የኢህአዴግ በደሴ ከተማ ቁማር መዘዝ ድብቅ አጀንዳ

ቅርስነታቸውን አጥተው የተገደሉት ሸህ ኑሩ እና የኢህአዴግ አመልካች ጣት!

ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይ(ምንሊክ ሳልሳዊ ብሎግ)
የኢቲቪ መስኮት የዘወትር ደንበኛ ሆነው አንድ ሰሞን ክፋኛ ጥላቻን ያተረፉትና እራሳቸውን የቀጥተኛዋ መንገድ ናሙና አድርገው ሲስሉልን የነበሩት ግለሰብ ትላንት ሰኔ 27 ምሽት ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን መስማታችን ያሳዝናል፡፡ የዚህች ቁማር መዘዝም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ግለሰቡ በኢቲቪ መስኮት ብቅ እያሉ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ሲያውኩ እና ፊትና ላይ ሲጥሉ የነበሩ ሲሆን በተለይ በደሴ ከተማ ውስጥ አሳዛኝ ተግባሮችን ሲፈፅሙ እንደነበር ዘወትር የፌስቡክ ገፆች የዘገቡት ሐቅ ነው፡፡ በእርግጥ ግለሰቡ ይህች የኢህአዴግ-አህባሽ አመጣሽ ንፋስ ከመንፈሷም በፊት እጅጉን አስቸጋሪና ዑለማዕ የማይወዱ እንደነበሩ አንድ ታላቅ አዛውንት አውግተውኛል፡፡ እኔም “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጭቆና በፀረ-ሽብርተኝነት ሽፋን” በተሰኘው መፅሀፌ ውሥጥም አካትቻቸው ነበር፡፡ግለሰቡ በዚህች ሁለት ዓመታት ውሥጥ ንፋሱ አድልቧቸው፣ያሻቸውን ተናግረው፣ያሻቸውን አስደብድበው፣ያሻቸውን አድርገው ፍፃሜያቸው ይህ ሆኗል፡፡
እራሴን ወገቤን ብሎ ሣይናገር
እንዲህ ሆኖ ቀረ የወሎማ ነገር!
እንደተባለው ለወሎ የጭቃ ውስጥ እሾህ ሆነው ገርፈው ለገራፊ ዳርገውታል! ቅሉ ከእርሳቸው ጀርባ መዶሻ እንዳለ ቢገባንም የእርሳቸው ሚስማርነት ግን የደሴዎችን ልብ ያደማ ነበር፡፡ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ በግለሰቡ እውቅናና ትዕዛዝ በርካቶች ተደብድበዋል፣በርካቶች አልቀሰዋል፣ከሚወዷቸው የአላህ ቤቶችም እንዳይደርሱ ተገድደዋል!
ከአማራ ክልል ግዛቶች ውሥጥ ወሎ ላይ የበረታው ግርፊያ መነሻው ሸህ ኑሩ ብቻ ናቸው ብለን ባናምንም እጃቸው እንደነበረበት ግን የወሎየዎቹ እምባና የዘወትር ስሞታ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡የሐይማኖ አባቶች ታስረዋል፣ተዋክበዋል፣መስጅዶች ተነጥቀዋል፣ ምዕምናኑ በመስጅድ ውሥጥ ሳሉ በፓሊስ ይደበደቡ ዘንድ ሟች ባደረጉት ግብዣ መሳጅዶች በፓሊስ ቤት ጫማ ተደፍረዋል! ኢስላምን የማጥፋት ዘመቻው በተለይ በወሎ ጠርዙን የረገጠበት ምክንያት ነገ በታሪክ የሚመመርና ከሰቆቃው ጀርባ ያሉ አካላትም በህግ መጠየቃቸው የማይቀር ነው፣ በታሪክም መወቀሳቸው አይቀሬ ነው፡፡የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ሟችን መውቀስ ባለመሆኑ ወደ ነጥቤ ልለፍ፡፡
የትላንትናው የኢቲቪ ዜና ጠርጥር መጠርጠር አይከፋም ብሎኛል! ግለሰቡን እንደ ሀገራዊ አርበኛና ባለውለታ አድርጎ ማቅረብ አልመሰለኝም የኢቲቪ አለቆች አካሔድ ይልቁንስ ያች ሁለት አመት ስንጨቀጭቃችሁ የነበረው የአክራሪዎች ሽብር በተግባር እየተረጋገጠ ነው የሚል አንድምታን ማስተላለፍ ነው የተፈለገው! የሞቱን ዜና መዘገብ ያስፈለገበት ዋናው ድብቅ አጀንዳ ይህ ነው! ሞታቸውን ለሰማን ሁሉ ካዘንበትም ምክንያቶች አንዱና ዋናው ይህ መሆኑ አልቀረም! የኢህአዴግ አመራሮች በተንኮልና በድራማ አቻ የሚገኝላቸው አይደሉም! ይህች ግድያ ለኢህአዴግ የተመቻቸች ኳስ ናት!
የነዚያ ታሳሪ ፋኖዎች ልፋትና ትጋት ይህ እንዳይሆን ነበር፡፡ መስጅዶቻችን የ እውቀት፣የኢባዳ፣የሙስሊሙ ማህበረሰብ ችግሮች ማቀለያና የሹራ ቦታወች እንዲሆኑ እንጅ የደም አበላ የሚያጥባቸው፣የሙስሊሙ የግፍ እንባ የሚጎርፍባቸው እንዳይሆኑ ነበር፡፡ዛሬ ግን ይሔው መስጅድ አካባቢ ሰው ይገደላል፡፡በግድያው ላይ የህዝበ ሙስሊሙ እጅ እንዳለበት ለማሳበቅና ለመቀሰር በማለምም ኢቲቪ ይህን የመርዶ ዜና ባወጀበት ወቅት ያስተጋባው ሲሆን አዲሱ መጅሊስም ግለሰቡ በአክራሪዎች ነው የተገደሉትና ህብረተሰቡ ይህን ሊሸከም አይገባም የሚል አንድምታ ያለው መግለጫ ሰጥቷል፡፡ጥያቄው እዚህ ላይ ነው! በእርግጥ ህዝበ-ሙስሊሙ የ70 ዓመት አዛውንትን በመግደል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል ብሎ ያምናል ወይ? ብለን ስንጠይቅ በፍፁም! የሚል መለስ እናገኛለን! ለምን ካሉ እኔ እንዲህ እላለሁ፡
1. የኢህአዴግ መንግስት ህዝበ ሙስሊሙን በአሸባሪነትና በአክራሪነት እየፈረጀና እየከሰሰ አልፎም የከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ዶክመንተሪዎችን በመድረስ ኢትዮጵያ በአክራሪ ኃይሎች ተፅዕኖና ስጋት ውሥጥ ናት የሚል ክስ ያቀርባል፡፡ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ እኛ አሸባሪ አክራሪ አይደለንም! በሐገራችንም ላይ የኢኮኖሚ፣የዘር፣የፓለቲካ አክራሪነት እንጅ የሐይማኖት አክራሪነት መገለጫዎች የሉም! ፓለቲካ ወለድ የሽብር ተግባር እንጅ ሐይማኖት ወለድ የሽብር ሁከትም የለብንም! ብሎ ከመሞገት አልፎ ሠላማዊ መሆኑን ለማሳየትና ለማስረዳት ጠጠር ያልተወረወረበት፣አቧራ ያልተበተነበት ረጅም የሠላማዊ ትግል ስረዓትን ለኢትዮጵያችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያኑም ጭምር አስተዋውቀዋል፡፡ የዚህ እልህ አስጨራሽ ረጅም ሠላማዊ ትግል አካሔድ አላማ በመንግስት የሚነሱ ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን በተግባር በማሳየት የኢህአዴግን ክስ እርቃን ማስቀረት ነው፡፡ለዚህም ሲባል ኮሚቴዎቹን እንደ በግ አሳልፎ ከመስጠትም ባሻገር በርካታ ወንድሞቹን በተቀነባበር የኢህአዴግ መራሹ ኦፕሬሽን በሞት ሲያጣ እልሁን ውጦ፣ሀዘኑን በሆዱ አፍኖ ከማንባትና ስሞታ ከማሰማት ውጪ አንዳችም ግብረ-መልስ ለመስጠት የሞከረበት ጊዜ የለም፡፡ታዲያ ይህን ከፍተኛ መሰዋዕትነት የሚጠይቅ ሠላማዊ ትግልን እያደረገ ባለበት ሁኔታ እንዴትስ ከዚህ ግብ በተቃራኒ የሚውል ተግባርን ሊፈፅም ይችላል? በፍፁም! ከላይ በጠቀስኩት ዓላማ ላይ የረገጠ ህዝብ ይህን ተግባር ይፈፅማል ማለት አሳማኝ አይሆንም!
2. የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴዎችን መገበርን፣የህዝበ ሙስሊሙን መገፋትና የበርካታ ሙስሊም ዜጎችን ህይዎትና ንብረት ዋጋ ያስከፈለው ትግል ዋና ዓላማ ከዚህ የግድያ ተግባር ግብ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የዚህ ትውልድ ጥያቄ ሙስሊሞችን አንድ የሚያደርግ፣አንዱ በሌላው ላይ እጁን የማይቀስርበት፣መንደር ወለድ ስያሜዎችና ታፔላዎችን መሰረት ያላደረገ እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኖ ለሁሉም ቡድንና ጀመዓ ተጠሪ ሊሆን የሚችል፡፡ መወቃቀስን ሳይሆን መመካከርን፣ጣት መቀሳሰርና መነቋቆርን ሳይሆን መቻቻልና መተሳሰብን፣ አሳልፎ መሰጣጠትና አንዱ የአንዱ እንቅፋት መሆን ሳይሆን መዋዋጥና መተናነስን፣በልዩነት ውሥጥ አንድነትን፣በኢስላማዊ ጥላ ስር ሊያቅፍ የሚችል የእኔና የእንትና ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተጠሪ ሊሆን የሚችል መጅሊሳዊ ተቋም ያስፈልገናል፡፡ለዚህም ደግሞ አሁን ያሉት አረሞች ተወግደው ለዚህ ታላቅ ግብ ብቁና ትጉህ የሆኑ አመራሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንምረጥ የሚል ነበር! ነውም! ይህን ሁሉ ዋጋ የጠየቀው ግብ! ታዲያ ይህን ትልቅ አጀንዳ (Big Picture) ይዞ የወጣ ህዝብን አንድ ግለሰብን ለዚያውም እዚህ ግባ የማይባል ትርጉም ያለውን ሠው በመግደል ሊጠረጠር ከቶ ይቻላል!
3. በእርግጥ ግለሰቡን በመግደል የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ትግል ምዕራፍና ጉዞ ትቂትም ቢሆን ማንፏቀቅ ይቻላልን? በፍፁም ይህ ግለሰብ ሽፈራው ተ/ማርያም፣በረከት ሰምዖን፣ኤልያስ ሬድማን፣የህውኃት ቱባ አመራር ወይም የኢህአዴግ ቁልፍ ሰው አይደለም! በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦችን እንኳን በመግደል ቂምን መወጣት ይቻል፣እልህን ማስተንፈስ ይቻል እንደሆነ እንጅ ሕዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሳውን ግብ መምታት ፈፅሞ አይቻልም! ምክንያቱም ህዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሳውን የመብት ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ሥርዓትን ባማስተካከልና በማጽዳት እንጅ ግለሰቦችን በማስወገድ ፈፅሞ ሊሣካ አይችልም! ይህ ትውልድ ደግሞ ይህን በቅጡ የተገነዘበ መሆኑን ከዚህ ረጅም ሠላማዊ ትግል ውጭ ሁነኛ ማስረጃ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ ሽፈራው ተክለማርያም ዳግማዊ ካሣ ምርጫን (አፄ ዩሐንስ 4ኛ) እንዲሆን ባልተፈቀደለት ነበር፡፡ እናም አንድን የ70 ዓመት ሽማግሌ ለዚያውም ከመንደራዊ አንበሳነት ውጭ እንደ ሐገር የጩጯን ያክል የማይመዝን ግለሰብን በማስወገድ ሐገራዊ ግብን መምታት ይቻላል ብሎ የሚታመን አይመስለኝም! ስለዚህም የኢቲቪና የመጅሊስ ጣት ቅሰራ ጉንጭ ከማልፋት ውጭ የወረወርኩት አንካሴ ተመልሶ ለራሴ መዘዝ ያለው ይመስላል!
እናም ሳጠቃልል ህዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሣውን ዓላማና ፅናት የረገጠ ማንኛውም ሙስሊም ይህን ተግባር ሊፈፅም ይችላል ብሎ ማሰቡ ብዙ የሚዋጥና አሳማኝ አይመስልም! ይልቁንም ከህዝበ ሙስሊሙ ዓላማ ውጭ የተሰለፉ አካላት ለዚህ ወንጀል ቅርብ ናቸው፡፡ እንዴት ካሉኝ
1. መንግስት እጅጉን ደክሞ በበርካታ ዲራማዊ ዶክመንተሪ ፊልሞች ለማሳመን ያልቻለበትን ጉዳይ አጠናክሮና በማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ፣ ይበልጥ ያስረዳልኛል ያለውን መረጃ ከማፈላለግና ከመፍጠር ወደ ኋላ አይልም እናም አንዲም ለፕሮፓጋንዳ ግብዓት ሁለትም እንደ ማስረጃ ለመምዘዝ በዚህ ቁማር ሊገባ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡
2. ግለሰቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዞኑ የመንግስት አመራራትና ከደህንነቶች ጋር በነበራቸው ግጭት ተገልብጠው ከህዝበ ሙስሊሙ ጎን ከተሰለፉ ኢህአዴግ ሊደርስበት የሚችለውን የፓለቲካ እና የአካሄድ ኪሳራ ለመከላከል ከወዲሁ የቤት ሥራውን ሊሰራ ይችላል! ምክንያቱም ግለሰቡ ሁነኛ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያው ነበሩና!
3. ኢህአዴግ በተለይም ወያኔዎችና የአመለካከት ልጆቻቸው ድርሳናቸው ሲገለጥ በዚህ ዓይነቱ የገድሎ ገዳይ ፍለጋ ቁማር እጅጉን የገዘፈ ታሪክ አላቸው፣የሙሴን፣የኃየሎምን፣የኢሀአፓ ወታቶችን፣የሀውዜን፣በኦነግ ፋይል የተካተቱ ሽብሮችን መመልከቱ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡
4. እራሳቸውን የዚህች አገር ልዩ ዋስትና አድርገው ከኢህአዴግ ደርብ ጋር ተጣብተው በኢህአዴግ ከለላ ስር እንደ አሜባ ሊራቡ የሚፈልጉት አህባሾችና ጀሌዎቻቸው ጠላቶቻችን ባሏቸውና በኢህአዴግ ክንድ ሊደቁሱት የሚፈልጉትን ህዝብ ላይ ነውር ለመፈለግ እና እራሳቸውን ከዚህ አይነቱ ተግባር የፀዱ የዋሆች አድርገው ለመሣል በዚህች ድራማ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡
እንግዲህ ጊዜ ጥሩ ነው፤መቆየት ደግ ነው ብዙ ያሳያል! በዚህ ግድያ ሁላችንም አዝነናል! ያዘነው አንድም ሙስሊም የማይበደልበትን ሥርዓት ለመፍጠር በሚደረገው ሠላማዊ ትግል ውሥጥ ዓላማውን መረዳት ያቃታቸው፣ትልቁን ግብ (Big Picture) መመልከት ተስኗቸው ወይም መረዳት ያልፈለጉ በጎች ከጅብ መንጋጋ በመግባታቸው ነው፡፡ ስለ ኢስላም እየተጨነቅን ስለታፔላ እንቅልፍ የሚያጡትን፣ስለ ሰብአዊነት እና ስለ ኢትዮጵያች እየለፈፍን ስለ ጎጥ የሚቆዝሙት ከሁለት የወጡ ጎመኖች ስለመሆናቸው ነው የምናዝነው፡፡አላህ የዚህ ዓይነቱን ውድቀት ከማይሰሙ ያድርገን፡፡ሟች አባታችንንም አላህ በእዝነቱ ይመለከታቸው ዘንድ ዱዓችን ነው! ይህ ጊዜ አልፎ ትልቁን ግብ ማሳየት ብንችልና ይቅር ተባብለን አባታችን እያልናቸው ልጆቼ እያሉን በቅርስነታቸው ቢሞቱ ኖሮ ምን ያክል ክብራችን በሆነ ነበር! ግን አልሆነም አላህ የወደደውንና የፈቀደውን አድርጓል!