በ2005 የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና ዲፓርትመንት አንድም ተማሪ ሳይቀበል ቀርቷል።

ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የሚያነሳ የሚጥለው ሁሉ በዚህ ሥርዓት ስም ቢሆንም፣ ምንም ዓይነት ትችት አልቀበልም ባይ ግትር አቋሙ ለእልፍ የአደባባይ ስህተቶች እየዳረገው እንደሆነ እያየን ነው። ታዲያ በዚህ ሂስ በናቀና በጠላ መንፈሱ ፍልስፍናን እንደጦር ፈርቶ ቢያዳክማት ይፈረድበት ይሆን? ለማንም ለምንም የማትመለሰውን ፍስፍናን ለመሸሽ ሲል ከጊዜ ወደጊዜ የትምህርት መስኩን የሚመርጡ ተማሪዎች ቁጥር መመናመንና ብሎም መጥፋት ሳያስጨንቀው በዝምታ አላየሁም አልሰማሁም ብሎ መቀመጡ በቂ የትችት መነሾ ሊሆን አይችልም ትላላችሁ? በሐሳብ ፍጭት ውስጥ ፖለቲካውን ከማሻሻል፣ ማኅበራዊ ስንክሳሮችን ከማጥራት፣ ምጣኔ ሀብቱን ከማሳደግ ይልቅ የ’ባለህበት ሂድ’ን ብሂል አውቆና ሳያውቅ መለማመዱ ለዚህ የዜጋ ክስረት ዳረገው። በ2005 የትምህርት ዘመን የፍልስፍና ትምህርትን ለማስተማር የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ አንድም ተማሪ ሳይቀበል ቀርቷል።

ኢሕአዴግ ይህ እንዳይከሰት ካበረከተው ይልቅ ችግሩ ይባባስ ዘንድ ያበረከተው አስተዋፅኦ ከባድ ነው። ከዚህ ይልቅ በሁሉም የትምህርት ዘርፎች የሠለጠነ ዜጋ ይህችን አገር ያጠናክራል፣ ይጠቅማል ብሎ ቢያስብና ሰፊ ንቃተ ህሊና እንዲፈጠር ቢያስብ የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ውዥንብሩን እያፀዳ ለትውልድ መፍትሔ የሚሆን ዜጋ ማፍራት ቢፈልግ ለተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች የሚያሳየውን እንክብካቤና አስገድዶ የማስተማር ስውር ብሎም ግልጽ ዘዴ በማኅበራዊ ሳይንሱም ዘርፍ በደገመው ነበር። እንደ ዩኒቨርሲቲ ያውም በዋናነት የማኅበረሰብ ሳይንስ የትምህርት ዘርፎችን የሚያስጠናው የስድስት ኪሎ ካምፓስ፣ አዳዲስ የፍልስፍና ተማሪዎችን ሳይቀበል ራሱን እንደ ምን ብሎ በዩኒቨርሲቲ ስም ሊጠራ ይደፍር ይሆን?

ገዢው ፓርቲ በጉልበት ሥራ ላይ ብቻ ባተኮረው የለውጥ አካሄዱ በእርግጥ በልቶ ለማደር ብቻ በሚፈልጉ ቁሳቁስ ፈላጊ ዜጎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ አያስደንቅም። ነገር ግን ምንም አልችልበት ያለውንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያበላሸ ጭራሽ ለራሱ የፖለቲካ ሥራ ማስኬጃ እያደረገው የመጣውን የትምህርቱን መስክ ማየት ይቻላል። ሕይወት በሆድ ብቻ የማትወሰን ሆና ሳለ የእያንዳንዱ ሰው የነፍስ ጥሪ፣ እምቅና ረቂቅ ሐሳብን በሚፈለገው መስክ እየቃኘ ከተፈጥሮ ዓላማ ውጭ ያደረጋቸው ብዙ ታዳጊ ዜጎች አሉ። ምናልባት አትኩሮተ ማሰላሰል (critical thinking) የሚባል ነገር ስለማያውቅ አገርን የሚያህል ነገር እያስተዳደረ የሕይወትን ዓላማ ሲደፈጥጥ ምንም አይመስለው ይሆናል። ለዚህም ይመስላል በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በንቃት ለዕድገት መሣሪያነት የምታገለግለውን ፍስልፍናን አቅሟን እያዳከመና እየሸሻት የመጣው።

ለሕዝብ ንቃተ ህሊና መጎልበት፣ ከፖለቲካ ዲስኩር ይልቅ ፍልስፍና የምትጫወተውን ሚና በጊዜ ተረድቶ  የእያንዳንዱን ዜጋ አዕምሮ የላቀና የበቃ ማድረግ ሲገባው፣ በተቃራኒ መንገድ እየተጓዘ የማኮላሻ ድርጊት መፈጸሙ አግባብ ሊሆን አይችልም። ይህም አካሄድ ዛሬም ብዙ ዋጋ እያስከፈለን ነው ነገም ገና ብዙ አሳር ሳያስቆጥረን አይቀርም። ቀደም ብለን እንዳልነው ሕይወት ሆድን ከመሙላትና ለሆድ ከመኖር ባለፈ ታላቅ መንፈሳዊ ዓላማ የታጨቀች ጭምር ናት። ምናልባት አስከፊው ድህነታችን ይህንን አንኳር ጉዳይ ቢያጨልምብን አይፈረድብንም። ለብዙ የዓለም ሥልጣኔ መነሻና መሠረት መሆን የቻለችውን የአቴናን ሀገረ መንግሥት ብንመለከት ግን፣ ከዛሬ የኢኮኖሚ ተረጂነቷ በላይ ትርጉም ያለው ሕይወት ኑረውና ሥራ ሠርተው ባላፉት ጥንታዊ አሳብያኖቿ ብሎም ሕዝቦቿ ልባችን በአድናቆት ስለሚሰረቅ ከፍ ያለ አክብሮት ሰጥተን እንድናልፍ እንገደዳለን።

ወደ ዘመነ ተሃድሶ መጥተን የፈጠራንና የአስተሳሰብን ምጥቀት ያየን እንደሆነ ግን በተወሰነ መልኩ አስቀድመን ምጣኔ ሀብትን ማሳደግ ተገቢና ዋና ነገር ልናደርገው እንችላለን። ለምሳሌ በዘመነ ተሃድሶ ወይም በዳግም ውልደት ዘመን የነበረችውን የጣሊያኑዋን ሀገረ መንግሥት ፍሎረንስ ከተማ እንመልከት። ማኪያቬሊን፣ ሊዎናርዶ ዳቪንቼን፣ ራፋኤልን፣ ወዘተ የመሳሰሉ ባለምጡቅ አዕምሮ አሳቢያንና የፈጠራ ሰዎች የማበርከቷ ምስጢር አንድም ምጣኔ ሀብቷ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ይገኝ ስለነበር ጭምር ነው። ይህም አሳብያኑንና የፈጠራ ሰዎቹ የግል ቤተ መጻሕፍት በራሳቸው ወጪ እስከማደራጀት ድረስ የገንዘብ አቅም እንዲኖራቸው ማስቻሉ፣ በሥራዎቻቸው ላይ ጥራትና ልቀት እንዲያገኙ ማገዙን እናያለን። በዘመነ ተሃድሶ የጣልያን አምስቱ ሀገረ መንግሥታት ምጣኔ ሀብት ከፍተኛ በመሆኑ በወቅቱ ጣልያን በአምስት ከተሞች ተከፋፍላ እንኳን የማትቀመስ አድርጓት ሊቆይ ችሏል።

 ልማት መቅደም አለበት። ይኼ አያጣላንም። ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አቴና አልያም እንደ ፍሎረንስ ወጥ ሕዝብ አይደለም። የብዙ ብሔር ብሔረሰቦች አገር ናት ኢትዮጵያ። ሰፊና ብዙ ባህል፣ ታሪክና ቅርስ  የታጨቀባት። ይህንን ከእኔ በላይ አታውቁም የሚለን ኢሕአዴግ የብሔር ብሔረሰቦችን እኩልነት ከማክበርና ከማስከበር አልፎ አንድ ኢትዮጵያን በልዩነት በሚያምኑ ልጆቿ ለመፍጠር ሲደክም ግን እያሳየን አይደለም። ለዚህም እንደ ምስክርነት ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም ተማሪዎች የማይጠበቅ ዘረኛ አስተሳሰብ ያላቸው ታዳጊዎችን የሚሸሽግበት ሥፍራ ማጣቱን መጥቀስ ይቻላል። ይህንን እንደገዛ እንደራሴ አባባል ሳስቀምጠው ‘ሰዎች ሚዛናዊና ምክንያታዊ አስተሳሰብ የሚይዙበትን መንገድ (በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ) የፍልስፍና ትምህርትን መጠቀም ስላልቻለ ወይም ስላቃተው አልያም ስላልፈለገ እየተከሰተ ያለ ችግር ነው።’

 ፍልስፍና ባሕሪዋ፣ ምርምሯና ጭንቀቷ በቀበሌ የታጠረ እንቆቅልሽ ላይ አይደለም፡፡ ከላይ የጠቀስኩትን እሳቤ የሚጋሩኝ ወይም የሚደግፉኝ በርካቶች ናቸው። ይህ ፍፁም አመዛዛኝ የመሆን አቅምን በፍልስፍና ትምህርት ያለመገንባት ችግር ከዘረኛ አስተሳሰብ ቀጥሎ፣ በተቃራኒ ፆታ አስተሳሰብ ላይ ያልተገራን ጠማማ ፍርድ እያዳበረ ዛሬ ዛሬ የምንሰማውን ግለሰቦች የሚዘፈቁበት የማኅበራዊ ሕይወት ቀውስ እያስከተለ ነው፡፡ እስከመቼ ለዚህ ችግር ዘላቂ መፍትሔ ማፈላለጉት ትተን እንቀመጥ ይሆን?
    
 አገር ማለት ሕዝብ ነው። ሕዝብ ክልል ባበጀለት ዳር ድንበሩ ሉዓላዊነቱ ተረጋግጦ የሚኖር ብቻ ሳይሆን እርስ በእርሱ ሲሰፋም ከመላው ዓለም ጋር የሚገበያይ፣ የሚማማር፣ አብሮ የሚኖር፣ ያለውን የሚያካፍል፣ የሚያስተምር ነው፤ መሆንም ያለበት እንዲያ ነው። ቀደም ሲል እንዳልኩት ሕይወት ዓላማዋ ሆድ አይደለም። ሆድ መሰንበቻ ነው። የሕዝብ ምጣኔ ሀብት እያንዳንዱ ግለሰብ በነፍስ ወከፍ ተካፍሎ የሚጠቀምበትና የሚገለገልበት እንጂ፣ የመጨረሻ የመኖር ግቡ እዚያ ላይ ተቋጥሮ ከዋናው የተፈጥሮ ዓላማ ያዋጣል ተብሎ የሚጋዝበት ነገር ሊሆን አይገባም። በባሕል ዕድገት ውስጥ፣ በእምነት ዕድገት ውስጥ፣ በሐሳብ ዕድገት ውስጥ መኖርን የመሰለ የሕይወት ስጦታን የማጣጣም ዋና ተልዕኳዊ መብታችን ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሊጥሰው አይገባም።

ሶቅራጦስ ሚሊጦስ የተባለውን ዓቃቤ ሕግ በምፀት እንዲህ ይለዋል “ያ አገሩን ወዳድ ደጉ ሰው” ይህንን የምፀት፣ የይቅርታ አድራጊነትና አለማወቅን በጥበብ የሚነግር አባባል ዛሬ እኔ ተውሼ ኢሕአዴግን ‹‹ያ ፈላስፋ ፈሪው አገር ወዳዱ ኢሕአዴግ›› ልለው ወደድኩ። ይህም ከላይ ለመዳሰስ በሞከርኳቸው ነጥቦች የተነሳ ነው። አገራችን ጠንካራ የልማት ሠራዊት ኖሯት በቁስ ሀብት ብቻ ብትበለፅግ ማን ዞር ብሎ ያያታል? አቴናን በእዝነ ህሊናችን ስናስብ ከፈላስፋዎቿ፣ ከጊዜው አንፃር አስገራሚው የሰፋኔ ሕዝብ ሥርዓቷ ቀድሞ አክሮፖሊ ይከሰትልናል? ወይስ ፍሎረንስን ስናስብ ዳቪንቼ የተወለደባት ከተማ ከማለት ይለቅ ስለሀብታም ነጋዴዎቿ ማውጋት ይቀናናል? ሕዝቧ የነበረው ከሌላው የተሻለ የተደላደለ ኑሮ ይታሰበናል? የጠዋት ጤዛ የሚያደርገንን አካሄድ ለምን እንመርጣለን?

የታይታ የታይታው ቀላል ስለሆነ? ውይይትና ክርክር እነማንን ሲገል አየን? ኢሕአዴግ በአገር በትውልድ ጉዳይ ሕዝቡን ለምን ባይተዋር ማድረግ ይቀናዋል? ያለባህል ዕድገት፣ ፍልስፍናዊ እሳቤ ልቀት፣ የኅብረተሰብ ንቃተ ህሊና መጎልበት የትኞቹ ናቸው የታላቋ አገር ባለቤት የተባሉት? ምነው ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ የስንቱን አገር ልምድና ተሞክሮ ሲፈትሽ ይኼን ይኼን ረሳው? የፍልስፍና ትምህርት ለብዙ ችግራችን መፍትሔ የምናገኝበት ሰፊ የጥበብና ዕውቀት መስክ ነው። ብንጠቀምበትና ታዳጊዎችን ብንኮተኩትበት ነገ ከመፍትሔ መፍትሔ የምናማርጥላቸው አሳብያን ሞልተው ሲተርፉን ማየት እንችላለን። ፍልስፍናንና ፈላስፋን መግደል ይብቃ!
 ከምንልክ ሳልሳዊ ብሎግ  ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው ysocratos@yahoo.com ማግኘት ይቻላል፡፡