የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲ.ፒ.ጄ ሰለሞን ከበደ በአስቸኳይ ይፈታ ሲል ጠየቀ

እውቁ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋቹ ሲ.ፒ.ጄ (Committee To Protect Journalists) በቅርቡ በደህንነቶች ታፍኖ የተወሰደው የቀድሞ የሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት ማኔጂንግ ኤዲተር በአስቸኳይ ይፈታ ሲል ጠየቀ፡፡ መሰረቱን አሜሪካን ኒውዮርክ ያደረገው ሲ.ፒ.ጄ ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ሰለሞን ከበደ ከሁለት ሳምንት በፌት በመንግስት ኃይሎች ተወስዶ ማእከላዊ ወህኒ ቤት ከታሰረ በኋላ ከቤተሰብም ሆነ ከጠበቃው ጋር እንዳይገናኝ እቀባ ተጥሎበታል፡፡ ሰለሞን አሁን ያለበት የጤንነት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ጨምሮ የገለጸው መግለጫው እስከአሁን ምንም ክስ እንዳልተመሰረተበትና ፍርድ ቤትም ቀርቦ የ28 ቀናት ማለትም ለየካቲት ስድስት ቀጠሮ እንደተሠጠው አውስቷል፡፡

ሰለሞን ከበደ አሁን ከስርጭት በታቀበችው በየሙስሊሞች ጉዳይ መጽሔት ማጂንግ ዳይሬክተር በመሆን በሳል ጽሑፎችን ለሙስለሊሙ ህብረተሰብ ሲያቀርብ የቆየ ሲሆን እነደ ሲ.ፒ.ጄ መግለጫ የአሁኑ እስርም መነሻ ይኸው በመጽሔቱ ላይ ሲያበረክታቸው በነበሩ ጽሁፎች መነሻነት ነው፡፡ መግለጫው ከሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የሙስሊሞች ጉዳይን ጨምሮ ቢያንስ ሶስት የህትመት ውጤቶች ስራቸውን እንዲያቆሙ መገደዳቸውንና የአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ ዘጋቢ ታስራ እንደነበር፤ ዩሱፍ ጌታቸው ደግሞ አሁንም በእስር ላይ እንደሚገኝ አስታውሷል፡፡ የሲ.ፒ.ጄ የምስራቅ አፍሪካ ቢሮ አማካሪ ቶም ሩድስ እንዳሉት ‹‹ሰለሞን የታሰረው ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሚፈጸምበት ማእከላዊ እስር ቤት በመሆኑ ጉዳዩ ያሳስበናል፤ ባለስልጣናትም በአስቸኳይ ይልቀቁት›› ብለዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰብአዊ መብቶች ተቆርቋሪው ሂውማን ራይትስ ዎች (Human Rights Watch) ከሰሞኑ ባወጣው የፈረንጆች 2012 አመታዊ የአገራት የሰብአዊ መብት ሪፖርት ኢትዮጵያን አስመልክቶ ባካተተው ሀተታ የሙስሊሙ ማህበረሰብ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት በእስር እየተንገላቱ መሆን፣ ፖሊስ በሰላማዊ ሙስሊም ተቃዋሚዎች ላይ በኦሮሚያ እንዲሁም በአዲስ አበባ አወሊያ መስጊድና አንዋር መስጊድ የወሰዳቸውን የሀይል እርምጃዎች፣ በሀምሌ 2004 በርካታ ሙስሊሞች ከተለያዩ አካባቢዎች በገፍ መታሰራቸውን፣ ጋዜጠኛ ዩሱፍ ጌታቸው ቤቱ ተከብቦ እና ሙያውን የሚያከናውንባቸው ንብረቶች ተቀምቶ ለእስር መዳረጉን፣ ከሙስሊሞች ሰላማዊ ተቃውሞ ጋር ተያይዞ የታሰሩ በርካታ ሙስሊሞች በእስር ቤትም ስቃይ ማስተናገዳቸውን ዘርዝሯል፡፡