በሙስና የተገኙ ሃብቶች መረጃዎቹ እንዳይወጡ ታፍነዋል::አቅም አልባ ቁርጠኝነት !!!

የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽንን አንዳንድ የኅብረተሰብ ክፍሎች ‹‹ተቋሙ ጥርስ የሌለው አንበሳ ነው›› የሚያተኩረው ትንንሽ አሳዎች ላይ እንጂ ዋናውን የችግሩ ሰንኮፍ መንቀል አቅም የለውም፡፡ ራሱ ተቋሙም ቢሆን ከሙስና የፀዳ አይደለም፡፡ የውስጥ አቅሙ ጠንካራ አይደለም የሚሉት ትችቶችን ሲሰነዘሩበት ቆይተዋል፡፡ አንድ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣንም ግንዱ ላይ ሳይሆን ቅርንጫፍ ላይ እንደሚረባረብ መናገራቸው አይዘነጋም፡፡

ኮሚሽኑ በበኩሉ ከሥነ ዘዴና ሥነ ምግባር ትምህርት አንስቶ በሕዝቡ ውስጥ የፀረ ሙስናና ሥነ ምግባር ትምህርቶችን በስፋት እየሰጠ መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከሶ የማስቀጣት ወይም ጥፋተኛ የማሰኘት አቅሙ (Conviction Rate) ከ92 በመቶ በላይ መድረሱንም ይናገራል፡፡ በእርግጥም አዲስ አበባ ከተማን በመሰሉ ከተሞች በመሬት ወረራ ላይ በቅርቡ ደግሞ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ጋር ተያይዞ የወሰዳቸው ዕርምጃዎች ተቋሙን ሕይወት አሰጥተውታል፡፡ ብዙዎች ‹‹ይኼ ጅምር በየዘርፉ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል›› የሚሉትም ከዚሁ መነሻ ይመስላል፡፡ ተጠናክሮ ካልቀጠለ ግን ከዘመቻና ከፕሮፓጋንዳ ጋር ተያይዞ ገጽታው ይበላሻል፡፡ ቢዘገይም ኮሚሽኑ የሀብት ማሳወቂያና ማስመዝገቢያ አዋጅ ቁጥር 668/2002 ይዞ ብቅ ሲል ብዙዎች በመልካም ጅምር አንስተውታል፡፡ በወቅቱ የኮሚሽኑ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ግርማ ወርቁ እንደገለጹትም የአዋጁ ፀድቆ ሥራ ላይ መዋል ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀረ ሙስና ስምምነትና የአፍሪካ ኅብረት የፀረ ሙስና መዋጊያ የመከላከያ ስምምነት የተቀበለችውን ግዴታ ለመወጣት ያስችላታል፡፡ ሕጉ እነዚህ ጥቅሞች ቢኖሩትም ዋነኛ ዓላማው ግን በአገሪቱ ሙስናን ለመታገል ነው ብለዋል፡፡

‹‹ሕጉ በውጭ አማካሪዎች ተዘጋጅቶ ኢትዮጵያዊ መልክ እንዲኖረው ተደርጓል?›› ሲሉ የገለጹት ኃላፊው የሚመዘገበው ሀብት የቱ ነው? ማን ይመዘግበዋል? የመረጃው ትክክለኛነት እንዴት ይረጋገጥ? ተደራሽነቱ እስከምን ድረስ ነው? መረጃ ለሚጠቁሙ ሰዎች የሚደረግ ጥበቃ፣ ሐሰተኛ መረጃ በሰጡ ሰዎች ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ፣ ወዘተ ሌሎች በቂ አንቀጾችንም ማካተቱን ነበር ያስረዱት፡፡

የተመዘገበው ሀብት የት አለ?
የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቁ ዋነኛ ዓላማ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ነው፡፡ ብዙዎች በተለይ የሕዝብ ሥልጣን ይዘው ከጉያችን የወጡ ባለሥልጣናት ምን እንዳላቸው በግልጽ እንድናውቅ ነው ይላሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ ሀብት ተመዝግቧል ተብሎ ከሚቆለፍ ቢያንስ የዋና ዋና የአገሪቱ መሪዎችና ባለሥልጣናት ሀብት ቢታወቅ ከምንም በላይ መተማመን ይፈጠራል፤ የሚነዛ አሉባልታና ውሸትም ይወገዳል በማለትም ያስረዳሉ፡፡

የፀረ ሙስና ኮሚሽን በበኩሉ እስካሁን ድረስ 50 ሺሕ የሚደርሱ ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራጮችን ሀብት መመዝገቡን ገልጿል፡፡ የአገልግሎት ኃላፊዎችና ከዚያ በላይ የሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች፣ እንዲሁም ሌሎች የመወሰን፣ የመቆጣጠር፣ ፈቃድ የመስጠት፣ ወዘተ ሚና ያላቸው ሀብታቸውን አሳውቀዋል ብሏል፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል የተያዘውን መረጃ በኤሌክትሮኒክስ ኮፒ ደኅንነቱ በተጠበቀ አኳኋን ለመያዝ የወሰደው ጊዜ፣ በሌላ በኩል የምዝገባ ሥራው ባለመጠናቀቁ ይፋ ማድረግ እንዳልተጀመረ በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አስረድቷል፡፡ ይህ ማለት ግን በሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩ ባለሥልጣናትና የመንግሥት አካላትን ለመክሰስ እንደ ማስረጃ አይመዘዝም ማለት እንዳልሆነ ነበር ኮሚሽነሩ ያብራሩት፡፡


በዚህ አባባል የማይስማሙ ወገኖች ግን ቢያንስ ቀስ በቀስ ከላይ ወደታች ይፋ ማድረግ አለበት ይላሉ፡፡ በጉዳዩ ላይ ጥናት ያደረጉት የሕግ ባለሙያዎች የባለሥልጣናትንም ሆነ የዜጎችን ሀብት የማሳወቅ ተግባር ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ያለ ጉዳይ እንደሆነ ያስረግጣሉ፡፡ በዓለም ላይ 150 የሚደርሱ አገሮች የሀብት ማሳወቅና ምዝገባ ሕግን የአጠቃላይ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና እንቅስቃሴ አንዱ አካል በማድረግ ሥራ ላይ አውለዋል ብለዋል፡፡

ከላቲን አሜሪካ አገሮች አርጀንቲና፣ ቦሊቪያ፣ ብራዚል፣ ቺሊ፣ ጃማይካ፣ ሜክሲኮ፣ ኒካራጉዋና ፓራጓይ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎች በሙሉ ሀብታቸውን የማስመዝገብ ብቻ ሳይሆን ለሕዝብ የማሳወቅ ሕግን በተግባር አውለዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በተለይ ሜክሲኮ በየዓመቱ ከ100 ሺሕ በላይ የሚደርሱ የሀብት ማሳወቂያ ምዝገባዎችን በፋይል እንደምትይዝ ተመልክቷል፡፡

በአፍሪካ ያለው የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ሕግን ግን ‹‹በክፍተት የሚጠቀስ›› ሲሉ ይወርፉታል፡፡ ለአብነት ያህል በኬንያና በማላዊ የጥቅም ግጭትን የተመለከቱ ሕጎች ቢወጡም ጥርት ያለ የሀብት ምዝገባ ሕግ ወጣ ሊባል አይችልም፡፡ ይነስም ይብዛም የደቡብ አፍሪካ ሕግ የተሻለ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህን የተከተለ ነው፡፡ ብዙዎቹ ‹‹ለፎርሙላ›› ሀብት ይመዘገባል ቢሉም ለሕዝብ ግልጽ አድርጎ በማስተችት ረገድ የጎላ ክፍተት እንደታዩባቸው ከሌሎች ክፍለ አኅጉራት ጋር አነፃፅረው ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ አዋጅ 668/2002 ትግበራ ‹‹መመዝገብ ግን የማይገለጽ›› (ሚስጥራዊ) ወይም ‹‹Confidential›› እንዳይሆን ብዙዎች ይሰጋሉ፡፡ 

የተመዘገበው ሀብት ትክክል ነው? በምንስ ይረጋገጣል?
ኢትዮጵያውያን በልማዳችን ያለንን ንብረት የማሳወቅ ባህል የለንም፡፡ ብዙው ሰው ‹‹የለኝም›› ማለት ይቀናዋል፡፡ እንኳንስ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ይቅርና ሀብታሙም ቢሆን ገቢውን አይነግርም፡፡ (ለነገሩ ከኖረው የዘልማድ የግመታ የግብር ሥርዓት ጋርም ስለሚያያዝ ይመስላል) ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል እንዳለ መረዳት የሚቻለው ውጤታማ የሆኑ አርሶ አደሮችና የጥቃቅን አነስተኛ አንቀሳቃሾች ሳይቀሩ በሚሊዮን ያካበቱትን ሀብት መግለፅ መጀመራቸው ነው፡፡ ያም ቢሆን በድምሩ ሲታይ አሁንም መሻሻል ይቀረናል፡፡ በዚህ ሁኔታ የተመዘገበው ሀብት ምን ያክህል ትክክል ነው? በምንስ ተረጋገጠ? በሌሎች ስም ‹‹ዘወር›› ሊደረግስ አይችልም? ሲሉ የሚጠይቁ አሉ፡፡

አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በቅርብ የሚያውቋቸው የበታች የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በስማቸው (በቤተሰባቸው) ሁለት ሦስት ቦታ አላቸው፡፡ ተሽከርካሪዎች፣ የግል ድርጅት፣ ወዘተ ያላቸው እንዳሉም ይናገራሉ፡፡ በአዲስ አበባና በዙሪያዋ የኦሮሚያ ከተሞች በበርካታ ቦታዎች ቤት የገነቡትንም እንዲሁ ይላሉ፡፡ እነዚህ አካላት ምን እንዳስመዘገቡ ያለማወቃችን በፀረ ሙስና ትግል ለመሳተፍ አልተመቸንም በማለት ያስረዳሉ፡፡ የኮሚሽኑ የሕግ አገልግሎት ኃላፊ አቶ ግርማ ወርቁ ግን አንዳንድ ሰዎች የመንግሥት ኃላፊዎች ሀብት መመዝገቡ ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ፡፡ ይህ ሥጋት የሚመጣው የሁሉም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሀብት ቢመዘገብ የሕጉ የመከላከያ አቅም ከፍ ይላል ከሚል አስተሳሰብ ነው፡፡ ነገር ግን ዋናው ይህን ሥራ የሚሠራው አካል አቅም ኖሮት ቁርጠኛ ማድረጉ ላይ ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡

ወደፊት መረጃው ተጣርቶ በተገቢው የቴክኖሎጂ አማራጭ ከተያዘ በኋላ ሕዝብ እንዲተቸውም ሆነ በተለያየ መንገድ እንዲረጋገጥም ይደረጋል፡፡ ከአገራችን ቤተሰባዊ ትስስር (Extended Family Relations) ጥብቅ መሆን አንፃር ምዝገባው የራስን፣ የትዳር ጓደኛን፣ ለአቅመ አዳምና ሔዋን ያልደረሱ ልጆችን ሀብት ብቻ መሆኑ በቂ እንዳልሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡

በእርግጥ የዓለም አቀፍ ተሞክሮውም የሁሉም ዜጋ ሀብት ይመዝገብ አይልም፡፡ (ገቢ የማግኘት መብትንም ሊገድብ ይችላልና) ተግባራዊ ይደረግ ቢባልም የሚቻል እንዳልሆነ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በሕዝብ ውክልና የማስተዳደር ሥልጠና የተሰጣቸው አካላት ግን ግዴታ አለባቸው፡፡ ስለዚህ የፀረ ሙስና ኮሚሽን መፍጠን ያለበት የተመዘገቡ ሀብቶችን ሕዝቡ አይቶ እንዲተች የማድረጉ ሥራ ላይ ነው፡፡ ካልሆነ ግን ግልጽነትን ከመገደቡም ባሻገር የመረጃውን ትክክለኛነት አስረግጦ መናገር የሚቻለው አይኖርም፡፡

ሀብት እንኳን ባያስመዘግብ ድንገት ‹‹ዱብ›› ያለ ሀብት ለምን አይጠየቅም?
የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ሕግን በተገበሩ አገሮች የገጠመው አንዱ ችግር ሀብት የማሸሽና በሌላ ሰው ስም የማዞር ድርጊት ነው፡፡ በዚህ ረገድ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ይፋ በሚያደርጋቸው ሪፖርቶች ከብዙዎቹ ታዳጊ አገሮች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ወደ ሌላ አገር ባንኮች ይወጣል፡፡ ለኢንቨስትመንትም ይውላል፡፡ ምንጩ ሙስና ብቻ ነው ባይባልም፣ ከእኛም አገር ባለፉት 10 ዓመታት እስከ 200 ቢሊዮን የኢትዮጵያ ብር ወደ ውጭ እንደወጣ መዘገቡን እናስታውሳለን፡፡ 

በአገር ውስጥም በአንድ ጀንበር ወይም በጥቂት ዓመታት ሀብታም ለመባል የደረሱ፣ ለአቅመ አዳም (ሔዋን) እንኳን ያልደረሱ ወጣቶች ተበራክተዋል ስንል፣ ለዘመናት በድህነት ወይም በዝቅተኛ ገቢ ውስጥ የኖረ ያለአሳማኝ ልፋትና ሥራ ተቀይሮ የሚያድር ሰው መመልከትም የጤነኛ ኢኮኖሚ ማሳያ አይደለም ማለት ነው፡፡ ለዚህም ነው ‹‹ንፋስ አመጣሽ ሀብት›› የሚባለው ገለጻ ከንግግር ባለፈ ተገቢው ማጣራት ይደረግበት የሚባለው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢነትን የማይሸከም ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚያስችል ሕግ ሊኖር የግድ ነው፡፡ እዚህ ላይ የአንድ አገር ተሞክሮን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከኮሙዩኒስት ሥርዓት መፈራረስ በኋላ ሙስና ካስቸገራቸው የምሥራቅና የመካከለኛው አውሮፓ አገሮች አንዷ ስሎቫኪያ ነች፡፡

ሮይተርስ በቅርቡ እንደዘገበው አገሪቱ ያወጣችው አዲስ ሕግ ከ630 ሺሕ ዶላር በላይ ንብረት ያላቸው ሰዎች የንብረቱን ምንጭ እንዲያስረዱ ወይም ማንኛውም ዜጋ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ዓቃቤ ሕግም ግለሰቡ ንብረቱን ከየት እንዳገኘ እንዲያስረዳ የመጠየቅ መብት እንዳለው በሕጉ ተደንግጓል፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች ምንጩ ግልጽ ያልሆነን ሀብት የመውረስ መብት ተሰጥቷቸዋል፡፡ በእርግጥ ይህ አካሄድ መጠኑ ይለያይ እንጂ በብዙዎቹ አገሮች እየተጀመረ ይመስላል፡፡ አምኒስቲ ኢንተርናሽናል በድረ ገጹ እንደገለጸው፣ በአውሮፓ የሚገኙ ሁሉም አገሮች የመንግሥት ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሀብታቸውን የሚያስመዘግቡበትና የሚያሳውቁበት ሥርዓት አላቸው፡፡ ‹‹ድንገት የመጣ ሀብትንም›› መቆጣጠር ጀምረዋል፡፡ ይህ ደግሞ ብዙዎቹ በጋራ ከመሠረቱት ማኅበር (The Group of State Against Corruption of the Council) መጠናከር ጋር እየተያያዘ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ሙስና በሥልጣን (በመንግሥት መዋቅር) ብቻ ሳይሆን ከግሉ ሴክተር (ባንክ፣ አክሲዮን፣ ታክስ፣ ኢንቨስትመንት) ጋር የተሳሰረ ነው፡፡ ስለሆነም በማደግ ላይ ባለው ኢኮኖሚ ውስጥ የሚቀየር የሰው ሕይወት እንደሚኖር እያሰብን፣ የሚበለፅጉ ሰዎች እንደሚበዙ እያመንን፣ ‹‹ድንገት የከበረን›› እንዴትና ምን ሠርቶ ማለት እንደሚገባ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ ሕዝቡ ብቻ ሳይሆን መንግሥት ራሱ ተጠያቂነትና ግልጽነት የተላበሰ የሕግ ማዕቀፍ ቀርጾ መተግበር ይገባዋል ይላሉ፡፡

 ማጠቃለያ
ኢትዮጵያ ለመንግሥት ተሿሚዎችና ሠራተኞች ዝቅተኛ ደመወዝ ከሚከፍሉ አገሮች ቀዳሚዋ ነች፡፡ ከ400 ዶላር በላይ ደመወዝ የሚያገኝ ባለሥልጣን እንደሌለ ልብ ይሏል፡፡ ትንሹም ከ30 ዶላር በወር አይበልጥም፡፡ ይኼ እውነታ ከአገሪቱ ኢኮኖሚ መነቃቃት ጋር እየታየ ሊስተካከል ይገባዋል፡፡ ካልሆነ ግን በሌላ መንገድ መደጎም ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ የመንግሥት የሥራ ሰዓት ሰርቆ ትርፍ ሥራ መጨመር፣ አለፍ ሲልም ለብልሹ አሠራር የሚጋለጠው መበራከቱ አይቀርም፡፡

የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ደመወዝ ዝቅተኛ ነው ቢባልም (በእኛ አገር ደረጃ ሲታይ ደሃ የሚባሉ አይደሉም) ለዚህ ምክንያቱም ገቢ እንዲያገኙ ተብሎ ሳይሆን፣ ለተሰጣቸው ኃላፊነት የሚመጥን ጥቅማ ጥቅም ይመደባል፡፡ የነዳጅና የቤት ወጪ መንግሥት ይደጉማል፡፡ የውጭ ጉዞና የመስክ ሥራ ክፍያም ቀዳዳ ይሸፍናል ይላሉ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች፡፡ ስለሆነም እንደማንኛውም ዜጋ ባለሥልጣናት አንድ መኖርያ ቤት ቢኖራቸውና በመካከለኛው ደረጃ ቢኖሩ ኃጢያት አይደለም፡፡ (አንዳንዱ ፅንፈኛ አሁንም የበላይ አመራሩ በትግል ወቅት እንደነበረው ተጎሳቁሎ እንዲታይ፣ ልብስ ለብሶና አጊጦ እንዳይኖር ሲመኝ ማየት አሳዛኝ ነው) ከልክ አልፎ ሲንበሸበሽ፣ በዙሪያው ያሉ ዘመድ ወዳጆቹን ‹‹ቱጃር›› ሲያደርግ ግን ማነህ? እንዴት ተሳካልህ? ማለት አገር ከመጠበቅና ሕግ ከማስከበር በላይ የዕድገት መሰላሉንም ለሌሎች ለማስተማር ይረዳል፡፡

ከዚህ አንፃር ገፍቶ ያልሄደው የሀብት ማስመዝገብና ማሳወቅ ግዴታ ሊተገበር ይገባል፡፡ ድንገት በልፅጎ መገኘት ጋብ ሊል የሚችለውም ይህ ግልጽነትና ተጠያቂነት እውን መሆን ሲችል ነው፡፡ ካልሆነ ግን በላቡ ሠርቶና ለፍቶ የሚያድረው እያኮሰሰ፣ ሙሰኛውና ግብረ አበሮቹ ግን እያበጡ መሄዳቸው አይቀርም፡፡ ሐሜትና አሉባልታው የሚቆመውም የአዋጁ መጋረጃ ሲገለጥ ነው፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን ሆይ ተናፋቂውን መረጃ አሳውቀን! ቢያንስ ቀስ በቀስ!
ስከ ወረዳ ድረስ ያሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ተመራጮችን ሀብት መመዝገቡን ገልጿል፡፡ የአገልግሎት ኃላፊዎችና ከዚያ በላይ የሆኑ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ሠራተኞች፣ እንዲሁም ሌሎች የመወሰን፣ የመቆጣጠር፣ ፈቃድ የመስጠት፣ ወዘተ ሚና ያላቸው ሀብታቸውን አሳውቀዋል ብሏል፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል የተያዘውን መረጃ በኤሌክትሮኒክስ ኮፒ ደኅንነቱ በተጠበቀ አኳኋን ለመያዝ የወሰደው ጊዜ፣ በሌላ በኩል የምዝገባ ሥራው ባለመጠናቀቁ ይፋ ማድረግ እንዳልተጀመረ በቅርቡ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርት አስረድቷል፡፡ ይህ ማለት ግን በሙስና ወንጀል የሚጠረጠሩ ባለሥልጣናትና የመንግሥት አካላትን ለመክሰስ እንደ ማስረጃ አይመዘዝም ማለት እንዳልሆነ ነበር ኮሚሽነሩ ያብራሩት፡፡
በ16/06/05  based on Reporter & anti-corruption report