ለተከታታይ አስር ቀናት የሕሊና እስረኞች ላይ ምስክር መደመጥ ይጀምራል::

በመሪዎቻችንና በሌሎችም የሕሊና እስረኞች ላይ ነገ ምስክር መደመጥ ይጀምራል

ምስክሮች ዛሬ የማጠቃለያ ስልጠና ተሰጥቷቸዋል፤

ከነገ ጀምሮ ምስክሮቹ ለሚደመጡባቸው አስር ቀናት አገር አቀፍ ዱአ እንዲደረግ ታዟል፤

አላህ በመስካሪዎቹ ላይ ተአምሩን እንዲያሳየን ሁሉም በዱአ እንዲበረታ ታዟል፤

ከሐምሌ አጋማሽ ጀምሮ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ታስረውና ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞባቸው በማእከላዊ ለአራት ወራት ያህል የቆዩት በፊርማችን የመረጥናቸው ኮሚቴዎቻችንና ሌሎች የህሊና እስረኛ ወንድሞቻችን በተከሰሱበት የጸረ ሽብር ሕግ መሰረት ከነገ ጀምሮ ምስክሮች ይደመጡባቸዋል፡፡ ምስክርነቱ የሚደመጠው የበአላትና እረፍት ቀናትን ሳይጨምር ለተከታታይ አስር ቀናት እንደሆነም ታውቋል፡፡ መሪዎቻችን ለመወራት ያክል ከመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር በጠረጴዛ ዙሪያ ሲወያዩ ከቆዩ በኋላ ነገሮች ተቀልብሰው በተመሰረተባቸው የሽብር ወንጀል አቃቤ ሕግ 197 (አንድ መቶ ዘጠና ሰባት) የሰው ምስክሮችን አቀርባለሁ ብሎ መግለጹ የሚታወስ ሲሆን አዲስ የጸረ ሽብር ሕግ ስለሚፈቅድልኝም የምስክሮቹን ስምም ሆነ መልካቸውን ለደህንነታቸው ስል አሳልፌ አልሰጥም ሲል በክሱ ቻርጅ ላይ ገልጿል፡፡ ሆኖም አቃቤ ሕግ ያሰበውን ያህል ምስክሮች ማግኘት አንዳልቻለና ለመመስከር ፈቃደኛ የሆኑ በርካታ ሰዎችም በሐሰት አንመሰክርም የሚል ምላሽ በመስጠት ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው ተሰምቷል፡፡ ይህን ተከትሎም መንግስት አዳዲስ ምስክሮችን ከሰሞኑ ሲመለምል እንደሰነበተ ተሰምቷል፡፡

ይህ በእንዲህ አንዳለ ኮሚቴዎቻችን ላይ ከነገ ጀምሮ በሐሰት እንዲመሰክሩ የተመለመሉ የሐሰት መስካሪዎች ዛሬ ሙሉ ቀን በማእከላዊ ወህኒ ቤት ስልጠና ሲሰጣቸው መዋሉ ታውቋል፡፡ ዛሬ ጠዋት ጀምሮ በፕሮጀክተር በመታገዝና የኮሚቴዎቻችንን እና ሌሎች ታሳሪዎችን ፎቶዎች በማሳየት አቃቤ ሕጎች ለሀሰት መስካሪዎቹን ‹‹እንዳትሳሳቱ ይህ እከሌ ይባላል፣ የምትመሰክሩትም እንዲህ እንዲህ እያላችሁ ነው›› በማለት ሲያለማምዱዋቸው እና ሲያስጠኗቸው አምሽተዋል፡፡ ይህ የዛሬው ስልጠና እስከአሁን ለመስካሪዎቹ ሲሠጡ ለነበሩ ስልጠናዎች ማጠናቀቂያ እንደሆነም ታውቋል፡፡ ሆኖም በሐሰት መስካሪዎቹ በተለይም አንዳንድ ሽማግሌዎች ‹‹ኧረ በደንብ አይታይም፤ አልገባንም›› ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ መስካሪዎቹ በስልጠናው ሲመሰክሩ ምንም መደንገጥ እንደሌለባቸውና ከፌዴራል እስከ መከላከያ ድረስ ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸው ተነግሯቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የሰሩት ወንጀል ካለ መንግስት እንደሚምራቸውና ከወረዳ ጀምሮ እስከ ፌዴራል ድረስ ከሚገኙ የመንግስት አካላት የተለያዩ ጥቅማጥቅምች እንዲያገኙ የድጋፍ ደብዳቤ እንደሚጻፍላቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡

ምንም እንኳ መስካሪዎቹ ከመንግስት መሰል የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ቃል ቢገቡላቸውም መንግስት መሰል ጉዳዮች ላይ ካለው ልምድ በመነሳት ቃል የተገባው ነገር ፈጽሞ ተፈጻሚ እንደማይሆንላቸው አንድ አንድ ምንጮች ገልጸዋል፡፡ አሰልጣኞቹ የመስካሪዎቹን ሞራል ለመጠበቅ እና ለማደፋፈር ‹‹እናንተ በአሁን ሰዐት የሃገሪቱ ትልቅ ባለውለታዎች ናችሁ›› እስከማለት የደረሱ ቢሆንም በሐሰት መስካሪዎቹ ዘንድ ያለው ፍርሃት ግን ከፍተኛ መሆኑ ታውቋል፡፡ ለዚህ ፍርሃታቸው ማስታገሻም ለእያንዳንዱ መስካሪ በነፍስ ወከፍ እስከ 4 የሚደርሱ ደህንነቶች ተመድቦለታል፡፡ አንዳንድ መስካሪዎች ግን ፍርሃታቸው አይሎ ‹‹ነገ ህዝቡ መጥቶ ፎቶግራፍ እንዳያነሳን ጥበቃ ይደረግልን›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

መስካሪዎቹ ብዙዎቹ ያለፍላጎታቸው በማያውቁት ጉዳይ ሊመሰክሩ እንደሆነ ለቤተሰባቸው ከመናገራቸው ውጪ ማንም እንደማያውቅባቸው ቢያምኑም ከምስክርነቱ በኋላ ስማቸው እና ምስላቸው ለህዝብ እንደሚበተን በማወቅ በከፍተኛ ሁኔታ ሰግተዋል፡፡ ዛሬ መስካሪዎቹ ለምሳ እረፍት በወጡበት ወቅትም ሲጨንቃቸውና ትካዜ ሲወራቸው ታይተዋል፡፡ ጭንቀቱ የምርም ነገ ቀብር ላይ ስለሚጠብቃቸውና ረሱል ሰ.ዓ.ወ የከፋ ወንጀል አድረገው በጠቀሱት የሀሰት ምስክርነታቸው (ሸሀደተ ዙር) ጉዳይ ከሆነ አሁንም ግዜ እንዳላቸው መግለጽ ያሻል፡፡ በሐሰት መስክሮ በዱንያም በአኺራም የሚገጥማቸውን የሁለት አለም ኪሳራ ከመቀበል ባለመመስከራቸው መንግስት የሚፈጽምባቸውን ጥቂት እንግልት በጸጋ ቢቀበሉ ይሻላቸዋል፡፡ ሰውን ከመፍራት አላህን መፍራት ከምንም የላቀ ነውና፡፡

እኛም ከነገ ጀምሮ የሚካሄደውን የሀሰት ጉባኤ አላህ በተአምሩ የመሪዎቻችን ሰላማዊነት የሚያጸድቅበት፣ የሀሰተኞችም ሴራ የሚከሽፍበት ከምንም በላይ በመሪዎቻችን እና በሌሎችም ወንድሞቻችን ላይ ያለ ወንጀላቸው በሐሰት የሚመሰክሩ ግለሰቦችን መጨረሻን አላህ በቀናት ውስጥ እንዲያሳየን አብዝተን ዱአ ማድረግ እንጀምራለን፡፡ የሀሰት ጭፍሮች እውነትን በስልጠና እና በዱንያ ግሳንግስ ለመናድ የሚያደርጉትን ጥረት አላህ በተአምሩ ውድቅ አድርጎ እንዲያሳየን በጾም፣ በሰላት፣ በቁኑት፣ በሰደቃና ዱአ በርትተን በቀን በለሊት እንለምነዋለን፡፡ ከነገ ጀምሮም ሁሉም ሙስሊም ዘወትር ከነበረው መንፈሳዊነቱ የበለጠ ጊዜ ሰጥቶ በዱአ እንዲበረታ አደራ እንላለን፡፡ አላህ የተበዳዮችን ዱዐ የሚሰማ፤ የአማኞችንም እንባ የሚያብስ ጌታ ነውና፡፡

አላሁ አክበር