የ4 ኪሎው ቅጽል ወያኔያዊ የገደል ማሚቱ /ክሽፈት 2/

አሁንም እደግመዋለሁ ክብርና ሞገስ ለወጣቱ የቀለም ቀንድ እኔን ከጨለማ ሊያወጣ ወጣትነቱን መፅሃፍ ውስጥ ለቀበረው ኡስታዜ ሀሰን ታጁ!! አዎ! እደግመዋለሁ! ዛሬም ለአላህ ስል አወድሃለሁ፡፡ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ገፆችን የተየበች ብዕርህ ብታስከፋኝ ሀሳቦችህን ባለኝ መረጃ መሰረት ላቃና እንሆ እፅፋለሁ!!
ትላንት በክፍል አንድ ፅሁፌ ላይ መንግስት የኢስላምን ደረጃና መደብ የሸነሸነበትን ደረጃ (standard) የኡስታዝም ብዕር ገቢራዊ አድርጋው በመመልከቴ እጅጉን አዝኛለሁ፡፡ ”የኢትዮጵያ እስልምና” ስትል ለኢስላም ዜግነትን ስትቸር አነበብኩና ያች የማውቃት ብዕር አልመስልህ አለኝ! ከብዕሯ የምጠብቀው ኢትዮጵያዊ ሙስሊም እንድትል እንጅ የአራት ኪሎዎቹን ቅፅል (adjective) ትዋሳለች የሚልም እምነት አልነበረኝም! ለዚህማ ኢቲቪን ማን ያዘብን?

ሌላው ሳላሰምርበት የማላልፈው አዎ! የኡስታዝ ብእር ኢህአዴግን አታውቀውም! ኢህአዴግ የነቁ ሙስሊሞች እስካሉ ድረስ፣የተማሩ ሙስሊሞች እስካሉ ድረስ፣ታሪክን ቆፋሪ ሁነታን ተንታኝ ብዕርተኛ ሙስሊሞች እስካሉ ድረስ አርፎ አይተኛም! ምክንያቱም ሟቹ ሰውዬ ከ3 አመታት በፊት የነቁት ሙስሊሞች ናቸው ጠላታችን ብለው ኑዛዜ አስቀምጠዋልና! ዓለም አቀፋዊ ፀረ-ኢስላም እንቅስቃሴ ልዕልናው እስከቀጠለ ድረስ ኢህአዴግ የዚህ ዘመቻ የአፍሪካ መሪ ትርፍ አጋባሽ አንጃ ነው።በፀረ-ሽብር ዘመቻና ዛቢያ በተሽከረከረ ቁጥር ከእኛ በግብር ከሚያገኘው የላቀውን ገንዘብ ያገኛልና! ኢትዮጵያችን በጄኦግፊያዊ አቀማመጧም ሆነ ካላት ታሪካዊና ተጨባጭ ዓለም አቀፋዊው የርዕዮተ-ዓለም ፍትጊያና ፍጭት ባለቤቶች ይፈልጓታል፡፡

ከሶቭየት ህብረት መንኮታኮት ጋር አብሮ የተንኮታኮተውን የኮሚዩኒስት ርዕይት ተከትሎ ለምዕራባውያኑ ካፒታሊስት ርዕዮት ስጋትና እንቅፋት ነው በሚል በተለያዩ ጊዜ ወለድ አጀንዳዎች ለሚዘመቱ ፀረ-ኢስላም ዘመቻዎች በምእራባውያኑ የዘመቻው አውድማ አድርገው ያጯት ኢትዮጵያችን የምትመራው በኢህአዴግ ነው፡፡ኢህአዴግ ደግሞ ከነዚህ መንግስታት የሚወረወርለትን አጥንት በህዝቦቹ ደም የሚለውጥ መንግስት ስለመሆኑ ከኔ ይልቅ የሀሰን ብዕር ፍርሃት እየሸበባትም ቢሆን የምታውቅ ይመስለኛል።ዛሬ ጦርነት ንግድ መሆኑን ኡስታዝ የሚያጣው አይመስለኝም! ካጣውም ጠ/ሚ ኃ/ማርያምም በሲመታቸው ማግስት በፓርላማ ውሏቸው መናገራቸውን የሰማም ይመስለኛል!
ኢህአዴግ ለዚህች ንግዱ በተለይም ከደደቢት ጀምሮ ይዞት ለመጣው ፀረ-ኢስላም አቋሙ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ ያሰባቸውን ዲናዊ እንቅስቃሴዎችንና ተዋናዮችን በተለይም ዱዓቶች፣ሙስሊም ተማሪዎችና ምሁራን፣ሙስሊም ጋዜጠኞችና ፅሀፍቶችን፣ሙስሊም ፓለቲከኞችና አመራሮችን አንድም ሳይጨፈልቅ ወይም በ18ኛው ክ/ዘመን ስሌት ባሰፋላቸው ልብስ ውሥጥ እስካልተገኙ ድረስ ኢህአዴግ በኢሰላም ላይ ያወጀውን ዘመቻ የሚገታም አይሆንም። የኡስታዝ ብዕር መረጃ ያጠራት እዚህ ገደማ ነው፡፡ተቃውሞው መቀጠሉና መፋፋሙ ያስከተላቸው ኪሳራዎች ብሎ ከዘረዘራቸው መካከል በርካታ ዱአትና አሊሞች አገር ጥለው መሸሻቸው፣በሀገር ቤት ያሉትም በፍርሃት እንዲርዱ መሆናቸው፣ውጥረትና መፈራራት መንገሱ፡፡ወጣትና ህዝብ ተኮር የመስጊድ ፕሮግራሞች መቆማቸው….. እነዚህ ሰቆቃዎችና ኪሳራዎች ይመጡ ዘንዳ ኢህአዴግ ጥረት በማድረጉና ወደ ተግባር በመሄዱ ተቃውሞው ተጀመር እንጅ ተቃውሞው የፈጠራቸው ውጤቶች አይደሉም።በሀሰን ብዕር እይታ አሁን ያለው ሰቆቃና መከራ የእንቅስቃሴው ውጤቶች ናቸው፡፡እኔ ግን እላለሁ አሁን ያለው ሁሉ የኢህአዴግ ፀረ-ኢስላም አካሄድ የወለዳቸው የመከራ ውላጆች ናቸው። ኡስታዝ የማያውቃቸው ወጣቶችም እነዚህን ኢህአዴግ ወለድ መከራዎች ለመቃወምም ነው ድምፃችውን እያሰሙ ያሉት።የኡስታዝ ብዕር እንቅስቀሴው ከቆመ “መንግስት ካሉበት ብዙ አጣዳፊ ሐገራዊ አጀንዳዎች አኳያ በዚህ ሓይማኖታዊ አጀንዳ ላይ ብዙ ጊዜ ለመቆየት ፍላጎት ይኖረዋል ብዮ ማሰብ ይከብደኛል።…ውጥረቱ ሲረግብ አንፃራዊ እርቅና ሠላም ይወርዳል፡፡…አገር ጥለው የሸሹ ወንድሞች ወደ አገር ቤት ይመለሳሉ የተዘጉ የዳዕዋ አንደበቶች ቀስ በቀስ ይከፈታሉ፡፡የተቋረጡ የኢልም ማእዶች ዳግም ይዘረጋሉ” የሚል ግምት አስቀምጣለች!ለዚህም ነው የሐሰን ብዕር አንድም ኢህአዴግን አታውቀውም ወይም የአሁኑ ተቃውሞ ምንጭ አልገባትም እያልኩ ያለሁት! ለኢህአዴግ ይህ በኢስላምና በሙስሊሞች ላይ የጀመረው ዘመቻ አጣዳፊ ሐገራዊ አጀንዳው ነው!ኡስታዝ ያልተረዳው ይህንን ነው። በ5 አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ውሥጥ እንደ አንድ አጀንዳ ያካተተው መሆኑንማ በእቅዱ ትግበራ ማግስት በአቢይ አጀንዳነት ከመጀመሪያዎቹ እረድፍ ያሰለፍኩት አጀንዳዮ ነው በሚል ወደ ተግባር መግባቱ ነው፡፡የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ተጨባጭ ያላገናዘበና ጠርዘኛ የሆኑ የለቅሶ ቤት ወግ-ወለድ ጥናታዊ ፅሁፎችንና ስትራቴጅዎችን በየ መድረኮች ላይ ከማላዘን አልፎ ታሪካዊ ስህተት ውስጥ ያስገባውን ትግበራ የጀመረው አቢይ አጀንዳዬ ነው ብሎ ስለያዘው መሆኑን ለኡስታዝ ማስታዎስ ምጥ ለእናቷ ይሆናል ብዮ አምናለሁ! መንግስት ተገዶ ከዚህ አረንቋ ውሥጥ የተደፈቀና በማይፈልገው አጀንዳ እንዲቦዝን የህዝበ ሙስሊሙ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ነው የጎተተው የሚል አመክንዮ ከሀሰን ብእር መታየቱ በእጅግም ያሳምማል! እኔ የማውቀው ህዝበ ሙስሊሙ ተረጋግቶና ሰላም አግኝቶ በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊው ውሎው ድል ተቀዳጅቶ እራሱንና ሀገሩን እንዳያለማ ወደ አላስፈላጊ አጀንዳ ያገባው ኢህአዴግ ነው! እናም ጥያቄዎቻችን በሰለማዊ መልኩ በፍጥነት ቢመለሱልንና ኢህአዴግ ከኢስላምና ከሙስሊሞች ላይ እጁን ቢያነሳ ህዝበ ሙስሊሙ ካሉበት በርካታ አጣዳፊ አጀንዳዎች አኳያ በዚህ ተቃውሞ ላይ ብዙ መቆየት አይፈልግም ነው እያልን ያለነው።
,,የሀሰን ብዕር የተፋቻቸው አብሻቂ ቃላቶች,,
ከኡስታዝ ብዕር የማይጠበቁት የቀላት ወልምታዎችንም በዚህ ፅሁፍ ላይ በማንበቤ አጅግም አዝኛለሁ! ለአብነት ያክል “አንዋር መራሽ” የሚል ሐረግ አንብቤያለሁ! ያማል! እንዴትስ ኡስታዝ የአሜሪካ መራሹን ስያሜ ከአንዋሩ የአርነት ውሎ ጋር ሊያጣባው ፈለገ? እኔ የማውቀው የአንዋር መስጅድ የሠላም ዘማርያን የኢህአዴግ ተመራሽ ሲሆኑ እንጅ አንዋር መራሽ ሲሆንም አይደል! እናማ ኡስታዜ ወረድ ብለህም “አመፅ (ኡንፍ)” የሚል ቃልም ተጠቅመሃል! የትኛውን ተቃውሞ በዚህ አስቀያሚ ቃል እየገለፅከው እንደሆነ ባይገባኝም ይህች ቃል ኢህአዴግን እንጅ እኛን የምትገልፀን ባለመሆኗ ማረፊያዋን በፍርሃት አሊያም በሌላ ምክንያት የሳጣሃት ይመስለኛል! እንዲህም ትላለች የኡስታዝ ብዕር “ሕገ-ወጥነትን ለአመት ማባበል አይቻልም!” አዎ! እውነት ብልሃል ችግሩ ሕገ-ወጡ ማነው? የሚለው ላይ ይወሰናል እንጅ! የእኛ የአንዋር መስጅድ ውሎም ምክነያትና ግብ ይኼው ነው! መንግስት በሕገ-መንግስቱ ከተከለለት ድንበር አልፎ ድንበር ተጋፍቶናል! ሕገወጦችን እየሾመና እያሞገሰ ሕግ-አክባሪዎችን ለግዞትና ለስደት በመዳረጉ ሕገ-ወጥነትን መለዮው አድርጓታልና ይህን መለዬህን ለብሰህ ለአመት ማባበል አንችልም ነው እያልን ያለነው! በአርግጥ የአንተም ብእር የኢህአዴግን ክስ ተቀብላ “ሕገ-ወጥ የሆነ ተቃውሞ ነው” ብላ ማፅደቋን መክተቧ ያማል!
የኡስታዝ ብዕር ከሽፋ ልታከሽፋቸው የታለሙ ኮሚቴዎች
የኡስታዝ ብዕር ኮሚቴዎቹን በእርቅና ይቅርታ የማስፈታት አማራጭ ለማህበረሰባችን አነስተኛ ኪሳራ ያለው አማራጭ ነው ትለናለች ለዚህም አስረጅ ይሆናት ዘንድ ከ1997 የፓለቲካ እስረኞች ጋር እያሰናሰለች ትንተናዋን ሰጥታለች።ይህ ክሽፈት ነው የኡስታዝ ሀሰን ብዕር በእውኑም ከሽፋለች! ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ አመክንዬ ጎትታለች! እንዴትስ የፓለቲካ እስረኞቹን ከኮሚቴዎቹ ጋር ልታሰናስል ቻለች! የእኛ ታሳሪዎች ስለ ሠላምና ሥለ-ህግ ሰብከውና አስተምረው ስለ-ልማትና መረጋጋት እየሰበኩ ነው ወደ ግዞት የወረዱት! የሠላምን ኑዛዜ ተናዘው ነው ማዕከላዊ የከተሙት!ጥያቄያቸውም መንግስት የሐይማኖታችንን ድንበር ግፍቷል እንጅ የዙፋን የፓርላማ መቀመጫችንን ነጥቋል አይደለም! ሌላው ብዕሯ ስለ ይቅርታ አደራረጉ ሒደት እንጅ ከይቅርታ በኋላ ይቅርታ ጠያቂ የፓለቲካ እስረኞች ምን እንደደረሰባቸው አንዳችም አታወጋም! እናም ቋጥኙን ዘንግታ ጠጠሩን ልታቀል መሞከሯ ብዕሯ ከሸፈች እንድል አስገድዶኛል! ኮሚቴዎቹ በይቅርታ ቢፊቱ ምን ሊፈጠር እንደሚችልም የዘነጋችው ይመስለኛል።የናፈቅነውን የአቡበክርን፣የያሲንን፣የበድሩን…ድምፅ በየ መሳጅዱ ልንሰማ? የደዕዋ ሥራዎቻቸው እንደ አሸን ፈልተው ሬክላማቸውን በየ ግድግዳው ተለጥፈው ልናይ? በሐገራቸው በሰላም ልጆቻቸውን ሊያሳድጉ? ነፃነት አግኝተው ያሻቸውን የዳዕዋ ፕሮግም ሊያዘጋጁ? ከንቱ ምኞት ነው።አዎ! የኡስታዝ ብዕር ይህን ከመፃፏ በፊት የ97 ግዞተኞች በድህረ-ይቅርታ ምን እንደደረሰባቸውና በምን ሁኔታ ላይ እንዳሉ ማጥናት ነበረባት! የቅድመ-ይቅርታ ሒደቱን ታሪክ ኡስታዝ ሲያጠና ድህረ-ይቅርታውንም መመልከት ነበረበት!
ብእሯ ቀጥላለች ኮሚቴዎቹን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የሚያከሽፍ አስረጅዋን ስትመዝ “ወንድሞቻችንን የምንወድ ከሆነ፣የእነርሱና የቤተሰቦቻቸውን ህይዎት ብሎም አገልግሎት የሚያሳስበንና የሚያስፈልገን ከሆነ” ትላለች አዎ!በአርግጥ ይህን ማሰብ እንቅልፍ ይነሳል! እኛ በድሎት ውሥጥ ሆነን የአቡበክርን ልጆች እንባና መከራ፣የያሲንን ባለቤት ትካዜ መመልከት ያሳምማል፣የሸህ መከተን ልጆች ቁዘማ መመልከትም ያስለቅሳል! ግና ጥያቄው ያለው ይቅርታው ብቸኛ አማራጭ ነው ወይ? የሚለው ነው። በፍፁም የይቅርታ አማራጭ በይቅርታው ማግስት ዳግም የአቡበከርን ልጆች ያለ አባት ማሳጣት የበድሩን ባለቤት ዳግም በድሩን ማሳጣት እንጅ ሌላን ሊያተርፍ አይችልም! ኮሚቴዎቻችንን እናውቃቸዋለን ያለ ኢስላም ሊኖሩ የሚሞክሩ አንገት ደፍተው ሀቅን ደፍጥጠው ሊኖሩ የሚችሉ አይደሉም ከይቅርታ ማግስትም ከኢስላም ጋር ይኖራሉ! አዎ!በዚህ ጊዜ ዳግም ሲታሰሩስ? ምን አማራጭ ልናመጣ ነው? ከዚህ ሽንፈት ወለድ፣ በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ አማራጭ ውጭ ሌሎች አማራጮችን መጠቀም ይኖርብናል!ሌላ ምን? ማሰብ ያስፈልጋል! ኡስታዝ ሀሰን “የነርሱ መታሰር ለጥያቄዎቻችን የምንፈልገው አይነት መልስ ስለማግኘቱ እርግጠኞች አይደለንም” ይለናል እኔም እላለሁ የእነርሱ መፈታትም ለጥያቄዎቻችን የምንፈልገውን ዓይነት መልስ ስለማስገኘቱ እርግጠኞች አይደለንም! በእርግጥ ግዞተኛው ያሲን እንዳለው እነሱ ከድመቱ አንገት ላይ ቃጭሉን ያሰሩትን ዓይጦች ድርሻ ወስደዋል! ቃጭሉን አሳሪ አይጦቹ ተበልተው አርነትን አግኝተዋል የኛዎቹ ግን ዘብጢያ ተወርውረዋል የኢህአዴግ ሕገ-ወጥነት ግን እየሰፋና እየጠነከረ መጥቷል!
ዶክተር ኢድሪስ
የኡስታዝ ሐሰን ብዕር ስለ ዶክተር ብትመሰክር ከእኔ ይልቅ የዶክተርን ውለታ ትረዳለችና በነባሩ አቋሟ ላይ ሆና ታሪኩን ብትፅፍለት የምደሰት እንጅ የምከፋ አይደለሁም! ይሁን እንጅ እንደ ሐሰን ታጁ ሁሉ እኛ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች የዶ/ር ኢድሪስን ውለታ የምንክድም አይደለን! እንደዚሁም በኮሚቴዎቻችንና በትግላችን ላይ ውሐ ለመቸለስ የቃጣውን ክንዱንም አንዘነጋም! በእርግጥ ከበስተኋላ ይፋ የሆነው ማንነቱ ቢያስከፋንም እይታችንን ሊያንሸዋርርብን አይችልም! የኡስታዝ ሀሰን ብዕር ግን የዶክተርን ታላቅነት ስትመሰክር “የመፍትሔ አመላካች ፅሁፎችን (116 የሚሆኑ) ፅፏል።” ስትል በአስረጅነት ጠቅሳለች! እኔም እጠይቃለሁ የመፍትሔ አመላካች ፅሁፎችን መፃፍ የሕዝብ ተወካዮችን በአደባባይ ከመወንጀል ግድፈቱ ከቶ ሊያነፃው ይችላል? በፍፁም ፍቅር ሀቅን፣ውለታ ተጨባጭን1234 ለመቅበር ከሞከረችማ አደጋ ነው! ለዶክተር ያለን ፍቅር ሌላ በሚዲያ ቀርቦ ያቀረበው በደል ሌላ! አዎ! የኡስታዝም ብዕር ስለ 116 ገፆቹ ብቻም ሳይሆን ስለ ዶክተር ግድፈትም ልታስነብበን ይገባት ነበር!
አጠቃላይ ግምገማ
የኡስታዝ ሀሰን ብዕር በርካታ ግድፈቶችም ቢኖሯት የማይካዱ እውነታዎችንም ይዛለች ይህን በአላህ ፈቃድ በቀጣይ “የሀሰን ታጁ እውነታዎች” በሚል የማቀርበው ሲሆን ኡስታዝ በዚህ ፅሁፉ ላይ እጅጉን ፍርሃትና መራድ ይታይበታል፣የአመክንዬም መፍረስ ይስተዋልበታል “በሸሪዓው ሚዛን መሰረት የቂን (እርግጠኛ ነገር) ከአጠራጣሪ (ዞን) ይቀድማል፡፡ለጥርጣሬ ተብሎ ተጨባጭ እውነታ አይጨፈለቅም፡፡” ይልና ይህንኑ አመክንዬ የሚንዱ በርካታ የሀሳብ ፍሰቶችን በዚሁ ፅሁፎች ላይ አስተውያለሁ፡፡አንዳንድ የቃላት አጠቃቀሙም ቢሆን ገፊና ሚዛን አልባ ሆነውም አስተውያለሁ ለአብነት ያክልም ወጣቱን በስሜተኛነት በአላዋቂነት ለመግለፅ ሞክሯል።ወጣት የተባሉት ቡድኖች ተቃውሞው ለምን እንደሚቀጥል ከመዘዟቸው 7 ሀሳቦች ውሥጥ 5ቱ በጣም የወረዱና ወጣቱን የናቁ ናቸው፡፡ ይህም ኡስታዝ ለጥናቱ የተጠቀመው ናሙና (sample) በጥሩ ሁኔታ አለመመረጡንና ህዝቡን የማይወክል መሆኑን ነው፡፡የእንቅስቃሴውን ውጤት የገለፀበት ጥንካሬና አስረጅም ያን ያክል አርኪ አይደለም ይልቁንም “እንቅስቃሴው ኮሚቴዎቹ ከታሰሩ ወዲህ ትርፋማነቱ እየቀነሰ መጥቷል” ብሎ ያምናል! ይህም እራሱን የቻለ ጥያቄ ያስነሳል።አጠቃላይ የሆኑ የተለጠጡ ፍርሃትና ስጋቶች የፅሁፉን ብዙ ገፆች መያዛቸው ብቻ ሳይሆን የኢህአዴግንና ዓለም አቀፋዊውን የፓለቲካ አዙሪት ባለመረዳት ከዚህ ሁሉ የኢህአዴግ ዘመቻ በኋላም ወንድም ሐሰን ታጁ ኢህአዴግን በመልካምነቱ ይጠረጥረዋል አብዝቶም ተስፈኛ ሆኗል፡፡
ትችቴን በዚህ ሳገባድድ ግን አሁንም ኡስታዝ የኢትዮጵያ የምንግዜም ምርጥ መሆኑን በመመስከር ነው፡፡ጃሒል ሆኘ የእርሱን ብዕር ስተችም የእውነት ነገር ሆኖብኝ ነው፡፡   ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይ