የቡድን አንቅስቃሴ ያደርጋሉ የተባሉ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው !!!

ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸውብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት
በምርጫው እንቅስቃሴ ዙሪያ መንግሥት ለሦስት አባቶች ማስጠንቀቂያ ሰጠ
• በስመ ደኅንነት ያጭበረበሩ 40 ግለሰቦች ምርመራ እየተካሄደባቸው ነው
• እነንቡረ እድ ኤልያስ የመራጮች ዝርዝር እንዲሰጣቸው ጫና እየፈጠሩ ነው

ለስድስተኛው ፓትርያሪክ ምርጫ እየተደረገ በሚገኘው ቅድመ ዝግጅት፣ የየራሳቸውን ‹ምርጥ› ይዘው የቡድን እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉ አካላትን ያስተባብራሉ ለተባሉ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት መንግሥት ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መስጠቱ ተሰማ፡፡ ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት÷ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ እና የምሥራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ናቸው፡፡

ለሐራዊ ምንጮች የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ማስጠንቀቂያው የተሰጣቸው ሰኞ፣ የካቲት 11 ቀን 2005 ዓ.ም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ተጠርተው ሲኾን፣ ያነጋገሯቸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኀይለ ማርያም ደሳለኝና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አማካሪ አቶ ጸጋዬ በርሄ ናቸው፡፡ ባለሥልጣናቱ÷ የፓትርያሪክ ምርጫው ቤተ ክርስቲያኒቱ ባጸደቀችው የፓትርያሪክ ምርጫ ሕገ ደንብ መሠረት ብቻ መፈጸም እንደሚገባው መናገራቸው ተዘግቧል፡፡ ‹‹የራሳችኹን ሕገ ደንብ አክብራችኹ መሥራት ሲያቅታኹ በመንግሥት ላይ የሚቀርበውን ሰበብ ማስቆም አለባችኹ፤ በየካፌው፣ በየሬስቶራንቱ፣ በየሆቴሉና በየልኳንዳ ቤቱ እየተሰበሰቡ የሚመክሩትንና የምታስተባብሯቸውን ቡድኖችም መግታትና መቆጣጠር አለባችኹ፤›› የሚል ማሳሰቢያ መስጠታቸው ተነግሯል፡፡
ሦስቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በምርጫው ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ቡድኖች ስለመኖራቸው በማመን አስተያየት መስጠታቸው ተመልክቷል፡፡ የተለያዩ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን በቢሯቸውና በማረፊያቸው ሲያነጋግሩ የተለያየ ስምና መታወቂያ ይጠቀማሉ ስለሚባሉት የቡድኖቹ መሪዎችም ሊቃነ ጳጳሳቱ ሲያብራሩ፣ ‹‹የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት መታወቂያ የሚያሳዩና ከመንግሥት እንደተላኩ የሚናገሩ፣ መንግሥት እንዲመረጥ የሚፈልገው አቡነ እገሌን ነው፤ አቡነ እገሌን መምረጥ አለባችኹ፤ አቡነ እገሌን ካልመረጣችኹ የእገሌ ተቃዋሚ አባል ናችኹ ማለት ነው፣ እናሰራችኋለን፤ ከሥራ እናባርራችኋለን፤›› የሚሉ በመኾናቸውና ይህም በየዕለቱ የሚታዘቡት ጉዳይ በመኾኑ በመንግሥት ወደማማረር መድረሳቸውን አስረድተዋል ተብሏል፡፡
በዚህ ሳምንት ሰኞ ከብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱ ጋራ የተደረገውን ውይይት ተከትሎ የመንግሥት ስቭል፣ ፖሊስና ወታደራዊ ደኅንነት ጥምር ግብረ ኀይል በመንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽር ውስጥ ለሁለት ቀናት ባካሄደው ክትትልና አሠሣ፣ በስመ ደኅንነት ሲንቀሳቀሱ ነበር የተባሉ 40 ግለሰቦችን በትናትናው ዕለት በቁጥጥር ሥር ማዋሉ ተዘግቧል፡፡ አሠሣው እኒህ ስመ ደኅንነቶች በየፊናቸው ከሚመሯቸው ቡድኖች (የተለያዩ ሊቃነ ጳጳሳትን ለፕትርክና በማጨት የተስማሙ የመነኰሳትና ካህናት ስብስቦች ናቸው) ጋራ ያዘወትሯቸዋል በሚባሉ ካፌዎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎችና ልኳንዳ ቤቶች ተጠናክሮ ቡድኖቹን የመበተንና የማስጠንቀቅ ሥራ ሲሠራ መዋሉ ተነግሯል፡፡
በመንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽርና ዙሪያ ሲንቀሳቀሱ በጥምር የደኅንነት ኀይሉ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት 40 ግለሰቦች መካከል 35ቱ ተይዘው ማንነታቸውን ሲጠይቁ ያሳዩት መታወቂያ ሐሰተኛ ኾኖ ተገኝቷል፤ የአምስቱ መታወቂያ ደግሞ ትክክለኛ ቢኾንም ከሚመለከተው አካል ትእዛዝ ሳይሰጣቸው ራሳቸውን ለቡድናዊ ጥቅም አሰማርተው መገኘታቸው ተረጋግጧል ተብሏል፤ አብዛኞቹ ከክልሎች የመጡ፣ በአንድ ወገን የተሰጣቸውን ቡድናዊ ተልእኮ ለማስፈጸም የሚላላኩ እንጂ የመንበረ ፓትርያሪኩን መግቢያና መውጫ በሮች እንኳ በቅጡ የማያውቁ መኾናቸው በቁጥጥር ሥር ሲውሉ በታየባቸው መርበትበትና ድንጋጤ ይበልጥ ራሳቸውን ያጋለጡ መኾኑ ተገልጧል፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ወገኖች መንግሥት ‹‹ተጽዕኖ አላደረግኹም፤ ጣልቃ አልገባኹም›› ለማለት ያህል የወሰደው ርምጃ ሊኾን ይችላል በሚል መረጃውን በጥርጣሬ ይመለከቱታል፤ በአንጻሩ የምርጫው እንቅስቃሴ ከመንግሥት ቀጥተኛ እይታና ቁጥጥር ውጭ ሊኾን እንደማይችል ይከራከራሉ፡፡ ሌሎች ወገኖች ደግሞ መንግሥት በጥምር የደኅንነት ኀይሉ እያካሄደው ስለ መኾኑ የተዘገበው የቁጥጥር እንቀስቃሴ የየራሳቸውን ፓትርያሪክ አጭተው በመንበረ ፓትርያሪኩ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች÷ በአንድ በኩል የመንግሥትን የጸጥታ፣ የደኅንነትና የመከላከያ መዋቅሮች ለሚሹት ዓላማ ለመጠቀም የሄዱበትን ርቀት (በመንግሥት ቋንቋ የኪራይ ሰብሳቢዎችን ትስስር) የሚያሳይ ሲኾን በሌላ በኩል ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ክብሯን ለማስጠበቅ ካለመቻሏ የተነሣ የምትገኝበትን አስከፊ ተቋማዊ ውርደት/ዝቅጠት እንደሚያሳይ ተመልክቷል፡፡
በዚህ ዜና ርእሰ ጉዳይ እንደሰማነው ከቀድሞውም እንደሚታወቀው ሁሉ፣ የዚህ ተቋማዊ ውርደት መነሻዎች የእኛው ሊቃነ ጳጳሳት እንደኾኑ መጠቀሱ በእጅጉ የሚያሳፍር ነው፡፡ ቡድኖቹን በማንቀሳቀስ ረገድ÷ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ ለብፁዕ አቡነ ማቲያስ፣ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ‹‹ቀጣዩ ፓትርያሪክ ከወሎ መመረጥ አለበት፤ ጊዜው የወሎ ነው›› የሚለውን ቡድን (w – group) በመደገፍ ብፁዕ አቡነ ገብርኤልን ወይም ብፁዕ አቡነ ማቲያስ ዘካናዳን፣ ብፁዕ አቡነ አብርሃም ደግሞ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤልን በመደገፍ ስማቸው ይነሣል፡፡ የድጋፉ ስለምንነት በተለይ ለመጀመሪያዎቹ ሁለቱ በዋናነት ከጎጠኝነት ጋራ የተያያዘ ቢኾንም ሁሉም በቀጣይ ስለሚያገኘው ሹመት፣ ሥራ ወይም የኾነ ዐይነት ግላዊና ቡድናዊ ጥቅም ወይም አንዱ ሌላው ላይ ስላለው ቂምና ጥላቻ መኾኑ ደግሞ በእጅጉ ከማሳፈርም አልፎ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡
ሹመትና ሥራ ወይም የኾነ ዐይነት ሌላ ጥቅም ፈልጎ አሉታዊ የምርጫ ድጋፍ ማድረጉ፣ በቂምና ጥላቻ መነዳቱ በውጤቱ የሚገኘውን ሹመት መንፈሳዊ ወይም ከመንፈስ ቅዱስ ነው እንደማያሰኘው ግልጽ ነው፡፡ እስኪ ይህም ይኹን ብንል እንኳ፣ የየራሳቸውን ፓትርያሪክ አጭተው በየካፌው፣ በየሬስቶራንቱ፣ በየሆቴሉና በየልኳንዳው ተሰብስበው የሚዶልቱት የ‹መነኰሳት›፣ ‹ካህናት›ና ወይዛዝርት ስብስቦች ለሹመቱም ለሥራውም የሚታመኑ፣ የሚበቁም እንዳልኾኑ ባለፉት ዓመታት በሚገባ የምናውቃቸው ናቸው፡፡
‹‹አቡነ ማቲያስን ለማስመረጥ ቤቴንም ቢኾን እሸጣለኹ›› የሚሉት ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ
ለአብነት ያህል÷ ‹‹መንግሥት የሚፈልገው አቡነ ማቲያስን ነው፤ አቡነ ማቲያስን መምረጥ አለባችኹ፤ አቡነ ማቲያስን ካልመረጣችኹ እናስራችኋለን፤ እናባርራችኋለን›› በሚል እየተንቀሳቀሱ ያሉት እነ ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ፣ መጋቤ ካህናቱ ኀይለ ሥላሴ ዘማርያም እና ወ/ሮ እጅጋየሁ በየነ ምን እያደረጉ ነው? ቡድናዊና ግላዊ ጥቅም፣ ቂምና ጥላቻ የሚገፋቸው እኒህ ግለሰቦች፣ ለፕትርክና ሊመረጡ ይችላሉ ያሏቸውን ሌሎች ብፁዓን አባቶች ስም በየሚዲያው የማጥፋት ዘመቻ ይዘዋል፤ ሚዲያውም ያለአንዳች ሚዛናዊነት የእነርሱን ክሥ ያስተጋባል (የዛሬው ሰንደቅ ጋዜጣ አንዱ ነው፤ በዛሬው ዕለትም እኚህ ሴትዮ በአድልዎና በሕገ ወጥ መንገድ ከያዟቸው የቤተ ክህነት ቤቶች መካከል አንዱ የኾነውንና በአራት ኪሎ የሚገኘውን ቀራንዮ የጉዞ ወኪል የከፈቱበትን ቢሮ የሰንደቅ ጋዜጣ ማከፋፈያ አስመስለውት ውለዋል)፡፡ በስመ ደኅንነት የሚንቀሳቀሱ ነገር ግን የጸጥታና ደኅንነት ባልደረቦች የሚመስሉ በርካታ በገንዘብ የተገዙ ግለሰቦች መንበረ ፓትርያሪኩን እንዲያጥለቀልቁ ያደረጉት በቀዳሚነት እነእጅጋየሁ ናቸው፡፡
እነንቡረ እድ ኤልያስ በአዲስ አበባ አራቱ አህጉረ ስብከት፣ በባሕር ዳር፣ በደሴ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በአሰበ
ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ
ተፈሪና በጅጅጋ አህጉረ ስብከት ስልክ እየደወሉ ከጠቅላላው መራጭ ከ600 በላይ የሚኾኑ መራጮችን ስም ዝርዝር አሳውቁን እያሉ ጸሐፊዎችንና ሥራ አስኪያጆችን እያስገደዱና እያስፈራሩ ነው፡፡ በተወሰኑ አህጉረ ስብከትም ሥራ አስኪያጆቹ የካህናት፣ ገዳማትና አድባራት አበ ምኔቶችና እመ ምኔቶች እንዲሁም የምእመናን ተወካዮችን ሰብስበው ድምፅ መስጠት ያለባቸው ለአቡነ ማቲያስ መኾን እንደሚገባው በማሳሰቡ ረገድ ተሳክቶላቸዋል፡፡ ጉዳዩን በተመለከተ የአዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሁለት ጸሐፊዎችና ሥራ አስኪያጆች ለየሊቃነ ጳጳሳቱ ሪፖርት ያደረጉ ሲኾን ሊቃነ ጳጳሳቱ ብፁዕ አቡነ ዳንኤልና ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ለእነ ንቡረ እድ ኤልያስና ለተላላኪዎቻቸው ስመ ደኅንነቶች ጠንከር ካለ ማሳሰቢያ ጋራ ምላሽ መስጠታቸው ታውቋል፡፡
የእነእጅጋየሁ ድፍረት በዚህ ብቻ የሚያበቃ ሳይኾን አስመራጮችን በግልጽ እስከማጨናነቅም የደረሰ መኾኑም ታውቋል፡፡ ለአስመራጭ ኮሚቴው ቅርበት ያላቸው ምንጮች እንደሚያስረዱት የሴትዮዋ ድፍረት፣ ‹‹አቡነ እገሌ በዕጩነት መካተት ወይም መመረጥ እንደማይገባቸው የሚያስረዱ መጣጥፎችን በኮሚቴው ስብሰባዎች ላይ ለማስነበብ እስከ መሞከር የደረሰ ነው፤›› ይላሉ፡፡ የመረጃ ምንጮቹ የአንባቢውን ማንነት ባይገልጡ ም ሙከራው የአስመራጭ ኮሚቴውን ሰብሳቢ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን አስደንግጧል፤ በተለይም የታዋቂ ምእመናን ተወካዮቹን እነ ቀኝ አዝማች ኀይሉ ቃለ ወልድንና አቶ ዓለማየሁ ተስፋዬን ክፉኛ አስቆጥቷል፡፡ ‹‹በስመ ደኅንነቶቹ ላይ የተወሰደው ርምጃ አስመራጭ ኮሚቴውን ሳያነቃቃው አልቀረም፤›› ይላሉ የዜናው ምንጮች፡፡
የኾነው ኾኖ ነገ፣ የካቲት 14 ቀን 2005 ዓ.ም የስድስተኛው ፓትርያሪክ አስመራጭ ኮሚቴ አጣርቶ የመረጣቸውን አባቶች ለቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ የሚያቀርብበት ዕለት ነው፡፡ እስከ ትላንት ምሽት በነበረን መረጃ ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል፣ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል እና ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ከካህናትና ምእመናን በተሰበሰቡ ጥቆማዎች ብዛት ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸው ታውቋል፡፡
ቀደም ባስነበብነው ዘገባ እንዳስረገጥነው፣ በብዙ ዕጩዎች መጠቆም ለፓትርያሪክነት መታጨትን ወይም ለፓትርያሪክነት መመረጥን አያረጋግጥም፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴው መግለጫ ደጋግሞ እንደሚያሳስበው የጥቆማው መረጃዎች ለዕጩዎች መለያ እንደ ግብአት ብቻ የሚያገለግል ነው፤ ዕጩዎቹ እነማን እንደሚኾኑ የሚታወቁት ቅ/ሲኖዶስ በነገው ዕለት ከኮሚቴው ተለይተው በሚቀርቡለት አባቶች ላይ ተወያይቶ ስማቸውን በብዙኀን መገናኛ ይፋ ሲያደርግ ብቻ ነው፤ ፓትርያሪኩም የሚታወቀው የካቲት 21 ቀን በሚሰጠው የመራጮች ድምፅ ብቻ ነው፡፡