“ሠራዊቱና አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚለው ቀዩ መፅሃፍ ሠራዊቱ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ አለመሆኑን ያረጋግጣል::


የአረና ትግራይ ለዲሞክራሲና ሉዓላዊነት (አረና) ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ገብሩ አስራት በበኩላቸው፤ ስለ ኤግዚቢሽኑ እንዲሁም ስለ ወታደራዊ ተግባራቱ በሚዲያ እየቀረቡ ያሉትን ከመከታተል ባለፈ በአካል እንዳልተመለከቱት በመግለፅ፤ በአሉን አስመልክቶ እየቀረቡ ያሉት መሣሪያዎች ግን መከላከያው ብቃት ያለው መሆኑን የሚያስመሰክሩ ሆነው እንዳላገኟቸው አስታውቀዋል፡፡ የሀገራችን መከላከያ ሃይል ተጠናክሮ የሀገሪቱን ደህንነት በሚገባ እንዲያስጠብቅ እፈልጋለሁ የሚሉት አቶ ገብሩ፤ የኛ ተቀናቃኞች ዛሬ ታንክና ተዋጊ ጀት ከመገጣጠም አልፈው ኒውክለር እየሰሩ ባለበት ሁኔታ እነሱን የሚመጥን ዝግጅት ሳናደርግ የመከላከያው ብቃት አድጓል ማለት እንደማይቻል ይገልፃሉ፡፡ በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 87 ንዑስ አንቀፅ 5 ላይ የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነፃ በሆነ አኳኋን ያከናውናል የሚለውን ድንጋጌ መነሻ በማድረግ የገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም የሆነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ ለሠራዊቱም ዋና መመሪያና መንቀሳቀሻ መሆኑ ተገቢ አለመሆኑን አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ቀዩ መፅሃፍ እየተባለ የሚጠቀሰውና “ሠራዊቱና አብዮታዊ ዲሞክራሲ” የሚለው መፅሀፍ የሠራዊቱ ዋና መመሪያ መሆኑ መገለፁ፣ ተቋሙ ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ነፃ አለመሆኑን እንደሚያረጋግጥም አቶ ገብሩ ተናግረዋል፡፡የአረና ሊ/መንበር በቀመጠል ሲናገሩም፤ የሁሉም ነገር አድራጊና ፈጣሪ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ብቻ እንደሆነ ተደርጐ መቅረቡ እሳቸው ከሌሉ የሠራዊቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ምን ይሆናል የሚለውን ጥያቄ እንደሚያጭርና የሁሉም ነገር አድራጊ ፈጣሪ እሳቸው ከሆኑ ሌላው ከተላላኪነት የዘለለ ሚና የለውም የሚለውን አንደምታ አጉልቶ እንደሚያሳይም ገልፀዋል፡፡ የመድረክ አመራር አባል የሆኑት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ እንዲሁ ኤግዚቢሽኑን በጊዜ መጣበብ ሊመለከቱት እንዳልቻሉ፣ ነገር ግን በሚዲያ የሚተላለፉትን መልክቶች እና ህዝቡ የሚሰጠውን አስተያየት ማጤናቸውን በመጠቆም ስለወታደራዊ ሃይሉ የተጋነኑ መልክቶች የተላለፉ እንደሚመስላቸው ገልፀዋል፡፡ በበአሉ አከባበር ላይ የተንፀባረቀውም የመከላከያው የኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት እንጂ የሰው ኃይል ልማት፣ በመከላከያ ውስጥ የሚነሱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ መከላከያው ጥቃትን የመቋቋም አቅሙን የሚፈትሹ ጉዳዮች እንዳልሆኑ ያስታወሱት ፕ/ር በየነ፤ በተለይ በአሁኑ ሠዓት በአመራሩና በተራው አባል መካከል የጌታ እና የሎሌ አይነት የእዝ ሰንሰለት ነው ያለው የሚል ቅሬታ እንደሚቀርብ፣ በዚህ አይነት ቅሬታ ከሠራዊቱ የወጡ አባላት የነገሯቸውን በመጥቀስ ገልፀዋል፡፡
ይህን ወቅት ጠብቆ እንዲህ ባለ ሥነሥርዓት የወታደሩን አቅም የማቅረቡ ፋይዳ ምንድን ነው የሚል ጥያቄ አለኝ የሚሉት ፕሮፌሰሩ፤ “አሁን እየተወራለት ያለው የወታደራዊ ኢንዱስትሪ ከኢህአዴግ በፊት በነበረው ስርአት የተጀመረበት ሁኔታ ነበር፡፡ እነሱ ብቻ የጀመሩት አድርገው ማቅረባቸው ተገቢ አይደለም፤ አበልፅገነዋል፣ አሻሽለነዋል የሚሉ ከሆነ መልካም ነው፡፡ የሁሉም ነገር ጠንሳሽ ነን የሚለው ግን የሚያስኬድ አይደለም” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ አመራር እና የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሠይፉ፤ አውደ ትርዒቱን ገና እንዳልተመለከቱት ነገር ግን በሚዲያ የተከታተሉትም ሆነ ስታዲየም በነበረው የበዓሉ መዝጊያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው እንደታዘቡት፣ የመከላከያ ሃይላችን ጠንካራ ሆኗል ከሚሉት ሃይለ ቃሎች ውጪ ጠንካራ መሆኑን የሚያረጋግጡ ማሳያዎች እንዳልተመለከቱ ገልፀዋል፡፡ “ከዚህ የበለጠ በጣም የሚያስፈሩ የደርግ ሠልፎችን አይቼ አውቃለሁ” ያሉት አቶ ግርማ፤ የመከላከያ ቀን መከበሩ መልካም ሆኖ ሳለ ዓላማው ግልፅ ባለመሆኑ አልገባኝም፣ ከዚህ ቀደም ይወራ ከነበረውም የተለየ አዲስ ነገር አልቀረበም” ብለዋል፡፡
የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ራሱን ችሎ የወጣ ድርጅት መሆኑን ያስታወሱት አቶ ግርማ፤ ሆኖ ሳለ ከመከላከያ ጋር ተሳስሮ መቅረቡ በራሱ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ በአውደርዕዩ ላይ ቀረቡ የተባሉ እንደሰው አልባ ጀት የመሳሰሉት ለእይታ መቅረባቸውን ሲቃወሙም ተቀናቃኝ ሃይሎች ማክሸፊያውን ለማዘጋጀት እድሉን ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡
በኤግዚቢስን ማዕከል የቀረበውን መጐብኘታቸውን የገለፁት ኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ፤ እዚህ የፈጠራ አቅም ላይ መደረሱ በራሱ የሚደነቅ ሆኖ ሳለ የቀረቡትን ናሙናዎች ብቻ በማየት አጠቃላይ ወታደራዊ አቅማችን አድጓል ለማለት እንደማያስደፍር ተናግረዋል፡፡ “የመከላከያው አቅም በሚገባ ጐልብቷል ለማለት የቀረቡት ወታደራዊ ቴክኖሎጂዎች አድገውና ተባዝተው መቅረብ አለባቸው” የሚሉት አቶ ሙሼ፤ አንዳንድ ከወታደራዊ ቴክኖሎጂ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ነገር ግን በመከላከያ የኢንዱስትሪ ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች እንዳላስደሰታቸው ይናገራሉ፡፡

በግል ባለሀብቶች፤ ኢንቨስተሮች ሊከወኑ የሚችሉ የመኪና መጠጋገንና መገጣጠም የመሳሰሉት ሥራዎች ከመከላከያ እጅ ሊወጡ እንደሚገባቸውም አቶ ሙሼ አሳስበዋል፡፡ “የመኪና መጠጋገን የመሳሰሉ ስራዎች ውስጥ መንግሥትና የመንግሥት ተቋማት ሊገቡ አይገባም፤ ይሄን የግል ዘርፉ ሊሰራው ይችላል፡፡ አንዳንዶችም ሰርተው እንደሚቻል እያሳዩ ነው፡፡ መንግሥት የሚገባው የግሉ ዘርፍ ሊሸፍነው የማይችለው ሲሆን በቻ ነው” ያሉት አቶ ሙሼ፤ ወታደራዊ ተቋሙ እስካሁን የሰራውን በአጠቃላይ ቢያደንቁም ይበልጥ ትኩረት ሊሰጥ የሚገባው ኢትዮጵያ አንድ ችግር ቢገጥማት በብቃት እንድትከላከል የሚያስችላትን ታንክ፣ አውሮፕላን እና ሌሎች ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን በማምረቱ ላይ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡አዲስ አድማስ /ምንልክሳልሳውብሎግፖስት