የኮሎኔል ሳላህ ኦስማን አና የወታደሮቹ እርምጃ ለአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ የማስጠንቀቂያ ደውል ነው !!!

ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል

ትናንት ባመጹ ወታደሮች ተቋርጦ ነበር የተባለው የኤርትራ መንግሥት ቴሌቪዥን ስርጭት መቀጠሉ ተዘገበ ። በፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገባ መሰረት የኤርትራ መንግሥትም በዋና ከተማይቱ አስመራ ሁሉም ነገር ሠላማዊ መሆኑን አስታውቋል ። ይሁንና በጉዳዩ ላይ ለዶቼቬለ አስተያየታቸውን የሰጡ የፖለቲካ ተንታኞች ፣ ያመጹት የኤርትራ ወታደሮች እርምጃ በኤርትራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ የመባባሱና የአገዛዙ የመዳከም ምልክት መሆኑን ተናግረዋል ።

የኤርትራ ፕሬዝዳንት የአቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ቃል አቀባይ አቶ የማነ ገብረ መስቀል እንደ ትናንት ሁሉ ዛሬም አስመራ ሰላማዊ ናት ማለታቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ። አንድ የተቃዋሚ ድረ ገፅን የጠቀሰው AFP ወደ 100 ይጠጋሉ ያላቸው ትናንት የኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን የተቆጣጠሩ ያመፁ ወታደሮች አዛዥ እጃቸውን ለመስጠት መስማማታቸውን ዘግቧል።

የዘገባው እውነትነት ግን በሌላ ምንጭ አልተረጋገጠም ። አንዳንድ ምንጮችም የወታደሮቹን እርምጃ ከመፈንቅለ መንግሥት ጋር አስተካክለውታል ። በብሪታኒያው የጥናት ተቋም ቻተምሃውስ የአፍሪቃ ቀንድ ጉዳዮች አጥኚ አህመድ ሶልሜን ግን ከኤርትራ ትክክለኛ መረጃ ማግኘት በማይቻልበት ሁኔታ የተፈፀመውን ለማወቅ አዳጋች መሆኑን ነው ለዶቼቬለ የተናገሩት።

« መፈንቅለ መንግሥት ወይም በወታደሩ ውስጥ አመፅ ነበር ለማለት አስቸጋሪ ነው ። በአሁኑ ጊዜ የትናንቱ እርምጃ ውጤት ምን እንደሆነ ለማወቅ መጠበቅ አለብን ። ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሁኔታው ምን እንደሆነ አናውቅም ። ሆኖም የሆነ አይነት አመፅ እየተካሄደ ነው።»

በአንዳንድ ዘገባዎች እንደተጠቆመው ወታደሮቹ ህገ መንግሥቱ እንዲከበርና የፖለቲካ እሥረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቀው መግለጫቸው ትናንት በኤርትራ ቴሌቪዥን እንዲነበብ አድርገዋል ። የአፍሪቃ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪና የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር ማሃሪ ታደለ ማሩ የወታደሮቹ እርምጃ ለመንግሥት የማስጠንቀቂያ ደውል ነው ይላሉ።
የኤርትራው ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ይህን መሰሉ የአመፅ እንቅስቃሴ መካሄዱ ሲነገር የአሁኑ የመጀመሪያው ነው ። ይህ ወዴት ሊያመራ ይችላል ? ምንስ ያመለክታል ተብለው የተጠየቁት የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ሶልመን ሲመልሱ « ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለውጥ ማምጣት አለማምጣቱ ወደፊት የሚታይ ይሆናል ።

እኔ ግን ለውጥ ማምጣቱን እጠራጠራለሁ ። ኢሳያስ ሁኔታዎችን መቆጣጠር የሚችሉ ይመስለኛል ። ሆኖም በርግጥ ይህ እርምጃ በቅርቡ የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዶ ከድተው መኮብለላቸው ከተዘገበ በኋላ የተወሰደ 2 ተኛ እርምጃ ነው ። ስለዚህ በራሱ በአስመራ መንግሥት ውስጥ ውጥረቱ እየተጠናከረ የመምጣቱ ምልክቶች አሉ።»
የፖለቲካ ተንታኝ ዶክተር መሃሪም ተመሳሳይ አስተያየት ነው ያላቸው።

ትናንት በኤርትራ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ ያመፁ ወታደሮች ወሰዱ የተባለው እርምጃ የቻተም ሃውሱ ተንታኝ አህመድ ስልሜን እንዳሉት የህዝቡ ብሶት መገለጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ።

« የተደማመረ ነገር እንዳለ ይታያል የሰብአዊ መብት ይዞታው ወጣት ኤርትራውያን በግዳጅ ለውትድርና መመልመላቸውና በአነስተኛ ክፍያም ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ በመደረጉ በርካታ ወጣት ዜጎች ህይወታቸውን ለማትረፍ ወደ ሌሎች የአካባቢው ሃገራት እየተሰደዱ ነው። ስለዚህ ባለፉት 24 ሰአታት የተከናወኑት ድርጊቶች ለተፈፀሙት ሁኔታዎች እንደ ምሬት መግለጫ ሆነው ነው የሚታዩ ይመስለኛል ። ይህ እንደሚሆንም የሚጠበቅ ነው ። ሆኖም በኛ ግምት ይህ የአገዛዙ መዳከም ምልክት ነው። »
 http://www.youtube.com/watch?feature=player_embedded&v=QpJYE8vT1GQ#!