ድህነት ያናወጠው እውቀት በፈተና እና እውቀት አልባ መንግስታዊ አስተዳደር

ባልተማረ አስተዳደራዊ አጣብቂኝ ውስጥ የገባው የወያኔ ጁንታ የፈጠረው የትምህርት ፖሊሲ እና አስተዳደራዊ ሂደቶች ተማሪዎችን በጭንቀት ውስጥ ከመክተቱም በላይ ተስፋ የቆረጡ ትውልዶች እና የሚሰደዱ ወጣቶችን በኮብልስቶን ፖለቲካዊ ማሽን እያመረቱ መገስገስ አያዋጣም...እሱም ቆሟል እየተባለ ነው::ለተማሪዎች የሚሰጡት ፈተናዎች በሙያው ባልሰለጠኑ ሰዎች የሚዘጋጁ እና ከተማሪው የትምህርት መጠን ጋር የማይጓዙ የፈተና አቅርቦቶች ተማሪውን ከአገልግሎት ዉጪ  እያደረጉ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ::

ሀገርን እንመራለን እናስተዳድራለን የሚሉን ባለስልጣናት የ10ኛን ክፍል ብሄራዊ ፈተና አያልፉትም፡፡ በአለማችን ላይ ያሉት አንጋፋ ምሁራንም ቢሆኑ አያልፉትም፡፡ ምክንያቱም በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚሰጠው ፈተና አጋጣሚን እንጅ እውቀትን አይመዝንም፡፡

የተማሪው ቤተሰብ ጥንካሬ፤ የትምህርት ቤቱና የመምህራኑ ጥራት፤ የቤተሰቡ ገቢ፤ የወላጆቹ የትምህርት ደረጃ፤ በትምህርት ዙሪያ ያላቸው አቋም፤ የሚማርበት አገር የመሳሰሉትን በአጋጣሚ እንጂ በግል ጥረት አይገኙም፡፡ ፈተና ከእውቀት ይልቅ እነዚህን አጋጣሚዎች የበለጠ ይመዝናል፡፡

ከአሰቃቂ ወንጀሎች መካከል አንዱ በሴቶች ላይ የሚፈፀመው ነው፡፡ ወንድ ከሆነ ይወለድ ሴት ከሆነች ትውረድ ይባላል፡፡ ሴት ልጅ ግን የተመረጠች የተወደደች የታመነች መቅደስ ናት፡፡ ሴት ልጅ ሰውን በማህጽንዋ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን ተሸክማ ወደ ምድር ታመጣለች፡፡ በማህጸንዋ ውስጥ ወንዶች የጣሉትን ዘር ተቀብላ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ያለውን ህመም ታግሳ ለዐይን የሚያሳሳ ልጅ ትሰጣለች፡፡ ይህ ውለታዋ ሳይታይላት ዛሬም ተንቃ ተገፍታ ተረግጣ ትኖራለች፡፡

ሌላው አሰቃቂው ወንጅል በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ፈተና ነው፡፡ ይህ ሕቡዕ ወንጀል እያደረሰ ያለውን አደጋና ችግር የሰው ልጅ ገና አልተረዳውም፡፡ የሰው ልጅ እድገት በእናት ማህጸን ዉስጥ አይጠናቀቅም፡፡ በተለይ ከትምህርት ጋራ ቀጥታ ግንኙነት ያለው አንጎል እድገቱን እስከ 25 አመት ይቀጥላል፡፡ የፈተና ስርአት ግን ይህን ተጨባጭ እውነታ በመጣስ በእድገት ላይ ያለን ለጋ አንጎል በድብቅ በሚዘጋጅ የተወሳሰበ ፈተና ይቀጣል፡፡

በአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያሉ ተማሪዎች ፈተና በህይወታቸው ላይ የሚያመጣውን ተፅእኖ ለመገንዘብ አይችሉም፡፡ ምክንያቱም የነገውን ለማየት የሚረዳቸው የአንጎላቸው ክፍል ገና በእድገት ላይ ነው፡፡
ተማሪዎች ትምህርት ቤት ከተከፈተ ዕለት ጀምሮ የተማሩትን በመመልከት ለፈተና በመዘጋጀት አይቆዩም፡፡ ፈተና ሲቃረብ ግን መጽሐፍቶቻቸውንና ደብተሮቻቸውን መመልከት ይጀምራሉ፡፡ ሌሊቱን ሙሉ ለማጥናት ሲፋጠኑ ይታያሉ፡፡ ይህ የሚከሰተው የነገውን ለማስላትና ለማየት የሚያስችላቸው የአንጎል ክፍል እድገቱን ባለማጠናቀቁ ነው፡፡

በትምህርት ክፍለ ጊዜ አጋማሸና ማብቂያ ላይ ፈተና ይሰጣል፡፡ በተለይ የ10ኛና የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና እልህ አስጨራሽ ነው፡፡ ተማሪዎች ግን ለሚሰጡት ፈተናዎች ጠንካራ ዝግጅት ማድረግ እንዳለባቸው ሊረዱ አይችሉም፡፡ ተግተው ለፈተና በመዘጋጀት የሚያገኙት እውቀት በህይወታቸው ዘመን ሁሉ አጋር መሆኑን አያውቁትም፡፡

በዚህ ምክንያት ወላጆች ከልጆቻቸው ጋራ ብዙ እሰጣ አገባ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አጥኑ! ተማሩ! ይላሉ፡፡ ልጆችም ጥቅሙ ስለማይታያቸው ወላጆቻቸውን ማዳመጥ ያዳግታቸዋል፡፡ ተምረው ፈተና ላይ ጥሩ ውጤት በማስመዝገብ ስኬታማ ኑሮ መኖር እንደሚችሉ አያስቡትም፡፡ ይልቁንስ እለታዊ እርካታን በሚሰጡዋቸው ጨዋታዎች ላይ ማተኮርን ይመርጣሉ፡፡ ከመማር ዘግይቶ የሚገኝውን ጥቅምና እርካታ ግን አያውቁትም፡፡

የትምህርት ስርዐቱ የተዋቀረው ተማሪዎች በየደረጃው የተቀመጠውን እውቀት መቅሰማቸውን በፈተና እያስመሰከሩ ከደረጃ ወደ ደረጃ እንዲዘዋወሩ ነው፡፡ በአንደኛና በሁለተኛ ደረጃ ያሉ ተማሪዎች ግን ይህንን ስርዐት ለመረዳት እድሜአቸው አይፈቅድም::

ከእድሜአቸው አኳያ ሲታይ አይፈረድባቸውም፡፡ የማያውቁት ሃገር አይናፍቅም! ዛሬ ላይ ሆነው ነገን ማየት የሚያስችላቸው የአንጎል ክፍል ስላልዳበረ ጥቅሙን ሊረዱት አይችሉም፡፡ ስለዚህ በትምህርቱ ላይ አይተጉም፡፡
ተማሪዎች ምንም እንኩዋን ለፈተና ተግቶ በመዘጋጀት የሚገኘውን ጥቅም ሊያውቁት ባይችሉም ባለው ስርዐት ተጠቅመው ስኬት ለማምጣት አድርጉ የተባሉትን በጭፍን ማድረግ መቻል አለባቸው፡፡ ባጭሩ ተማሪዎች የማሰብ ሃላፊነታቸውን ለሌላ ወገን አሳልፎ መስጠት ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተዘዋዋሪ ፈተና ከማሰብ ሀላፊነታችን ጋር በረቀቀ መንገድ ያላቅቀናል፡፡ አንድ ሰው “አድርግ” የተባለውን ነገር ለማድረግ አእምሮው የሚጠይቀው ነገር አለ፡፡ አንድ ተማሪ በፈተና ጥሩ ውጤት ማምጣት ከፈለገ ግን በራሱ ማሰብ ትቶ በጭፍን ሰው ባሰበለት መንገድ መሄድ አለበት፡፡ ለፈተና አጥና ሲባል ማጥናቱ ምን አይነት ጥቅም እንዳለው አንጎሉ ማስላት ባይችልም እሺ በጄ ብሎ ማጥናት አለበት፡፡

ስለዚህ ፈተና የማሰብ ሐላፊነታቸውን በቀላሉ የሚሰጡ ሰዎችን ይመለምላል፡፡ እነዚህ ምልምሎችም አብዛኛውን የትምህርት እድሜያቸውን በሚያሳልፉበት ዘመን የመማር ጥቅሙን የራሳቸው አንጎል ማየት ስለማይችል ሌሎች ባሉዋቸው መንገድ ተመርተው ስኬታማ ሲሆኑ በኋለኛው እድሜያቸውም ከራሳቸው አስተሳሰብ ይልቅ በሌሎች ሰዎች አስተሳሰብ በጭፍን መመራትን ሳይወዱ እንዲመርጡ ያስገድዳቸዋል፡፡

በዚህ ምክንያት ዛሬ በአለማችን ላይ የተንሰራፋው የትምህርት ስርዐት በራስ ጭንቅላት ከመመራት ይልቅ በሌሎች ጭንቅላት መመራትን ያስገድዳል፡፡ የትምህርት ስርዐቱ የሌሎች ምርኮኛ ያደርጋል፡፡ ለብዙ አመታት በፈተና የተወገረ ምርኮኛ አንጎል ሰፋ አድርጎ ማሰብ ያቅተዋል፡፡ ሁል ግዜ የበላዮቼ ናቸው ብሎ ወደሚያስባቸው ስሜቱንና አይኖቹን ያቃናል፡፡ በራሱ ማሰብ እንዳይችል በልቦናው ላይ የአድማስ ድንጋይ ተቀምጦአል፡፡ እውቀት የሚስፋፋበት መስመር በፈተና ጠቦና መንምኖ ህዝብ እንዴት ይለወጣል?

ከዕለታት በአንድ ቀን አንዲት የገጠር ከተማ በኡኡታና እሪታ ተዋጠች፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሠላሳ አንድ አመታት በኃላ ያገኘው እድል የጨለመበት ዕለት ነበር፡፡ ታላቅ ሀዘን በህዝቡ ዘንድ ታየ፡፡ የዚያን አይነት ኡኡታና እሪታ ግን መታየት ያለበት ልጆች ከትምህርት ቤት በተለቀቁ ቁጥር ነበር፡፡ምክንያቱም በየዕለቱ ተማሪዎች በዓለም ዙሪያ ካሉ ተማሪዎች ጋር ይወዳደራሉ፡፡ ተገቢውን እውቀት ባላገኙ ቁጥር ብሄራዊ ሽንፈት ነው፡፡ ዞሮ ዞሮ ሀላፊነት ቦታ ላይ ተቀምጠው ያላቸውን እውቀት ተግባራዊ በሚያደርጉበት ግዜ የሚወዳደሩትና የሚደራደሩት ከአለም ዙሪያ ካሉ ምሁራን ጋር ነው፡፡

በውሃ ውስጥ እየጮኩኝ ነው! የሚያዳምጥ የለም! ምክንያቱም ይህንን ነገር አተኩረው መመልከት የሚገባቸው ሰዎች ራሳቸው የችግሩ ሰለባ ናቸው፡፡ አንጎላቸው ለአመታት በፈተና ተቀጥቅጦ ተደፍኗል፡፡ በተጨማሪም ያለንበት ደረጃ ላይ የደረስነው ያለን ከፍተኛ ብቃት በፈተና ተመዝኖ ነው ብለው ስለሚያምኑና የማሰብ ሃላፊነታቸውን አሳልፈው እውቀት መግበውናል ለሚሉዋቸው ህዝቦች ስለሰጡ ዙሪያው ገደል ነው፡፡

ከእደዚህ አይነት አጣብቂኝ ውስጥ ለመላቀቅ ጽኑ የሆነ ትግል ያስፈልጋል፡፡ ፈተና ከአለም የወረስነው ባህል ነው፡፡ ካለ ፈተና ምን ይውጠናል? ጌቶች ቅር ይላቸዋል ሳንል የማሰብ ሀላፊነታችንን ለማስመለስ እንጣር፡፡ ለምንድን ነው ተማሪዎች ፈተና በደረሰ ቁጥር መጽሀፍት ቤቶችን የሚሞሉት? ብለን ከአንጎል እድገት ጋራ ያለውን ግኑኝነት እንመርምር፡፡ አይዞን! አንፍራ! በተለይ ልጆች ወላጆቻችሁ በሃላፊነት ቦታ ላይ ካሉ አጥብቃችሁ ጠይቁዋቸው፡፡

ተምሮ ተምሮ ቁሳዊ ሀብት መሰብሰብና ትልቅ ህንጻ ረጅም ግንብ ላይ አደገኛ አጥር አጥሮ ዉሻ አሳድጎ ዘበኛ ቀጥሮ ሀብትን ማስጠበቅ ወይም ቆንጆና ውድ የተባለ መኪና መንዳት ነው አላማው? ግን እኮ አንዳንዴም ማሰብ ውስጣዊ እርካታንና ሰላም ይሰጣል፡፡ጋዜጠኞችም እስቲ አለምን እየመራን ነው ብዙ እውቀት አለን የሚሉትን ባለስልጣናት የ10ኛን ክፍል መልቀቂያ ፈተና
 ስጡዋቸውና ያልፉት
እንደሆነ ታዘቡ፡፡ ጸኑ ሸክም አስረው ተማሪን ተሸከም ለምን ይሉታል?


መራዊ ጎሹ ምንሊክ ሳልሳዊ