ኡስታዝ አቡበከር በቃሊቲ ድብደባ እየተፈጸመበት ነው

ሰበር ዜና

ኡስታዝ አቡበከር በቃሊቲ ድብደባ እየተፈጸመበት ነው

ከሌሎች የኮሚቴው እስረኞች ተነጥሎ ለብቻው እንዲታሰር ተደርጓል

‹‹ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ምን ይሰራል? ውሳኔ እንደሆነ ከባለስልጣናት ወርዶ በኢቲቪ በኩል ተወስኖብናል፡›› ኡስታዝ አቡከር

የሕዝበ ሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ከሰኞ ምሽት ጀምሮ በቃሊቲ ከፍተኛ ድብደባ እየተፈጸመበት አንደሆነ ታወቀ፡፡ ኡስታዝ አቡበከር ቀድሞ ከዩሱፍ ጌታቸው ጋር ታስሮበት ከነበረው ዞን ለብቻው ተነጥሎ ወደ ዞን አንድ መወሰዱ የታወቀ ሲሆን ባሳለፋቸው ሁለት ሌሊቶችም ከፍተኛ ግርፋት ሲፈጸምበት እንደነበር ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ኡስታዝ ትላንት ማክሰኞ ሰውነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ደካክሞና አባብጦ የታየ ሲሆን ከወትሮው በተለየ በአምስት ፖሊሶች ተከቦም ቤተሰቦቹ እንዳዩትና ቤተሰቦች ሀዘናቸውን መቆጣጠር አቅቷቸው ያለቅሱ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ዛሬም ሁኔታው የከፍ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ መንግስት በማእከላዊ ያደረሰው ስቃይና መከራ ሳይበቃው መልሶ ወደዚህ ተግባር ለምን እንደገባ ማወቅ ያልተቻለ ሲሆን ምንአልባትም ባለፈው ሳምንት በችሎት ፌት በተናገረው ንግግር ሳይሆን እንደማይቀር ተገምቷል፡፡

ኮቴዎቻችን ባለፈው ሳምንት በነበረው ችሎት የ‹‹ጂሐዳዊ ሐረካት›› መታየትን ተከትሎ ለፍ/ቤቱ አቤቱታ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆን ብዙዎቹ የህሊና እስረኞችም በፍ/ቤቱ አሰራር ላይ ቅራኔ እንዳላቸው ገልጸው ነበር፡፡ ፊልሙ በወቅቱ በኢቴቪ እንዳይተላለፍ ከታገደ በኋላ መንግስት በራሱ ሕጉን በመጣስ ፊልሙን ያስተላለፈው ሲሆን ፍ/ቤቱም ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ ሳያደርግ አድበስብሶ ለማለፍ መሞከሩና ውሳኔው ያለበት ሁኔታ አለመታወቁ አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ኡስታዝ አቡበከርም በቀዳሚነት ኮሚቴዎቹ የተሰባሰቡት እና የጠየቁት የእምነት ነፃት መሆኑን፤ ይህንን ህገ-መንግስታዊ መብት መጠየቅ እንደወንጀል ተቆጥሮ መከሰሳቸው አግባብ እንዳልሆነ በማንሳት፤‹‹የፍርድ ቤቱ ስራ አልገባንም፤ ለምን ትእዛዙ መድረስ አለመድረሱን ለማረጋገጥ እንኳን አልፈለገም፤ በግልጽ ህዝብ ሁሉ እንዳወቀው ትእዛዙ የኢቲቪ መዝገብ ቤት ደርሶ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ነው መልሶ ወጪ የሆነው፤ በማእከላዊ እስርቤት የሰቆቃ ተግባር የፈፀሙብን ሰዎች (ፍርድ ቤቱ ውስጥ ይገኝ ወደነበረው የማእከላዊ ገራፊ ኮማንደር ከተማ እየጠቆመ) የሰሩት ወንጀል ምንም ሳይሰማቸው አሁንም በፍርድ ቤት እኛን ወንጀለኛ ለማስባል ከህግ ውጪ ምስክሮችን እያስፈራሩ የሀሰት ምስክርነት ሲያስመሰክሩ ፍርድ ቤቱ ነፃ ሆኖ ይታዘባል ብለን ዝም ብለናል፡፡ አሁን ግን በህዝብ ፊት ኢቴቪ ወንጀለኛ መሆናችንን አውጇል፤ ከአሁን በኋላ ከፍርድ ቤቱ የምንጠብቀው ነገር ምንድን ነው? ፍርድ ቤቱ ከዚህ በኋላ ምን ይሰራል? ውሳኔ እንደሆነ ከባለስልጣናት ወርዶ በኢቲቪ በኩል ተወስኖብናል፡›› ብሎ ንግግር ያደረገ ሲሆን፤ አህመዲን ጀበልም በበኩሉ ‹‹የፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ኢቴቪ የደረሰው 11፡00 ሰአት ላይ ነው፤ ከዚህ ሰአት በኋላ የትኛውም የኢትዮጵያ ፍርድ ቤት አዲስ ጉዳይ ተቀብሎ አጣርቶ እግድ ሊሰጥ አይችልም፤ ትእዛዙ ይግባኝ ተብሎበታል ቢባል እንኳን ይግባኙ ሊሆን የሚችለው ጠዋት ላይ ነው፤ ኢቲቪ የፍርድ ቤቱን የእግድ ትእዛዝ በምሽት ጥሶ ዶክመንተሪውን ማቅረቡ እንዴት አያስጠይቀውም?›› የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር፡፡ አሁንም አቡበከር ድብደባ እየተደረገበት ያለው ምክንያት ይህ የፍ/ቤት አቤቱታው ሳይሆን እንዳልቀረ ተሰምቷል፡፡

የኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በአንቀጽ 19፣20 እና 21 ‹‹የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደዱም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት እንደማይኖረው እንዲሁም በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት እንዳላቸው በግልጽ ደንግጓል፡፡ ሆኖም ሕገ መንግስቱን እንዳሻው መጣስ ባህሪው ያደረገው መንግስት በየጊዜው ኮሚቴዎቻችንን ማሰቃየቱና ከፍርድ ቤት ውሳኔ በፊት አሸባሪ እያለ በሕዝብ ሚዲያ መዝለፉን ተያይዞታል፡፡ ዜጎች ደማቸውን ያፈሰሱለት ሕገ መንግስት እንደቀልድ በየእለቱ በከንቱ እየተጣሰ ይገኛል፡፡ ሕጉን ማን ሊያስከብረው እንደሚችልም ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡ ሁላችንም መሪዎቻችንን በዱአችን እናስባቸው፤ አላህ ከጨቋኞች እጅ ያውጣቸው፣ አሚን!