“በፍትህ እጦት ሳቢያ ኢትዮጵያዊነቴ ዛሬም አልተረጋገጠልኝም” ህዝበ ሙስሊም

ባለዙፋኖቹ ወገኖቻችን በውሥጣቸው ያነገሡትን የተሳሳተ አመለከካከት ጉድፉን በማሳየት ጉድፉን እንዴት ማስወገድ እንደሚቻልም ጭምር ልናቅጣጫቸው ይገባል።በመሆኑም ሙስሊሞች ለሽብርተኝነት ምሽግ እንዲንሆን የሚያስችለን ተክለ ቁመና እንደሌለን ከማስረዳትና በተግባር ከማሣየትም አልፈን የሠላም ዘብ፣ከሽብርተኝነት ጋር ደግሞ ፀብ መሆናችንን በተግባር ማሳየት ያስፈልጋል።
ኢህአዴግ የተያያዘውን ይህን የተዛባ የሽብርተኝነትና የአክራሪነት አረዳድ፣መብት ጠያቂውን ማህበረሰብ በሽብርተኝነት ፈርጆ ኃይል መጠቀም፣የአህባሽን አስተምህሮ ማስፋትና አንቅፋት ያለውን ክፍል በፕሮፓጋንዳ ማሸማቀቅና አጋር የመግዛት ዘመቻ ዶ/ር ሽፈራው ተ/ማርያም “የቤት ሥራችን “ ሲሉ ጠርተውታል።አቶ ኩማ ደመቅሳ ደግሞ በዚህ ዘመቻ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ያሉ የኢህአዴግ አመራር ከልማትና ከሥራ ለወራት ተዘናግተው እንደነበር በአንድ ሥብሠባ ላይ ይፋ አድርገዋል።ሙስሊሞች ሀገሪቱ እያደረገች ያለችውን የፀረ-ድህነት ትግልና ትንቅንቅ ላይ ጉልህ ድርሻ ሊኖራቸው ይገባል።በመሆኑም ኢህ-አደጋውያኑ ስህተታቸውን እንዲያርሙና ወደ ልማት እንዲያተኩሩ ለማድረግ፤“በፍትህ እጦት ሳቢያ ኢትዮጵያዊነቴ ዛሬም አልተረጋገጠልኝም” በሚል ከባለዙፋኖቹ ላይ ተስፋ እየቆረጠ ያለውን ህዝበ ሙስሊም ተስፈኛ እንዲሆን ለማድረግ የመፍትሄው አካል መሆን ከህዝበ ሙስሊሙ ይጠበቃል።
ሀገራችን ኢትዮጵያ ካላት ጅኦግራፊያዊ አቀማመጥ፣ከህብረ ብሔረዊነቷ፣የተለያዩ ህብረ ሐይማኖቶችንና አስተሳሰቦችን ያቀፈች መሆኗ ልዩና ቀልብ ሣቢ ሀገር ብትሆንም እነዚህ ስጦታዎቿ የአክራሪነት ምንጮችም ሊሆኑ ይችላሉ-ፍትህን ማጣጣም ካልተቻለና እኩልነትን ማስፈን ካልተቻለ።በተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የምንሠማው ዓይነት የለየለት የሽብር አደጋና ክስተት ባናስተውልም ከሁሉም ሐይማኖቶችም ሆነ ብሔሮች መካከል የአክራሪነት አመለካከት የተጠናወታቸው ግለሰቦች ወይም አንጃዎች የሉም ማለት አይደለም።
i. ለሽብርተኝንት ትክክለኛውን ትርጓሜ መሥጠት
ኤርያል ሜራሪ Terrorism as a Strategy of Insurgency በተሰኘ ጥናታዊ ፅሁፉ ላይ “ሽብርተኝነት አማፂ አንጃዎች በመንግሥት ላይ ወይም መንግሥትም በራሱ ህዝቦች ላይ ወይም የውጭ መንግሥታት በሌላው መንግሥት ላይ እንዲሁም አንዱ ህዝብ በሌላው ህዝብ ላይ የሚያውጁት ነው።” ይላል።ሽብርተኝነት ከሠላምና ከልማት ጋረ አብሮ ሊሔድ አይችልም።እናም ሽብርተኝነትን ለማስወገድ ለሽብርተኝነት ትክክለኛውን ትርጓሜ መሥጠት ያስፈልጋል።ከተፈጥሯዊው ትርጓሜ አፈንግጠን ፓለቲካዊ ትርጓሜና የፓለቲካ ትርፍ ለማግኘት ሽብርተኝነትን መተርጎም ዋጋ ያስከፍላል።ያልተዛቡ ጥናታዊ ፅሁፎችን መሠረት ያደረገ ትርጓሜ በሠጠነው ቁጥር ወደ መፍትሔው እየተጠጋን እንመጣለን።
የኢህአዴግ መንግሥት ለሽብርተኝነት ያለው አረዳድ የፓለቲካ ትርፍ ውላጅ በመሆኑ “አሸባሪነትና ሁከትን” እየዘራ ይገኛል።የግለሠቦችን የአክራሪነት መገለጫ ለህዝቦች በማላበስ ጺሙን ያስረዘመ፣ሱሪውን ያሳጠረ፣ሒጃብ ያጠለቀውን ሁሉ፣ግንባሩ ላይ የሱጅድ (ስግደት) ምልክት ያለውን ሁሉ በተንሸዋረረ መነፅር መመንዘሩ ዛሬ የሚስተዋለውን ዋጋ እንዲከፍል አድርጎታል።የህዝቦችን ንቃተ ህሌና መጨመር፣የህዝበ ሙስሊሙ ሁለንተናዊ ተሳትፎ ማደግ፣የሐይማኖት ትዕዛዛትን ተግባራዊ ማድረግን ሁሉ የሽብርተኝነት መገለጫዎች አድርጎ ማቅረቡ ሽብርተኝነትን ያነግሳል እንጅ ሊያጠፋው አይችልም።ደዕዋ ማድረግን፣ቁርዓን ከውጭ ማስመጣትን፣በመንግሥት ወንበር ላይ ሂጃብ አድርጎ ወይም ሱሪ አሳጥሮ መታየትን፣የሙስሊሙ መገናኛ ብዙሐን ማደግን የሽብር ተግባር አድርጎ ማቅረብ ይዘገያል እንጅ ሽብርተኝነትን ከመፍጠር ውጭ ፋይዳ ሊኖረው አይችልም።በመሆኑም ሽብርተኝነትን ከፓለቲካዊ ትርፍ ወይም የተዛቡ የጫት ቤት ጥናቶችን መሠረት አድርጎ ከመተርጎም መታቀብ አንዱ የሽብርተኝነት መፍትሔ ነው።
i. የሁከትና የሽብርተኝነት መንስኤዎችን ማጥናት
ጭቆናና የፍትህ እጦት የሽብርተኝነት እናቶች ናቸው፡፡ሰዎች ወደው አሸባሪ አይሆኑም፤በመንግሥትም ሆነ በሌላ ቡድን የሚደርስባቸውን ጭቆና ለመከላከል ሲሉ ወደ አመፅኝነትና የሽብር ተግባር ይገባሉ።የፍትህ መዛባት በህዝቦች ውሥጥ የተስፋ መቁረጥ ዘርን በመዝራት የሽብርተኝነትን ፅንስ መቋጠሩ አይቀርም።ጨለምተኝነትና ተስፋ መቁረጥ ህዝቦችን ወደ ሁከትና አመፀኝነት እንዲያመሩ ጉልበት ይሆናሉ።የሰው ልጆች ለጭቆና እስከ ማዕዜኑ ሊተኙ አይችሉም።ህልውናቸውን የሚፈታተን ግፍ ባጋጠማቸው ጊዜ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያደርጉት መፍጨርጨር መንገዱና ክብደቱ ይለያይ እንጅ ነብስ ያለው መንቀሳቀሱ አይቀርም።ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው ይህ ፍቀው ሊያስወግዱት የማይችል ህግ ነው።ድህነትና ኋላ ቀርነትም በራሳቸው ለሽብርተኝነት አቅም መሆናቸው አይቀርም።
ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ዛሬ ንቃተ ህሌናቸው ተለውጧል፣ፓለቲካዊ አቅማቸው አድጓል፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፏቸውም የሚጠበቀውን ያህል ባይሆንም ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል።ኢትዮጵያዊነትን እንደ መብት መመልከት ጀምረዋል።ለስጋት ናችሁ እባጭ ሊተኙ አይችሉም፣ዲናዊ ግንዛቤያቸው በጣሙን ተቀይሯል።ይህ የሚበረታታ ለውጥ እንጅ በስጋት ከጥግ ሆነው የሚመለከቱት አይደለም።ይህን ለውጥ ማስተናገድ የሚችል መዋቅርና ፓለሲ መንደፍ ያስፈልጋል።የቀድሞው ጠ/ሚኒስቴር መቻቻል ብለው ያቀረቡት “የታቦት ሸኚነት” ምሣሌ ኢህ-አደጋውያኑ ዛሬም ህዝቡን በዘመነ አፄ ዩሐንሰ ማንነቱ እያሠሉትና እየጠበቁት መሆኑን ያመላክታል።መንግሥት ለህዝበ ሙስሊሙ የነደፈው “ቁመሕ ጠብቀኝ” ስትራቴጅ የህዝበ ሙስሊሙን ሁለንተናዊ እድገት ማስተናገድ አልቻለም።ዓለም አቀፍ የፓለቲካው ሽሚያ በፈጠረው ስጋት ተከቦ ህዝበ-ሙስሊሙን በጅምላ በሽብርተኝነት መፈረጅ ዋጋ ማሰከፈሉ አይቀርም።ዲናዊ ትዕዛዛትንና ህግጋትን በሽብርተኝነት መፈረጅም ረጅም ጉዞ የሚያስኬድ ሊሆን አይችልም።ቁርዓናዊ ጭብጦችና ህግጋቶችን በአመፅ ቀስቃሽ መፈረጅም ፍፃሜው ዶግ-አመድ ነው የሚሆነው።
ኢህአዴግ ሽብርተኝነትን እንደ ሽፋን በመጠቀም በተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ላይ፣የፓለቲካ ሓያሲያን ጋዜጠኞች ላይ፣በሙስሊሙም ሆነ በክርስትና ልሒቃን በአጠቃላይ በህዝቦቹ ላይ እየፈፀመው ያለውን የሽብር ተግባር በማጋለጥና በመግታት የሽብርተኝነትን አደጋ መቀነስ ይቻላል።ፓለቲካዊ ቱርፋት ወለድ ያልሆኑ የፅንፈኝነት መንስኤዎችን በጥናት በማስደገፍ ለመንስኤዎቹ ፍቅርና ፍትህ ያካበበው መፍትሔ መፈለግ ብቻ ነው የሽብርተኝነትና የፅንፈኝነት ክትባቱ።
ሙስሊም ዜጎች ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ በመታወቂያ ከመኪና ማስወረድ፣ሀሣብን የመግለፅ መብትን ማፈን፣የዳዕዋና የዒልም ቦታዎችን በሽብር ካምፕ መፈረጅ፣ኡለማኦችና ምሁራንን ለወህኒ መዳረግ፣ሪዙ የተንዠረገገ ሱሪውን ያሣጠረን ሁሉ የደህንነት ኢላማ ማድረግ፣ኢስላማዊ መገናኛ ብዙሀንና ድርጅቶችን መከርቸም፣የመደራጀትና የመሰብሰብ ሕገ-መንግሥታዊ መብትን መንፈግ፣መሳጅዶችን ለወታደር ጫማ መዳረግ፣ህዝቦች ላይ የጥይት እሩምታ በመልቀቅ ንፁሐንን ወደ መቃብር ማዳፋት፣ሙስሊሞችን በሙሉ ማወከብና ማሠር አከራሪነትን ይወልዳሉ እንጅ ፅንፈኝነትን ማጥፋት አይቻላቸውም።መፍትሔው የዜጎችን መብት ማክበር፣ለሕገ-መንግሥታዊ መብቶች ትግበራ መጣርና የሕዝበ ሙስሊሙን ለውጥ እንደ መልካም ለውጥ ተቀብሎ የሚስተናገድበትን አግባብ መፍጠር ብቻ ነው።
ii. ብረት ለሽብርተኝነት አቅም እንጅ መፍትሔው ሊሆን አይችልም
ሽብርተኝነትንም ሆነ ሁከትን ለማስወገድ ሁነኛው መፍትሔ ፍትህን ማስፈን ነው።ጨለማ በብርሀን እንደሚረታ ሁሉ ጨለምተኝነትን ድል ለመንሳት ተስፋ ፈንጣቂ መሆን ያሻል።ህዝቦችን ወደ ፍቅር ለመጥራት የሚቻለው የፍቅር እጅ በመዘርጋት ብቻ ነው።ሠላምንና ኢ-ፍትሐዊነትን በአንድ ላይ ማስኬድ አይቻልም።የሠላም መቀናጆ ፍትህ ነው የግፍም መቀናጆ ቀውስና ሁከት እንጅ መረጋጋት ሊሆን አይችልም።
ሽብርተኝነትን መዋጋት የሚቻለው በፍቅር እንጅ በጦር አቅም ሊሆን አይችልም፤በጦር ህዝቦችን እንጅ ሠላምን መቆጣጠር አይቻልም።በነፍጥ አፈሙዝም አሸባሪዎችና ሁከተኞችን እንጅ ሽብርተኝነትንና ሁከትን መግደል አይቻልም። የሀሩን የህያን ሐሳብ የሚያጠናክሩት ሚስተር ረሽድ ዓሊ “ዘሂንዱ” ለተሰኘ ድህረ-ገፅ “እንደት ሽብርተኝነትን ማስወገድ እንችላለን?” በሚል ርዕሠ-አንቀፅ ስር “በይማኖትና በዘር ያልተገደበ ፍትሕ፣እኩልነት፣ይቅርባይነትና ድምበር ዘለል ፍቅር ብቻ ናቸው ሽብርተኝነትንና አሸባሪዎችን ማጥፋት የሚችሉት” በማለት ፍትህ የሽብር ክትባት መሆኗን ያሰምራሉ።
የኢህአዴግ መንግሥት ሽብርተኝነትን ለመዋጋት በሚል እየተጠቀመው ያለው የኃይል እርምጃ ሽብርተኝነትንና አመፅን ከመውለድ ውጭ ዘላቂ መፍትሔ ሊያመጣ አይችልም።ኢህአዴግ አክራሪነትንና ሽብርተኝንነት ለማጥፋት የሚያስችል ተክለ ቁመና መገንባት ያስፈልገዋል።አሁን በተግባር ያለው ኢህአዴግ ይህን ያሳካል ብሎ ለማመን ያስቸግራል።ይልቁንም ሽብረተኞችን መፍጠር የሚያስችል እንቅስቃሴ እያደረገ ነው።በስውር አጀንዳ ባረገዙ፣የስልጣንና የንዋይ ፍቅር በተጣባቸው ቡድኖች የተጠለፈው የኢህአዴግ መንግሥት አልቅቶቹን ከዓይነ ህሌናው ላይ አላቆ፣ቅንቅኖቹን ከእዝነ ልቦናው ላይ አራግፎ ወደ ህዝቦቹ ሊመለከት ይገባዋል።ሽብርተኝነትን እንደ ሽፋን በመጠቀምና በማስፋራራት ፕሮፓጋንዳ ዙፋን ሊረጋ አይችልም ለህዝቦች ፍትህን በገፍ አቅርቦ ከህዝቦች ፍቅር በመውሰድ እንጅ!!
ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይየኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጭቆና በሽብርተኝነት ሽፋን ውስጥ ከሚለው ያልታታመ መፅሀፌ የተወሰደ