ቻይናዊያን ኢትዮጵያን ሊያለሟት ወይንስ ቅኝ ሊገዟት…?

ቻይናውያን ለስራ የተንቀሳቀሱባቸውና ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ ገንብተው የሰፈሩባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ሰላምና መረጋጋት የላቸውም፡፡ በተለይም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ደግሞ ድሃው ገበሬ ነው፡፡

ከራሳቸው ከዜጎቿ አንደበት ወጥቶ አንደተረጋገጠው ኮምዩኒስቷ ቻይና በዋነኝነት ለኮንስትራክሽን ስራ ወደ አፍሪካ አገሮች በተለይም ወደ ኢትዮጵያ የምትልካቸው ወጣቶች ከአስራ አምስት ዓመት እስከ እድሜ ይፍታሽ እስር የተፈረደባቸው ከባድ ጥፋት የፈፀሙ ወንጀለኞችና ወሮበሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ድሃዋ አገራችን ኢትዮጵያ ለሀብታሟ ቻይና በእስር ቤትነት እያገለገለች ነው ማለት ነው፡፡

 
 ጣሊያን ቅኝ ሊገዛን በመጣበት ዘመን ለፍርፋሪ ያደሩ የንጉሱ ሹማምንት የሆኑ መኳንት፣ የኃይማኖት፣ የዘመናዊ ትምህርትና የስነ-ጽሁፍ ልሂቃን የፋሽስት ጉዳይ አስፈፃሚና ተላላኪ በመሆን በገዛ አገራቸውና ድሃ ወገናቸው ላይ መቸም ቢሆን ታሪክ የማይረሳው ክህደት ፈፅመዋል፡፡ ከጻኅፍት አፈወርቅ ገ/ኢየሱስንና ብርሃኑ ድንቄን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዛሬም በዚህ ዘመን በተመሳሳይ ሁኔታ የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ከቻይናዊያን ጋር በመመሳጠር የአገራቸውን ብሄራዊ ማንነትና ጥቅም አሳልፈው በገንዘብ በመሸጥና የጎስቋላ ወገናቸውን ሰብአዊ መብት በማስረገጥ ባቋራጭ እየበለጸጉ ይገኛሉ፡፡

ከጎንደር ባህር ዳር ያለው ጎዳና የአስፋልት ግንባታ ሲሰራ በጎንደር ማክሰኝት ከተማ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ከአካባቢው ህብረተሰብ ሲነፃፀር ያማረና የዘነጠ መኖሪያ ቤት ከመስራት አልፈው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በባንክ እስከማከማቸት ደርሰው ነበር፡፡ አንዳንዶቹማ ጭራሽ ሃፍረታቸውን ሽጠው በልተው በአየር ባየር የሲሚንቶ፣ የብረታብረት፣ የድንጋይ፣ የአሸዋና የነዳጅ ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ በዚያ ዓይን ያወጣ ስርቆትና ዝርፊያ ጥልፍልፎሽ መረብ ውስጥ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦችም ለጥቅም ሲሉ አርስበርሳቸው በጥይት ተገዳድለዋል፤ በጩቤ ተራርደዋል፡፡ በተጨማሪም የማክሰኝትና አካባቢዋ ህብረተሰብ የዕለት ከዕለት ኑሮ መንገዱ ተገንብቶ እስኪያልቅ ድረስ መረጋጋት ያልሰፈነበትና ስጋት የተጋረጠበት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በጎጃም መርጦ ለማርያም አከባቢ የሚገኙ የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ደግሞ ከቻይናዊያን መሃንዲሶች ጋር በስውር በመዋዋል የጥራት ደረጃው በእጅጉ የወረደ የአስፋልት መንገድ አንዲገነባ ሲያደርጉ ስራው በሚመለከተው ኢትዮጵያዊ መሃንዲስ ተደርሶባቸው ኢትዮጵያዊዩ መሃንዲስ ሴራውን በማጋለጥ አስፋልቱን ለማስፈረስ ሞክሮ በካድሬዎቹ ዛቻና ማስፈራሪያ አገሩን ኢትዮጵያን ጥሎ ለመሰደድ በቅቷል፡፡

አሁንም በዚያው በጎጃም አዴት ዙሪያ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ቻይናዊያን እሳት በውስጡ በቋጠረ የኤሌክትሪክ ሽቦ አንገቷን አንቀው በማንጠልጠል አንዲትን ሴት ህይወቷን በመቅጠፋቸው የአካባቢ ገበሬ ለተቃውሞ ሲወጣ በካራቴ እየዘረሩ ጨርሰውታል፡፡

ባጠቃላይ ቻይናዊያን ለግንባታ ስራ ተሰማርተው ወንጀል ያልፈፀሙባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሉም፡፡ አሁንም በነቀምቴ ባኮ መንገድ ስራ ሳይት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የዚሁ እጣ ነው እየደረሰባቸው የሚገኙት፡፡ የአሰላና አካባቢዋ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መቼም ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አንድ ቻይናዊ የገልባጭ መኪና ሾፌር የጫናቸውን ኢትዮጵያዊ የቀን ሰራተኞች ልክ አንደማይጠቅም ቆሻሻ መንገድ ዳር ላይ ገልብጦ እንደደፋቸውም ተሰምቷል፡፡ ቻይናዊያን በኢትዮጵያዊያን ላይ ግፍ የሚፈፅሙት በጥቅማጥቅም ያሰሯቸውን “የመንግስት” ካድሬዎች መከታና ከለላ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም አይነት ወንጀል በህብረተሰቡ ላይ ፈፅመው ይከሰሱ ወንወጀላቸው ተድበስብሶ ይቀራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ጥቃቱን በራሱ መንገድ እንዳይከላከል በጥቅም ምክንያት ከቻይናዊያን ጋር ባበሩ ፌደራል ፖሊሶችና የአካባቢው ታጣቂ ሚሊሻዎች የሚደርስበትን አፀፋ ይፈራል፡፡ 
ደግነቱ ዘውዱ ታድያ ይህ ሁሉ ልማት ወይንስ ቅኝ ግዛት…?