ህዝብን ማታለል ክፉ እርግማን ነው፡፡ የማታ ማታም ያስከፍላል፡፡

ስለግልፅነት እያወራን የበለጠ ሚስጥራዊ የምንሆን ከሆነ ያው መዋሸት ነው፡፡ ዛሬ ያልነውን ነገ ካልደገምነው ያው መዋሸታችን ነው፡፡ ሰውን በሸራ ኳስ እያጫወትን እኛ በካፖርተኒ የምንጫወት ከሆነ ያው ማጭበርበራችን ነው፡፡ ያለአቅማችን ጉልበተኛ ነን ማለትም ሆነ ጉልበተኛ ሆነን ምስኪን ኮሳሳ ነን ማለትም ያው መዋሸት ነው፡፡ እያየን አላየንም፣ እየሰማን አልሰማንም፣ እያጠፋን አላጠፋንም ማለትም ያው መቅጠፍ ነው! “ያብዬን እከክ ወደ እምዬ ልክክም” ያው መዋሸት ነው! “ካፈርኩ አይመልሰኝ” ማለትም ያው መዋሸት ነው! አስገድደን የምንፈፅመውም ሆነ ዋሽተን የምናሳምነው፣ አሊያም በገንዘብ የምንደልልው፤ የዘወትሩን ሰው ቢያስጨበጭብልንም የክቱን ሰው ያሳዝናል፡፡
 
በመዋሸት የተገነባ አመኔታ ከጥርጣሬ የፀዳ አይሆንም፡፡ አንድ ፀሀፊ እንዲህ ይለናል፤ “የመጠራጠር አዝማሚያችን፤ ከምክንያታዊነታችንና ከእውነታው እያራቀ እሚወስደን፤ በቡድናዊ አመለካከት ውስጥ ስንገባ ነው፡፡ ሁላችንም በየውስጣችን ያለውን ጥርጣሬ፤ የህዝብ ሞቅ-ሞቅና የመንገኝነት ባህል ያበረታታዋል፤ ያጋግለዋል፡፡ ዕምነተ-ሰብ (cultist) የሚያጠቃው ደጋፊ (ቲፎዞ) በቀላሉ ሥልጣን ይሰጣል የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ 

ተንኮለኛ አገዛዝን በፈለግህ ጊዜ፡- በሰዎች ያልተፈፀሙ ምኞቶች ላይ በመጫወት እነዚያን ህዝቦች እንደመንጋ ልትነዳቸውና ፍፁም ሠልጣን ልትጐናፀፍባቸው ትችላለህ፡፡ በፅኑ ማስታወስ የሚገባህ ነገር ደግሞ፤ እጅግ ስኬታማ የምትሆነው ሃይማኖትን ከሳይንስ ጋር ቀላቅለህ ስትጠቀም ነው፤ በጣም የረቀቀውን ቴክኖሎጂ ወስደህ፤ ከአንዳች ክቡር ዓላማ፣ ከማይጨበጥ እምነት ወይም አዲስ አይነት ፈውስ ጋር አጣብቀው፡፡ ያኔ መንጋው ህዝብ ይከተልሃል፡፡ አንተ ሳትሻ ልዩ ልዩ ትርጉም ይሰጥልሃል፡፡ አንተ የሌለህንና ያላሰብከውን ችሎታና ሥልጣንም ሰጥቶህ ቁጭ ይላል!” ይሄ እርግማን ነው፡፡ እርግማኑ በመንግሥትም፣ በተቃዋሚም፣ በሰባክያንም፣ በምዕመናንም አንፃር ብናሰላው ያው ነው፡፡ ህዝብን ማታለል ክፉ እርግማን ነው፡፡ የማታ ማታም ያስከፍላል፡፡

የሌለ ጀግና መፍጠርም ሆነ፤ ያለን ጀግና መካድ ሁለቱም ማታለል ነው፡፡ በከፋ መልኩ ሲታይ ራስንም ማታለል ነው፡፡ የሰው ዓላማ የኔ ነው ማለትና የሌላውን ስም የራስ ማድረግ፤ ከኢኮኖሚ ዘረፋም የከፋ ዘረፋ ነው፡- “ገንዘቤን የወሰደ ሰው፣ ወሰደ እንበል ከንቱ ነገር የእኔም የእሱም የዚያም ነበር፡፡ ግና ስሜን የሰረቀኝ፤ የማያከብረውን ወስዶ፣ እኔን በግልፅ አደኸየኝ!” ይለናል እያጐ፤ በፀጋዬ ገ/መድህን ብዕር ልሳን፡፡ ውሸት እንደማግኔት መግነጢሳዊ ኃይል አለው፡፡ ማግኔት፤ በአንዳች የማይታይ ኃይል ባካባቢ ያሉ ነገሮችን ይስባል፡፡ እነዚያ ነገሮችም በፈንታቸው የመሳብ ኃይል ያበጃሉ - ባካባቢያቸው ያሉትን ነገሮች በተራቸው ይስባሉ፡፡ ያንን ኃይል ይዘው ይቆያሉ፡፡

ሰዎችም በአንድ ውሸት ሲሳቡና ያንን ውሸት የራሳቸው ሲያደርጉ ከዚያ የሚለያቸው ኃይል አይኖርም፡፡ ኦርጅናሌ ዋሾውን እንደተአምረኛ ያዩታል፡፡ በዙሪያው ይከባሉ፡፡ እንደመንጋም ይነዳሉ፡፡ (ግሬት ዴ ፍራቼስኮ) በየፖለቲካና ኢኮኖሚያዊ ጉዳያችን አንፃር የሌለንን አለን፣ ያለንን የለንም ብለን ከዋሸንና ካሳመንን፤ ተከታያችን ሊደሰትበት፣ አልፎም ሊኮራበት ይችላል፡፡ ያም ሆኖ እንደማናቸውም ነገር ውሸትም ከጥቅም ውጪ የሚሆንበት ጊዜ (expiry date) አለው፡፡ የዘንድሮ ካፒታሊዝማችን በሶሻሊዝማችን ላይ፤ ዲሞክራሲያችንም በፊውዳላዊ መሰረታችን ላይ፣ “ቫለንታይን ዴይም” በሌለ ፍቅራችን ላይ የተጣደ ከሆነ፤ በሽሮ ላይ ቅቤ ባናቱ ጠብ እንደማድረግ አይነት ነው፡፡ ሹሯችን ዛሬም ያችው ሹሯችን ናትና! ዋናው ነገር እውነቷን፣ እቅጯን አለመርሳት ነው፡፡ “ሸንጐ ተሰብስቦ ለሚስቱ እውነቱን የማያወራ ባል አያጋጥምሽ!” ነው ነገረ-ዓለማችን!