የሳንሱር ማጭድ ያሰቃየው ደራሲ

ሎሬት ፀጋዬ

በኢትዮጵያ የዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ውስጥ በመድረክ የቀረበ ቀዳሚ ተውኔት ሆኖ የሚቆጠረው፤ ፊታውራሪ ተክለሐዋርያት ተክለ ማርያም የደረሱት “የአውሬዎች ተረት (ፋቡላ)” ነው፡፡ ይህ በግጥም የተዘጋጀ ድርሰት በ1903 ዓ.ም ተጽፎ ለልጅ እያሱ የተበረከተ ሲሆን፤ በቴአትር መልክ የቀረበው ግን በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመነ መንግሥት አልጋ ወራሹ ራስ ተፈሪ እንዲታይ በፈቀዱ ጊዜ ነበር፡፡ ቴአትሩም ተዘጋጅቶ ንጉሣዊው ቤተሰብና መኳንንት በተገኙበት በቴሬስ ሆቴል መድረክ ላይ ቀርቦ ታይቷል፡፡ ይሁን አንጂ ተውኔቱ ለጊዜው ፖለቲካ የማይስማማ፣ መኳንንቱንና ቤተክህነትን የሚነቅፍ (ሳቲር) ነው ተብሎ እንዳይታይ ተከለከለና ታትሞ ተሸጦ የነበረው የቴአትሩ መጽሐፍም ከሕዝብ ዘንድ ተለቅሞ እንዲሰበሰብ ተፈረደበት፡፡ ይህ ቴአትር እንግዲህ በአገራችን እንዳይታይ በይፋ ክልከላ የተደረገበት የመጀመሪያው ቴአትር መሆኑ ነው፡፡
ምንም እንኳ በዚህ ጊዜ ሳንሱር ወይም ቅድመ ምርመራ በሕግ ተደንግጐ ሥራ ላይ የዋለ ባይሆንም፤ “በአውሬዎች ተረት” ቴአትር ላይ የተጣለበት ገደብ፣ በኢትዮጵያ በተውኔት ሥራ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የተተገበረ ሳንሱር ተደርጐ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ምንልክሳልሳዊ በመሆኑም በኢትዮጵያ የሳንሱር ጋሬጣ በመርዛማ እሾሁ የትእይንተ ጥበብን ተክል እየወጋ ማቁሰል የጀመረው፣ ተውኔት ገና በቡቃያ ላይ እያለ ነበር ማለት ነው፡፡ የሳንሱር በትር በቴአትር ጥበብ ላይ ሲሰነዘር ተውኔት ገና በተመልካቹም ሆነ በባለሙያው ዘንድ እምብዛም ያልተለመደ እና ያልተስፋፋ አዲስ ባህል ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሳንሱር በተደራጀ መልክ ሥራ የጀመረው በፋሺስት ኢጣሊያ አምስት የወረራ አመታት ጊዜ ውስጥ ሲሆን ተቆጣጣሪ መስሪያ ቤቱም የፖለቲካ ቢሮ (Officio Politico) ተብሎ ይታወቅ ነበር፡፡ ከነፃነት ማግስትም በኋላ ይህ መስሪያ ቤት እንደ አዲስ ተዋቅሮ ለአሰራሩም ሕግና ደንብ ወጣለት፡፡
ሚያዝያ 21 ቀን 1935 ዓ.ም “የቴአትርና የሲኒማ አደራረግን ስለመመርመር” የወጣው አዋጅ ቁጥር 37/1935 በትእይንተ ጥበባት ላይ የተጣለውን ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር) ሕጋዊ መሰረት ሰጥቶታል፡፡ ከዚህ አዋጅ በኋላ ሳንሱር የፅልመት አደረጃጀቱን አጐልብቶ ሙሉ አካል የሚያጐድልበት ስለቱን፣ ውጦ የሚያስቀርበትን የጨለማ ቋቱን አሰናድቶና አድብቶ ከተውኔት ጀርባ ቆመ፡፡ መልከ ጥፉን በስም ይደግፉ እንደሚባለው ለዚህ እኩይ የሳንሱር ተግባር አላማ ነው ተብሎ በአዋጅ የተገለጠው ግን “የሕዝቡን ፀጥታና ንፅህና ከብልግና መጠበቅ ነው” የሚል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በተግባር እንደታየው ሳንሱር አካለ ጐደሎ ያደረጋቸው ወይም ጭራሹኑ እንዳይታዩ የከለከላቸው ተውኔቶች፤ የሕዝብን ፀጥታ የሚያውኩ ወይም ለመልካም ጠባይ ተጣራሪ የሆኑ ናቸው ተብለው የተገመቱ ሳይሆኑ፤ ለአገዛዙ ፖለቲካ አደገኛ ናቸው የተባለ ስራዎች ነበሩ፡፡
በዘውድ መንግሥትም ሆነ በደርግ ዘመን ሳንሱር የሚከናወንበት ጥርት ያለ መመሪያ ያልተዘጋጀለት በመሆኑ፤ የተከለከለውና የተፈቀደው በውል ስለማይታወቅ ለሳንሱር ሹማምንት የግል አስተያየት ሰፊ በርን ከፍቷል፡፡ አንዳንዴ የቴአትሩ ይዘት ከመርማሪዎቹ የመረዳት አቅም በላይ ሆኖ ሲገኝ፤ ተውኔቱ ግማሽ በግማሽ እንዲቆራረጥ ወይም እንዲታገድ ይወሰንበታል፡፡ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን በ1978 ዓ.ም ቴአትርን እና የሳንሱር አሰራርን አስመልክቶ ለተዘጋጀ አንድ ጥናት በሰጠው አስተያየት፤ “አንድ ሕዝብ የማወቅ ደረጃውን የኪነ ጥበብ ብስለት ደረጃው ይወስነዋል፡፡ የሳንሱር ባለሙያዎች፣ የኪነጥበብ ብስለታቸው ደካማ በመሆኑ በራሳቸው ውሱንነት ነው ማንኛውንም ነገር የሚወስኑት፡፡ የቀረበላቸው የፈጠራ ሥራ ጥበቡ የበሰለ ከሆነ ጣእመ ትርጉሙ ስለማይገባቸው ይከለክሉ ነበር፡፡ አሁንም ይከለክላሉ፡፡
ምክንያቱም ሰው በተፈጥሮው የማይገባውን ይፈራል… በአሁኑ ሰዓት ደራሲያንን ወዲህ ሳንሱርን ወዲያ ማዶ ያደረገው የሳንሱር ባለሙያዎች አላማ ነው፡፡ ራሳቸውን እንደ ፖለቲካ ጠባቂዎች ያደርጋሉ፡፡ ማንኛውንም ነገር ከፖለቲካ ጋር ያያይዙታል፡፡ አእምሯቸው በዚህ ረገድ ስለተገራ ፖለቲካዊ ይዘት የሌለው ነገር ሁሉ ፖለቲካ መስሎ ይታያቸዋል” ብሎ ነበር፡፡ ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ከአገራችን ደራሲያን መካከል በሳንሱር የተነሳ ብዙ መከራ የተቀበለ፤ የጥበብ ትሩፋቶቹም በዚህ የጨለማ አሰራር ከፍ ያለ አደጋ የደረሰባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ፀጋዬ ሳንሱርን የሚረዳበት እና የሚገልፅበት መንገድ እንደ አንድ ተራ ፀረ ጥበብ የጨለማ አሰራር በመመልከት ብቻ ሳይሆን፣ ይህ እኩይ አሰራር የተፈጠረበትን ጥንታዊና ታሪካዊ መሰረት በመመርመር ጭምር ነው፡፡ ፀጋዬ ይህንን ተግባር ሲያስረዳም፤ “በስልጣን ሰይፍና በብዕር (The Sword and the Pen) መካከል ያለ ትግል ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ፣ ወደፊትም የሚኖር አሳዛኝ እውነታ ይመስለኛል… ባህል ህይወት ነው፣ ሳንሱር ግን ማጭድ ነው፡፡ አንዱ ህይወት ያበስራል፣ አንዱ ህይወት ይቆርጣል፡፡ ብዕር የዘራውን ፍቅር ስልጣን በማጭድ ይቆርጣል፡፡ ብዕር የሕዝብ እፅዋት አትክልተኛ ነው፡፡
ጠመንጃ ደግሞ የእፅዋት አራጅ ነው፡፡ አንዱ በትጋት የተከለውን ታዳጊ ተክል፣ በትጋት ያለመለመውን ፀአዳ ሌላው በፋሺስታዊ ድንፋታ ይጨፈጭፋል፡፡ የዓለም የጥበባት ማዕከሎች ሁሉ የሕዝቦች ፍቅር መዝሪያ መድረኮች ናቸው፡፡ የሀገር መውደድ ብስራቶች (manifestation) ናቸው፡፡ እነዚሀን የሚቆርጥ የየዘመኑ የስልጣን ማጭድ ደግሞ “ሳንሱር” ይባላል… በሮማ ኢምፓየር ጊዜም፣ “ታላቁ ቆራጭ ወይም ታላቁ ሳንሱር፡፡ (The Great Censor) ተብሎ የሚጠራው ኢምፔረር ኔሮ ራሱ ነው፡፡ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ጊዜም ዋናው የብዕር ቆራጭ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ ምክትል ርእሰ ብሔሩ [ጠቅላይ ሚኒስትሩ] ታማኝ የብዕር ቆራጮች ነበሩ፡፡ ቀለማችን የተደፋብን፣ ብዕራችንና ልሳናችን የተቆረጠብን፣ የተፈለጠብን እናውቀዋለን” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡. ባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን ጥበብን አስመልክቶ ያደርጋቸው በነበረው ቃለ መጠይቆችና ውይይቶች ወቅት፤ ስለ ሳንሱር ሳያነሳ ያለፈበት ጊዜ የለም ለማለት ይቻላል፡፡ ፀጋዬ ስለ ሳንሱር ሲያወሳም፤ ሳንሱር የጨቋኝ መንግሥታትን ሰይፍ ወክሎ እንደሚቆም፣ ፍልሚያውም በዚህ የጨለማ የሰይፍ ኃይልና በብርሃናማው ብዕር መካከል መሆኑን፣ የጥበብን ጥንተ ታሪክ እየጠቀሰ ያስረዳ ነበር፡፡ ፀጋዬ እንዲህ ስለ ሳንሱር የሚጮኸውና የጨለማ ስራውንም ባገኘው መድረክ የሚገላልጠው ከማንም በላይ በሳንሱር የተነሳ ስራዎቹ ፍዳቸውን በማየታቸው የተነሳ ነበር፡፡
በኢትዮጵያ ዘመናዊ ቴአትር ታሪክ ውስጥ እንደ ሎሬት ፀጋዬ ገብረ መድህን በሳንሱር የተነሳ የተሰቃየ ደራሲ የለም፡፡ ሳንሱር የፀጋዬን ስራዎች እየተከታተለ ማነቅ የጀመረው ገና ከጠዋቱ ከ1950ዎቹ መግቢያ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ ጊዜ አንስቶ ከሰላሳ አመታት በላይ የሳንሱር ፅልመታዊ መጋረጃ ስራዎቹን ሲጋርድበትና ሲያምቅበት ከመቆየቱም በላይ፤ የሳንሱር ጦስ ወደ ግል ህይወቱ ተሸጋግሮ ኑሮን አክብዶበታል፡፡ ሎሬት ፀጋዬ በሳንሱር ሳቢያ በጥበብ ሥራዎቹ ላይ የደረሰበትን ግፍ የዛሬ አስር አመት ግድም እንዲህ ገልጦት ነበር፡፡ “ከፃፍኳቸው 41 ቴአትሮች ውስጥ (ከተረጐምኳቸውና በእንግሊዝኛም ከፃፍኳቸው ጭምር)፣ አሥራ ሁለቱን ሳንሱር ሙሉ በሙሉ አግዶብኛል፡፡ ሃያ አንዱን ቆራርጦብኛል፡፡ ሶስቱን ግማሽ ለግማሽ ጐራርዶብኛል፡፡ አራቱ ግን ገና ለመድረክ [አልቀረቡም] ከሶስቱ የሥነ ግጥም መፃህፍቶቼ ውስጥ (ሁለቱ ገና አልታተሙም)፣ በሰላሳ ሰባት ነጠላ ዝርዝር ግጥሞቼ ምክንያት፣ የሳንሱር ቢሮ፣ የፀጥታው ክፍል ቢሮና የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቴ ቢሮ ከፍተኛ ሹማምንት ገስፀውኛል፡፡ ቀጥተውኛል፡፡ ዝተውብኛል፡፡ በአንዲት “ጆሮ ገድፍ” በምትባል ትንሽ ቴአትር ምክንያት የጃንሆይ መንግሥት ፀጥታ ቢሮ፣ ለሃያ አራት ሰዓት በቁጥጥር ስር አውሎኛል” ብሏል፡፡
የፀጋዬ ቴአትሮችን በሳንሱር መቆራረጣቸው ወይም መከልከላቸው አልበቃ ያላቸው ሹማምንት “ጆሮ ገድፍ” እና ”አቡጊዳ ቀይሶ” የተሰኙት ድርሰቶቹ እንዲታሰሩ ወስነውባቸው ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ተንሰራፍቶ ከነበረው የሳንሱር መአት ተርፈው ለመድረክ የበቁት የባለቅኔ ሎሬት ፀጋዬ የተውኔት ሥራዎች “የደም አዝመራ”፤ “የሾህ አክሊል” እንዲሁም በዘውድ መንግሥት ፍፃሜ ዋዜማ ላይ የቀረበው “ሀሁ በስድስት ወር” እና ድህረ ደርግ የታየው “ሀሁ ወይም ፐፑ” ብቻ ናቸው፡፡ ጋሼ ፀጋዬ በእንግሊዝኛ የተፃፉ ስምንት ያህል ቴአትሮች ያሉት ሲሆን በውጪ አገር የቀረቡ የጥናት ሥራዎች በመሆናቸው ከሳንሱር ምርመራ ርግማን ለመትረፍ ችለዋል፡፡ በተለይ በደርግ ዘመን ፀጋዬ ከሥራ መታገድ እስከ እስር ድረስ የዘለቀ አደጋ በህይወቱ ላይ ሊደርስበት የቻለው የሳንሱር ክፍል ለፀጥታው መስሪያ ቤት ስለ ቴአትሮቹ ባቀረበው ሪፖርት የተነሳ ነበር፡፡ ለወቅቱ የመንግሥት ፖለቲካ ተቃራኒና አደገኛ ናቸው ተብሎ ሪፖርት የቀረበባቸው ተውኔቶች ፀጋዬ “እናት ዓለም ጠኑ” ሲል ወደ አማርኛ የመለሰው (Mother Courage) የተሰኘ የብሬሽት ድርሰት፣ “አቡጊዳ ቀይሶ” በሚል ከፋንሽን (Fanshen) ወደ አማርኛ የተረጐመው ድርሰት እና ጋሞ የተባሉት ነበሩ፡፡ በዚህ የተነሳም ፀጋዬ ቴአትር ከሚያዘጋጅሪት መድረክ ላይ በድንገት ተጠልፎ ተወስዶ ወደ ወህኒ እንዲወረወር ተደርጓል፡፡ የደረሰበት አደጋ ያሳሰባቸው የሴኔጋል ፕሬዚዳንት የነበሩት ወዳጁ ሴዳር ሴንጐር፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል እንዲሁም (Pen International) ከእስር እንዲፈታ ለደርጉ በተደጋጋሚ ባቀረቡት ብርቱ ተማፅኖ የተነሳ ፀጋዬ ከነህይወቱ ከደርግ እስር ቤት ለመውጣት ችሏል፡፡ ከእሥር ከተፈታ በኋላ የነበሩት ስድስት አመታት ግን ፀጋዬ ከሥራና ከደሞዝ ታግዶ በአይነ ቁራኛ እየታየ የቆየባቸው የግዞት ዘመናት ነበሩ፡፡ በ1983 ዓ.ም የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ፣ ፀጋዬ ገብረ መድህን ሰላም ወይም አጥፍቶ መጥፋት የሚል መልዕክት ያዘለውን “ሀሁ ወይም ፐፑ” የተሰኘ ቴአትር በአማተር ተዋንያን አማካይነት ለህዝብ አሳይቶ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይኸው ቴአትር በአዋሳ ከተማ ለሕዝብ በቀረበበት ጊዜ ታጣቂዎች ባነሱት ብጥብጥ የተነሳ የቴአትሩ ተዋንያን በቆንጨራ፣ በሰደፍና በዱላ ጉዳት ደርሶባቸው ነበር፡፡ ይህም አዲሱ መንግሥት ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ ፀጋዬን በጥበባዊ ሥራው ላይ የገጠመው የመጀመሪያው ችግር ሆነ፡፡
ምንም እንኳ የኢህአዴግ መንግሥት ማናቸውንም ሃሳብን የመግለፅ ነፃነት የሚገድብ ቅድመ ምርመራ (ሳንሱር)ን ያነሳና መዋቅሩንም ያፈራረሰ ቢሆንም፣ የፀጋዬ ሥራዎች ግን በቴአትር ቤቶች የመታየት ፈቃድ በተደጋጋሚ እየተነፈጋቸው ለመድረክ ሳይበቁ ቀርተዋል፡፡ በተለያየ ጊዜ ፈቃድ ከተነፈጋቸው የፀጋዬ የተውኔት ሥራዎቹ ውስጥ “ሀሁ በስድስት ወር”፣ “ቴዎድሮስ”፣ “አጤ ምኒልክ” እና “ቴራቲረኞች” የተሰኘ ምፀታዊ ኮሜዲ ይገኙበታል፡፡ ፀጋዬም በጣም ያሳዘነውንና ይህንን ስውር የክልከላ ድርጊት “[መንግሥታዊ] ድፍን ዝምታ ወይም የመልስ አልባ ዝምታ ሳንሱር” ነው በማለት ስም አውጥቶለት ነበር፡፡ ሳንሱር በህግ የተከለከለ ቢሆንም በተለያየ አይነት ስምና አቀራረብ የጥበብ ጋሬጣ እየሆነ መሄዱንና በሌላ አገርም ይህንን አስመልክቶ ያለውን ልማድና አሰራር ጋሼ ፀጋዬ ሲናገር፤ “ለምሳሌ ዛሬ “ግምገማ” የሚለው ቃል በሥነ ጥበባት ሥራዎች ላይ ሲከሰት የሳንሱር የክርስትና ስም ሆኗል፡፡ በእንግሊዝ አገር ደግሞ ስሙን ሳይለውጥ ዛሬ “የብሪቲሽ ሳንሱሮች ቦርድ” (British Board of Censors) ቢባልም አልፎ አልፎ አፈፃፀሙ በርካሽ ሲኒማዎች ላይ እንጂ በስነ ፅሁፍ፣ በስዕል፣ በሙዚቃና ቴአትር ላይ ከቶም አይሰራም፡፡ የሀገር መውደድ አርማን የሚያንፀባርቁ ስራዎችንም አይቃወምም” ብሏል፡፡ ፀጋዬ ከሳንሱር የጨለማ ኃይል ጋር እየተፋለመ ያሳለፋቸውን አመታት አስመልክቶ እንዲህ ብሎ ነበር፡- “በብዕር ህይወቴ ውስጥ በየዘመኑ መንግሥቶች የሥነ ልቡና ተፅእኖዎች፣ መንገላታቶች፣ የደሞዝ መቁረጫዎች፣ የዝውውር መቀጫዎች፣ ዛቻዎች፣ ዘለፋዎች፣ እስሮች ወዘተ (በግድ የለመድኳቸው ቢሆኑም) ደርሰውብኛል፡፡ ሌሎች የዓለም ደራሲያን በተለይ የብዕር ታላላቆቼ በህይወታቸው የከፈሉትን ፅዋ ስመለከተው ግን እፅናናለሁ፡፡
የኛ “ዙሩ በዛ” እንጂ በስልጣን ሰይፍና በጥበብ መካከል ያለ ትግል ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደፊትም የሚኖር አሳዛኝ እውነታ ይመስለኛል” ከአንድ ሰው አማካይ እድሜ በላይ በቆየው የፀጋዬ ጥበባዊ ህይወት ወስጥ ሽልማት፣ ሹመት፣ ሽረት፣ እስራትና ከሥራ መታገድ ተራ በተራ ተፈራርቀውበታል፡፡ ይሁን እንጂ ከመጀመሪያው እስከ መጨረሻው እንደታማኝ ጓደኛው ከፀጋዬ ሳይለየው የቆየው ግን የሳንሱር መሰናክል ነበር፡፡ ሳንሱር ነፃ አስተሳሰብን በማገድ የደራሲን ብዕር የማዶልዶም ተፈጥሮ ያለው ቢሆንም፤ የፀጋዬ ብርቱ የፈጠራ ኃይልን ግን ለዚህ የፅልመት አሰራር ሳይንበረከክ በርካታ ተውኔቶችን ለማፍራት ችሏል፡፡ ሳንሱር ፀጋዬ ጥበባዊ ሥራዎቹን በመድረክ እንዳያቀርብ እያፈነ እና እየቀነጣጠበ ቢያስቀርበትም፤ ተስፋ አስቆርጦ ብዕሩን እንዲጥል ስላላደረገው የአፈናው ዓላማ ተሳክቶለታል ለማለት አይቻልም፡፡
ባየህ ኃይሉ ተሠማ አንደከተበው