ሁሉም ሀይማኖቶች ከመንግስት ጣልቃገብነት ነፃ ሆነው አያውቁም፡፡በሀይማኖት መካከል የመንግስት ጣልቃ -ገብነት!!

የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት አንቀጽ 11 ቁጥር 3 ”መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፤ ሀይማኖትም በመንግስት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም ” ይላል፡፡በሀገራችን ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ በወታደራዊው ደርግ እንዲሁም አሁን ስልጣን ላይ ባለው ወያኔን ጨምሮ ሁሉም ሀይማኖቶች ከመንግስት ጣልቃገብነት ነፃ ሆነው አያውቁም፡፡
ፍትህ፣ ነጻነት፣ እኩልነት እና አንድነት ለብዙ ሀይማኖቶች መሰረታዊ እሴቶች ናቸው፡፡ እነዚህ እሴቶች ላለፉት 21 ዓመታት በዘረኛው የወያኔ መንግስት እየተሸረሸሩ እና እየተመናመኑ ዛሬ ከነአካቴውም ለመጥፋት ተቃርበዋል፡፡ ስለመሰረታዊ የሰው ልጅ መብት እና ነጻነት እንዳይወራ የወያኔ የጥይት አፈሙዞች በእያንዳንዱ ሰው እና የህዝብ አገልግጎት መስጫ ተቋማት ላይ ተደቅኗል፡፡የእምነት ቦታዎችንም ሳይቀር በመድፈር ህዝበ-ምዕመኑ የኔ የራሴ የሚለው የአምልኮ ቦታ እና የአምልኮ ስርዓት እንዳይኖረው እያደረገ ነው፡፡
ከዚህ ቀጥሎ ወያኔ ከፍተኛ ቁጥር በያዙት በክርስትና እና በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ እያደረሰ ያለውን ወከባ እና ጥቃት በጥቂቱ እንመልከት፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ዙሪያ
የወያኔ አደገኛ ጥፋት በ1984 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን አራተኛ ፓትርያርክ የሆኑትን አቡነ መርቆሪወስን ከእምነቱ ቀኖና ውጭ በህገ-ወጥ መንገድ ከስልጣን በማባረር ይጀምራል፡፡ በምትካቸው ዘረኛ ተልእኮውን የሚያስፈጽሙለትን አባ ጳውሎስን ወደ ስልጣን በማምጣት ቤተክርስቲያኗ ለሁለት እንድትከፈል እድርጓል፡፡አባ ጳውሎስም የተሰጣቸውን የጥፋት ተልእኮ እስከ እለተ-ሞታቸው ድረስ ሲፈጽሙ እና ሲያስፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ ከእርሳቸው ሞት በኋላ ባለፉት ትቂት ወራት ሊደረግ የነበረው እርቀ-ሰላም ሂደት በወያኔ ጀሌዎች እንዲሰናከል ተደርጎ ወያኔ አላማውን ሊያስፈጽሙለት የሚችሉትን አቡነ ማትያስን ከህዝበ-ክርስስቲኑ ፈቃድ ውጭ ስድስተኛ ፓትርያርክ አድርጎ ሹሟል፡፡ በዚህም ምክንያት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት አሁንም በወያኔ ጥብቅ ቁጥጥር ስር በመውደቁ ህዝበ-ክርስቲያኑ በከፋ ሀዘን እንደተዋጠ ነው፡፡የቤተክርስቲያኗም ህልውና ከምንጊዜውም በላይ የከፋ አደጋ ላይ ወድቋል፡፡
ቤተክርስቲያን ካሳለፈቻቸው የመከራ ዘመናት ሁሉ አሁን ባለንበት ወቅት እጅግ የረቀቀ የጥፋት እና የተንኮል ሴራ ተደቅኖባታል፡፡ወያኔዎች ያለምንም ይሉኝታ እና ፍራቻ የዘረጉትን የጥፋት ሴራ እየፈጸሙት ይገኛሉ፡፡
ባስረጅነት ለመጥቀስ ያክል መናኝ ባህታውያን በጸሎት ተወስነው የሚኖሩባቸውን ታሪካዊ ገዳማት እንደ ታላቁ የዋልድባ ገዳምን በልማት ስም ይዞታውን በመቆጣጠር የቅዱሳን አባቶችን መካነ መቃብር አሳርሰዋል ፤ ዝቋላ አቦ፣አሰቦት ገዳም የመሳሰሉትን በእሳት እንዲቃጠሉ አድርገዋል፡፡ይሁን እንጂ ገዳማቱ በህዝብ ርብርብ ሙሉ በሙሉ ከመውደም ቢድኑም እሳቱን ለማጥፋት ግንባር ቀደም የሆኑ እና በቤተክርስቲያን ላይ የሚደርሰው ጥፋት እንዲቆም አቤት ያሉ ሰዎች በወያኔ የደህንነት ሀይሎች ተደብድበዋል፣ታስረዋል ፣የተወሰኑት እስካሁን የገቡበት አይታወቅም፡፡
የወያኔ አገዛዝ ባንድ በኩል መንግስት በሀይማኖት ጉዳይ ታልቃ አይገባም እያለ በሌላ በኩል ደግሞ የፖለቲካ ካድሬዎችን የሀይማኖት ካባ እያለበሰ በየቤተ-ክህነቱ በመሰግሰግ የማምለኪያ ቦታዎችን ወደ ገንዘብ መሰብሰቢያ ተቋማነት እየቀየራቸው ይገኛል፡፡ዛሬ አዲስ አባባ ውስጥ ምዕመናን በብዛት የሚሄዱባቸው እንደ መንበረ-ፓትርያሪክ ቅድስት ማሪያም፣ቦሌ መድሀኒያዓለም፣ የካ ሚካኤል ፣መርካቶ ራጉኤል፣አዲሱ ሚካኤል የመሳሰሉት አብያተ-ክርስቲያናት የሚመሩት በእምነት አባቶች ሳይሆን ወያኔ ምእመኑን እንዲከፋፍሉለት እና ገንዘብ እንዲሰበስቡለት በላካቸው የቄስ ካባ በለበሱ ካድሬዎች ነው፡፡በአንጻሩ ስለኢትዮጵያ አንድነት ቀን ከሌሊት የሚጽልዩ አባቶች እንደጠላት ተፈርጀው ለእስር ፣ለእንግልት እና ለግድያ ተዳርገዋል፡፡ለህዝበ-ምእመኑ እና ለቤተክርስቲያኗ ነፃነት ክብር ደንታ የሌላቸው ወያኔዎች የእግዚያብሄርን ቤት የፖለቲካ እድሜ ማራዘሚያቸው በማድረግ ለህዝበ ክርስቲያኑ ያላቸውን ንቀት በገሀድ እያሳዩ ነው፡፡
በእስልምና እምነት ተከታዮች ዙሪያ
በተመሳሳይ መልኩ በእስልምና እምነት ተከታች ላይ እየተፈጸመ የሚገኘው የእምነት አፈና ተባብሶ ቀጥሏል፡፡የህዝበ- ሞስሊሙ መሰረታዊ ጥያቄዎች
 የአወሊያ ትምህርት ቤት አስተዳደር በህገ-ወጥ መንገድ መቀየር
 እምነቱን በበላይነት የሚመራው የእስልምና ጉዮዳች ምክርቤት (መጅሊስ) ከመንግስት ጣልቃ-ገብነት ነፃ ይሁን
 በመንግስት አነሳሽነት የተጀመረው የሀባሽ አስተምህሮት ሁሉም የእስልምና እምነት ተከታዮች በግድ እንዲቀበሉት የሚካሄደው ወከባ ይቁም
 እንዲሁም ያለ አግባብ በሀሰት ክስ ተወንጅለው ለእስር የተዳረጉት የሀይማኖት መሪዎቻችን ከእስር ይፈቱ የሚሉ ናቸው፡፡
ዞሮ ዞሮ የሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄ በህገ መንግስቱ የተደነገገው ሀይማኖትን ያለመንግስት ጣልቃ ገብነት የመከተል መብት ይከበር የሚል አግባብነት ያለው ጥያቄ ነው፡፡
ነገር ግን ወያኔ ያለመደበትን መብት ማክበር ዛሬ ደርሶ ከየት ያምጣው?
ወያኔ የህዝበ-ሙስሊሙን ጥያቄ መልሻለሁ ብሎ ካወጀ ጀምሮ መልሱ ያልተመለሰለት መላው ኢትጵያዊ ሙስሊም “ድምፃችን ይሰማ” በማለት በሰላማዊ ትግል መብቱን ለማስከበር በአደባባ ከወጣ ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡በዚህም በጣም የተደናገጠው እና የፈራው ወያኔ ሰላማዊ ትግሉን ለማኮላሸት
ያልፈነቀለው ድንጋይ ፤ያልቆፈረው ጉድጓድ የለም፡፡ኮሚቴዎቻቸውን ከማሰር አንስቶ ከሙስሊሙ
ማህበረሰብ ፈቃድ ውጭ ምርጫ አካሂዷል፤የአንድነት እና የሰደቃ ፕሮግራሞችን እንዳይካሄዱ አግዷል፡፡
ኢቲቪ የተለያዩ ቅጥረኛ ሀባሾችን ሰብስቦ ውይይት በሚል ስም የህዝበ-ሙስሊሙን ሰላማዊ ትግል ጥላሸት ለመቀባት ጥፘል፡፡ከዚህም አልፎ በመላ ሀገሪቱ የሰላም ድምጽ በሚያሰማው ህዝብ ላይ የዱላ እና የጥይት ናዳ አውርዶበታል፡፡በዚህ ድርጊቱ በአሳሳ፣በሀረር፣ እንዲሁም በደሴ የንጹሀንን ህይወት ቀጥፏል፡፡ይህ ሁሉ ጥረት ውጤት ያላስገኘለት ወያኔ ሌላ አማራጭ ብሎ የያዘው ሙስሊም ያልሆኑ ወገኖች ሙስሊሞችን በጥርጣሬ እንዲመለከቱ ማድረግ ነው፡፡”ሙስሊሞች አክራሪ በመሆን እስላማዊ መንግስት ሊያቋቁሙ ነው፣ክርስቲያኖችን ለማጥፋት እየሰሩ ነው”በማለት አደገኛ ፕሮፖጋንዳ በአደባባይ አሰራጭቷል፡፡ለዚህም ማረጋገጫ ከሚሆኑት መካከል በኢትዮጵያ ቴሌቭዥን የተላለፈው “ጀሀዳዊ ሀረካት” የተሰኘው በሀሰት የተቀነባባረ ዘጋቢ ፊልም ይጠቀሳል፡፡ይህ ፊልም የወያኔ ጭካኔ የተሞላበት የእስረኞች አያያዝ እና የምርመራ ሂደት የተጋለጠበት እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ለወያኔ ያላቸው ታዛዥነት እና በሀገሪቱ የህግ የበላይነት አለመኖሩ በግልጽ የታየበት ነው፡፡
በመጨረሻም
በሀገራችን ኢትዮጵያ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ የመጣው የእምነት ነፃነት እጦት ሁላችንንም ከምንጊዜውም በላይ ሊያሳስበን የሚገባበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡የኢትዮጵያ ህዝብ በአብዛኛው የታሪክ ዘመኑ በእምነት፣በዘር ፣በቋንቋ፣በፖለቲካ ልዩነት ቢኖረውም ተከባብሮ እና ተሳስቦ የሚኖር ህዝብ መሆኑ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንባገነኖች በፈጠሩት የከፋፍለሎ መግዛት ፖሊሲ ሀገራችን ልትወጣው ከማትችለው የውድቀት እና የጥፋት አፋፍ ላይ ቆማለች፡፡ይህንን አደጋ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘን ማክሸፍ ግዴታችን ነው፡፡ ሊገጥመን ከሚችለው የማይበርድ ደም አፋሳሽ የእርስ በርስ ግጭት እና እልቂትም የምናመልጠው ዛሬ ሀላፊነታችንን አውቀን ፈጥነን ስንንቀሳቀስ ብቻ ነው፡፡በዚሁ አጋጣሚ የክርስትናም ሆነ የእስልምና እምነት ተከታዮች ከሌሎች ወገኖቻችን ጋር ተባብረን የሀገራችን እና የህዝባችን ጠላት የሆነውን ወያኔ በምንችለው መንገድ ሁሉ እንድንታገለው ጥሪ አቀርባለሁ፡፡
አመሰግናለሁ፡፡  በዮሴፍ ሽፈራው(ከጀርመን)