የወያኔ ቡዳዊ አይን በሙስሊም እና በምሁራኖቹ ላይ ለምን አተኮረ???

እጅግ አዛኝና ሩህሩህ በሆነው በአላህ ሥም
ከዘመናዊው ትምህርት እንግድነት ዘመናት በፊት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እጅጉን የሚያስደንቁም ዘመኑን የቀደሙ ኢስላማዊ የእውቀት ማዕከላት ነበሯቸው።እነዚህ ማዕከላት በኢስላማዊው ኔትዎርክ የተሳሰሩ እንጅ የመንግስት ድጋፍ ኖሯቸውም አያውቅ፣እንዲያውም በንጉሳኑና በአካባቢ ሹማምንቶች በአይነ ቁራኛ የሚታዩም ነበሩ።በአንድ አካባቢ የነገሡ (ጦሪቃ ተሰጥቷቸው የተሾሙ) የትላንት አባት መሻኢኾች በተሾሙበት አካባቢ ማህበረሰብ ተቀባይነት የመስጅድና የመድረሳ ቦታዎችን ከገነቡ በኋላ የአካባቢውን ማህበረሰብ ልጆች ያስተምራሉ፡፡

ደረሰነት እጅጉን ያልተጠና ግና እጅግም ትንግርት የታሪክ ክምር ነው።በደረሰነት ቤት ሁሉ አለ የሒሳብ፣የጅኦግራፊ፣የፊቂህ፣የህግ፣የሰዋሰው (ነሕው)፣የተፍሲር፣የሀዲስ ቀለም ቀንዶች ፈርተውበታል።ሎጂክ (መንጢቅ) ዘመናዊው ዩኒቨርሲቲ ከመግባቷ በፊት ኢትዮጵያውያን አበው መሻኢኾች እጅጉን ተጠበውባታል።ብቻ ብዙ ነው ገድሉ የአጥኛለህ ቢያስብልም ዛሬ ይህ አይደለም አጀንዳዮ አዎ አጀንዳዮ እነዚያ የሒሳብ የጅኦግራፊ ልሒቃን እነዚያ የሰዋሰው አመክንዮ የቀለም ቀንድ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ይረሱና ደብዛቸው ይጠፋ ዘንድ ታሪካቸው ሳይጠና እውቅናን ሳይቸሩ ዘመናት ነጉደዋል።
የምሁርነት አሊያም የማህይምነት መቋጫው አማርኛ አሊያም ግዕዝኛ ሆነና አያሌ ልሒቃን እልፍ አእላፍ መሻኢኾች መሀይም ከረጢት ውስጥ ተፈረጅው አለፉ።የዘመናዊውን ትምህርም እንዳይቋደሱ ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ሆነና እስላምና አስኮላ ሳይተዋወቁ የዘእምነገደ ደርብ ተናደ!!ለምን ቢሉ የእስላም መኖሪያ ቆላና ጠረፍ የአስኮላ ግንባታ ደጋና መሐል አገር! ታዲያ እንዴትስ ይገናኛሉ? ስንቅ ቋጥረው የዘመናዊ ትምህርቱን የተዳፈሩትም ከስዩመ እግዚአብሔሩ ህዝባዊ ኑሮ እድገት መሰሪ ተንኮል ሊያመልጡ አልቻሉም።የየኔታው መምህር የደህና አደራችሁ መልስ “እግዚአብሔር ይመስገን” መሆን ነበረበትና! የአረፋና የኢደል ፊጥር ጊዜም ፈተና ይሠጥ ነበርና መቼ ኢድን ያው ቁና መቼስ በሙሐመድ ተጠርተው ዩኒቨርስቲ ይገቡ ዘንድ ፈቃድ ነበርና ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን በፍርድ ቤት እስካላረጋገጡ ድረስ ብዙ ነው ወዳጄ የቱንስ አወጋኻላሁ የቱንስ እተወዋለሁ ብቻ ሆድ ይፍጀው ነው! ሆድ ይፍጀው!
በዚህ የመከራ ድግስ በዚህ የተንኮል መኣት አልፈው ለመንግስት አሽከርነት የበቁትም ሁሌም በስጋት የሚስተዋሉ እንጅ በቀላሉ የሚተውም አይደሉ! የሀገር ፍቅር ስሌቱ ማተብ ነው።የኢትዮጵያዊነት ዋስትናው ገዳም ወለድ ነው።አዎ!ሐሌታ ለአለማቱ ጌታ ምስጋና ለአላህ ይህም ታሪክ ሊሆን ዛሬ ሙሐመዶች አስኮላ ከትመዋል! ግና ምን ወግ አለው! ማይማን ሙስሊም አበውን የደርቡ ስጋት የዙፋኑ መናወጥ ምክንያት ናቸው ሲል እስላም ለምኔ! ሲል ሾተል የሰበቀው የሰሎሞናዊው ዘእምነገደ ይሁዳ ዙፋን ዳግም ህያው ይሆን ዘንዳ የዩሐንስ ባለአደራዎች የባለራዕዩ ዩሐንስ መሪያቸውን ቃል ሊፈፅሙ በዚህ ባልታደለ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም ላይ ዳግም ጦር ሰብቀዋል።
የወያኔው መንግሥት በሙስሊሙ ላይ ለዘመቸው ዘመቻ እጅጉን እንቅፋት የሆኑበት ሙስሊም ምሁራን መሆናቸውን በሰፊው በመረዳቱና ከግማሽ ክፈለ/ዘመን የትግል ስትራቴጅው መጥቀው የተገኙትና አልያዝ አልጨበጥ ያሉት ሙስሊሞች ጀርባ ምሁራን ሊኖሩ እንደሚችሉ ከመገመትም ባሻገር የድምፃችን ይሰማ ሠላማዊው ተቃውሞ ቀያሽ ፊደል የቆጠሩ መሆናቸው የገባው መንግስት የያዘውን የፀረ-ኢስላም ዘመቻ በድል ለመቋጨት ምሁራኑን መቀነስ ሟቹ ጠ/ሚኒስቴር እንዳሉት ታቦት ሸኚ ማይም እስላሞች የመፍጠር ረጅም እቅዱ አንዱ ክፍል ነው።
አዎ! በዚህ የሰለማዊ ተቃውሞ ውሥጥ የተማሩ ሙስሊሞች አሉ! ከዩኒቨርስቲ የወጡ ምሁራን ቀላል ሚና እንደሌላቸው እና የተማረው ሙስሊም ማህበረሰብ ሰፊ ድጋፍ እንዳለው የተረዳው መንግስት ምሁራንን መግፋትና ማኮላሸት አንድኛው ስትራቴጅው ነው።መንጌንም ይህች አባዜ ሞክሮት ነበር አሉ ምሁራኑ የኢሀአፓ፣የመኢሶን ወዘተ አባል እየሆኑ ቢያስቸግሩት በዘመቻ ሰበብ ወደ ገጠር ሸኛቸው አሉ። አዎ መንጌ አልጠቀማትም ከነዘመቻዋ ወደ ዝምባባዌ ዘምታ ቀረች! ዙፋን ለፈርኦን ላይፀና ሂትለር ህያውነትን ላይላበስ አጼ ዩሐንስና ባለአደራው መለስም አፈር ከመቃም ላይዘሉ የጥበት አጃጋሬ መሆንን መርጠዋል።የኢህአዴግ ዩኒቨርሲቲዎች ደግሞ የጥበቱ መሞከሪያ ናቸው የኢህአዴግ ፀረ-ኢስላም ዘመቻ አውድማዎች ናቸው።ሴት ሙስሊም ምሁራን በአልባሳት ሰበብ ከትምህርት ይፈናቀላሉ ፓንት ቀረሽ ለባሾች ምስጋናንና ሹመትን ይቀዳጃሉ! ሙስሊሞች የፈተና ሰሞን ትንኮሳንና አስር ቤትን ይቀምሳሉ ሌሎች ተረጋግተው ሲፈልጉ ላይብራሪ ሲፈልጉም ዶርም ያነባሉ! ባለ ረዥም ጺማሞች ባለ ጅልባብ አህቶች ካፌ እንዳይገቡ በማድረግ በምግብ ይቀጣሉ ሌሎች ወገኖች ግን ትኩረት ወደ ትምህርት ይሆን ዘንዳ ዩኒቨርስቲው ይጥራል።ክርስቲያን ወገኖች በአቅራቢያቸው ከሚገኝ አጥቢያ ቤተ-ክርስቲያን አማካኝነት የመንፈሳዊ የቲዎሎጅ ትምህርት ተምረው ሌላ ድግሪ ይዘው ይወጣሉ።የአመራር (leadership) እና ሌሎች ወሳኝ ስልጠናዎችን እያገኙም ይመረቃሉ የኛዎቹ ሙስሊም ተማሪዎች ግን ዳኢ ከጋበዙ አንኳን ከነዳኢያቸው ወደ ቸርከሌ ይወረወራሉ።አዎ! የዚህ ሁሉ ግፍ የዚህ ሁሉ ጥበት ዓላማ የሚቀዳው ሙስሊሞችን ከትምርት በማራቅ ሰምቶ አደር ትውልዶችን መፍጠር ከሚለው የኢህአዴግ እቅድ የሚመነጭ ነው። መፍትሔው ታዲያ ምን ድን ነው? ዝም ብሎ መመልከት? በፍፁም ! ይህን ያነበበ ሁሉ በየቤቱ በስራ ቦታው በማህበራዊ ድህረገፆች ጭምር ሊወያይበት ግድ ይላል።በቅርቡም ኢንሻአላህ ከኛ በኩል መፍትሔ ያልነውን ትቂት እንላለን።