ዘረፋ በአደባባይ--በጎንደር ዩንቨርስቲ የሚሰራው ወያኔያዊ እኩይ ተግባር ሲጋለጥ::

ጎንደር ዩኒቨርስቲ በሙስና፣ በአመራሮቹ ስርአተ አልበኝነትና ለገዢው ፓርቲ ያላቸው ታማኝነት እና አጎብዳጅነት ከጊዜ ጊዜ የዩኒቨርስቲውን እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብ ከማሳፈሩ እና ከማስገረሙ አልፎ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ድህረ ገፆች እንዲሁም በኢሳት፣ ዶቸቨሌ እና በቪኦኤ ራዲዮ ጣቢያወች የዩኒቨርስቲውን አመራሮች እኩይ ድርጊት የሚያጋልጡ መረጃወች እየወጡ ይገኛሉ። ዩኒቨርስቲው ውስጥ የተስፋፋው ሙስና እስከ ፓርላማ ድረስ መነጋገርያ ከሆነ በኋላ የአንድ ሰሞን ወግ ሆኖ ዝም ቢባልም የሙስናው መጠን ግን መጠኑ ሰፍቷል። በተለይ ዩኒቨርስቲው ከመንግስት በጀት እና ከውስጥ ገቢ የሚሰበስበውን ገንዘብ ተጠቅሞ የሚያከናውናቸው የተለያዩ ግንባታወች፣ ግዥወች፣ እንዲሁም የሌሎች ፕሮጀክቶች ወጭወች ከሚገባው በላይ የተጋነነ ሲሆን፣ ለረጅም ጊዜ የተቀመጡ ሂሳባቸው ያልተዘጋና ሆን ተብለው ለይደር የተቀመጡ ገንዘብ ነክ ሰነዶች በጣም ብዙ ሲሆኑ፣ እነዚህ ሂሳቦች ለምንድን ነው የማይዘጉት? ለምንስ አይዘጉም ብለው የሚጠይቁ የፋይናንስ ባለሙያወች አርፋችሁ ተቀመጡ አለበለዚያ ዩኒቨርስቲውን መልቀቅ ትችላላችሁ የሚል ማስፈራርያ እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ከፌድራል የሚላኩ ኦዲተሮች ሲመጡ ደግሞ የዩኒቨርስቲው አመራሮች ጉዳቸው እንዳይወጣ ከ 40ሺህ እስከ 50ሺህ ብር ድረስ በጉርሻ መልክ ስለሚደርሳቸው የዩኒቨርስቲውን የገማ አሰራር በመሸፈን መልካም ሪፖርት ለፌድራል ኋላፊወቻቸው ያቀርባሉ። በተመሳሳይ የዩኒቨርስቲው የቦርድ ፕሬዝዳንትም ዶ/ር ስንታየሁ ወ/ሚካኤል ወደ ዩኒቨርስቲው ሲመጡ እንዲሁ ደጎስ ያለ ብር በፖስታ እየታሸገ የአፋቸው ማዘጊያ ይበረከትላቸዋል።

የዩንቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መንገሻ አድማሱ ከልክ በላይ በሆነ ሙስና እና በብቃት ማነስ ይታማሉ። እንዲያውም የዩኒቨርስቲውን የተማሪወች መዝናኛ ክበብ በጨረታ አሸንፎ ከያዘው ግለሰብ ጋር በመሆን በጎንደር ከተማ ውስጥ HARD ROCK CAFE የሚባል ሬስቶራንት እና ካፌ በጋራ ከፍተው እየነገዱ ሲሆን፤ ይህ ሬስቶራንት እና ካፌ ስራ ሲጀምርም መርቀው የከፈቱት እሳቸው ናቸው። የሚያስገርመው ነገር በሚስጥር ሬስቶራንት እና ካፌ መክፈታቸው ሳይሆን ዩኒቨርስቲው አንዳንድ ስብሰባወች እና ፕሮግራሞች ሲኖሩት ለምሳ እንዲሁም ለተለያዩ ግብዣወች ሁልጊዜም እዚሁ ሬስቶራንት እና ካፌ ያለ ጨረታ የሚከናወን ሲሆን የሚከፈለውም ገንዘብ ሆን ተብሎ ድርጅቱን ለማክበር እጅግ ከመጠን በላይ የተጋነነ ሲሆን ለምሳሌ 100 ሰወች ምሳ ቢበሉ ዩኒቨርስቲው ከ300 ሺህ ብር በላይ ይከፍላል ብዙውን ጊዜም ለአንድ ጊዜ ግብዣ ከ 500ሺህ እስከ 700ሺህ ብር እንደሚከፈል ውስጥ አዋቂወች ይጠቁማሉ። በእንደዚህ አይነት እና በሌሎች መንገዶች ዩኒቨርስቲው እየተመዘበረ ሲሆን ይህንን ሁኔታ የሚያወግዙ ሰወች በተለያየ መንገድ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል። በጣም የሚያናድደው ደግሞ የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ሰላዮችን አዘጋጅተው እሳቸውን የሚቃወም ግለሰብ ካለ በሰላዮቻቸው አማካኝነት መረጃ እየተቀበሉ እርምጃ መውሰዳቸው ነው።

ፕሬዝዳንቱ ይህን ሙስናቸውን ለመሸፈን ለገዢው ኢህአዴግ ታማኝነታቸውን በተለያየ መንገድ የሚገልፁ እና ያሳያሉ። ለአብነት ያክል ጠቅላይ ሚኒስተሩ በሞቱ ጊዜ ከሁሉም ዩኒቨርስቲወች በመቅደም ሰራተኛው ጥቁር የሀዘን ልብስ ለብሶ በመውጣት ሀዘኑን እንዲገልፅ በማስታወቂያ የዩኒቨርስቲውን ማህበረሰብ ከማስገደድ አልፈው የክፍል ሃላፊወች የስም ቁጥጥር እንዲያደርጉና ባልተገኘው ሰው ላይም እርምጃ እንደሚወሰድ አሳስበው ነበር። ከዚያም ባለፈ ማንንም ሳያማክሩ በማናለብኝነት ርካሽ ተወዳጅነት ለማግኘት ሲባል ብቻ ከከተማው ወጣ ብሎ ጠዳ የሚገኘውን አዲሱን የግብርና ካምፓስ መለስ ዜናዊ ካምፓስ ተብሎ እንዲጠራ አድርገዋል። በነገራችን ላይ ፕሬዝዳንቱ ፕሮፌሰር የሆኑት በቅርቡ ሲሆን ለፕሮፌሰር የሚያበቃ በቂ የምርምር ስራ ሳይሰሩ ያልሰሩትን እንደ ሰሩ ተደርጎ በዩኒቨርስቲው ቦርድ የፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ ሲሆን፤ ከዚሁ ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰወች የቦርዱን ውሳኔ በግልፅ የተቃወሙ ቢሆንም ድምፃቸው እንዲታፈን የተደረገ ሲሆን የፕሬዝዳንቱ ሴክሬታሪ ሚስጥራዊ መረጃ ለሌሎች ግለሰቦች ሰጥተሻል ተብላ ከስራ ተባራለች ከተወሰነ ጊዜ በኋላም ተሻሽሎላት ደረጃዋን ዝቅ አድርጋ ሌላ ስራ እንድትሰራ ተደርጓል። እኒሁ ፕሬዝዳንት አንድ ሰሞን ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን ተክተው የኢትዮጵያ ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ በጎንደር ከተማ ሲወራ/ሲያስወሩ ነበር። የሚያወሩትም የሳቸው የቅርብ ሰወች ነበሩ።

በቅርቡ የሚያስተምራትን ተማሪ አስገድዶ የደፈረው የተማሪወች ዲን የአስገድዶ መደፈሩ ዜና በተለያዩ ሜዲያወች ከተሰራጨ በኋላ በሁኔታው የተደናገጡት እና ሌላ ገመናቸው እንዳይወጣ የፈሩት የዩኒቨርስቲው አመራሮች ወዲያውኑ የግቢውን ማህበረሰብ የሚያስፈራራ እና በተለያዩ ማህበራዊ ድህረ ገፆች ስለ ዩኒቨርስቲው የሚፅፉ እና መረጃ የሚያቀብሉ ሰወች ላይ እርምጃ እንወስዳለን የሚል ማስታወቂያ በፕሬዝዳንቱ ፊርማ ተፈርሞ በተለያዩ ቦታወች እንዲለጠፍ አድርገዋል። በመቀጠልም በዩኒቨርስቲው የተለያዩ ካምፓሶች አስቸኳይ ስብሰባ በመጥራት መረጃ የሚሰጡ ግለሰቦችን አጋልጡ የሚል ይዘት ያለው አጀንዳ ይዘው በተለመደው የሞኝ ማስፈራርያቸው ሰራተኛውን ሊያስፈራሩ ሞክረዋል ከእንግዲህ በኋላም ማንንም እንደማይታገሱና መረጃ በሚያሾልኩ ሰወች ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ ዝተዋል። በዚሁ ጊዜም ለጀርመኑ ዶቸቨሌ ስለ አስገድዶ መድፈሩ መረጃ ሰጥተሃል በማለት በዞኑ የብአዴን ፅ/ቤት ትእዛዝ ፕሬዝዳንቱ አቶ ደማስ የሚባሉትን የዩኒቨርስቲውን ላይብረሪ ሃላፊ ከስራ አባረዋቸዋል። በነገራችን ላይ አስገድዶ የደፈረው የተማሪወች ዲን ወደ ፍርድ ቤት ሳይቀርብ ከእስር ተለቋል ይህም ለምን እንደሆነ እርግጠኛ ባይኮንም አንዳንድ ሰወች እንደሚሉት ነፃ የተለቀቀው ሰውየው ባለው ፖለቲካዊ ታማኝነት እና የግቢው የብአዴን አስተባባሪ ስለሆነ ነው ይባላል። የተደፈረችው ተማሪም ትምህርቷን አቋርጣ ወደ ሀገሯ ሄዳለች።

ሌላው የጎንደር ዩኒቨርስቲ አስገራሚ ነገር ደግሞ የመረጃ መረብ ደህንነት(INSA) ከዘጋቸው የፖለቲካ ይዘት ካላቸው ድህረ ገፆች በተጨማሪ ዩኒቨርስቲው ደግሞ ርካሽ የፖለቲካ ተወዳጅነት ለማግኘት የተወሰኑ ድህረ ገፆች ብቻ እንዲሰሩ በማድረግ ሁሉንም አይነት የፖለቲካ ድህረ ገፆች ከመዝጋቱም በተጨማሪ ሌሎች ሳይቶችን በመዝጋታቸው ANTI VIRUS እና ሌሎች ፕሮግራሞችን መጫን የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል። ይህንን ለማድረግም ዩኒቨርስቲው የተጠቀመበት ቴክኖለጂ የተለያዩ የመስበርያ ሶፍትዌሮች እና ብሮውዘሮችን ተጠቅሞ መስበር እና መክፈት እንዳይቻል ተደርጎ ለየት ባለ እና በከፍተኛ ወጭ የተገዙ መሳሪያወችን በመጠቀም ነው። በነገራችን ላይ ጎንደር ዩኒቨርስቲ በቅርቡ በከፍተኛ ገንዘብ የተገዙ የመሰለያ፣ ድህረ ገፅ መዝጊያ ቴክኖለጂወችን አስገብቶ በስራ ላይ ያዋለ ሲሆን ማንኛውም ሰራተኛና ተማሪ የሚያደርገውን የመረጃ ልውውጥ እንደሚከታተሉና አንታወቅም ብለው መረጃ የሚሰጡ ሰወች ካሉ ይጠንቀቁ በማለት የዩኒቨርስቲው አመራሮች ሰራተኛውን እያስፈራሩ ናቸው።