Where you from? ‹‹ከየት ነህ?››


(ምኒሊክ ጥቁር ሰው)  

ምኒልክ  ሳልሳዊ ብሎግ  

አሜሪካን ሀገር በተለያየ አጋጣሚ የምተዋወቃቸው አብዛኞቹ ነጮች የሚጠይቁኝ ጥያቄ “Where you from?” የሚል ነው፡፡ ታዲያ አሁን እንደበፊቱ ደረቴን ነፍቼ ኢትዮጵያዊ ነኝ ለማለትና ማንነቴን ለመግለፅ አንገቴን የሚያስደፉኝ በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታዋን ሳይሆን የረሃብና የድርቅ ተምሳሌትነቷን፤ ፖለቲካዊ ኪሳራዋን፣ ኢኮኖሚያዊ ድቀቷን፣ የዜጎቿን ዓለም-አቀፋዊ ስደተኝነት እና ሌሎችም ውጥንቅጥ የሞላባቸውን አስቀያሚ ገፅታዎቿን ሳይቀር አብዛኞቹ ያውቁታል፡፡ አንዳንዶቹ በሚገርም ዓይነት ሁኔታ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር መኖሯንም በፍፁም አያውቁም፡፡ አረ አንዳንዴስ ሳስበው ክፉ ክፉ ነገራችንን ብቻ እያነሱ ከሚያሸማቅቁን ጭራሽ ባያውቁን ነው የሚበጀው፡፡
ታዲያ ከአስገራሚ ጥያቄዎቻቸው ውስጥ በከፊል፡-

• ‹‹ሀገራችሁ ምግብ የለም፤ ሕዝቡ አሁንም ድረስ ይራባል?››
• ‹‹መንግሥታችሁ ጎሪላ ፋይተር (ሽምቅ ተዋጊ) ነው አይደል?››
• ‹‹ለመሆኑ ዋሻ ውስጥ ነው የምትኖሩት ወይስ ቤት አላችሁ?››


የመሳሰሉት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ከሚያጋጥሙኝ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ አንዳንዶቹማ ስለ ኢትዮጵያ መልካም ነገሮቿን ልነግራቸው በሞከርኩ ቁጥር ‹‹ታዲያ አገራችሁ አንተ እንደምታወራላት ደህና ሀገር ከሆነች ለምን እዚህ መጣህ?›› በሚል ጥያቄ ያፋጥጡኛል፡፡ በዚህ ምክንያት አሁን አሁን ኢትዮጵያዊ ነኝ ከማለት ይልቅ የተለመደው ‹‹ከየት ነህ?›› ጥያቄ ሲመጣ ‹‹Somewhere in Africa›› ‹‹ከአፍሪካ አካባቢ›› ማለትን መርጫለሁ፡፡ ታዲያ ምንቦጣኝ? ለምን ልሳቀቅ? አንጋፋዋና ዝነኛዋ ድምፃዊት አስቴር አወቀ ስለሀገር ባዜመችው አንድ ዜማዋ ላይ ‹‹ከየት ነሽ ጥያቄ ሆዴን ያስብሰኛል›› ያለችው ለካንስ ወዳ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ እዚህ አሜሪካ ያሉ አንዳንድ ኢትዮጵውያን ልጆቻቸውን ለመቆጣት ሲፈልጉ ‹‹ዋ! እምቢ ካልክ ኢትዮጵያ ነው የምወስድህ!›› ይሏቸዋል፡፡ አሜሪካ የሕፃንትና የሴቶች መብት በጣም የተከበረበት ሀገር ስለሆነ ከዚህ በላይ ምንም ሊሏቸውና ሊያደርጓቸው አይችሉም፡፡ ታዲያ እነዚህ ሕፃናት ገና በለጋ አዕምሯቸው ስለኢትዮጵያ ምንድነው ተቀርፆባቸው የሚያድጉት? ኢትዮጵያ ማለት ‹ሲዖል›፣ ‹የገሃነም ደጃፍ›፣ ወይም ለነሱ ቀረብ በሚል ቋንቋ ‹ጓንታናሞ ቤይ›?

በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ራሳችን የገዛ ልጆቻችንን ዛሬ እንደዚህ ካበላሸናቸው ነገ መልሰን እናቃናቸው ብንል እንዴት ይሆንልናል? አንድ ዛፍ መቃናት የሚችለው ገና በችግኝነቱ እንጂ ትንሽ ከፍ ካለ አበቃለት፡፡ መቼም እኛም ሆንን አሁን ያለው ታሪክ ተወደደም ተጠላ ጊዜውን ጠብቆ ያልፋል፤ ነገርግን በነገይቱ ኢትዮጵያ ላይ የራሳችን የሆነ ምን ዓይነት አሻራ ነው ጥለን የምናልፈው? በእንዳንዳችን ሕሊና ውስጥ ሊታሰብበትና መልስ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ ቸር ይግጠመን፡፡ምንልክ ሳልሳው ብሎግፖስት