የተደፋው የሃሰን ታጁ ቀለም ሲታፈስ/ክሽፈት 1/

የአላህ ራህመትና እዝነት ለተወዳጁ ኡስታዜ ይሆን ዘንዳ ዱዓዬ ነው! ሀሰን በአላህ ይሁንብኝ ለአላህ ብዬ በጣምም እወድሃለሁ! ለአንተ ያለኝን ክብርና ሞገስ ብዕሬ ልትከትብ ይሳናታል ግና መምህር ሆይ! ለአንተ ያለኝ ፍቅርና ሞገስ የከሸፈች ብዕርህን ከመተቸት እንዳያሳብዬኝ አንተው ባስተማርከኝ መሰረት እንዲህ ስል ብዕርህ መክሸፏን አሊያም ጉዞ ወደ መክሸፍ ማለቷን አሳውቅሃለሁ፡፡ልሒቅነትህ የኔን የአፃፃፍ ድክመት እንደሚረዳኝ በማሰብም ፅሁፍህን በገባኝ መልኩ አብጠልጥየዋለሁ፡፡
ኡስታዝ ሀሰን ታጁ የፃፈውና በነ አቢይ ጣሰው ለህዝብ ይፋ የሆነውን ፅሁፍ ባነበብኩ ጊዜና ተገረምኩም እራሴንም ጠየቅኩም ግና ፅሁፉ የሀሰን ታጁ ብዕር መክሸፏን አበሰረኝ፡፡ሀሰን ይህ የተቃውሞ አካሔድ ሌላ መንገድ ቢፈለግለት ይልና በተለይም የጁሙዓ ተቃውሞዎች መቋረጥ እንዳለባቸው አልፎም ኮሚቴዎቹን ለይቅርታ ያቅዳቸዋል።ለትነተና እንዲመቸውም ሁለት ቡድኖችን ፈጥሯል አንደኛው ተቃውሞው እንዲቀጥል የሚፈልግ ወጣትና ሁለተኛው ደግሞ ተቃውሞ ይቋረጥ የሚሉ ልሂቃን ናቸው።
እንግዲህ ከዚህ ይጀምራል የሀሰን ብዕር ክሽፈት ወጣቶችን አላዋቂ፣ስሜተኛ፣ጃሂል አድርጋ ለማቅረብ ሞክራለች አሊሞች ምሁራንና የሀገር ሽማግሌዎች ብሎ የሰየማቸው ቡድኖች ደግሞ የሀሰን ሃሳብ የሚደግፉ ብቻ ሳይሆኑ በወጣቱ ላይም ጣት የሚቀስሩ ናቸው።በዚህ ፅሁፉ ጃሂልና ዓሊም ብሎ ቢከፍለው የተሻለ ይሆን ነበር! ያ ካልሆነ ግን ሀሰንን ያገኙት ወይም ያገኛቸው ወጣቶች (ተቃውሞ እንዲቀጥል የሚሹት) ፅኁፉ በገለፃቸው የአስተሳሰብና የእውቀት ደረጃ ካሉ ኡስታዝ ውሎው ከማይማን ጋር ነው ለማለት እደፍራለሁ፡፡የተሳሩ ወንድሞቻችንን ግፍ እንበቀላለን፣መንግስትን እንጥላለን፣ሙቀቱ ደስ ይላል፣መንግስትን እናናደውና ተቃውሞውን እንደበቅበታለን በሚል የአስተሳሰብ ምንዱባን ውስጥ ሆነው ይህን ታሪካዊ ትግል የተቀላቀሉ ወጣቶች እንኳን በኡስታዝ ዙሪያ በኔ በኩል ካሉ “ኢትዮጵያችን የት ነው ያለችው?” ያስብላል።እኔ የማውቃቸው ወጣት የትግሉ አጋሮች የሚታገሉበት የጠራና ውሃ የሚቆጥር ዓላማ አላቸው።ይህም ኢህአዴግ በኢስላምና በሙስሊሞች ላይ የሚያደርገውን ጭቆናና ግፍ መቃወም ነው።እናም ለኡስታዝ የምለው አንተ የጠቀስካቸው ወጣቶች እንደ ህዝብ ባይጠፉም እንደ አቢይ የትግሉ አራማጆችና ተዋናዮች ግን የሉም ነው!
የብዕሯ ክሽፈት ግን ጡዘቱን የነካው አሁን ላይ የበኩር ጥያቄዎቹ ሞተዋል በማለቷ ነው። እኔ ግን እላለሁ ጥያቄዎቹማ ከጥንት ልፍስፍስ ጮርቃነታቸው ጎልምሰውና ደርጅተው ዛሬ ጥርስ አውጥተዋል! ከተራ የመጅሊስና የአወሊያ ጥያቄ ወደ ኢስላምና ሙስሊሞች ህልውና ይከበር ተቀይሯል።
የአህባሽ በሃይል ለመጫን የተደረገው ሙከራ የሀሰን ብዕር እንደከተበችው ሞቶ አልተቀበረም ይልቁንም ይበልጥ ጉልበቷን ጨምራ አቅሟን አደርጅታ በአራት ኪሎ አፈሙዝ ጦንችታለች ተገዳዳሪዎቿን አንድም ወደ ስደት አንድም ወደ ግዞት አግዛ ያለ ተቀናቃኝ በየመሳጅዳችን ገብታለች።የነ አህመድን ጨሎ ድንበሯን አልፋ ከገጠር እስከ ከተማ ባሉ ማሳጅዶቻችንና አቢዮታዊ አህለ ሱና ወልጀመዓ አደረጃጀት ከፌደራል እስከ ቀበሌ ደርጅታለች? እና ኡስታዜ እኛ ወይስ የአህባሽ ጉዞ ሞቶ የተቀበረው? አህባሺያኑ ዙፋን ተሰጥቷቸው በኮሚቴዎቻችንና በቀለም ቀንድ ዓሊሞቻችን ላይ የ”ሚህና” ችሎት ጥለው ችሎት ላይ በተሰየሙበት ወቅት እንዴትስ የሀሰን ብዕር የአህባሽ ጉዳይ ሞቶ ተቀብሯል ልትለን ቻለች? ምኑ ነው የሞተው ብዬ እንዲጠይቅ እገደዳለሁ ሱሪውን ያሳጣረ፣ፂሙን ያንዠረገገ፣አህባሽኛ ወግ ያልጠረቀ፣እጁን በኮሚቴው ላይ ያልቀሰረ፣ለሚህናዊው ችሎት እውቅና ያልሰጠ ሁሉ ጠዋት ወጥቶ ማታ ቤቱ በሰላም ስለመመለሱ እርግጠኛ ባልሆነበት ወቅት አህባሽ እንዴት ሞታል ልትለን ቻለች ብእሯ?
እቃ እቃ ነው ምርጫ?
የኡስታዝ ብዕር ተቃቀውሞው መጅሊስን የምርጫ ባህል ማስቀየር መቻሉን ይጠቅስና ከአንግዲህ “የእድሜ ልክ መጅሊስ” አይኖረንም ይላል፡፡…ይቀጥልናም “በሂደቱ ያለን ቅሬታ እና አስተያየት እንዳለ ሆኖ ወደ ኋላ መመለስ ይቻላል ብዮ ግን አላምንም” ይላል! እኔ ግን እላለሁ የመጅሊስን የምርጫ ባህል ከመስጅድ ወደ ቀበሌ መዞሩ አሊያም ፍፁም የልጅ እቃ እቃ የሚመስል ምርጫን እንደ ልዩ ለውጥ አድርጌ መቀበል አልችልም።ሰፊውን ሕዝበ-ሙስሊም ያላሳተፈ፣በኢህአዴጋዊው አህለ-ሡና ወልጀመዓ የተደራጁ ሙሾ አውራጆችና የመለስ ሙት መንፈስ አምላኪዎች (ኦኩንቶች) ከቀበሌ የተሰገሰጉበትን ምርጫ እንዴትስ ልዩ ለውጥ ያመጣ ልንለው እንችላለን? ለኔ ግን የአሁኑ ምርጫ የሚሰጠኝ ትርጉም ሌላ ነው! መንግስት ሙስሊም ዜጎቹን የናቀበትና በግልፅ ያዋረደበት! ኦርቶዶክሱን በቀበሌ ወይም ሌላውን በቀበሌ ብሎ የማይሞክረውን በሙስሊሙ ላይ እውን አድርጎታል ይህ ፍፁም ንቀት ነው! በደልም ነው!ከአሁን በኋላ የእድሜ ልክ መጅሊስ ባይኖረን የእድሜ ልክ ቁጭትና የቀበሌ ምርጫዎች ግን ይኖሩናል! የኡስታዝ ብዕር በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ያሳረገችው ታሪክ አይለወጥም ወግ በእርግጥ ያስደነግጣል? እኔ ግን እላለሁ ለምን ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም? ወቅትን መመለስ ባንችልም የምርጫውን ንቀትና ጉድፎች ግን መልሰን አራት ኪሎ እንዲሰበሰቡ ማድረግ እንችላለን።የሙስሊሙን ድምፅ ግን ከቀበሌ ወደ መሳጅዶቻችን መመለስ እንችላለን። የኢህአዴግን ስውር እጆች ወደ ብብቶቻቸው እንዲመሰሉ ማድረግ ግን እንችላለን።
የኡስታዝ ብእር ክሽፈቷን ቀጥላለች አዲሱ መጅሊስ ለውጥ ላይ ነው ትለናለች! “በአዳማ ያደረጉት ጉባኤ አጠቃላይ መንፈስ መጅሊስ የአቅጣጫ ለውጥ እያደረገ መሆኑን አመላካች ነው።” የኡስታዝ ሀሰን ብእር ለውጥን እንዴት ነው ያሰላችው? ዛሬም ድረስ አህባሽ የመጅሊሱ ኦፊሲያሊያዊ እምነት ሆኖ ሌላው ጀመዓ ወደ ስደትና ግዞት እንዲገፋ የሰቆቃው ባለድርሻ በሆኑበት ወቅት እንዴት ለውጥ ላይ ናቸው ለማለት የሀሰን ብዕር ደፈረች? ሙስሊም ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ለማእከላዊው ጓንታናሞ ሲገበሩ ሙስሊም ልሒቃን በመንግስት ሚዲያ ሲብጠለጠሉና ሲበየኑ ከዳር ሆኖ የሚዲያ ጉልበት የሆነ ድርጅት፣ሙስሊም ምሁራንና ሰራተኞች በየስራ ቦታቸው በስም በፂማቸው፣በሒጃብ ኒቃባቸው የእነ እነቶኔ ጣት ሲቀሰርባቸውና ሲባረሩ አንዳችም ለማለት ያልደፈረ ሺባ አደረጃጀት እንዴት እራሱን ማቅናት ይቻለዋል? መንግስት በሙስሊም ህዝቦቹ ላይ ዳግማዊ ቀይ ሽብርን ሲያውጅ፣በህዝቦች መካከል የኢንተርሀምዌ ሽል ሲጠነስስ ሃግ ያላለ! የኡማውን ጩኸትና እንባ ከመጤፍ የቆጠረ መጅሊስ እንዴት ለውጥ ላይ ነው ብሎ አሰበ? አዲሱ አመራር ከመጣ ወዲህ የድሮዎቹ አመራሮች ያሳሰሯቸውን ኮሚቴዎች ለማስለቀቅ ምንስ ጥረት አደረገ? እንጃ! ብቻ የሀሰን ብዕር ክሽፈቷ አስደንጋጭ ነው።
የሀሰን ታጁ ብዕር ኢህአዴግን ፈፅማ አታውቀውም “የሃገራችን የሴኪዩላር ስርኣት ኢ-ሃይማኖታዊ ሲሆን ግብግቡና ጭፍጨፋው ከተራዘመ ግን ወደ ሁለተኛው ዓይነት(ፀረ-ሐይማኖታዊ) ሴኪዩላሪዝምነት ልንገፋው እንችላለን።” ብላ ፅፋለች። አዎ! የኔና የኡስታዝ ትልቁ ልዩነት የሚመነጨው ከዚህች መሰረታዊ አስተሳሰብ ነው። እኔ ባሉኝ መረጃዎች የኢህአዴግ መንግስት በተለይም በኢስላም ላይ የሚከተው ርዕይት ፀረ-ሐይማኖታዊ እንጅ ኢ-ሐይማኖታዊ ፈፅሞ አይደለም።ኢ-ሐይማኖታዊ ሴኩዩላሪዝም “አትንካኝ አልነካህም! እጅህን አውጣ እጄን ላውጣ!” ከሚል ጭብጥ የፈለቀ ነው! ታዲያ ኡስታዝ ኢህአዴግ ኢስላምን ለማንኮታኮት አልተንቀሳቀሰም እያልከን ነው? ሒጃብና ሶላትን በህግ ለመከልከል አልሞከረም አያልከን ነው? ከቁርዓን የተመዘዙ ከሀዲስ የተሳቡ ጥቅሶች የአሸባሪነት ምንጭ ሆነው የፀረ-ሽብር ህግ አንቀፅ ተጠቅሶባቸው ሙስሊሞችን ወደ ዘብጢያ እንዲወረወሩ አልተደረገም እያልከን ነው? በጁሙዓ ኹጥባ አቢዮታዊ ዴሞክራሲ አልተሰበከም አያልከን ነው? ዱዓቶች በመስጅድ ውሥጥ ዳዕዋ እንዳያደርጉ ኢህአዴግ መራሹ መጅሊስ ህግ አላወጣም እያልከን ነው? ዲናችን በኢህአዴጋዊ አመዳደብ ነባርና አዲስ? ኢትዮጵያዊና የውጭ?...ተብሎ ደረጃ አልወጣለትም እያልከን ነው? በእረግጥ ይህን አንተም ፅሁፍ ላይ አይቻለሁ በአላህ ፈቃድ ክፍል ሁለት ትችቴ ላይ አቀርበዋለሁ፡፡ ይቀጥላል…..
ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይ