በብሔር ቋንቋ እየለካንና በድንበር እየከለልን ማውራት፣ ለብዙዎቻችን የሥልጣኔ ምልክት እስኪመስለን ድረስ እየገፋንበት ነው፡፡

“አፄ ቴዎድሮስ ሱዳናዊ ይሆኑ እንዴ!?”Written by  ገዛኸኝ ፀ (ፀጋው) 


  • ጀግና ሁሉም ይፈራዋል፤ እርሱ ሁሉንም ባይፈልግም…
  • ጀግንነት ባህሪው የሆነ ሰው ፣ብሔር ሳይለይ ድንበር ሳያበጅ ጀግናን ያከብራል!
  •                                                           (ምንሊክ ሳልሳዊ)ከተወሰኑ ጊዜያት ወዲህ እውነትን እና እውቀትን በብሔር ቋንቋ እየለካንና በድንበር እየከለልን ማውራት፣ ለብዙዎቻችን የሥልጣኔ ምልክት እስኪመስለን ድረስ እየገፋንበት ነው፡፡ እውነት እና/ወይም እውቀት በብሔር ሚዛን ሲሰፈሩ፣ በድንበር ተከልለው ሲተነተኑ፣ ከተፈጥሯቸው ጋር እየተጣሉ መሆኑ ሁሉ አልገባን እያለ ነው፡፡ በርግጥ፣ እውነት እና እውቀት እራሳቸው ፈልገው አይደለም ከተፈጥሯቸው ተገስሶ፣ የህልውና መሠረታቸው ተገፎ፣ ባህሪያቸውን አጥተው፣ በደባልና ወረተኛ ፀባይ እየተሽሞነሞኑ የሚቀርቡት፣ በድንቁርና ምክንያት ነው፡፡ ድንቁርና በሁለት መንገድ ሊከሰት ይችላል፤ አንድም ካለማወቅ እውነትን ወይም እውቀትን ሲያጡ፤ አንድም በማወቅ እውነትን እና እውቀትን ሲክዱ፣ ሲጠየፉ፡፡ ሁለቱም መልኮች ከሥልጣኔ ይርቃሉ፤ ያርቃሉ፡፡
ሁለቱም መልኮች ከዘመናዊነት ያፈነግጣሉ፤ ያስፈነግጣሉ፡፡ ርቀታቸውም ሆነ ፍንገጣቸው ግን አንፃራዊ ልዩነትም እንዳለው ይታወቃል፡፡ የመጀመሪያው ማለቴ “አለማወቅ” ከአጥፊነት ወይም ከወንጀለኝነት ባያድንም በአንፃራዊነት እዳው ገብስ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ለማወቅ በተዘጋጁበት መጠን ያህል፣ ወደ እውነት እና እውቀት በተጋለጡበት ደረጃ ያህል፣ በድንቁርና ላይ ድልን መቀዳጀት ይቻላልና፡፡ ድንቁርና የባህሪ መሆኑ ቀርቶ፣ እንደ ጊዜያዊ ደባል ፀባይ ከላያችን ላይ ተገፎ ይጠፋል፡፡ ድንቁርና አይሰለጥንብንም ማለት ነው! የድንቁርና ሁለተኛው መልክ እውነትንም ሆነ እውቀትን እያነበነቡ፣ ሰዋዊ መንፈስን በእነሱው ለመግራት ካለመፍቀድ ይመነጫል፡፡ የሚያነበንቡትን እውነት እና/ወይም እውቀት ገቢራዊ አለማድረግ፣ መጠየፍ ወይም መካድ ሁሉ ያስከትላል፡፡ በዚህ ጊዜ ድንቁርና የበሃሪ እየሆነ ይሄዳል፤ ወይም ትህትናውን ከቀነስነው፣ ድንቁርና መገለጫ ባህርይ ሁኖናል ማለት ይቻላል፡፡
እያወቁ የሚያጠፉን “ሰዎች” ወይም ቡድኖች ምን ማድረግ ይቻላል!? ስለዚህ ይኼ ሁለተኛው የድንቁርና መከሰቻ መልክን ለማጥፋት እና በሌላ ለመተካት አስቸጋሪ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ድንቁርና ይሰለጥንብናል ማለት ነው፡፡ ድንቁርና የሰለጠነበት ማህበረሰብ ፣ ከፍ ሲልም ህብረተሰብ፣ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ ቢያስገነባም ሆነ ቢገነባለት፣ ቀለበት መንገድ ቢያሰራም ሆነ ቢሠራለት፣ የ3 ሚሊዮን ብር መኪና (“ሀመር”) ቢያስገዛም ሆነ ቢገዛላት፣ የሥልጡኖቹ ልሳን እንግሊዝኛም በሉት ፈረንሳይኛ ቢያወራም ሆነ ቢወራለት ወዘተ… ሥልጣኔ የሩቅ ግቡ ነው፡፡ “ዘመናዊነት” ማስመሰያው እንጂ ከሰዋዊ ግብሩ ተጠንፍፎ የሚኖረው ባህሪው አይሆንም፡፡ ከመነሻውም “የዘመናዊነት” መገለጫ እሴቶች (Values) ጋር አይተዋወቅም፤ ለመተዋወቅም ዝግጁ አይደለም፡፡
በዚህ ማህበረሰብ ውስጥ እየኖሩ ለእውነት እና/ወይም ለእውቀት የሚተጉ፣ ሥልጣኔን የባህርያቸው ለማድረግ የሚሹ ታዲያ አቤት ያለባቸው መከራ!? እውነትን እና እውቀትን በብሔር ሚዛን ለመለካት የሚቋምጥ ሥልጣኔ ጥዩፍ ማህበረሰብ ዝቅ ሲል ግለሰብ፤ “የጀግንነት” መለኪያው፣ ማህበረ ባህላዊ ብያኔው ከድንቁርና ሊመጣ ይችላል፡፡ መሠረቱ በተንሻፈፈ ሚዛን የሚሰፍር፣ ፍርደገምድል ዳኛ ሊሆን ይችላል፡፡ “ጀግንነት” ከልቡ ሽቶ የባህሪው የሚያደርገው ግብሩ ሳይሆን፣ መስሎ የሚታይበት ፀባዩ፣ የሚያስፈራራበት መታሠበያው ይሆናል፡፡ በአንድ ወቅት በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ ይመስለኛል፣ በደቡብ ወሎ ዞን ባለ አንድ ወረዳ፣ ድንገተኛ ስብሰባ ተጠራ፡፡ የወረዳው ምክር ቤት ግልጽ ባልሆነ መስፈርት ከየመስሪያቤቶቹ የተወሰኑ ሰዎች፣ በስብሰባው ላይ እንዲገኙ ጥሪ ማስተላለፉ ተሰምቷል፡፡ ዕለቱ አርብ ይመስለኛል፡፡
በወረዳው አንድ ለእናቱ በነበረው አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርት ቤት የተወሰኑ መምህራን ስብሰባ ላይ እንዲገኙ ሁለት ሰዓት አካባቢ ጥሪ ተላለፈ፡፡ ስብሰባው የሚጀመረው ሦስት ሰዓት ላይ መሆኑም አብሮ ተነግሯል፡፡ የትምህርት ቤቱን ፀጥታ የሚቆጣጠሩ አንድ የፈረቃ መሪ መምህር ብቻ እንዲቀሩ ተደረገና ዋና እና ምክትል ርዕሰ መምህሮቹን ጨምሮ፣ የትምህርት ክፍል ሃላፊዎች፣ የፈረቃ መሪዎች ወዘተ. ወደ መሰብሰቢያው አዳራሽ ተመምን፡፡ እርግጥ ነው፣ ሁለት መምህራን በስም ተለይተው ስብሰባው ላይ እንዲገኙ ለርዕሰ መምህሩ ቀጭን ትዕዛዝ ተላልፎላቸዋል፡፡ በአዳራሹ በግምት ወደ መቶ የሚጠጉ ተሰብሳቢዎች ተገኝተዋል፡፡ እንደተለመደው ሦስት ሰዓት የተባለው ስብሰባ አራት ሰዓት አካባቢ ተጀመረ፡፡ ሰብሳቢዎቹ የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ፤ የወረዳው የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊና ምክትል አስተዳዳሪው ነበሩ፡፡ ሁለቱ አጃቢና የሚነሱ ጥያቄዎች መላሺ ሲሆኑ፣ የመወያያውን አጀንዳ የሚያቀርቡ ወይም የተዘጋጀውን ጽሑፍ የሚያነቡ ምክትል አስተዳዳሪው ናቸው፡፡ የመወያያ ጽሑፍ አንባቢው ሰው፣ “የዛሬ ስብሰባ አጭር ነው…ከምሣ ሰዓት በፊት ነው የሚያልቀው የዛሬው የመወያያ አጃንዳ ዲሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ምን እንደሆነ እና የአማራ ብሔርተኝነት እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል…” እያሉ ሲያነቡ፣ በተለይ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ማልጐምጐም ጀመሩ፡፡
በርግጥ አስተዳዳሪው በተለይ አብዛኞቹ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መምህራን ወደተቀመጡበት አካባቢ እያፈጠጡና እየተገላመጡ ነበር - ወረቀቱን የሚያነቡት፡፡ በርግጥ ይህ የማወያያ ወረቀት ከፌደራል መንግሥቱ ጀምሮ ደረጃውን ጠብቆ፣ ወረዳ ላይ የደረሰ እንጂ ምክትል አስተዳዳሪው ያዘጋጁት እንደነበረ ይገመታል፡፡ በነገራችን ላይ እኚህ አወያዩ ምክትል አስተዳዳሪ፣ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ የ11ኛ ክፍል የማታ ተማሪ ነበሩ፡፡ ተማሪው አስተዳዳሪ ወረቀቱ በታላቅ ስሜት ማቅረባቸውን ቀጥለዋል፤ ግልምጫቸውም በርትቷል፡፡ መካከል ላይ፣ “አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት የታገለ ጀግናችን ነው…” ሲሉ ጉምጉምታው ወደድንገተኛ ጩኸት ተቀየረ፡፡ አወያዩ ብዙም አልተደናገጡም፤ ይልቅ አይናቸውን እያጉረዘረዙ፣ “ይኼ የነፍጠኝነት፣ የትምክተኝነት ስሜት ነው…አዳምጡ” ብለው ሃይል በተቀላቀለበት ንግግር አስጠነቀቁ፡፡ አዳራሹ በፀጥታ ተዋጠ፤ አወያዩ ጮክ እያሉ ማንበባቸውን ቀጠሉ፤ “በመሳፍንቱ ዘን ቴዎድሮስ ተቀናቃኞቹን በጦር እያንበረከከ የቀጣቸው የተጠናከረ የአማራ ብሔርተኝነት ለመመሥረት ነው…” አይነት ስሜታዊ ንባባቸውን አጠናቀቁና እዚህ ላይ ውሳኔያቸው አሰሙና ቢባል የሚሻል ይመስለኛል) በተነሱት ጉዳዮች ላይ የሞቀ ውይይት እንዲደረግ ጋበዙ፡፡
በመርህ ደረጃ ውይይቱ ጀመረ፡፡ ግን፣ አንድም ተሰብሳቢ ትንፍሽ አላለም፡፡ አዳራሹ እንኳን ከመቶ በላይ ሰው ያለበት፣ ዝንብም ባሉት ንብም ያረፈበት አይመስልም፡፡ ምክትል አስተዳዳሪው ዝምታ ፀረዲሞክራሲነት ነው” በማለት ሂሳቸው እያስፈራሩ፣ ሳይላቸው እየተማፀኑ፣ ተሰብሳቢው አስተያየት እንዲሰጥ ለማድረግ ተፍጨረጨሩ፡፡ አንድም የሚናገር ጠፋ፡፡ የትምህርት ጽ/ቤት የብአዴን ጽ/ቤት ሃላፊዎቹም የቻሉት ማስፈራሪያም፣ መማፀኛም ንግግር ለማድረግ ሞከሩ፡፡ አሁንም አስተያየት ጠፋ፡፡ በድርጅታዊ አሠራር ይመስላል፣ ከተሰብሳቢው መካከል ያሉ የወረዳው ምክር ቤት ሥራ አስፈፃሚ እጃቸውን አውጥተው ንግግር ማድረግ ጀመሩ፡፡ ንግግራቸው የተጠና ቃለ ተውኔት ስለሚመስል፣ አስተያየት ሰጪው ቀሽም ተዋናይ እንደሆኑ ታወቀባቸው፡፡ “…ቴዎድሮስ እንደምታውቁት የታወቀ ጀግና ነው…የአማራ ብሔርተኝነትን ለመመሥረት ሲፋለም ጀግንነቱን አለም ነው ያወቀው…” አይነት የሥራ አስፈፃሚው ቃለ ተውኔት፣ ተሰብሳቢውን እንደገና ለጉርምርምታ ዳረገው፡፡ ሰውዬው ተናግረው ቁጭ ሲሉ፣ አዳራሹ እንደገና ወደ ዝምታ ቀፎነቱ ተቀየረ፡፡ ሌላ ሰው አስተያየት አለመስጠቱ ሰብሳቢዎቹን ከሚጠበቀው በላይ እያበሳጫቸው መጣ፡፡
በኋላ፣ ተራ ስድብ ሁሉ ጀመሩ፤ “…አንዳንዶቹ ሙሁራዊ ትምክተኝነት ይወጥረናል…ይኼ ባህሪያችን መተንፈስ አለበት…ምክንያቱም ፀረ - ዲሞክራሲያዊ፣ ፀረ ልማት አስተሳሰብ ስለሆነ ማለት ነው…” የሚሉ ስሜታዊ አስተያየቶችና ማስፈራሪያዎች መነሻቸው ከመድረኩ ሆኖ መድረሻቸው አብዛኞቹ የ”ሀይስኩል” መምህራን የተቀመጡበት አካባቢ እንደሆነ በአዳራሹ ውስጥ ባሉ ሰዎች ሁሉ የታወቀ ይመስላል፡፡ ዝምታ በተንጠላሠበት አዳራሽ ውስጥ፣ ወደ አንድ ስምምነት የመጣ፣ ዝምታዊ መግባቢያ ተፈጥሯል… ከተሰብሳቢው መካከል አንድ እጅ በድንገት ወጣ፡፡ እጅ ያወጣው ሰው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቱ የታሪክ መምህር ነው፡፡ መድረኩን የሚመሩት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪው የመምህሩን ስም ጠርተው፣ “ቀጥል አስተያየትን አጠር አርገህ!” ሲሉ አሁንም ተሰብሳቢው በተለይ ተናጋሪው መምህር ባለበት ረድፍ አካባቢ የተቃውሞ ጉምጉምታ ተሰማ፡፡ ተቃውሞው ለሰብሳቢው ስሜታዊ አነጋገርና ድምፀት ነበር፤ ተግሳፁ የራሱ የሆነ ቅኔ ነበረው፡፡ አብዛኛው ተሰብሳቢ የቅኔውን ሰም ይገምታል፡፡
ወርቁን ግን በጣም ጥቂቶች ነበር ቀድመው ሊያውቁት የሚችሉት፡፡ እጅ ያወጣውና አጠር ያለ አስተያየት እንዲሰጥ የተፈቀደለት ወጣቱ የታሪክ መምህር፣ “…እኔ መቼም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተወግተዋል የሚል በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ፀሐፊ የተፃፈ ታሪክ አላነበብኩም፤ አፄ ቴዎድሮስ ከዘመናቸው ቀድመው ያስቡ የነበሩ፣ ለሃገራቸው አንድነት የተፋለሙ ብሎም፣ እየሩሳሌም ድረስ ተሻግረው ለሰው ልጆች ነፃነት ሊዋደቁ ያሉ ባለርዕይ መሆናቸውን ነው የተማርኩት፡፡ እኔም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተዋድቀዋል ብዬ አላስተማርኩም” ሲሉ ከፍተኛ የሆነ ሣቅና ጭብጨባ ተሰማ፡፡ የጭብጨባውም ሆነ የሣቁ መሪዎች ወይም ጀማሪዎች፣ የቅኔው ወርቅ የገባቸው በጣት የሚቆጠሩ የ”ሀይስኩል” መምህራን ነበሩ፡፡ በኋላ እነሱን ተከትሎ አዳራሹ ሁሉ በጭብጨባ ተናጋ፡፡ የቅኔው ወርቅ፣ በአዳራሹ መንሾካሾኪያ ነበር፡፡
ውድ አንባቢያን የቅኔውን ወርቅ እናንተም የገመታችሁት መሰለኝ፡፡ የመወያያ ወረቀቱን ያቀረቡትና የታሪክ መምህሩን ስም ጠርተው “አጠር አርገህ” አስተያየትህን ስጥ ያሉት የወረዳችን ምክትል አስተዳዳሪ፣ የተናጋሪው የታሪክ መምህር የማታ ተማሪ ነበሩ፡፡ “…እኔም አፄ ቴዎድሮስ ለአማራ ብሔርተኝነት ተዋድቀዋል ብዬ አላስተማርኩም” የሚለው የመምህሩ አስተያየት፣ ለአወያዩ “ከወዴት የዘረፍከውን ታሪክ ነው የምታነበንበው!?” አይነት የአንድምታ ፍካሬ ወይም ትርጓሜ ነበረው፡፡ የቅኔ ታሪኩ ወርቅም ይኸው ነው፡፡ አወያዩ አስተዳዳሪ በጣም መናደዳቸው አስታወቀባቸው፡፡ የአዳራሹንም ፀጥታ መቆጣጠር አልቻሉም፡፡ የሰማ ላልሰማ፣ “የታሪክ ተማሪው ለታሪክ መምህሩ ያልተፃፈ ታሪክ እያስተማረ ሳይሆን እየሰበከ” መሆኑ አስተጋባ፡፡
“ተማሪው ነው እንዴ?” የምትለው ጥያቄ፣ ከመድረኩ እስከ አዳራሹ ጫፍ ውስጥ ለውስጥ ተናኘች፤ ተሰብሳቢውን አብሰከሰከች… ለዚህ ትዝታ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን የሁለተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ወረቀቱን በቅማንት ማህበረሰብ ላይ ካደረገ አንድ ወጣት ተመራማሪ ጋር በድንገት የጀመርነው ወግ ነበር፡፡ ተመራማሪው፣ ሰሜን ጐንደር ጭልጋ ወረዳ የሚኖሩ የቅማንት ማህበረሰቦችን ሲያነጋግር፣ በማህብረሰቡ የጀግንነት መለኪያው ምን እንደሆነ ለማወቅ ጠየቀ…የተድበሰበሰ መልስ ሲሰጠው፣ “አሁን በዚህ ማህበረሰብ ጀግናችሁ ማን ነው? ለምሣሌ ለጐጃሞች በላይ ዘለቀ፣ ለጐንደሮች አፄ ቴዎድሮስ እንደሆኑት…” ብሎ ሳይጨርስ፣ አዛውንቶቹ የቅማንት ማህበረሰብ አባላት እግራቸውን አንስተው ሳቁበት፡፡ ቀጥለው፣ አንደኛው አዛውንት፣ “አጤ ቴድሮስ ደግሞ የአማራ ጀግና ሆነ?” ብለው በምፀት ሳቁበትና፣ “አፄ ቴዎድሮስ የቅማንት ተወላጅ…የቅማንት ጀግና” መሆናቸውን የተለያዩ የቃል ታሪኮችን (Oral Narratives) እየነገሩ ሊያሳምኑት መሞከራቸውን ነገረኝ፡፡ የዛሬ አመት አካባቢ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሚገኘው የመኮንን አዳራሽ፣ በበላይ ዘለቀ ዙሪያ በተዘጋጀ መድረክ ላይ፣ የበላይ ዘለቀን ጐጃሜነትና የበላይ ዘለቀን ወሎዬነት ለማስረገጥ የደቂቃዎች ሙግት እንደነበሩ አስታውሳለሁ፡፡
“ጀግንነት” የምንለካበት መሥፈሪያው ላይ ያለውን የአስተሳሰብ ልዩነት ትተን፣ እስከ አሁን ባለው “ሀገራዊ” መግባባት ብንስማማ፣ “ጀግንነት” ማድነቅ፣ ጀግንነትን ለመላበስ መሞከር ነው ያለብን ወይስ ጀግናውን እሱ ሳያውቀውና ሳይፈልገው፣ እኛ በምናበጀው አጥር አስገብተን የጀግና ወገን መሆናችንን ነው ማስመስከር ያለብን? የትኛው ነው የሥልጣኔ ማሳወቂያ? እኛ ጀግና ለመምሰል፣ ሳይፈልጉ ጀግኖችን በአንድ ጠባብ ጉርኗችን ለመክተት መፈራገጥ አለብን!? በነገራችን ላይ አፄ ቴዎድሮስ ትግሬ መሆናቸውን ለማሳመን የወረቀት ማስረጃ የሚያጣቅሱ የዋሆች አሉ፡፡ ከብሔር ጋጣቸው ሳይወጡ የሞነጨሩትን የሻገተ ዶሴ አጣቅሰው፣ የአፄ ቴዎድሮስን ኢትዮጵያዊነትና ሩቅ አሳቢነት የሚነጥቁ የሚመስላቸው ደካሞች አሉ፣ ከብሔር ጉያችን ለመወተፍ በመቸኮል በእናታቸው አያት በኩል የኦሮሞ ዘር እንዳለባቸው ለማሣመን፣ የሰው መጽሐፍ ታሪኩን ገለባብጠው ደግመው እስከ ማሳተም የደረሱም ያለ ዕዳው ዘመቻ ምስኪን ኢትዮጵያዊያን ያጋጥሙናል (እዚህ ላይ የፈንታሁን እንግዳን፣ “ታሪካዊ መዝገበ ሰብ” መጽሐፍን ከገጽ 327-334 አንብባችሁ “ድንቁርናችን” እስኪ እንታዘበው)፡፡እርግጥ ነው ጀግናን ሁሉም ይወደዋል፡፡
ጀግንነትንም ሁሉ ይመኛል፣ ጽንፈኛ አካሂያዳችን ግን ጀግናን እንደሚያመክን ብሎም “ጀግንነት” የሚባለውን መንፈስ ሁሉ እንደሚነጥቅ ማወቅ እንደተሳነን ነው ወይም አውቀን በድፍረት አጥፍተን እየጠፋን ነው፡፡ ጀግና ሁሉም ቢፈልገውም፣ እሱ ግን ሁሉንም እንደማይፈልግ አልተረዳንም፤ ጀግና ጀግናን ነው የሚያከብረው፡፡ በላይ ዘለቀ፣ ከፈሪ ጐጃሜ ይልቅ፣ ጀግና ኦሮሞን ነው የሚመርጠው፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከፈሪ ጐንደሬ ወይም “ቅማንቴ” ይልቅ፣ ደፋሩን ትግሬ ነው የሚፈልገው፡፡ “ጀግና፣ ጀግናን ያከብራል” የሚባለው ሀገረሰባዊ ብሂል መሠረት የሌለው እንዳይመስለን፡፡ አርቆ አሳቢው ኢትዮጵያዊ ገብረሕይወት ባይከዳኝ፣ አፄ ምኒልክን ለማመስገን፣ ለማወደስ አፄ ዮሐንስን መስደብ እንደማያስፈልገን የመከረው የዛሬ መቶ ዓመት አካባቢ ነው፡፡
ለገብረሕይወት አፄ ዮሐንስም አፄ ምኒልክም ሁለቱም ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ከመሆናቸው በፊት፣ “ሰው” መሆናቸው በሥራቸው ብቻ ተመዛኝ እንደሚያደርጋቸው በመረዳቱ ይመስለኛል፤ የሚያሳዝነው ግን ከመቶ ዓመት በኋላ የነገብረሕይወትን እሳቤ ማጤን የተሳነን “ደንቆሮዎች” እጅግ እየበዛንና በድንቁርናችንም እየሰለጠንን መምጣታችን ነው፡፡ ወደ ታሪክ መምህሩ ትዝታዬ ተመለስኩ፤ የ”ሀይስኩል” መምህሮቹ ከተቀመጥንበት አካባቢ ሌላ መረጃ አፈተለከ፡፡ የታሪክ መምህሩ አስተያየቱን ሰጥቶ ቁጭ እንዳለ፣ “ወገኛ! ለዚህ ነው ከስልሳው ሃያ ሰባት (27/60) ያገኘው…” ሲል ሁላችንም ሳቅን፡፡ ሰብሳቢዎቹ፣ የሥነሥርአት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ አንድ ሌላ መምህር፣ “…ኧረ ደሞ! የቋራውን መሬት አስታውሰው አፄ ቴዎድሮስ…ኧረ ሱዳናዊ ነው እንኳን አላሉ” ሲል ሌላ ሣቅ መጣ፡፡ ከሰዓት በኋላ፣ ትምህርት ቤት ስንገባ ስብሰባ ያልገቡ መምህራን፣ “አፄ ቴዎድሮስ ሱዳናዊ ይሆኑ እንዴ!?” ብለው ጥርጣሬያቸውን ጠየቁ፡፡
በዚህ ዕለት ምሽት ታዲያ፣ ምክትል አስተዳዳሪው ተማሪያችን ወደ ክፍል አልመጡም ነበረ… የታሪክ መምህሩም ደፋሮች በድንቁርናቸው የሚፈጥሩት ጥፋት አሳስቦት ይሁን ወይም በሌላ ብቻ በአመቱ የኢህአዴግ አባል ሆኖ ማገልገል ጀመረ፤ ዛሬ በአማራ ክልል፣ በደቡብ ወሎ ዞን ያለ አንድ ትልቅ ባለሥልጣን ነው፡፡ በጥሩ አስተዳዳሪነቱም በተደጋጋሚ የክልሉ ተሸላሚ ነው፡፡ ተማሪው አስተዳዳሪያችን አሁን የት እንዳለ አላውቅም…ዛሬ የአሥተሳሰብና የአሠራር ለውጥ እንደሚፈጥር ግን ተስፋ አደርጋለሁ…በቃ!