሴ ገፍቶበታል፡፡ በአዲስ አበባ አስሩም ክፍለ ከተማዎች ወጣቶች ላይ ባተኮረ መልኩ ‹‹የአዲስ አበባ አህለል ሱና ወል ጀምዓ ወጣት ሱፍይ ማህበር›› በሚል ስያሜ ባለፈው እሁድ ብቅ ያለው ይኸው አዲሱ የአህባሽ አደረጃጀት ሙስሊም ከሆኑ የወንድና ሴት ነዋሪዎች ፎረምና ከፓርቲ አባላት፣ እንዲሁም ባለፈው የመጅሊሱ ቅርጫ ‹‹ተመርጠናል›› ካሉ ጥቂት ወጣቶች እንዲውጣጣ የተደረገ መሆኑ ገና ከጅምሩ ‹‹የኢህአዴግ ሃይማኖታዊ ክንፍ›› የሚል ስያሜ አሰጥቶታል፡፡

እኒሁ አህባሽ አባላቶቹ ማህበሩ ባለፈው እሁድ በአገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ባዘጋጀው የመክፈቻ ፕሮግራሙ ላይ የተገኙ ሲሆን የማህበሩ ፕሬዝዳንት ነስረዲን መሀመድ የህዝበ ሙስሊሙን ትግል ሲያጥላላና ሲተች ተስተውሏል፡፡ ‹‹ማህበራችን አክራሪና ፅንፈኛን በማጋለጥ ለመንግስት ያስረክባል›› ሲል ከኢህአዴግ ጸረ ሙስሊም ዘመቻ አንጻር አሰላለፉ ከየት ወገን እንደሆነ በማሳየት የዛተው ይኸው ግለሰብ ‹‹ጥቂት አክራሪዎችና ጽንፈኞች በእምነት ሰበብ ያለአግባብ እየተጠቀሙ ለእስልምና፣ ለሃገርና ለህዝብ ስጋት ሆነዋል›› ሲል ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞችን ዘልፏል፡፡

መንግስት ከአመት በላይ ለቀረበለት ጥያቄ መልስ በመስጠት ፋንታ በሃይማኖት ውስጥ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት የበለጠ ግልጽ በማድረግ ጫና መፍጠሩን ቀጥሏል፡፡ በህዝበ ሙስሊሙ ዘንድ አንዳችም ተቀባይነት የሌለውን አዲስ አንጃ ለመጫን ማህበራት እና ኮሚቴዎች በየቀኑ ቢቋቋሙ እንኳ ሊያሳኩት የሚችሉት አለመሆኑ እስካሁንም ስናይ የቆየነው እውነት ነው፡፡ ህዝበ ሙስሊሙ በተጨቆነ ቁጥር ለመታገል የበለጠ አስገዳጅ ምክንያት እያገኘና፣ ወኔውም እየጋለ ሄዷል፡፡ ይህንን የህዝብ ባህሪ ከታሪክ እውቀት መረዳት ባይቻል እንኳ ከትግላችን የአንድ አመት ጉዞ አካሄድ ማስተዋል ግን እጅግ በጣም ቀላል ተግባር መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ መንግስት ማህበራትን በየቦታው በማቋቋምና ህዝቡ አንቅሮ የተፋቸውን አህባሾች እየሰበሰበ በወንፊት ውሀ እንዲቀዱለት ከመጠየቅ ለህዝቡ ሕገ መንግስታዊ ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ተመራጭ ነበር፡፡
ድልም ከአላህ እንጂ ከሌላ አይደለም!

አላሁ አክበር!