ኢየሱስ እና ሌሎች አማልክቶች፡ አሉ የሚባሉ መመሳሰሎች ሲፈተሹ!

ግደይ ገብረኪዳን

በ ዚህ ጽሑፍ[1]በመጽሐፍ ቅዱስ የሰፈረው የኢየሱስ ክርስቶስ ታሪክ ከሌሎች “ቀድመውት ነበሩ” ከሚሏቸው አማልክቶች ታሪክ የተኮረጀ ወይም የተቀዳ ነው በማለት ብዙዎችን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ከመጽሐፍ ቅዱስ ያገኙትን እውነት በመፈተን ትክክለኛ ያልሆነውን ታሪክ ሊያስጨብጡ በተለያየ ዘዴ ጥረት የሚያደርጉ ሰዎች ሃሳቦችን እንዳስሳለን፡፡ እንዲህ የሚደርጉት ለዘመናት በተለያየ ዘዴ የኢየሱስ ክርስቶስን አስተምህሮ እና የገለጸውን እውነት ለማጥፋት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የዚህ ሴራ ሰለባ የሚሆኑት ደግሞ በአብዛኛው እውነት ፈላጊ የሆኑ እና ማንኛውንም መረጃ ለመዳሰስ ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎች ናቸው፡፡ ስህተታቸውን ማሳየት እጅግ ሲበዛ ቀላል ነው፤ ምክንያቱም የተቀዳ መሆኑን ለማሳየት የሚጠቀሙበት ዘዴ ከምርምር እውነት የራቀ እና ከፍተኛ የማጭበርበር ተግባር የሚታይበት በመሆኑ ነው፣ በዚህም አንባቢዎቻቸውን ከእውነት ያርቃሉ፡፡ እውነተኛ ዋና ቅጂ ጽሑፎችን ማነጻጸሩ ብቻ መልስ ይሆናል፤ የየእምነቶቹ ዋና ጽሑፎች በላይ ምስክር ሊኖር አይችልምና፡፡ ተኮረጀባቸው የሚባሉቱን እውነተኛ ዋና ጽሑፎችን ከፈተሽን በኋላ አሉ የተባሉት ጽሑፎች የሌሉ ወይም ተለጥጠው ያለ አግባብ የተተረጎሙ ሁነው ይናገኛቸዋለን፣ እንዲህ የሚሸፍጡት ጸሐፍያን አንባቢው ስለ ሌሎች እምነቶች በቂ ግንዛቤ የሌለው መሆኑን ተስፋ በማድረግ ነው፡፡

 በዚህ ጽሑፍ፡ (1) ክሪሽና (2) ቡድሃ (3) ሆረስ (4) ዞሮአስተር (5) ሚትራስ (6) አቲስ (7) ዳዮኒሰስ-ባኩስ (8) ተሰቀሉ ስለተባሉ አማልክት፤ በዝርዝር እንፈትሻለን፡፡ መግቢያ ድረ-ገጹን ብትፈትሹ በአረመኔዎቹ አማልክት እና ኢየሱስ መካከል ተመሳሳይነት አለ የሚሉ በተመሳሳይ መልኩ የተሳሳተና የተባሉትን አማልክት ዋና መጻሕፍቶችን የማያጣቅሱ ብዛት ያላቸው ጽሑፎችን ማግኘት ይችላሉ፡፡ የተባሉትን አማልክት መጻሕፍት ቢያፈላልጉ ግን ይህ አባባል ፍጹም ስህተት መሆኑን ይደርሱበታል፡፡ አንባቢው በዚህ ጽሁፍ ውስጥ ከአረመኔዎቹ ተቀዳ የሚለው ንድፈ ሃሳብ /"Pagan Copycat Theory"/ የሐሰት ለመሆኑ በራሱ እንዲያረጋግጥ ዋና ጽሑፎቹን የሚያገኝበት ማጣቀሻዎች እንዲካተቱ አድርገናል፡፡ ተጠራጣሪው፤ እኚህ አማልክት እኮ ከኢየሱስ ሕይወት ዘመን በፊት ነበሩ፤ የሕይወት ዘመን ቅደም ተከተል ብቻውን ውይይቱን አላስፈላጊ ያደርገዋል የሚል ነጥብ ሊያነሳ ይችላል፡፡ ምላሹም፤ ልብ ሊባል የሚገባው ክርስቶስ ከመምጣቱ በፊት ስለእርሱ ሕይወት፣ ሞት እና ተልእኮ በብሉይ ኪዳን የሚገኙ ነቢያት የተነበዩአቸው ወደ 300 የሚሆኑ ዝርዝር ጽሑፎች መኖራቸውን ነው፡፡ እኚህ ትንቢቶች ከውልደቱ ከ 450 እስከ 1,500 ዓመታት በፊት የተጻፉ ናቸው፡፡ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስትያኖች ከሌሎች እምነቶች ኮረጁ የሚለው ሃሳብ እንደ ድንግል ውልደት፣ ከሞት መነሳት፣ እና የአባት-ልጅ ትስስር ከአብዛኞቹ ተኮረጀባቸው ከሚባሉት ቀድሞ የነበሩ ጭብቶች መሆናቸውን ከግንዛቤ ያስገባ አይደለም፡፡ በተጨማሪም አብዛኞቹ ሂስ አድራጊዎቹ አገኘነው የሚሏቸው ተመሳሳይነት የሚያሳዩ ጽሑፎች ከመጽሐፍ ቅዱስ በኋላ የተጻፉ ናቸው፡፡ ክፍለ ዘመናት እየተቆጠሩ በሄዱ ቁጥር እየተጨመረባቸውም ይሄዳል፣ ይህም ይበልጥ ሕይወታቸው ከክርስትና ጽሑፍ ጋር እየተመሳሰለ እንዲሄድ አድርጓል፡፡ በኢየሱስና በሌሎች አማልክት መካከል ያለው ዋናው ልዩነት የኢየሱስ ሕይወት በታሪክ ማረጋገጥ ይቻላል፣ ውልደቱና ሞቱን የሚያስረዱ በርካታ መዛግብት አሉ፣ በዘመኑ የተከናወኑ ታሪካዊ ክስተቶች በታሪክ ጸሐፍን የተመዘገቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም በትክጅል ተመዝግበው ይገኛሉ፣ የይሁዴ-ክርስትና እምነት ምንጭንም መመልከት ይቻላል፡፡ ሌሎቹ ግን በታሪክ የተመዘገበ ምንጭ (መነሻ) የላቸውም፣ በተጨማሪም በታሪካቸው ሆነ ስለሚሉት ነገር የሚገልጽ ዓመት ወይም እለት የላቸውም፡፡ በዛም አለ በዚህ ተኮረጀ የሚባለው ሃሳብ የሐሰት መሆኑን ስለምናሳይ፣ ቀድሞ ማን መጣ የሚለው መከራከርያ ዋጋ ቢስ ይሆናል፡፡ ተጠራጣሪው፤ የታሪካዊ ክስተቶች በትክክል መስፈራቸው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክጅለኛነት እንዴት ያስረዳል? ብዙ የልብ ወለድ ጸሐፊዎች ፈጠራቸው የእውነት እንዲመስል እውነተኛ ሰዎችን እና ቦታዎችን ያካትታሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ በምን ይለያል? ይላል፡፡ ምላሹም፡ ታሪካዊ ክስተቶችን በትክክል መዘገቡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነትን አያሳየንም ሆኖም ግን፣ ስለ ታማኝነቱ ግን ምስክር ይሆናል፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ሌሎቹ ትክክለኛ ያልሆኑ ቦታዎችንና ሰዎችን ቢጠቅስ ተአማኒት አይኖረውም ነበር፡፡ እውነቱን ማበጠርያ ወንፊት ከእንግዲህ የትኛውም ታሪክ ተቀድቶ ነው የሚል ሃሳብ ሲገጥማችሁ የሚከተሉትን መሰረተ እውነት የሚከተሉ ጥያቄዎችን ጠይቁ፡- ቃላት አጠቃቀም፡ አንደኛው የይሁዴ-ክርስትያን ቃላት አጠቃቀምን ልብ ማለት ነው፡፡ በታሪክ ሃይማኖታዊ ስነ-ስነስረዓት አካክ የሆነ በውሃ የመታጠብ በዓል የነበራቸው ብዛ ሃይማኖቶች ነበሩ፣ ሆኖም ይህ ግን ጥምቀት አልነበረም፡፡ ፖለቲካዊና ሃይኖታዊ ቡድኖች በጋራ ተሰብስው የሚበሉበት በዓል ይኖራቸው ይሆናል፣ ይህ ግን ሥጋ ወደሙ (ቁርባን) አልነበረም፡፡ አማኞች አምላካቸውን የንደ አዳኝ ሊቆጥሩት ይችሉ ይሆናል፣ ሆኖም ሲጠበቅ የነበረ አዳኝ መሲህ ግን አይደለም፡፡ የተለያዩ ሃይማኖቶች ከሞት በኋላ ሕይወት ስለመኖሩ ሊያስተምሩ ይችላሉ፣ ገነት እና ገሃነም ስለሚባሉ ቦታዎች ግን አያካትቱም፡፡ ሃያስያን እኚህ ቃላቶችን እየተጠቀሙ ንጽጽራቸው ጠንካራ መሆኑን ለማሳየት ይሞክሩ ይሆናል፣ ይህ ግን የይሁዴ-ክርስትያን ቃላቶችን ያለአግባቡ መጠቀምን የሚያሳ ነው፡፡ ዘመን አቀማመጥ፡ ንጽጽራዊ ማስረጃ ተብሎ ሲቀርብላችሁ፣ የሚከተለውን ጥያቄ አስከትሉ፡- 1) የቀረበው አካል በብሉይ ኪዳን ከሰፈረው የመሲሃዊ ትንቢቶች ቀድሞ ነበርን? (አብዛኞቹ አይቀድሙም፡፡) 2) ማስረጃው የተገኘበት ዘመን ከክርስትና ይቀድማል? (በተመሳሳይነት የቀረቡት አብዛኞቹ ሃይማኖት ጽሑፎች እና ምስል /ቅርጽ ከክርስትና በኋላ የተሰሩ ናቸው፡፡) 3) ይህ አካል ከክርስቶስ ሕይወት ዘመን ቀድሞ ነበር? (ለምሳሌ እንደ የታይና አፖሎኒየስ አይቀድምም፡፡) ቦታ፡ ለምሳሌ ሃያስያኑ በደቡብ አሜሪካ የሚገኝ (ለምሳሌ እንደ ኩዌትዛልኮትል /Quetzalcoatl) ክርስትና ላይ ተጽእኖ አሳድሯል ካሉ፣ ይህ የቦታው መለያየት የሐሰት ለመሆኑ ያስረዳናል፡፡) ተምሳሌትነት፡ ንጽጽሩ ሲቀርብ ተምሳሌታዊ ፍቺው ምን ሊሆን እንደሚችል ጠይቁ፡፡ ለምሳሌ በጥንት ዘመን የነበሩ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ቡድኖች በጋራ የሚመገቡት የእራት ግብዣ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል ሆኖም ግን ይህ እንደ ክርስትያን ቁርባን ያለ ጥቅም ያለው አይደለም፡፡ ተከታዮች አምላካቸውን እንደ አዳኝ ሊቆጥት ይችላሉ ሆኖም ግን ከውርስ ሃጥያት እና ጥፋት የሚያወጣ አድርገው አይወስዱትም፡፡ ምንጮች፡ ንጽጽሩ የተደረገው በእውነትም ጥያቄው ውስጥ ከተካተቱት እምነቶች መጻህፍት የተወሰደ መሆኑን ያረጋግጡ፡፡ (አብዛኞቹ መቼም አያጣቅሱም፡፡) አብዛኞቹ የሚያጣቅሱት እንደነርሱ ሃሳብ የሚያራምድ ሌላ ጸሐፊን ነው፡፡ ዋናውን መጸሐፍ ሲጠቅሱ ደግሞ ቅጹን ወይም የስንኙን ቁጥር መጥቀስ ይዘነጉና፣ ይህ የት ቦታ እንዳለ ያልተረጋገጠ ስንኝ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ግን የቱ ጋር እንዳለ ከነስንኙ ይጠቅሳሉ፡፡ ተገኘ በተባለበት እምነት ይህ ማጣቀሻ እቅጩኑ የቱ ጋር እንዳለ ይጠይቁ፡፡ በመጨረሻም በዚህ ጽሑፍ ደጋግመን እንደምናየው አብዛኞቹ ሃይማኖቶች እንደ ክርስትያን እምነቱ የሚቀበለው ቀኖናዊ መጽሐፍ ቅዱስ የላቸውም፡፡ ጽሑፎቻቸው ክፍለ ዘመናት እየገፉ በሄዱ ቁጥር እንደሚቀያየሩና እንደሚጨመርባቸው የሚቀበሉት ነው፡፡ ሃያስያኑ በሚያጣቅሱት ምንጭ ዋና ጽሑፍ አስረግጠው ቦታውን ከጠቀሱ፣ ከክርስትና በፊት ስለ መጻፉ ጠይቁ፡፡ (አብዛኞቹ አይቀድሙም፡፡) (1) ክሪሽና በሂንዱ እምነት ክሪሽና የቪሽኑ ስምተኛ አቫታር ነው፡፡ [አቫታር ማለት አማልክቱ የሰው ወይም የእንሰሳ አካል ይዘው ሲፈጠሩ የሚሰጣቸው መለያ ነው፡፡] በክሪሽና እና ኢየሱስ መካከል አለ ስለከሚባለው መመሳሰል ምንጩ ሁሉ ኬርሴ ግሬቭስ የተባለ የ19ኛው ክፍለ ዘመን ጸሐፊ ሁኖ ነው የሚገኘው፡፡ ይህ ጸሐፊ ክርስትና ከአረመኔዎች ተረት የመጣ ነው ብሎ ያምናል፡፡[2] የክሪሽና ፍቺ፡ ሃያስያኑ ክሪሽና ማለት ክርስቶስ ማለት ነው ቢሉም፣ በሳንስክሪት በእውነቱ ክሪሽና ማለት ጥቁር/ሩ ማለት ነው፣ በተረቱ ክሪሽና ጠቆር ያለ ሰማያዊ ቆዳ ያለው ነው ተብሎ ይታመናልና፡፡ ክርስቶስ ማለት ግን ቅቡእ ማለት ነው፡፡ ሃያስያኑ ይህ የተሳሳተ ሃሳባቸውን ለማስፋፋት ክሪሽናን በእንግሊዘኛ Krishna ተብሎ ከሚጻፍበት ትክክለኛው ፊደላት ሌላ Chrishna / Christna አድርገው ይጽፋሉ፡፡ ድንግል ውልደት፡ ክሪሽና በድንግልና ተወለደ የሚል ታሪክ የለም፣ ወላጆቹ ከእርሱ በፊት ሰባት ልጆች ወልደዋልና፡፡ ድንግል ውልደት የሚለው ደግሞ የክርስትያኖች ፈጠራ አይደለም፡፡ በ700 ዓ.ዓ የተጻፈው ትንቢተ ኢሳይያስ ከድንግል ስለሚወለደው መሲህ ይናገራል፡፡ ይህ ትንቢት ከክርስቶስ ውልደት 700 ዓመት በፊት እና ከክሪሽና ደግሞ ከ 100 ዓመት በፊት ይህ መጽሐፍ በሰዎች እጅ ነበር፡፡ (ትንቢተ ኢሳይያስ 7፣ 14[3]) ሃያስያኑ ክሪሽና ድንግል ከሆነች ማያ ከምትባል ተወለደ ይላሉ፣ ሆኖም ግን የሂንዱ ጽሑፎች የሚሉት ሌላ ነው፣ የልዕልት ዴቫኪ እና የባሏ ቫሱዴቫ ስምንተኛ ልጅ ነው፡- “ብራህማን በምድር ትከላከል ዘንድ ከቅዱስ ዴቫኪና ቫሱዴቫ ተወልደሃል፡፡” ይላል መጽሐፋቸው ማሃባሃራታ፡፡[4] የሕጻናቱ ጭፍጨፋ፡ ሃያስያን ከክሪሽና ልደት በፊት ጨካኝ የሆነ መሪ ሕጻናት እንዲገደሉ አሳውጆ ነበር ይላሉ፣ ሆኖም ግን የሂንዱው አፈ ታሪክ የሚለው የዴቫኪ የቀደሙት ስድስት ልጆቿ በአጎቷ ወይም አክስቷ ልጅ በሆነው ንጉስ ካምሳ ነበር የተገደሉት፣ ይህም ከልጆቿ ባንዱ እጅ ትሞታለህ የሚል ትንቢት ስለነበር ነው፡፡ በክርስትና ግን ሄሮደስ ከሁለት ዓመት በታች የሆናቸው ወንዶች ህጻናት እንዲገደሉ ነበር ያሳወጀው፣ የሂንዱው ግን ካምሳ የዴቫኪ ልጆችን ብቻ ነበር የገደለው፡፡ የማንንም ሳይለዩ ወንዶች ሕጻናትን እንዲገሉ አላሳወጀም፡ “ስድስት ልጆችም ለዴቫኪ ተወልደውላት ነበር፣ ካምሳም እነዚህ ስድስት ልጆች እንደተወለዱ በተከታታይ ገደላቸው፡፡” ይላል መጽሐፋቸው ባጋቫታ፡፡[5] የወላጆቹ መሰደድ፡ ሃያስያኑ የክሪሽና ወላጆች ከካስማ ለማምለጥ ወደ ማቱራ ተሰደዋል፣ ከሄሮደስም ለማምለጥ የኢየሰሱ ወላጆች ወደ ሙቱሪያ ሄዱ ይላሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ማርያም እና ዮሴፍ ወደ ግብጽ መሰደዳቸውን ያስረዳል እንጂ ወደማይታወቅ ሙቱርያ የተባለ ቦታ ሄዱ አይልም፡፡[6] በተጨማሪም የክሪሽና ወላጆች ለማምለጥ እንኳ እድሉ እንዳልነበራቸው ይነግረናል - ልክ እንደተወለደ ሊገድለው የክሪሽና ወላጆችን አስሯቸው ነበር፡- “[ቫሱዴቫ] እና ባለቤቱ ምን ስህተት ፈጸሙ? የዴቫኪ ስድስት ሕጻናት ልጆቿን ለምን ካስማ ገደላቸው? [ቪሽኑስ] ለምንድን ነው በካስማ እስር ቤት የቫሱዴቫ ልጅ ሁኖ እራሱን ሥጋ ያለበሰው?” ይላል ባጋቫታ፡፡[7] እረኞች፣ ጠቢባኑ (ሰብአ ሰገል)፣ ኮከብ፣ እና ግርግም (በረት)፡ በክሪሽና ውልደት ግዜ ምንም አይነት እረኛ ወይም ጠቢባን የሚባል ነገር አልተጠቀሰም፡፡ ክሪሽና በወላጆቹ በተያዘ ሚስጥር ነበር በእስር ቤት ነበር የተወለደው (ሃያስያኑ እንደሚሉት በበረት አይደለም)፡፡ በዚህ ሁኔታ ለንጉሱ ሊናገሩ ጠቢባን ይመጣሉ ማለት የማይሆን ነው፡፡ እንጨት ሰሪ አባቶች፡ እንደ ክርስቶስ ምድራዊ አባት (ማለትም ጠባቂው ዮሴፍ)፣ የክሪሽና አባትም እንጨት ሰሪ ነው ይባላል፡፡ ይህ ግን በየትኛውም የሂንዱ ጽሑፍ ላይ የማይገኝ ነገር ነው፡፡ እንዲያውም አባቱ ቫሱዴቫ ከመኳንንት ወገን ነው፣ በማቱራ መኳንንት ቤት ውስጥ ነበር ዴቫኪን ያገባት፡፡ ክሪሽና የካምሳን ቁጣ ለማምለጥ በሚሸሽበት ግዜ ጠባቂ አባቱ የነበረው ናንዳ ነበር ይህም ከብት አርቢ ነበር፡ “አንተ እጅጉኑ የምትወደደው ከብት አርቢው ናንዳ አይደለህ፡፡” ባጋቫታ፡፡[8] ስቅለት፡ ሃያስያኑ ክሪሽና ተሰቅሏል ቢሉም ይህ በሂንዱ ጽሑፎች በየትኛውም ቦታ አይገኝም፡፡ አሟሟቱ በግልጽ እንደሚከተለው ተጽፏል፡ ክሪሽና ጫካ ውስጥ እያለ በስህተት የአዳኝ ቀስት እግሩን ትመታ፡፡ አንዳንድ ሃያስያን ይህን ያላግባብ በመለጠጥ ከዛፉ ግንድ ጋር ቀስቱ ስላጣበቀው ተሰቀለ ማለት ነው ይላሉ፡፡ በተጨማሪም እግሩ ጋር መቁሰሉ ከክርስቶስ እጅ እና እግር ጋር መቁሰል ይመሳሰላል ይላሉ፡፡ ይህ ሲበዛ ሞኝነት ያለበት ሃሳብ ነው፡፡ አንድ ሰው ስሙን ዛፍ ላይ ለመጻፍ እየፈቀፈቀ እያለ ጎኑን ቢሞነጭር ተሰቀልኩ ሊል ነው ማለት ነው፡፡ የክሪሽና አሟሟት ይልቁኑስ ከግሪኩ አፈ ታሪክ አኪለስ ጋር ይመሳሰላል፡ “ስሙ ጃራ የተባለ ሃያል አዳኝ መጣ፣ አጋዘን ፈልጎ፡፡ ምድር ላይ በከፍተኛው ዮጋ ቅርጽ ተኝቶ የነበረውን [ክሪሽናን] አጋዘን መስሎት ተሳስቶ እግሩ ጋር ወግቶ ያደነውን ለመያዝ በፍጥነት መጣ፡፡” ማሃባራታ፡፡[9] ትንሳኤ፡ ሃያስያን ክሪሽና ወደ መቃብር ወርዶ ከሶስት ቀን በኋላ ለብዙ ምስክሮች ታይቷል ቢሉም ይህን የሚያሳይ አንዲትም ማስረጃ የትም አይገኝም፡፡ እውነተኛው ታሪክ ግን ክሪሽና ወድያው ወደ ሕይወት በመመለስ አዳኙን ብቻ በማናገር ለሰራው ይቅር እንዳለው ይናገራል፡ “እርሱም [አዳኙ] እግሩን [የክሪሽናን] ነካ፡፡ ባለ ከፍተኛ መንፈሱ አነጋገረውና ወደ ላይ ሄደ፣ ሰማያዊ መኖርያቸውን በሚደንቅ ውበት ሞልቶ፡፡” ማሃባራታ፡፡[10] በኢየሱስ እና ክሪሽና ትንሳኤ መሃል የሚታዩት ግልጽ ልዩነቶች የሚከተሉት ናቸው፡ የኢየሱስ ትንሳኤ ሞት እና ሃጥያትን ድል ነስቷል፡፡ የክሪሽና ትንሳኤ በሰው ልጅ ላይ ያስከተለው ነገር የለም፡፡ በአዲስ ኪዳን መሰረት ኢየሱስ እስከ 500 ለሚጠጉ እማኞች ታይቷል፡፡ ክሪሽና ለአንድ አዳኝ ብቻ ነበር የታየው፡፡ ኢየሱስ ከሞት የተነሳው ከሶስት ቀን በኋላ ነበር፡፡ ክሪሽና ወደ ሕይወት የተመለሰው ወድያው ነበር፡፡ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተልእኮ እስኪሰጣቸው ድረስ ወደ ሰማይ አላረገም ነበር፡፡[11] ክሪሽና ግን ወድያውኑ ወደ ቀጣዩ ሕይወት “ሄደ” ይላል፡፡ ኢየሱስ ሊሆን ያለውን ሁሉ ቀድሞውኑ ያውቅ ነበር፡፡ ክሪሽና ስለ ሞቱ የሚያውቀው አንዳችም ነገር አልነበረውም፡፡ ኢየሱስ ያረገው አካላዊነት ወዳለው ዓለም (ገነት) ነው፡፡ ክሪሽና ወደ አእምሯዊ ሕላዌ (ወይም ማወቅ ወደማይቻል ቦታ) ነው የተሸጋገረው፡፡ በገነት (ክርስትና) እና በኒርቫና (ሂንዱ) መሃል እጅግ ሰፊ የጭብጥ ልዩነት ነው ያለው፡፡ የመጨረሻው እራት፡ የመጨረሻው እራት እየተባለ በተለምዶ የሚታወቀው ክርስቶስ ለመጨረሻ ግዜ ከሃዋርያቱ ጋር ለፋሲካ የበሉበትን ግብዣ ነው፡፡[12] ክሪሽና የመጨረሻ እራት በዓል አክብሯል ይባላል፣ ይህ ግን በሁለት ምክንያቶች የውሸት ሃሳብ መሆኑን ማየት ይቻላል፡- 1) በሂንዱ ጽሑፎች በየትኛቸውም ቦታ ክሪሽና የመጨረሻ የእራት ግብዣ አድርጓል ሚል የለም፡፡ 2) ክሪሽና የሚሞትበትን ቅጽበት ቀድሞ አያውቅም ነበር፣ እንዲህ የመሰለ የመጨረሻ እራት ግብዣ የሚያደርግበት ምክንያት አይኖረውም፡፡ የእባቡን አናት ሲቀጠቅጥ ተስሏል፡ ዘፍጥረት 3፣ 15 ላይ መሲሃዊ ትንቢት አለ፣ ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር የሚያደርገውን መንፈሳዊ ውግያን የሚያሳይ፡፡[13] ሃያስያን ክሪሽናም የሴቲቱ ዘር የሆነና የእባቡን ጭንቅላት ያቆሰለ ተብሎለታል ቢሉም፣ ይህ ሃረግ ከክሪሽና ጋር በተያያዘ የትም ቦታ ላይ አልተጠቀሰም፡፡ የተጻፈው ነገር ክሪሽና ተምሳሌታዊ ሳይሆን በእውን ከእባቦች ጋር የገጠመው ክስተት ነው፡፡[14] የቀሩ ልክ የሚመስሉ ማጣቀሻዎችና መልሳቸው ክሪሽና የቪሽኑ ሰብአዊ ስጋ ለብሶ ተገለጠበት ነው፡፡ ይህ ከላይ ሲታይ አንድ ይመስላል፣ ልክ እንደ ክርስትና አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ፣ ክርስቶስ ወልድ ነው፤ ሆኖም ግን የሂንዱ ሶስትዮሽ ቪሽኑ፣ ሺቫ እና ብራህማ ነው እንጂ ቪሽኑ፣ ክሪሽና እና መንፈሳዊ አምላክ አይደለም፡፡ ክሪሽና የመሳፍንት ዘር አለው፡፡ ክሪሽና በቀጥታ ከነ ማቱራ ማሳፍን ቤት ሲወለድ፣ ኢየሱስ ግን ከዳዊት ዘውዳዊ ዘር ሐረግ የተገኘ ቢሆንም በቀጥታ የተወለደው ግን ከመሳፍንት ቤት ሳይሆን ከማርያም እና ከጠባቂዋ ዮሴፍ በድህነት ነው የተወለደው፡፡ ክሪሽና እንደ አዳኝ ነበር የሚታየው፡፡ ኢየሱስ ህዝቡን ከጥፋት ያወጣ የዘልአለም-መንፈሳዊ አዳኝ ሲሆን፣ ክሪሽና ግን ህዝቡን ከጨቋኙ የካምሳ አገዛዝ ያዳነ ምድራዊ-ተዋጊ አዳኝ ነበር፡፡ ክሪሽና አብዝቶ በየጫካው ይጾም ነበር፡፡ ከዚህ ሊጠጋጋ የሚችለው ማጣቀሻ ቢኖር ለተመስጦ ወደ ጫካ ውስጥ ይገባ የነበረ መሆኑ ነው፡፡ የቀሩ የተሳሳቱ ማጣቀሻዎች ክሪሽና ዋሻ ውስጥ ነው የተወለደው፡፡ በእውነቱ ክሪሽናም ሆነ ኢየሱስ ዋሻ ውስጥ አልተወለዱም፡፡ ክሪሽና እስር ቤት ውስጥ ነው የተወለደው፡፡ ክሪሽና ሐጥያት የሌለበት ሕይወት ነው የኖረው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ኢየሱስ ሕይወት ዘመኑ አንዳችም ሐጥያት እንዳልሰራ በግልጽ የተቀመጠ ሲሆን፣ የሂንዱ ጽሑፎች ግን ክሪሽና የፈጸማቸውን የሴሰኝነት ተግባራትና የተለያዩ ወሲባዊ ድርጊቶቹን አስፍረውታል፡፡ ክሪሽና በታህሳስ (ዲሰምበር) 25 በፈረንጆች አቆጣጠር ተወለደ፡፡ በእውነቱ የክሪሽና ልደት ክሪሽና ጃንማሽታሚ እየተባለ የሚታወቀው የሚከበረው በሂንዱ ወር ባድራፓዳ ውስጥ ነው፣ ይህም ከፈረንጆቹ ነሐሴ (ኦገስት) ወር ጋር የሚገጥም ነው፡፡[15] በተጨማሪም ደግሞ ፈረንጆቹ በሚያከብሩት ግዜ ወይም እለት አይደለም የኢየሱስ ትክክለኛ ልደት፡፡ ልደትን በዚህ እለት ያደረጉት ከባህል ተጽእኖ ነው፡፡ ክሪሽና ትንሽዬ ገጠራማ ሰፈርን ከአደጋ ለመከላከል ተራራ አንቀሳቅሷል፡፡ ኢየሱስ የሚከተለውን ብሏል፡- “ኢየሱስም፡- ስለ እምነታችሁ ማነስ ነው፤ እውነት እላችኋለሁ፥ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ፡- ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።”[16] ከተራራው መንቀሳቀስ ውጪ እኚህ ሁለት አረፍተ ነገሮች ሰፊ የጭብጥ ልዩነት አላቸው፡፡ የክሪሽና ጽሑፍ በአካል ተራራ ስለማንቀሳቀስ የተጻፈ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለው ግን ስለ እምነት ኃይል የተነገረ ተምሳሌታዊ ንግግር ነው፡፡ መደምደምያ፡ ክፍለ ዘመናት በገፉ ቁጥር የሂንዱ ጽሑፎች እነርሱም እራሳቸው አማኞቹ እንደሚቀበሉት ሲቀየሩና ሲጨመርባቸው መጥተዋል፡፡ የኋለኞቹንና የቀደሙትን የሂንዱ ጽሑፎች ብናነጻጽር ስለ ክሪሽና ሕይወት በተመለከተ ፑራናስ፣ ባጋቫታ፣ እና ሃሪቫምሳ የተሰኙ ስራዎች ተጨምረውባቸዋል፡፡[17] እኚህ ጽሑፎች ከክርስቶስ ልደት በኋላ የተጨመሩ ስለመሆናቸው በተመራማሪዎች የተረጋገጡ ናቸው፡፡ ተጠራጣሪው የሚከተለውን ሊያነሳ ይችላል፡ በሂንዱ ልማድ መሰረት ባጋቫታ ፑራና በ3,100 ዓ.ዓ በቭያሳ እንደተጻፈ ይታመናል፡፡ በ2,000 ዓ.ዓ እንደደረቀ የሚታመነውን የቨዲክ ሳራስቫቱ ወንዝን እስከ ሰላሳ ግዜ ይጠቅሰዋል፡፡ ምላሹም የሚሆነው፡ ይህ ሃሳብ ባጋቫቲ ረዥም እድሜ አስቆጥሯል ለሚለው መከራከርያ ተደጋግሞ የሚነሳ ነው፡፡ ይህ ግን በብዙ ምክንያቶች ውኃ የማይቋጥር መከራከርያ ነው፡፡ አሁን ላይ በጠፋው የባቢሎን አጸዶች ውስጥ የተከናወነ ልብ ወለድ ብጽፍ የጽሑፉን ውልደት እንደማያራዝመው ሁሉ፣ ባጋቫቲ ፑራና የጠፋውን የቨርዲክ ሳራስቫቲ ወንዝ መጥቀሱ፣ እድሜውን አያረዝመውም፡፡ ጥንታዊ ወንዞችን መጥቀስ የጽሑፉን እድሜ ሳይሆን የታሪካዊ እውቀትን ነው የሚያሳየው፣ ከወንዙ ፍቅር ካላቸው ደጋግመው ሊጠቅሱት የሚጠበቅ ነውና፡፡ በተጨማሪም እኚህ ጽሑፎች (ፑራናስ፣ ባጋቫታ፣ እና ሃሪቫምሳ) ከአንደኛው ክፍለ ዘመን በፊት የተጻፈ አንዳችም ስራ የላቸውም፡፡ የቀደሙት የሂንዱ ጽሑፎች እንኳ በሰው እጅ እያሉ፣ የክሪሽናን ሕይወት የሚዘረዝሩቱ አልነበሩም፡፡ በመጨረሻም ባጋቫታ ፑራና የተጻፈበት ቋንቋ እና ሰዋስው ከጥንታዊው የህንድ ቋንቋ ጋር የሚሄድ አይደለም፡፡ (2) ጓተማ (ቡድሃ) ጓተማ በ 563-483 ዓ.ዓ ዘመን ይኖር እንደነበር ይታመናል፡፡ ጓተማ በህንድ የህብረተሰብ ቅርጽ (ካስት) ስርዓት መሰረት በተዋጊዎች መደብ ከሚገኝ ቤተሰብ የተወለደ ነው፡፡ በኋላም ቡድሃ (አብርሆት ያለው) ለመሆን ያበቃውንና አብርሆት ሊያገኝ እና የቡድሄነት (ቡድሂዝም) እምነት ሊመሰርት ችሏል፡፡ እንደ ዞሮአስተር (ከስር አለ) በሕይወት ዘመኑ ስለ እርሱ የተጻፈ እጅግ ትንሽ ነው፣ ግዜ ባለፈ ቁጥር የሚባሉት ነገር እጹብ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡[18] ድንግል ውልደት፡ ጓተማ ከሱድሆዳና እና የሃያ ዓመታት ሚስቱ ከሆነችው ማያ ነው የተወለደው፡፡ ሃያስያን ማያ ድንግል ነበረች ቢሉም፣ ንጉሱ ከሌሎቹ ሁሉ የሚወዳት ሚስቱ እንደመሆኗ ድንግል አለመሆኗን ልናገናዝብ ይገባል፡፡ በተጨማሪም ደግሞ የቡድሃ ስራዎች የተሰኘው የቡድሃ መጽሐፍ ማያ እና ሱድሆዳና ወሲባዊ ግንኙነት እንደነበራቸው ይመሰክራል (ሁለቱ የፍቅርን ጣእም ቀመሱ … ይላል[19])፣ አብዛኞቹ የእግሊዘኛ የመጽሐፉ ቅጂዎች ይህን ሐረግ አያካትቱም፡፡ የጓተማ ውልደት ዝርዝርን ከቅዱሳን ጽሑፎች ስብስብ ገጽ ማግኘት ይቻላል፡፡[20] ምንም እንኳ ማያ ንጽሕት ተደርጋ የምትቀርብ ቢሆንም፣ የቡድሃን ውልደት በሚመለከት በድንግልና ስለመጽነስ የተጠቀሰ ነገር የለም፣ ሊሆንም የሚችለው ልክ እንደ ክሪሽና ታሪክ በማህጸን ውስጥ እያለ የመሸጋገረር ክስተት ነው፡ “ከቦድሂሳትቫሶች ሁሉ የላቀው ከቦታው በቀጥታ ተወርውሮ ከቱሺታ ገነት ነዋሪዎች መሃል ሆነ፣ በሶስቱ ዓለማት መካከል በፍጥነት በማለፍ፣ በድንገት ግዙፍ ባለ ስድስት ጥርስ እንደ ሂማልያ የነጣ ግዙፍ ዝሆን ሁኖ ከማያ ማህጸን ገባ፡፡” ቡድሃ ካሪታ፡፡[21] ተጠራጣሪው እንዲህ ሊል ይችላል፡ ማያ በሚለው እና ሜሪ (ማርያም) በሚለው ስም መሀከል ያለው መመሳሰል ምንድን ነው? ምላሹም፡ በእንግሊዘኛ ፍቺያቸው ቃላቶቹ ተመሳሳይ ቢመስሉም በዋና ቋንቋዎቹ መሃከል የሚሰጣቸው ፍቺ ለየቅል ነው፡፡ ማያ በሳንስክሪት በሃሰት የታየ (ኢሉዥን) ማለት ሲሆን፣ ሜሪ (ማርያም) በእብራይስጥ የመረረ እንደማለት ነው፡፡ ጠቢባኑ (ሰብዐ ሰገል)፡ ክርስቶስ በጠቢባን እንደተጎበኘ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡[22] በቡድሂስት ጽሑፎች ስለ ጠቢባን የሚናገር ጽሑፍ እስካሁን ለማመሳከር ማግኘት አልቻልንም፣ ሆኖም ግን ከክርስትና በኋላ በተጻፉት ላይ የሚከተሉት ይገኛሉ፡ አንደኛው ግልባጭ፡ አንድ ባህታዊ (አስቲክ) (ጠቢባን አይደለም) ልጁ ታላቅ ሃይማኖታዊ መሪ እንደሚሆን ከአማልክቱ እንደተነገረው ሊያስረው ጎብኝቶታል፡፡ ይህን ከሰሙ በኋላ ብራህማዎች ማለትም በህንድ ህብረተሰብ ቅርጽ መሰረት ከከፍተኛ ቀሳውስት መደብ የሆኑት (ጠቢባን አይደለም) አንድ አንድ ልጆቻቸውን እንደ ትንቢቱ ሁናቴ ተከትለው ውጠየቱን በመቀበል ለመስጠት ወሰኑ፡ “ከንጉሱ ሱድሆናዳ ቤተሰብ ልጅ ተወልዷል፡፡ ከሰላሳ አምስት ዓመት በኋላ፣ ብድሃ ይሆናል፡፡ … ወጣቱ ልኡል ቡድሃም ሆነ ንጉስ፣ ሁላችንም አንድ አንድ ልጅ እንሰጣለን፡ እናም ቡድሃ ከሆነ ከተዋጊው መደብ በሆኑ ባህታውያን ተከታዩና በዙርያው የሚሆኑ ይሆናል፤ ንጉስ ከሆነ ደግሞ ከተዋጊው መደብ በሆኑ መሳፍንት [ይከበባል]፡፡” ጃታካ፡፡[23] ሁለተኛው ግልባጭ፡ በጓተማ ውልደት ግዜ ትንቢት ተናጋሪ (ጠቢባን አይደለም) ጓተማ ታላቅ ሃይማኖት ሞሪ እንደሚሆን ይነግረዋል፡ “ታላቁ ትንቢት ተናጋሪ ወደ ንጉሱ ቤት መጣ፡፡ “ልጅህ ለታላቅ እውቀት ሲባል ተወልወዷል፡፡ ግዛቱን (መንግስቱን) በመተው፣ ለዓለማዊ ነገሮች ባለመጨነቅ፣ በዓለም ያለውን ጭለማ ለማጥፋት እንደ እውቀት ፀሐይ ወደ ፊት ያበራል፡፡” ቡድሃ-ካሪታ፡፡[24] የወርቅ፣ እጣን እና ከርቤ ስጦታ፡ ክርስቶስ በውልደቱ ግዜ እኚህ ስጦታዎች እንደመጡለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል፡፡[25] አሁንም እንዲህ ያለው ነገር ለቡድሃ ሲደረግለት አናይም፣ ከክርስትና በኋላ ከተጻፈ ሌላ ጽሑፍ ጋር ተለጥጦ ለማገናኘት ከሚደረግ ሙከራ በስተቀር፡፡ አማልክቱ (ጠቢባን አይደለም) ለጓተማ የሰንደል፣ ዝናብ፣ አበባ (ዋተር ሊሊ) እና ነጭ ባህር ዳርቻ የሚበቅል አበባ (ሎተስ) (የቡድሄዎች ምልክቶች) እንዳመጡለት ይናገራል፡፡[26] ይህ ግን ምንም አይደንቅም ሁሌም የነገስታት ውልደት በዚህ ዓይነት አከባበር የሚታጀቡ ናቸውና! በኮከብ የተመሩ፡ ምንም ዓይነት የከዋክብት ምልክት የሚነገርበት ቦታ የለም፣ ሆኖም ግን ከክርስትና በኋላ በተጻፉት ላይ እጅግ የተራራቀ ንጽጽር አግኝቻለው፡ አንደኛው ግልባጭ፡ ብርሃማዎቹ ጓተማ ላይ የቡድሃ ምልክቶችን[27] ያገኙ እንደሆነ ንጉስ ወይም የሃይማኖት መሪ እንደሚሆን ለማየት ፈትሸውታል፡፡ ምልክቶቹ የሰማያት ምልክቶችን የሚያመላክቱ ሳይሆኑ ቡድሃ የሚሆን ላይ የሚታዩ አካላዊ መለዮዎች ናቸው፡ “የወደፊቱን ቡድሃ ምልክቶችና ባህርያት ለመመልከትና የእጣ ፈንታውን ትንቢት ለመናገር ጠየቁ [ብራህማዎቹ]፡፡ እንዲህ ያሉ ምልክቶችንና ባህርያቶችን የያዘ ሰው በቤት ውስጥ ኑሮ ከቀጠለ፣ የሁሉ ንጉስ ይሆናል፡፡ ዓለምን ከተወ ደግሞ ቡድሃ ይሆናል፡፡” ጃታካ፡፡[28] ሁለተኛው ግልባጭ፡ አማልክቱ በተፈጥሮ የተገለጹ ተአምራትን ቢያሳዩም፣ ነቢዩን የመራ ኮከብ ታየ የሚል ግን የለም፡፡ ሆኖም ግን እኚህ ምልክቶች ምን እንደሆኑ በዝርዝር ተነግሮናል፡ “ሰውነቱ እድሳት እንዲነቃቃ ከሰማይ ሁለት የውሃ ወንዞች፣ እንደ ጨረቃ ብርሃን የደመቁ፣ የሙቀትም የቅዝቃዜም ኃይል ያላቸው፣ በዛ አጋር በሌለው ሰው ጭንቅላት ላይ አረፉ፡፡ … አማልክቱ ሰማይ ላይ ነጭ ዣንጥላ ይዘው ከላቀው ጠቢቡ ላይ ምርቃታቸውን አንሾካሾኩ፡፡ … ከዛም በምልክቶች እና በንስሃ [ጸሎቱ] ውልደቶችን ሁሉ በውልደቱ የሚያጠፋውን ለማወቅ የቻለው ታላቁ ትንቢት ተናጋሪ አሲታ ወደ ንጉሱ ቤተ መንግስት መጣ፡፡ ታላቁ ትንቢት ተናጋሪም የንጉሱን ልጅ በግርምት ያዘው፣ እግሮቹ የመዘውሩ ምልክት ያለባቸው፣ የእጁና እግሩ ጣቶች በክብ ጸጉሮች ተጠላልፈው፣ በቅድንቦቹ መሃከል ክብ ጸጉር ያለው፣ እና እንደ ዝሆን ብርታት ያለ ምልክት ያለው፡፡” ቡድሃ ካሪታ፡፡[29] ታህሳስ (ዲሰምበር) 25፡ ምንም እንኳ ይህ እለት ኢየሱስን እንደማይመለከት ያየን ቢሆንም የጓተማ ልደት የሚከበረው ግን በጸደይ ወራት ውስጥ በሚገኘው ቬሳክ ወር ውስጥ በተከታዮቹ ይከበራል፡፡[30] ጨካኝ ንጉስ ሊያጠፋው ሞክረሯል፡ እንደ ሕጻኑን ኢየሱስ የጓተማን ሕይወት ሊያጠፋ የሞከረ አለ ተብሎ የተጻፈበት ቦታ የለም፡፡ የተጻፈው ነገር የሚለው ንጉሱ አባቱ ከሃይማኖታዊ የአገልግሎት ሕይወት ወደ ምድራዊ የዘውዳዊ ቅንጦት ሕይወት ሊስበው እንደሞከረ ብቻ ነው፡፡ ትንቢት ተናጋሪው ልጁ ወደ ሃይማኖታዊ ሕይወት እንዲያመራ የሚያደርጉ አራት ምልክቶችን ያያል ብሎ ሲነግረው፣ ንጉሱ ጠባቂ ሰራዊቶቹን እንዲህ ዓይነት ነገር እንዳይከሰት ልጁን ከብበው እንዲጠብቁት ነግሯቸዋል፡[31] “ንጉሱም አለ፡- “ዓለምን እንዲተው ልጄ ምንድን ነው የሚያየው?” “አራቱ ምልክቶች፡፡” “የምን አራት፡፡” “የደከመ ሽማግሌ፣ የታመመ ሰው፣ የሞተ ሰው፣ እና ባህታዊ፡፡” “ከዚህን ግዜ ጀምሮ” አለ ንጉሱ “እንዲህ ያለ ሰው ወደ ልጄ እንዳይመጣ አድርጉ፡፡ ቡድሃ መሆን ለልጄ አይጠቅመውም፡፡ ማየት የምመኘው ልጄ ሉዓላዊ ገዢና ባለ ስልጣን ሁኖ ነው …፡፡” እንዲህ ከተናገረ በኋላ ሩብ ሊግ ርቀት የሚያህሉ ጠባቂዎች በአራቱም አቅጣጫ በእያንዳንዳቸው አኖረ፣ እኚህ አራቱ ሰዎች ወደ ልጁ እይታ እንዳይመጡ፡፡” ጃታካ፡፡[32] የነገስታት ዘር፡ እንደ ክሪሽና ጓተማም በቅንጦት ውጥ በቀጥታ የተወለደ የመሳፍንት ልጅ ነው፡፡ ኢየሱስ የዘር ሃረጉ በርቀት ከንጉስ ዳዊት የሚገኝ ሲሆን፣ የተወለደው ግን በድህነት ውስጥ ነው፡፡ እድሜ ዘመን ክንውኖች፡ ኢየሱስ በ 12 ዓመቱ ሙክራብ ውስጥ ያስተማረ፣ የአዲስ ኪዳን አስተምህሮውን በ 30 ዓመቱ የጀመረና፣ በ 33 ዓመቱ የሞተ ሲሆን፤ ጓተማ ግን ከዚህ ጋር ግንኙነት በሌለው መልኩ በ 15 ዓመቱ ትምህርቱን ጨርሶ፣ በ 16 ዓመቱ አግብቶ፣ በ 29 ዓመቱ ባህታዊ ሁኖ፣ አብርሆት በ 35 ዓመቱ አግኝቶ፣ በ 80 ዓመቱ ሙቷል፡፡[33] ስቅላት፡ በየትኛውም ቡድሄዎች ጽሑፎች ጓተማ ተሰቅሏል የሚል ማግኘት አይቻልም፣ ምንም እንኳ ሃያስያን ተሰቅሏል ቢሉም፡፡ እንዲያውም ጓተማ በተፈጥሮአዊ ምክንያት በ 80 ዓመቱ እንደሞተ ነው የሚነግተሩን ዋና ጽሑፎቹ፡፡ ተከታዮቹ ወደ ወንዝ አብረው ተከትለውት መቀመጫ አቅርበውለታል፡ ““መልካም ሁኑና መቀመጫ አሰናዱልኝ … ስለደከጀመኝ ማረፍ እፈልጋለው …፡፡” ከዛም [ቡድሃው] ወደ ጥልቅ ተመስጦ ገባና፣ በአራቱ ጃናዎች በማለፍ ወደ ኒርቫና ገባ፡፡” [34] ትንሳኤ እና እርገት፡ ከሞተ በኋላ የጓተማ አስክሬን ተቃጥሏል፡፡[35] “የተቀደሰውን ሰው ቅሪትንም አቃጠሉ፣ የንጉሰ ነገስቱንም ቅሪት ቢሆን ያደርጉ እንደነበሩት ሁላ፡፡” [36] ጓተማ ኒርቫና ላይ ከመድረሱ በፊት በሞት አልጋው ላይ ሁኖ ሁሉን የተመስጦ ደረጃዎች እንደተሸገረ ይነገራል፡፡ ቡድሄ እምነት መሰረት ኒርቫና[37] አካላዊ ቦታ ሳይሆን፣ አእምሯዊ ሕላዌ ነው፡፡ ክሪሽና ላይ እንዳነሳነው፣ የቡድሃ ወደ ኒርቫና መሸጋገር ከክርስትያን ገነት በእጅጉ ይለያል፡፡ ሃያስያን ስህተት ሁነው ተነጻጻሪ የሚሏቸው፡ በቅርጫት ዳቦ አእላፍን መገበ፡፡ በየትኛውም የቡድሄ ጽሑፍ እንዲህ አድርጓል የሚል የለም፡፡ ተራራ ላይ እንደ ብርሃን ማብራቱ፡፡ ምንም እንኳ መንፈሳዊ አብርሆት ላይ ቢደርስም፣ አካላዊ ለውጥ አላደረገም፡፡ ይህም የሆነው ደግሞ ተራራ ላይ አይደለም፣ ቡድሃ አብርሆቱን ያገኘው ከቦዲ ዛፍ ስር ነው፡፡[38] የእባቡን ጭንቅላት መቀጥቀጥ፡፡ እንደ ክሪሽና በዚህ ርእስ ተጠርቶ አያውቅም፣ ሆኖም ግን በኋላ ላይ በመጡ ጽሑፉች ላይ የእውን እባብ የገደለበት ገጠመኝ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም ግን ቀድመን እንዳየነው ይህ ርእስ ለኢየሱስ የተሰጠው በተምሳሌታዊነቱ ነው፡፡ የድህነት ቃል ኪዳን፡፡ ኢየሱስ የንዋይ ፍቅር እንዴት ከዘልአለማዊ ሕይወት እንደሚያርቅ አስጠንቅቋል እንጂ ሁሉም በድህነት እንዲኖር አላስተማረም፡፡[39] ተመሳሳይ መዓርጎች፡ መልካም እረኛ፣ አናጢ፣ አልፋና ኦሜጋ፣ [የሰዎች] ሃጥያት ተሸካሚ፣ የአማልክት አምላክ፣ ሊቅ፣ የዓለም ብርሃን፣ አዳኝ፣ ዘልአለማዊ ወዘተ.፡፡ ሆኖም ግን ጓተማ አምላክ ነኝ አላለም፣ እኚህን መዓርጎች በእርሱ ላይ ማድረግ ግልጽ ስህተት ነው፡፡ ከኢየሱስ ጋር የተጋራቸው መዓርጎችና ቡድሄ ጽሑፎች ውስጥ ማግኘት የሚቻሉት ጌታ፣ መምህር፣ እና የተቀደሰው የሚሉት ናቸው፡፡ መደምደምያ፡ ቡድሄ ከሂንዴ እምነት ጋር ብዙ ጭብጦችን የሚጋራ በመሆኑ (ከተቀራራቢ ቦታም እንደመመንጨታቸው) በቡድሃ እና ክሪሽና ታሪክ መካከል ይበልጥ መቀራረብን እናገኛለን፣ ከቡድሃ እና ኢየሱስ ይልቅ፡፡ (3) ሆረስ እንደ ግብፅ አንጋረ-ተረት (ሚቶሎጂ)፣ ሆረስ[40] በመጀመርያ የራ[41] እና ሃቶር[42] ልጅ እና የኢሲስ[43] ወንድም/ባል እንደሆነ ይታመን ነበር፡፡ በኋላም እንደ ኦሳይረስ[44] እና ኢሲስ ልጅ ተደርጎ ይወሰድ ጀመር፣ ሃቶርና ኢሲስ እንደ አንድ አካል መወሰድ ሲጀምሩ፡፡ ሆረስ የሰማይ፣ የፀሃይ እና የጨረቃ አምላክ ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን፣ የጭልፊት ራስ ባለው ሰው ነበር ተመስሎ የሚቀርበው፡፡ ድንግል ውልደት፡ የሆረስን ውልደት በተመለከተ ሁለት የተለያዩ ታሪኮች አሉ (ሁለቱም ድንግል ውልደትን አያሳዩም)፡ አንደኛው ግልባጭ፡ ሃቶር የሚልኪ ወይ እናታዊ መገለጫ ነች፣ ሆረስን እንደፀነሰች የተነገረን ሲሆን፣ ባለቤቷ ራ የግብጽ የፀሐይ አምላክ ነው፡፡ ሃቶር (የሰማይ አምላኪቱ) የምትወከለው ወተቷ የሚልኪ ወይን ባመጣችው ላም ነው፡፡ በባለቤቷ ራ ፈቃድ ሆረስን ወለደች፡ “እኔ፣ የቴቤሷ ሃቶር፣ የአማልክታቱ እመቤት …” ይልና በተወሳሰበ ቋንቋ አምላኳ በሴትና በላም መልክ ስጋ መልበሷንና ለአምለኳ መቅረቧን ይናገራል፡፡ የግርጌ ማስታወሻውን ይመልከቱ፡፡[45] ሁለተኛው ግልባጭ፡ የሆረስ እናት ኢሲስ መሆኗን የሚነግረንን ታረክ ስንፈትሽ ደግሞ ኢስስ ድንግል እንዳልነበረች ይነገረናል፣ የኦሳይረስ እመበለት፡፡ ኢሲስ አስማት ተጠቅማ ኦሳይረስን ከሞት አንስታ ገዳዮን የሚበቀል ልጅ እንድትወልድ እንዲገናኛት አድርጋለች፡፡ ከዛም ኢሲስ በሞተው በሏ ዘር ልትፀንስ ችላለች፡፡ እዚህም ድንግል ውልደት አይታይም፡ “ልቡ አርፎ የነበረውን [ኦሳይረስ]፣ [ኢሲስ] አልንቀሳቀስ ያለው ክፍሉን [ብልቱን] እንዲነሳ በማድረግ፣ ከእርሱ ዋና ነገሩን [የዘር ፍሬውን] ወሰደች፣ ከዚህም ወራሽ [ሆረስ] ለማግኘት ቻለች፡፡” እንግሊዘኛውንና ምንጩን ከግርጌ ማስታወሻ ይመልከቱ፡፡[46] የአባት እና ልጅ ውህደት፡ ሃያስያን የክርስትያን ሦስትነት (ምስጢረ ሥላሴ) ከኦሳይረስ፣ ራ፣ እና ሆረስ በዋናነት ሲታይ እንደ አንድ አምላክ ሊታዩ ስለሚችሉ ከዚህ ጭብጥ የተወሰደ ነው ይላሉ፡፡ ሆረስ ከኦሳይረስ ሞት በኋላ ስለተወለደ የሆረስ ትንሳኤ፣ ወይም ዳግም መፈጠር ነው እየተባለ ሊታመን ችሏል፡ “በሆረስ ስም የሚበቀልል፣ የአባቱን የተበቀለ፡፡” [47] ክፍለ ዘመናት ባለፉ ቁጥር ግብጻውያን ኦሳይረስ እና ሆረስ አንድ እንደሆኑ አድርገው እየወሰዷቸው መጥተዋል፡፡ ሆኖም ግን ልጅ-እንደ-አባት ንጽጽር ሃቶር ወደ ኢሲስ የተቀየረችበትን ታሪካዊ የለውጥ ሂደትን ነው የሚያሳየው እንጂ ሚስጥረ ሥላሴን አያሳይም፡፡ መጀመርያ ሆረስ የራ ልጅ ሁኖ እናየዋለን፣ ከዛ ከራ ጋር እኩል ይሆናል፣ ከዛም ራ አንድ የሆረስ ገጽታ ሁኖ መታየት ይጀምራል፡፡ ልክ እንደ ሃቶር እና ኢሲስ አንዱ አካል ከሌላው ጋር መደባለቁን ነው የምናየው፡፡ በግብጽ አንጋረ-ተረት እያንዳንዱ አምላክ የየራሱ ጅማሮ አለው፣ ከሌላው አምላክ በመወለድ፡፡ በክርስትና ስነመለኮት አብ እና ወልድ ሁሌም አንድ ሁነው ኑረዋል፣ ሁለቱም መጀመርያም መጨረሻም የላቸውም፡፡ የኢየሱስ ውልደት መፈጠሩን የሚያሳይ አይደለም - ስጋ ለብሶ መምጣቱን ብቻ እንጂ፡፡ በተጨማሪም የአባት-ልጅ ጭብጥ በመጀመርያው ክፍለ ዘመን ክርስትያኖች የተፈጠረ አይደለም፡፡ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነ መሲሕ እንደሚወለድ ከውልደቱ 1,000 ዓመት በፊት ትንቢቶች በብሉይ ኪዳይ ሰፍረው ይገኛሉ፡፡[48] ስቅለት እና ትንሳኤ፡ ሆረስ ተሰቅሏል የሚል አንዳችም መረጃ የለም፣ ሞተ የሚለው ቀርቶ፡፡ ሆረስ ከሞት እንደተነሳ አድርገን ልናቀርብ የምንችለው የሆረስና ኦሳይረስ መቀላቀልን ከወሰድን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት መላምት ደግሞ መውጫ ከሌለው አዙሪት ይከታል፣ ይህን ልብ ያሉ የቀድሞ ግብጾች በኋላ ላይ ግጭቱን ለማስታረቅ እምነታቸውን አድሰውታል፡፡ በግብፅ ተረት ኦሳይረስ ውግያ በገጠሙ ግዜ በሴት ሰውነቱ እንዲከፋፈል ተደርጓል ወይም በሳጥን ታሽጎ አባይ ወንዝ ውስጥ ተጥሏል፡፡ ከዛም ኢሲስ የኦሳይረስን ሰውነት መልሳ ገጣጥማ ኦሳይረስን ወደ ሕይወት መልሳ ሞቱን የሚበቀል ልጅ እንዲያስፀንሳት አደረገች (በትክክለኛው ወደ ሕይወት ሙሉ ለሙሉ አልተመለሰም ነበር ወደ ሕያዋን ዓለም መመለስ ተከልክሎ ነበርና)፡፡[49] “[ሴት] ቅርጽ የወጣለትና የተዋበ ሳጥን አመጣ፣ በንጉሱ ሰውነት ልክ ያሰራውን …፡፡ ሴትም ሰውነቱ ከዚህች ሳጥን ጋር ልክ ለሆነው ሳጥኑን እንደሚሰጥ ተናገረ …፡፡ ኦሳይረስም ወደ ፊት መጣ፡፡ በሳጥኑ ውስጥ ተኛ፣ በሁሉም በኩል ልክ ሆነው፡፡ ይህን አሸናፊነቱን ግን መጥፊያው በነበረው በዛ ጭለማ ሰዓት በታላቅ ዋጋ ነበር ያገኘው፡፡ ሰውነቱን ከማንሳቱ በፊት የሴት ክፉ ተከታዮች በድንገት ወደፊት መጥተው መቆለፊያውን ዘጉት፣ በፍጥነትም በሚስማር መትተው በእርሳስ አሸጉት፡፡ እናም እጅግ የተዋበው ሳጥን የሕይወት ትንፋሽ ለተለየችው መልካሙ ንጉስ መቀበርያ ሳጥን ሆነ፡፡” [50] ታህሳስ (ዲሰምበር) 25 ተወለደ፡ አሁንም በድጋሚ ይህ እለት ከኢየሱስ ልደት ጋር ግንኙነት የሌለው መሆኑን በመገንዘብ ነው የምንቀጥለው፡፡ የሆረስ ልደት በእውነቱ ይከበር የነበረው በኮኢያለክ[51] (ኦክቶበር/ኖቨምበር) ወር ውስጥ ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሃያስያን በዊንተር ሶሊስታይስ ነው የተወለደው ቢሉም፣ ይህ የሚያሳየው ከአረመኔዎቹ እምነት ሶሊስታሶችን እንደ ቅዱስ አድርገው ከሚወስዱት ጋር ያለውን ትስስር ብቻ ነው የሚያሳው፡፡[52] አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት፡ ከላይ ሲታይ ይህ ንጽጽር ትክክለኛ ይመስላል፣ ሆኖም ግን የሆረስ “ደቀ መዛሙርትን” ቀረብ ብለን ስናያቸው ደቀ መዛሙርት መሆናቸው ይቀርና የመግብተ አዋርህ (ዞድያክ ሳይንስ) አስራ ሁለቱ ምልክቶች ሁነው እናገኛቸዋለን፣ የሰማይ አምላኩ፡፡ አሁንም በዚህ ማሳሳቻ ዙርያ ከዚህ ቀደም ያቀረብኩት በስፋት የሚዳስሰውን ጽሑፍ ይመልከቱ፡፡[53] የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የእውን የሰው ልጆች የሆኑ፣ በሕይወት ኑረው የሞቱ፣ ጽሑፎቻቸው እስከዛሬ ድረስ የሚነበቡ፣ ሕይወት ታሪካቸው በታሪክ ጸሐፍያን የተመዘገበ ሰዎች ናቸው፡፡ የሆረስ “ደቀ መዛሙርት” የሚሏቸው በእውን የከዋክብት ስብስብ ምልክቶች ስለሆኑ የጻፉትና ያስፋፉት የሆረስ አስተምህሮ የላቸውም፡፡ አስራ ሁለት የመግብተ አዋርህ (እና አስራ ሁለት ወራት [በግሪጎራውያን ቀመር]) መኖሩ ከኢየሱስ አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ጋር መመሳሰሉ የንጽጽር ዋጋ አይኖረውም፡፡ [በአስራ ሁለት ጥማር የሚመጡ ሌሎች ቡዙ ነገሮችን እናውቃለንና፡፡] የተራራው ክስተት፡ ሃያስን ኢየሱስና ሆረስ በሚነጻጸር መልኩ ሁለቱም ተራራላ ጠላታቸውን ተጋፍጠዋል ይላሉ፡፡ ይህን እያንዳንዱ ሁኔታ ምን እንደሚመስል ከመዘርዘር የሁለቱን የተራራ ክስተት የሚያሳዩ ጥቅሶቻቸውን በማስቀመጥ አንባቢው ግልጽ ልዩነታቸውን እንዲፈርድ ይደረጋል፡ ኢየሱስ፡ በምድረ በዳው ኢየሱስ ጾሙን ከጨረሰ በኋላ ሰይጣን ኢየሱስን ከሰገደለት የዓለምን ሁሉ ዘውድ እንደሚሰጠው እየነገረ ይፈትነዋል፣ ኢየሱስ ግን አሸነፈው፡፡[54] ሆረስ፡ በጦርነት ግዜ ሴት የሆረስን ዓይን ሲያወጣ፣ ሆረስ ደግሞ የሴትን (አንዳንዴ ሴዝ ይባላል) ቆለጥ ይገነጥላል፡፡ በኋላ ላይ የበላይነቱን ለማሳየት ሴዝ ከሆረስ ጋር ወሲብ ሊፈጽም ያነሳሳል፡፡ ሆረስ የሴዝን የዘር ፈሳሽ በእጁ ይዞ በቅርብ ወዳለው ወንዝ ወረወረው፡፡ በኋላ ሆረስ የራሱን ዘር አፍስሶ በሰላጣ አድርጎ ለሴዝ ያበላዋል፡፡ ሁለቱም ሆረስና ሴዝ ግብጽን ለመግዛት ይገባኛል ብለው እንዲፈረድላቸው አማልክቱ ፊት ይቆማሉ፡፡ ሴዝ ሆረስ ላይ የበላይነት አለኝ ሲል የዘር ፈሳሹ ወንዝ ውስጥ ይገኛል፡፡ ሆረስ የበላይ እንደሆነ ሲፈተሽ የዘር ፈሳሹ ሴዝ ውስጥ ይገኛል፣ ስለዚህም ግብጽን እንዲገዛ ተሰጠው፡፡[55] ተጠራጣሪው እንዲህ ሊጠይቅ ይችላል፡ በሴት እና በሰይጣን ነሃከል ያለው የስም መመሳሰል ዋጋ አይኖረውም? ምላሹም፡ ሴት ተለዋዋጭ ስሞች አሉት ሴዝ፣ ሱቴክ፣ ሰተሽ እና ሰተህ፡፡ ሴት የሚለው ቃል ዋና ፍቺው የሚደንቅ፣ ወይም የማይነቃነቅ አምድ እንደማለት ነው፡፡ ቃሉ ላይ ሲቀያየር የሚከተለውን ፍቺ ይሰጣል ግርማዊ፣ የበላይ እና በረሃ ማለት ነው፡፡ ሰይጣን የሚለው ከሴማዊ ስር የመጣ ሲሆን፣ ተቃውሞን ይወክላል፡፡ ከመውደቁ በፊት የሰይጣን የመጀመርያ ስያሜ ሉሲፈር ወይም የብርሃን መልአክ ማለት ነው፡፡ ሰይጣን የሚለው ቃል ባላንጣ የሚወክል ሲሆን፣ ይህም ማንነቱን ይወክላል፡፡ ሱለቱም ቃላት አንድ ዓይነት ፊደሎች ቢጋሩም ትርጓሜያቸው ግን ለየቅል ነው፡፡ የፊደላቱ አቀማመጥ ከዋና ስር ቃላቶች የመጡ ሲሆን ማንነታቸውን የሚወክሉ የተለያየ ፍቺ ያላቸው ናቸው፡፡[56] ተመሳሳይ መዓረጎች፡ ሃያስያን ሆረስ እንደ ኢየሱስ ተመሳሳይ መዓረጎች ለምሳሌ መሲሕ፣ አዳኝ፣ የሰው ልጅ፣ መልካም እረኛ፣ የእግዚአብሔር በግ፣ መንገድ፣ እውነት፣ ብርሃን፣ ሕያው ቃል የሚሉ ነበሩት ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን እኚህ መዓረጎች ሆረስን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋሉበት አንዲትም ማስረጃ የለም፡፡ በተለይ ዋና መነሻው እብራይስጣዊ ጭብጥ የሆነው መሲህ የሚለው ይገኛል ማለታቸው የማይታመን ነው፡፡ መደምደምያ፡ የትኛውም ተገቢ ያልሆነ ማነጻጸርያ እንኳ ተጠቅሞ ቢቀርብ ሆረስ እና ኢየሱስ ምንም ተመሳሳይነት እንደሌላቸው ለማየት ችለናል፡፡ (4) ዞራስተር ዞራስተር ኢራናዊ ነብይ ሲሆን የዞራስትራዊነት መስራች ነው፡፡[57] የኖረበት ዘመን በአብዩ የሚያከራክር ሲሆን በስፋት ግን በንጉስ ሂስታስፔስ[58] ዘመን እንደኖረ ይታመናል፣ ይህም በ 6ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓለም የኖረ ያደርገዋል፡፡ በመላው አቬስታ[59] በእነኚህ ሁለት ሰዎች ነሃከል የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን የሚያሳ ማስረጃዎች ሞልተዋል፡፡አንድ ምሳሌ እንደሚከተለው ይገኛል፡ ““አምላክ የምፈራ ሰው ነኝ፣ የጽድቅ/ምርቃት ቃላትንም ነው የምናገረው” አለ ዛራቱስትራ ለወጣቱ ንጉስ ቪሽታስፓ “ኦ ወጣቱ ንጉስ ቪሽታስፓ! [ባርኬሃለው]” ቪሽታስፕ ያሽት፡፡[60] ድንግል ውልደት፡ በየትኛውም የዞራስትራዊ ጽሑፍ ድንግል ውልደትን የሚያሳ ጽሑፍ የለም፣ የውልደቱ ሁኔታም ከኢየሱስ ጋር የሚገናኝ አንዳችም ነጥብ የለውም፡፡ ስለውልደቱ የተሰጡት በእውን በጽሑፍ የሰፈሩት የዋና ቅጂ ማስረጃዎች እንደሚከተሉት ናቸው፡ አንደኛው ግልባጭ፡ የዞራስተር ወላጆች (ዱክዳኡብ እና ፖኡሩሻስፕ) እንደማንኛውም ሰው በትዳር የሚኖሩና ልጃቸውንም በተፈጥሯዊ መንገድ የጸነሱ ናቸው፡፡ ዞራስተር እንደተወለደ እንደሳቀ ይነገራል፣ በተጨማሪም የሚታይ የብርሃን በዙርያው ነበረው፡ “[ዞራስተር] ወደ ትውልዱ የመጣው በአባቱ ፖኡሩሻስፕ እና በእናቱ ዱክዳኡብ ነው፡፡ እየተወለደም እያለ እና በሕይወት ዘመኑ እንጽብራቂ፣ ብርሃን፣ እና ድምቀት ካለበት ያወጣ ነበር …፡፡” ዴንካርድ፡፡[61] ሁለተኛው ግልባጭ፡ በኋላ ላይ በዞራስትራውያን ተከታዮች ማሳመርያ ተጨምሮበት መጣ፡፡ በዞራስትራውያን ዋናው አምላክ አሁራ ማዝዳ[62] የዞራስተርን ነብስ በቅዱስ ሃኦማ[63] ተክል ውስጥ ያስገባዋል፣ ከዛም በዚህ ተክል ወተት ዞራስተር ተወለደ፡፡ በምድረ በዳ ተፈተነ፡ ዞራስተርም እምነቱን እንዲተውና በምድር ላይ በሁሉ አገሮች ላይ ስልጣን እንዲያገኝ በማለት በክፉ መንፈስ ተፈትኗል፡፡ ሆኖም ግን ይህ ታሪክ የሚገኘው በቨንዲዳድ ላይ ነው፣ ይህ የዞራስትራውያን ጽሑፍ የክፉ መናፍስትን በተመለከተ ያለውን ሕጎች የያዘ ሲሆን የተጻፈው ደግሞ ከ 250 – 650 ዓ.ም ነው (ከክርስቶስ ሕይወት ከዘመናት በኋላ፡ “እንደገና የክፉው ዓለም ፈጣሪ፣ አንግራ ማኢንዩ እንዲህ አለው፡ “ፍጥረቶቼን አታጥፋ፣ ኦ ቅዱስ ዛራቱስቱራ …፡፡ የማዝዳ አምላኪዎችን መልካሙን ሃይማኖት ተወው እና እጅጉኑ የሚመች ነገር የሆነ … የሃገሮች ሁሉ ገዢ ትሆናለህ፡፡”” ቨንዲዳድ ፋርጋድ፡፡[64] የሴቲቱ ዘር፡ በብሉይ ኪዳን የዘው ልጆች አዳኝ የሴቲቱ ዘር እንደሚወለድ ይናገራል፡፡ ሃያስያን ይህ ጭብጥ የሴቲቱ ዘር ከሚባለው የስሙ ትርጓሜ የሆነው ከዞራስተር የተሰረቀ ነው ይላሉ፡፡ ይህን ሃሳብ በቁም ነገር የመረመረው የለም ምክንያቱም ዞራስተር የሚለው ስያሜ ከጥንት ሁለት የኢራን ቃላቶች የተሰራ ነውና፡ ዛሬታ (ሽማግሌ፣ ሀይል የሚያንሰው) እና አስትራ (ግመል) ማለት ነው፡፡ ዋናው የፋርስ ስሙ ዛራቱስትራ (ዞራስተር የግሪክ/የእንግሊዘኛ ፍቺ ነው) በቀጥታ ሲተረጎም ያረጁ የደከሙ ግመሎች ባለቤት ማለት ነው፡፡[65] በተጨማሪም ዞራስተር ቃል ስጋ ሆነ እና ሕያው ቃል ተብሏል ቢባልም ማስረጃ የለውም፡፡ ስብከቱን በ 30 ዓመቱ ጀመረ፡ እንደ ክርስቶስ ዞራስተር ማስተማር በ 30 ዓመቱ እንደጀመረ ይታመን ነበር፡፡ ምንም እንኳ ዞራስተር እራሱን ካገለለበት ቦታ ለማስተማር የወጣው በ 30 ዓመቱ ቢሆንም፣ አስተምህሮው በንጉሱ ቪስታሽፓ ተቀባይነትን እስኪያገኝ፣ 12 ዓመታት እስኪያልፉ ድረስ ተደማጭነት አልነበረውም፡፡ ኢየሱስ ግን ተከታዮችን ወድያው ሊያፈራ ችሏል፡፡ ኢየሱስ በ 33 ዓመቱ ሲሆን የተገደለው ዞራስተር ግን በ 77 ዓመቱ ነው የተገደለው፡፡ በተጨማሪም ግን ልብ ማከት ያለብን እኚህ የዞራስተር ሕይወት ታሪክ እውነታዎች እስከ 225 ዓ.ም (ከክርስትና 200 ዓመት በኋላ) የተጻፉ ናቸው፡፡ ስርዓተ ቁርባን፡ ሃያስያን የዳቦ-ወይን ቅዱስ ቁርባን ከዞራስተር የመነጨ ነው ቢሉም እንዲህ ያለው ስርዓት የትም ታይቶ አያውቅም፡፡ ቀሳውስቱ የሥጋ፣ አበባ፣ ወተት፣ ዳቦ፣ ፍራፍሬ፣ እና ቅዱስ ውሃ መስዋእቶችን ቢቀበሉም በዞራስትራውያን የሚከናውን ተምሳሌታዊ የሆነ የቁርባን ስርዓት አልነበራቸውም፡፡ ሃኦማ ተክል የሚጠጡት ፈሳሽ ነበራቸው፣ ሆኖም ግን ይህ በክርስትያኖች የሚከበረውን የሥጋ ወደሙ የመቀበል ዓይነት ፋይዳ አልነበረውም፡፡[66] ሐይማኖታዊ አስተምሆሮዎች፡ ሃያስያን በዞራስትራውያን እና ክርስትና አስተምህሮዎች መካከል መመሳሰል አለ ይላሉ፡፡ እስኪፈተሸ ድረስም ከላይ ሲታዩ ያሉ መስለው ይታያሉ፡ ሁለቱም በመልካም እና ክፉ መሃከል የሚደረግ መንፈሳዊ ውግያን ያስተምራሉ፡፡ ይህ ልክ ነው፣ ግን ደግሞ ይህ ለሁሉም እምነቶች ልክ ነው፡፡ በዞራስትራውያን ዋናው አምላክ አሁራ ማዝዳ ሲሆን በይሁዴ-ክርስትና እምነት ብቸኛው አምላክ እግዚአብሔር (አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ) ነው፡፡ በዞራስትራውያን ባላንጣ አንግራ ማኢንዩ ነው፣ በክርስትና ግን ሰይጣን ነው፡፡ በዋናነት ግን ዞራስትራዊነት ጥዳዊነትን ያስተምራል፣ ማለትም መልካሙ አምላክና ክፉው አምላክ እኩል ፈጣሪዎች አድርጎ ይስላቸዋል፣ ይህ በሁሉ የምስራቅ እምነቶች የሚንጸባረቅ ነው በሩቅ ምስራቆቹ ዪን ያንግ የሚሉት ተጠላልፈው ክብ ውስጥ በሚሳሉት ነጭና ጥቁር የሚወክሉት፤ በይሁዴዎች የክህደት ካባላ ትምህርት በተጠላለፉት ሁለት ትሪያንግሎች የሚወክሉት፤ በግኖስጢሳውያን ከጥንታዊ የግብጽ አስተምህሮ የወሰዱት በ “ቶ” ቅርጽ የሚወክሉት፤ በፍሪሜሶኖች በባለ ሁለት ራስ ንስር የሚወክሉት የጥንዳዊነት አስተምህሮ ሲሆን፤ ሁለቱ ተቃራኒ ጉልበቶች እኩል ናቸው ሰው ከመረጠው ጋር መገናኘት ይችላል የሚል አስተምህሮ ነው፡፡ በክርስትና ግን ሰይጣናዊው ክፉው በመልካሙ እግዚአብሔር ፈቃድ ስር ነው፣ ክፉውም ዘልአለማዊ አይደለም፡፡ ድህነት / መዳን፡፡ ዞራስትራዊነት በመጨረሻው ፍርድ ሁሉም ሰው እንደየስራው ይፈረድበታል ይላል፡፡ ክርስትና በተጨማሪም ክርስቶስን መቀበልና ባለመቀበልም ይፈረድባቸዋል፡፡ ፍርድ፡፡ ዞራስትራዊነት ሁሉም ሰዎች በመጨረሻ ይድናሉ ይላል፡፡ ክርስትና የኃጥአን እጣ ፈንታ ዘልአለማዊ ነው ይላል፡፡ አንድ አምላክ፡፡ ዞራስተር በመጀመርያ አንድ አምላክ ተቀበሉ ብሎ ያስተማረ ሲሆን የዞራስተር ቀሳውስት በኋላ ላይ ሌሎች አማልክት ጨመሩ፡፡ ሁሉም ሰዎች ይነሳሉ፡፡ ከዘመነ ፍጻሜ ላይ ሁሉም ሰው ይነሳል ብሎ ዞራስተር ያስተምራል፡፡ ክርስትናም እንዲህ ያስተምራል፣ ይህ ግን የሚሆነው ለፍርድ ነው፡፡ ለሰዎች ሃጥያት ሲል ነበር የተገደለው፡ ዞራስተር በ 77 ዓመቱ በቤተ አምልኮው መሰውያ ላይ በወራሪ ሃይሎች በሆኑት ቱራኒ ወራሪዎች ነበር የተገደለው (ምንም እንኳ ይህ የሚያጠያይቅ ታሪክ ቢሆንም)፡፡ የሆነው ሁኖ ሞቱ ለሃጠያት ማስተሰርያ ነው የሚል የትም ቦታ የተጻፈ የለም፡፡ መደምደምያ፡ አብዛኞቹ የዞራስትራዊ ጽሑፎች የተጻፉት ከክርስትና በኋላ ክፍለ ዘመናት ከተቆጠሩ በኋላ ነው፡፡ ከኢየሱስ ሕይወት ዘመን በፊት የተጻፉ የዞራስተር ሕይወት ታሪኮች (ጋታዎቹ[67]) የያዙት ነገር ግልጽ ያልሆኑ ቅኔያዊ ጽሑፎች ሲሆኑ ስለ ሕይወቱ ብዙም የሚሉት የላቸውም፡፡ በኋላ ላይ ከእርሱ ጋር የተያያዙት ድንቅ ክስተቶች፣ በዞራስተራውያን ቀሳውስት የሐይማኖቱን ሳቢነት ለመጨመር የታከሉ ናቸው፡፡ (5) ሚትራስ ሚትራስ የሚትራስነት[68] ሃይማኖት ዋናው አምላክ ነው (ከሚትራ የፐርሺያው ጦረኛው መልአክ ጋር እንዳያሳስተን)፡፡ የሚትራስ ትክክለኛ አፈ ታሪክን ማወቅ አይቻልም፣ አብዛኞቹ ዋና ጽሑፎች የጠፉ ሲሆኑ የቀሩት ብጥስጣሽ ናቸው፡፡ ያሉት ማስረጃዎች ስነ ጥበባዊ ቅርፃ ቅርፆች ናቸው፡፡ ለዚህ ፍተሻ የሮማውያንን ሚትራስነት እንዳስሳለን፣ ሃያስያን ይህኛው ሚትራስ ነው ለኢየሱስ ታሪክ ምንጭ ሆነ ስለሚሉት (ምንም እንኳ በቀላሉ ያሉት ዋና ማስረጃዎች ከክርስትና በኋላ የተሰሩ መሆናቸውን በማሳየት መከራከርያውን ማፍረስ ቢቻልም)፡፡ በተጨማሪም የሮማ ሚትራስነት የመጣው ከእብራይስጥ የመሲሃዊ ትንቢቶች ክፍለ ዘመናት የተፈጠረ ነው፡፡[69] ልብ ይባል፡ በሚትራይዝም ቀድሞ ተጠቃሽ የሆነው ተመራማሪ ፍራንዝ ኩሞንት የፐርሺያው ሚትራ እና የሚትራስነት ሚትራስ አንድ የሆኑ አድርጎ ያቀርባቸው ነበር፡፡ አብዛኛዎቹ ምርምሮቹ በ1800ዎቹ የተጠናቀሩ ሲሆን የሞተውን የሚትራስነት ሃይማኖት ለመመርመር የመጀመርያው ሰው የነበረ በመሆኑ ግኝቶቹ ያለተቀናቃኝ እንደ ትክክል ተወስደው ነበር፡፡ የ 20ኛው ክ/ዘመን ጽሑፎችን ካየን የኩሞንት ግኝቶች ያለ ጥያቄ እንደ እውነት ይቀርቡ እንደ ነበር ማንበብ እንችላለን፡፡ ቆይተው በኋላ የመጡ ታሪክ ተመራማሪዎችና ስነ ቅርስ አጥኚዎች (አርኪኦሎጂስቶች) ባደረጓቸው ጥናቶች ነበር የኩሞንት ንድፈ ሃሳቦች ስህተት መሆናቸውን ያሳዩት፡፡ ይን ለማየት በ1911 የተጻፈውን ኢሳይክሎፒድያ ብሪታኒካንና[70] በቅርቡ የወጡ ምርምሮችን ማነጻጸር ይቻላል፡፡ በዋሻ ውስጥ ተወለደ፡ ክርስቶስ ዋሻ ውስጥ ያለ የከብቶች መቆያ ውስጥ እንኳ ቢወለድ ከሚትራስ ጋር አንድ አያደርገውም ሚትራስ ከዋሻ አልተወለደምና፣ የተወለደው ከድንጋይ ነው ወይም ከድንጋይ ነው የተገኘው፡፡ የታህሳስ ዲሰምበር ውልደት፡ ብዙ በዓሎች ከዊንተር ሶሊስታይስ ጋር እንዲገጥም ወደዚህ ወር ተጨፍልቀዋል፡፡ ገናም በዲሰምበር 25 እንዲከበር ያደረጉት በዚል ልማዳቸው ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ይህን እለት የሚጠቅስ ጽሑፍ የለም፡፡ ስለዚህ አሁንም በድጋ ይህ ነጥብ ዋጋ እንደሌለው እናስታውስ፡፡[71] እረኞች በውልደቱ ነበሩ፡ ከሁሉ የቀደመው የሚትራስ ውልደትን የሚያሳይ ማስረጃ ያለው ከአለት ሲፈልቅ የሚያሳየው ቅርጽ ነው፣ በቅርጹ እረኞች የሚመስሉ ሰዎች ሲያግዙት ይታያል (ይህ ጥያቄ የሚያስጭር ነው ምክንያቱም ውልደቱ ከሰዎች መፈጠር የቀደመ ነው ተብሎ ይታሰባልና!)፡፡ ሆኖም ግን ይህ ነጥብ በኋላ ላይ ይህን ግጭት ልብ ባላሉ ሰዎች የተጨመረ መሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ይህ ቅርጽ ከልደተ ክርስቶስ በኋላ በ4ኛው ክ/ዘመን የተሰራ ነው፡፡[72] ድንግል ውልደት፡ በሚትራስነት እምነት ድንግል ውልደት የሚባል ነገር የለም፡፡ ቀደምት ቅርጾች ላይ ሚትራስ ከአለት ሲወጣ በግልጽ ያሳያሉ (ባቀረብናቸው ሶስት ስእሎች ላይ እንደሚታየው፡ ከላይ ወደታች ሦስተኛውን ይመልከቱ)፡፡ አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት፡ ሚትራስ አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት አልነበሩትም፣ ከዚህ የማገናኘት ሙከራ ጋር በተያያዘ አንድ የማይመስል ነጥብ መጥቀስ ይቻላል፡፡ በቀረቡት ስእሎች በሁለቱ ላይ (አንደኛውና ሦስተኛው ላይ) ሚትራስ በአስራ ሁለቱ የመግብተ አዋርሕ ምልክቶች ተከቧል፡፡ ሃያስያን እኚህን የመግብተ አዋርህ ምልክቶች ሞራቸውን ተከትለው ነው አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት ጋር ሊያገናኙ የሚጥሩት፡፡ ይህ ከስነ ከዋክብት ጋር የማገናኘት ጥረት፡ የከሰረው የፀሃይ አምልኮንና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ በሚለው ጽሑፍ ተዳስሷል፡፡[73] አንዳንዶች አቋማቸው ተቀባይነት እንዲኖረው ሲሉ የተጋለጠውን የፍራንዝ ኩሞንት ንድፈ ሃሳብን ይጠቀማሉ፡ ምስሎቹ የሚትራስ አስራ ሁለት ደቀ መዛሙርት የመግብተ አዋርህ ምልክቶች ያለው ልብስ አድርገው ነው ይላሉ፡፡ ዋና ቅርጾቹ ላይ ምንም ዓይነት ጽሑፍ የሌለ እንደመሆኑ ይህን ሃሳብ ለከየት እንዳመጡት አይገባም፡፡ (የላይኛውን ምስል ይመልከቱ፡፡) ታላቅ አስተማሪ፡ በሚትራስ ጽሁፎች ውስጥ እየተዟዟረ የሚያስተምር ስለመሆኑ የሚገልጽ ጽሑፍ የለም፡፡ የሆነው ሁኖ የሰው ልጆች ከአማልክቶች ጥበብ መቀበላቸውን የሚናገሩ እምነቶች ብዙ እንደመሆናቸው ይህ ነጥብ ዋጋ አይኖረውም፡፡ ሐጥያት ማስተሰረይ፡ ሚትራስ ሐጥያት አስተሰርይዋል የሚለው ነበገር እንዴት የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ይህ ነገር በየትኛው ጽሑፍ ማስረጃ የማይገኝ ነው፡፡ ሚትራስ ሕይወት ለመፍጠር ሲል ሙክት በሬ መስዋእት ሲያደርግ የሚያሳይ ማስረጃ አለ፣ ይህ ግን በገዛ ደሙ ሐጥያት ማስተሰረይን አያሳይም፡፡ አንዳንዶች ሙክቱንና ሚትራስን አንድ እንደሆኑ አድርገው ለማቅረብ ይሞክራሉ ይህ ግን አብዛኞቹ የሚትራስ ተመራማሪዎች አይቀበሉትም፡፡ የመጨረሻ እራት፡ ሚትራስ ግብዣ ላይተገኝቶ የሚያሳዩ ሁለት ቅርጾች አሉ፡፡ የመጀመርያው ከሙክቶ መስዋእት ከተደረገ በኋላ ሚትራስ ከሂሎስ ጋር አብረው ሲበሉ የሚያሳይ ነው፡፡ ሌላኛው ሚትራስ ወደ ገነት ከአማልክቱ ጋር ለመሆን ከመሄዱ በፊት ከፀሐይ ጋር ሲመገብ ያሳያል፡፡ ሆኖም ግን በአካባቢው ለማይታዩ (ለምናባዊ) ደቀ መዛሙርቱ ወጣ ያለ ነገር ይናገራል፡ “ከእኔ ከእርሱ ጋር እርሱ ከእኔ ጋር አንድ ይሆን ዘንድ ከሥጋዬ የማይበላና ከደሜም የማይጠጣ አይድንም፡፡” ሆኖም ግን ይህ ጥቅስ በኋላ ላይ በመካከለኛው ዘመን የተጨመረ ሲሆን ሚትራስ እንደተናገረውም አልተጻፈም! ስቅላት፡ ሃያስያን ሚትራስ ተሰቅሏል ቢሉም ይህን የሚያሳይ ቅርጽም ሆነ ጽሑፍ ግን የለም፡፡ እንዲያውም ስቅላት ይቅርና የመሞት ነገር ከሚትራስ ጋር የሚያያዝ የለም፡፡ ዋና ማስረጃቹ ምድራዊ ተልእኮዎቹን ጨርሶ በሰረገላ በሕይወቱና በመልካ ጤና እንደተወሰደ ነው የሚያሳዩት፡፡ እሁድን አውደ ዓመት፡ ይህ ቢያንስ ለሮማ ሚትራስነት ትክክለኛ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሁሉም ሃይማኖቶች ቅዳሜና እሁድን እንደበዓል የሚያስቡ እንደመሆናቸው የመገጣጠም 50/50 አጋጣሚ አለው፣ ደግሞም በሳምት ካሉት ቀናት ውስጥ 1/7 እድል አለው፡፡ ሆኖም ግን ክርስትያኖች ከቅዳሜ በተጨማሪ እሁድን እንደ በዓል የጨመሩት እሁድ በአዲስ ኪዳን በተሰራባት ተአምራትና የክርስቶስ ትንሳኤም በመሆኗ ነው፡፡ ተመሳሳይ መዓረጎች፡ አንዳንድ ንጽጽሮች ቢገኙም፣ ሃያስያኑ የሚያቀርቡት ንጽጽር ግን ያላግባብ ከዋናው ነጥብ የተለጠጡ ናቸው፣ በቀጥታ አንድ አይነት ቃላት ሃያስያኑ እንደሚሉት የሉም፡፡ ከስር በተደጋጋሚ የሚነሱና ስህተትየሆኑትን እናያለን፡ አዳኝ፣ መሲህ፡፡ ሚትራስ በእነዚህ ፍጹም ተጠርቶ አያውቅም፡፡ እንዲህ ዓይነት ዓላማ ሳይኖረው እንዴት ነው የሚጠራው እንዲህ ተብሎ? መሲህ[74] የእብራይስጥ ቃል ሲሆን ይህን ከሚትራስ ጋር የማገናኘቱ ሙከራ ጥያቄ ያስጭራል፡፡ የእግዚአብሔር በግ፣ መልካም እረኛ፡፡ ሃያስያን መስዋእት ያደረገውን ሙክት ይዞ የተቀረጸውን ለዚህ ማስረጃ አድርገው ያቀርቡታል፣ ይህ ግን ወለፈንዴ ነው፣ ሙክቱ መስዋእት ተደርጓልና፡፡ በተጨማሪም ሚታራዊነት ከመፈጠሩ በፊት በብሉይ ኪዳን ስለ በግ እና እረኛ ተጽፏል፡፡ የአምላክ ልጅ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የለም ሆኖም ግን ለሃያስያኑ በነጻ እንደምርቃት እሺ እንበላቸው፣ ሚትራስ የአሁራ ማዝዳ ልጅ መሆኑን ነው የሚሉ ከሆነ፡፡ መንገድ፣ እውነት እና ብርሃን፣ የዓለም ብርሃን፡፡ እንዲህ ያለው ስም የለውም ሆኖም ግን ተዋጊው የብርሃን መልአክ የሚል ማግኘት ተችሏል ይህ ግን የኢራኑ ሚትራስ ነው እንጂ የሮማው ሚትራስ አይደለም፡፡ አንበሳ፡፡ አሁንም ቃል በቃል አንድ ባይሆንም ንጽጽር አለ፣ የሰማይ አንበሳ ተብሏል ከመግበተ አዋርህ ምልክት የሊዮ (አንበሳ ኮከብ) ጋር በማያያዝ ነው ግን፡፡ አሁንም ግን ልክ በግ እንደሚለው ከብሉይ ኪዳን ላይ ሚትራስነት ከመፈጠሩ በፊት ነበር የይሁዳ አንበሳ የሚለው ጥቅም ላይ የዋለው፡፡ ሕያው ቃል፡፡ ሚትራስ አንዳንዴ ሎጎስ ይባላል ይህም ቃል ማለት ነው፣ ሆኖም ግን ሕያው ቃል ግን ተብሎ አያውቅም፡፡ አስታራቂ፡፡ ሚትራስ በመልካ እና ክፉ መሃከል አስታራቂ ነበር ተደርጎ የተቀረጸው፣ ሆኖም ግን ኢየሱስ አስታራቂ የሆነው በእግዚአብሔር እና ሰው መሃከል ነው፡፡ ስነ መለኮታዊ ንጽጽር፡ በአብዛኞቹ እምነቶች አንድ ሊሆኑ የሚችሉ ነጥቦችን አቅርቢያለው፡፡ የተሻለ አርእስት ስላጣሁ ግልጽ የሆነውን ማስቀመጥ ብለነዋ፡ 1. ሚትራስነት በተከታዮቹ መሃከል ጠንካራ የጋራነት ስሜት ነበር፡፡ (በነገራችን ላይ አባል እንዲሆኑ ወንዶች ብቻ ነበር የሚፈቀድላቸው፡፡) 2. ሚትራስነት የሰው ነፍስ ዘልአለማዊ መሆኑን ያስተምራል (ሚትራስነትን የቀደመው በኦሪት ግዜ ይሁዴ እንደዛው ነበር የሚያስተምረው፡፡) 3. ሚትራስነት ግብረገባዊ ሕይወት መምራትን አጽንኦት ሰጥቶ ያስተምራል (ሚትራስነትን የቀደመው ይሁዴነትም እንደዛው ነበር፡፡) 4. ሚትራስነት መልከሙና ክፉው ስለሚባለው ሃሳብ ያምናል (የቀደመው ይሁዴነትም ያምናል፡፡) 5. ሚትራስነት ሁሉም ሕይወት ከአማልክት መነጨ ብሎ ያስተምራል (የቀደመው ይሁዴነትም እንዲሁ ይላል፡፡) 6. ሚትራስ ተአምራት አሳይቷል … 7. ሚትራስነት የምድር መጥፋትን አስተምሯል … የተሳሳቱ ንጽጽሮች፡ በሃያስያን የሚጠቀሱት የሚከተሉት ንጽጽሮች በጥንት ቅርፆችም ሆነ ባልጠፉ ጽሑፎች ላይ የሌሉት ናቸው፡ ሚትራስ አስተምህሮውን በ 30 ዓመቱ ጀመረ (ስለማንኛውም ነገር በተመለከተ እድሜው አልተጠቀሰም፡፡) ሚትራስ ቀብር ቤት ነው የተቀበረው (ከነሕይወቱ መሆኑ ነው?)፡፡ ከዚህ ጋር ሊያያዝ የሚችል ነጥብ በየዓመቱ በዊንተር ሶሊስታይስ ከአለቶ ዳግም ይወለዳል የሚል አለ (ይህ ግን የተጨመረው በኋላ ላይ ነው)፡፡ ሚሥጥረ ሥላሴ (ግዜ ባለፈ ቁጥር የአማልክቱ ብዛት ሚትራስነት ላይ እየተጨመረ ቢሄድም ሦስትዮሽነት ያላቸው አንድም የሉም)፡፡ መደምደምያ፡ አሁንም ዳግም ንጽጽሮቹ የማይመሳሰሉ፣ የፈጠራ ወይም ለማገናኘት ያለአግባብ የተለጠጡ መሆናቸውን አይተናል፡፡ (6) አቲስ አቲስ[75] እንደአምላ ይመለክ የነበረው ዛሬ ላይ ቱርክ ተብሎ በሚታወቀው መሬት ነው፣ በኋላ ላይ በመላው ሮማ ሊስፋፋ ችሏል፡፡ አብዛኞቹ በአቲስና ኢየሱስ መሃከል ያሉት ምስስሎሽ የተጠመዘዙ አልያም ፈጠራ ናቸው፡፡ ይህን ንኡስ ርእስ ካነበባችሁ በኋላ ኢየሱስ-አቲስ ምስስሎሹ ከሁሉ የባሰው ወለፈንዴ ሃሳብ ሁኖ ታገኙታላችሁ፡፡ ዲሰምበር 25፡ ይህ እለት ከክርስትና ጋር ግንኙነት እንደሌለው ተገልጽዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ እለት ከአቲስ ጋር በተገናኘ አይነሳም - ከዓመታዊ የፀደይ ወቅት መመለስ ጋር በተያያዘ ነው የሚነሳው፡፡ ድንግል ውልደት፡ አፈ ታሪክ እንደሚለው ከሆነ ባለ ሁለት ጾታ አውሬ የሆነው አግዲስቲስ[76] የዜኡስ[77] ዘር ሁኖ ከምድር ይነሳል፡፡ አግዲስቲስ ሳንጋርየስ[78] ወንዝን ይወልዳል/ትወልዳለች፣ ይህም ወንዝ ናና[79] የተባለች ኒምፍ አስገኘ፡፡ ናና ደግሞ የአልሞንድ ፍሬ በደረቷ ስትይዝ ወይም የአልሞንድ ዛፍ ስር ስትቀመጥ ፍሬው እግሯ ላይ ከወደቀ ትጸንሳለች፡፡ ናና ልጇን ጥላ ሄደች፡፡ ልጇንም ፍየል አሳደገው፡፡ ከአጠቃላይ ንባቡ የምንረዳው አቲስ የተወለደው ናና የዜኡስ የዘር ፈሳሽ የፈሰሰበት የአልሚንድ ዘር በመጽነሷ ነው፡፡ ስቅላት፡ ይህ ንጽጽር ሙሉ ለሙሉ ሐሰት ነው፡፡ አቲስ ሊያገባ ሲል ለራሱ/ሷ ስለፈለገው/ችው አግዲስቲስ እንዲያብድ አደረገው/ችው ከዛም አቲስ እራሱን ዛፍ ስር ሁኖ ሊያኮላሽ ብልቱን ይቆርጣል፤ ከዛም ደሙ ይፈሳል፡፡ ሃያስያኑ የአቲስ ዛፍ ስር መሞት ክርስቶስ “ዛፍ” ላይ ሞተ ብለው ለማነጻጸር ይጥራሉ፡፡ ክርስቶስ ጎኑን ተወግቶ የፈሰሰውን ደምም አቲስ በራሱ ብልቱን ሲቆርጥ ከፈሰሰው ደም ጋር ለማነጻጸር ይጥራሉ፡፡ ትንሳኤ፡ በአንደኛው ግልባጭ አግዲስቲስ ተምባሩ/ሯ ተጸጽቶ/ታ ዜኡስ የሚያምረውን የአቲስ ሬዛ እንዳይበሰብስ እንዳለ እንዲያቆየው ጠየቀ/ች፡፡ ለአቲስ ከሞት መነሳት የሚባል ነገር የለውም፡፡ አግዲስቲስ እና ታላቋ እናት[80] (ወይም ሳይቤሌ[81]) ዛፉን ተሸክመው ወደ መቃብሩ ሂደው በአቲስ ሞት አብረው ለቅሶ ተቀምጠዋል፡፡ እዚህም ትንሳኤ የሚል ነገር የለም፡፡ ከሞት መነሳት የሚባለው ነገር በኋላ ላይ የሚታየውም አቲስ ወደ ዛፍ ከተቀየረ በኋላ ነው፡፡ ማስተሰረይ፡ ሃያስያን አቲስ የተሰዋው የሰው ልጆችን ለማዳን ነው ቢሉም የዚህ ማስረጃ አንዳችም ነገር የለም፡፡ በመጀመርያ አቲስ ዛፍ መንፈስ እንደሆነና የተክሎች አምላክ መሆኑን ይነገረናል፡፡ ሞቱና ወደ ዛፍ መሸጋገሩ በዊንተር (የነጮች የበረዶ ክረምት) የተክሎች መሞትና በጸደይ ዳግም መመለሱን ለማሳየት ነው፡፡ አቲስ አዳኝ ሁኖ ለመጀመርያ ጊዜ ሊጠቀስ የቻለው በ6ኛው ክ/ዘመን ከክርስቶስ ልደት በኋላ ነው፣ ከዚህ ክርስትና ሊኮርጅ የማይመች ነው እጅግ አርፍዶ ነው የተጻፈው፡፡ በቤተ ቀብር መቀበሩ፡ አቲስ ቀብር ቤት ውስጥ መግባቱ የሚገለጸው ዛፍ ከሆነ በኋላ ወደ ታላቂቱ እናት ዋሻ ሲወሰድ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይህ ዋሻ ቤቷ ነው፣ ቀብር ቤት አይደለም፡፡ አባት-ልጅ ውህደት፡ እንዲህ ያለ ግንኙነት የለም፡፡ በጣም ለጥጠን ማገናኘት ከሞከርን የምናገኘው አቲስ የዜኡስ የልጅ ልጅ መሆኑን ነው፡፡ እስካሁን ስለ አቲስ በምናቀው ላይ ተመስርተን ይህ ያላግባብ የተለጠጠ ንጽጽር ሊሆን የማይችል መሆኑን ማወቅ እንችላለን፡፡ አቲስ እና ዜኡስ አንድ ናቸው ተብሎ መቼም ታምኖ አያውቅም፣ እንኳን እኩል ናቸው ሊባሉ ቀርቶ፡፡ ቁርባን፡ ሃያስያን ተከታዮቹ ዳቦና ወይን አድርገው የቁርባን ሥርአት ያከብሩ ነበር ይላሉ፡፡ እንዲህ ያለው ነገር የሚጠቀስበት ብቸኛው ቦታ የተባረከ መአድ ከከበሮ እና የብረት ከበሮ ላይ አድርገው ሲመገቡ ግዜ ነው፡፡ ምን እንደሚበሉ አልተጠቀሰም፡፡ ሃያስያን ዳቦና ወይን ነው ሊሆን የሚችለው ይላሉ፣ ይህ ግን ሊሆን የማይችል ነው ምክንያቱም በአቲስ በዓላት ግዜ ወይን ክልክል ነበርና፡፡ መደምደምያ፡ ከሚስኪኑ አቲስ ጋር በተያያዘ የምናያቸው ነገሮች የራስህን ብልት መቁረጥ፣ ወደ ዛፍ መቀየር እና የወንዝ ዘሮች ከፍሬ ልጆች ሲወልዱ ነው … እነዚህ ለማመሳሰል የሚጥር ቅል ራስ መሆን አለበት፡፡ (7) ዳዮኒሰስ ዳዮኒሰስ[82] የወይን ጠባቂ እላክ ተደርጎ ነው የሚታወቀው፣ ምንም እንኳ በግሪክ እና ሮማ የብዙ ነገሮች ጠባቂ/ባላደራ አምላክ ተደርጎ ቢወሰድም፡፡ በዚህም ምክንያት ሃያስያኑ ምንም መሰረት በሌለው መልኩ ዳዮኒሰስ የወይን አምላክ እና ኢየሱስ ወይን መጠጣቱን ለማያያዝ ይሞክራሉ፡፡ ዲሰምበር 25፡ ይህ እለት ለዳዮኒሰስ አይመለከተውም፡፡ ልክ እንደ አቲስ ከጸደይ መምጣት ጋር ተያይዞ ነው የሚታወሰው፡፡ ክርስትናንም አይመለከትም፡፡ ቀድመን ከአረመኔያውያንና ፀሐይ አምልኮ ጋር የተያያዘው የዊንተር ሶሊስታይስ በዓል መሆኑን ተመልክተናል፡፡[83] ድንግል ውልደት፡ የዳዮኒሰስ ውልደት በተመለከተ ሁለት ታሪኮች አሉ (ሁለቱም ድንግል ውልደትን አያመለክቱም)፡ ዜኡስ ከሙታን ወገን የሆነችውን ሴት ሴሜሌን[84] ያስረግዛል፣ በዚህም ሄራ[85] በጣም ትቀናለች፡፡ ሄራ ዜኡስ እንዲታያት እንድትጠይቀው ትመክራታለች፣ ሴሜሌም እንዳየችው ሙታን አማልክትን አይተው መኖር አይችሉምና ትሞታለች፡፡ ከዚህ በኋላ ዜኡስ ጽንሱን ወስዶ ከጭኑ ሰፍቶ እስኪወለድ ድረስ ያዘው፡፡[86] ዳዮኒሰስ የዜኡስ እና ፐርስፎኔ[87] ውጤት ነው፡፡ ሄራ ወድያው በቅናት ትሞላለች፣ እናም ህጻኑን ለመግደል ግዙፎቹን (ታይታንስ) ትልክበታለች፡፡ ዜኡስ ሊያድነው ቢመጣም ግን አርፍዷል - ታይታኖቹ ሁሉን ነገሩን በልተው ልቡ ብቻ ቀርቷቸው ነበር፡፡ ይህን ወስዶ ሴሜሌ ማህፀን ውስጥ ያስቀምጠዋል፡፡ እንደምናየው ድንግል ውልደት የለም፣ ሆኖም ግን ማህጸን ውስጥ ሁለቴ በመፈጠሩ የዳግም ውልደት አምላክ ሊሆን ችሏል፡፡[88] ተጓዥ መምህር፡ ዳዮኒሰስ ብዙ ተጉዟል ይባላል “የወይን ተክል ሚስጥርን” (ወይን መስራት) ሊያስተምርና እና ሃይማኖታዊ ስርዓቱን ሊያስፋፋ፡፡ (ኢየሱስ ግን በአይሁድ አገር ነበር ተወስኖ ሲያስተምር የነበረው)፡፡ እንደ ኢየሱስ መንፈሳዊ አስተማሪ ተደርጎ አይወሰድም ነበር፡፡ ቁርባን፡ በታይታኖቹ[89] ከተበላ በኋላ ዳዮኒሰስ ዳግም መወለዱን ለመዘከር፣ አምላኪዎቹ ሰው ወይም እንሰሳ ወስደው ይገነጣጥሉና ስጋውን በጥሬው ይበላሉ፡፡ ይህ ከክርስትና ቁርባ ጋር ሳይሆን ከታንታሉስ አፈታሪክ ጋር ነው የሚገናኘው፡፡ የድል አድራጊ አቀባበል፡ ሃያስያን ዳዮኒሰስ አህያ ላይ ሁኖ አረግ የሚያውለበልቡ ሰዎች ሲቀበሉት የሚያሳይ ስእል ይሳላል ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህ አገባቡ የተለመደ አካሄዱ ነው እንጂ ከየትኛውም ትንቢት መፈጸም ጋር የተያያዘ አንድ ምልክት አልነበረም፡፡ እኚህ አጃቢዎቹ ማኤናዶች[90] እና ሳቲርስ[91] ሲሆኑ የወይን አምላክን ምልክቱ የሆነውን አረግ በወይን ፍሬ ተጠላልፎ ይዘው የሚከተሉት ናቸው፡፡ ኢየሱስ ግን ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ሕዝቡ አቀባበል ሲያደርጉለት የዘምባባ ቅርንጫፍ (ይሁዴያዊ ምልክቶች) ይዘው ተቀብለውታል፡፡ መሲሐዊ ትንቢቱንም ዘፍጥረት 49፣ 11 ላይ ማየት ይቻላል (ከልደተ ክርስቶስ 1,400 ዓመት በፊት የተጻፈ - ከዳዮኒሰስ እጅግ በረዘመ ዘመን ቀድሞ)፡፡ አህያውን በወይን ግንድ አስሮ ተምሳሌታዊ በሆነ መልኩ ልብሱን በወይን እንደሚያጥብ (የሞቱ ተምሳሌት) ተጽፏል፡፡ በዚህች አንድ ዓረፍተ ነገር ላይ ግሪኮቹ/ሮማዎቹ አምልኮ ፈጠሩ እያልን ሳይሆን፣ ዳዮኒሰስ በግሪክ አንጋረ-ተረት ከመፈጠሩ በፊት እነዚህ ሦስት ነገሮች ተያይዘው አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ውስጥ እንደ ነበሩ ለማሳየት ነው፡፡[92] ውኃን ወደ ወይን፡ ዳዮኒሰስ ለንጉስ ሚዳስ[93] የነካው ነገር ሁላ ወርቅ እንዲሆን ኃይል የሰጠው አምላክ ነው፡፡ በተመሳሳይ የንጉስ አኒየስ ልጆች ለሆኑት ሴቶች[94] ደግሞ የነኩት ነገር ሁላ ወደ ወይን፣ በቆሎ ወይም ዘይት እንዲቀይሩ ኃይል ሰጥቷቸዋል፡፡ ዳዮኒሰስ የወይን አምላክ እንደመሆኑ ይህ የሚደንቅ ክስተት አይሆንም፡፡ ሆኖም ግን ዳዮኒሰስ ደግሞ ባዶ እቃዎችን በወይን ይሞላ እንደነበር አንጋረ-ተረቶች አሉ፣ ውኃን ወደ ወይን የመቀየር ተግባርን ግን ሲፈጽም አልተነገረም፡፡ ትንሳኤ፡ የዳዮኒሰስ ትንሳኤ የሚነገረው ታይታኖቹ ከበሉት በኋላ ዙኡስ በሌላ ማህጸን እንደገና እንዲያድግ በማድረጉ ነው፡፡ እንደምናየው ይህ ከክርስቶስ ትንሳኤ ታሪክ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ በተጨማሪም ዳዮኒሰስ ተከታዮቹን በዓሎቹን አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ ከአማልክቱ ጋር ሊሆን ወደ ኦሊምፐስ ተራራ “አርጓል” ከነሕይወቱና ጤናው፡፡ የህጻንነት ዳግም ውልደቱ እንደ አቲስ የተክሎች ኡደት ተምሳሌትነት፣ ኡደት ነው እንጂ ከሐጥያት ጋር የሚያያዝ ነጥብ የለውም፡፡ ተመሳሳይ መዓረጎች፡ ከስር ያሉት ያለ አግባብ ዳዮኒሰስ ከኢየሱስ ጋር ይጋራቸዋል የሚሏቸው መዓርጎች ናቸው፡፡ ከላይ ቀድመን የተራራቁ መመሳሰሎች ብናሳይም እዚህ ያሉት ግን ሙሉ ፈጠራዎች ናቸው፡ ንጉሶች ንጉስ፡፡ ዳዮኒሰስ ከፊል-አምላካዊ ነው ነበረው፡፡ ዜኡስ ነበር በአንጋረ-ተረቱ ዋናው አምላክ፡፡ ብቸኛ ልጅ፡፡ዜኡስ ከብዙ ሴቶች ጋር ግንኙነት የነበረው ሲሆን ብዙ ልጆችን ወልዷል፡፡ አልፋና ኦሜጋ፡፡ ዳዮኒሰስ የመጀመርያና የመጨረሻ አይደለም፣ አጀማመር ነበረው፡፡ የአምላ በግ፡፡ ዳዮኒሰስ ከበሬ፣ እባብ፣ ወይን እና አረግ ጋር ነው የሚያያዘው እንጂ ከበግ ጋር ዝምድና የለውም፡፡ ስለ ዳዮኒሰስ የምናገኛቸው መዓርጎች፣ በሬው፣ ፍየል ገዳዩ፣ ችቦው፣ የተራራው ዳዮኒሰስ፣ ስጋ በሊታው፣ ዳዮኒሰስ አረጉ፣ እና አዳኝ ( ይህ ግን በኋ ላይ የተጨመረለት በቀጣይ ሕይወት ሥጋዊ ደስታዎችን እንደሚሰጥ ሲናገር ነው፡፡ ከሄደስ ሊያዳናት የቻለው ሰው ሴሜሌን ብቻ ነው፡፡)፡፡ መደምደምያ፡ የኢየሱስ ታሪክ ከዳዮኒሰስ ተኮረጀ ማለት ወለፈንዴ ሐሳብ ነው፡፡ ይሁዴዎቹ ይህን የዳዮኒሰስ አንጋረ-ተረት አውቀው ቢሆን እንኳ በዚህ ተመስርተው መሲሐቸውን ሊፈጥሩ አይችሉም፣ እጅግ ሰፊ ልዩነት አላቸውና፡፡ (8) ተሰቀሉ ስለተባሉ አማልክት አሁን ደግሞ ሃያስያኑ ተሰቅለዋል የሚሏቸውን አማልክት ወደ መፈተሸ እንሄዳለን፡፡ አሁንም እኚህ ሃሳቦች የተነሱት በኬርሴ ግሬቭስ በተሳሳተው The World's Sixteen Crucified Saviors በሚለው ስራው ነው፡፡ ኦሳይረስ፡ ከላይ እንደተመለከትነው በሴት ወይም ሴዝ ተንኮል ነው የሞተው፡፡ ሳጥን ውስጥ እንዲገባ አድርጎ ወደ አባይ ወንዝ ከተተው፡፡ በተጨማሪም እስካሁን ባለን ማስረጃ የአፐሳይረስ ታሪክ ከክርስቶስ በፊት ነበር የሚለው (የክርስቶስ ታሪክ በኦሪትም አለና) ፈጠራ ነው፡፡ ኩኤትዛልኮአትል፡ የህ የደቡብ አሜሪካ አምላክ እንዴት የክርስቶስ ታሪክ አካል ሊሆን እንደሚችል የሚገርም ነው፡፡ የሆነ ሁኖ ይህ አምላክ ተሰቅሏል የሚል የለም፡፡ አንደኛው የታሪኩ ግልባጭ ለብቻ ከምትኖር ሴት “ቄስ” ጋር በመተኛቱ ተፀፅቶ እራሱን አቃጠለ የሚል ሲሆን ሌላኛው ደግሞ አማልክቱ በላኩት እሳት ተበላ ይላሉ፡፡ ክሪሽና፡ ክሪሽና እንዴት እንደሞተ አይተናል፡ ጫካ ውስጥ ተመስጦ ላይ እያለ በስህተት በአዳኝ ቀስት ተመትቶ ነው የሞተው፡፡ ታሙዝ / ዱሙዚድ፡ ታሙዝ[95] ኢሽታር ዘውዷ ላው ሁኖ ስታገኘው በመበሳጨቷ የላከቻቸው ርኩስ መናፍስት ነው የገደሉት የሚባለው፡፡ አለሴስቲስ፡ በአፈ ታሪከ እንደሚባለው አለሴስቲስ ለባሏ ስትል ከአማልክቱ ጋር ቃል ኪዳን ከፈጸመ በኋላ ልትሞትለት ትወስናለች፡፡ ግዜው ሲደርስ አለሴስቲስ አልጋ ላይ ነበረች፡፡ አማልክቱ በታማኝነቷ ይነካሉ፣ ያዝኑላትማል፣ ከዛም ከባሏ ጋር በአንድ አደረጓቸው፡፡ አቲስ፡ ከዚህ በፊት እንዳየነው፡፡ አቲስ ብልቱን በራሱ ከቆረጠ በኋላ ነበር ደሙ ፈስሶ የሞተው፡፡ ኢሱስ / ሄሱስ፡ ኢሱስ[96] የሚለው ስም ከእብራይስጥ ትርጓሜ የሆነው ኢየሱስ ከሚለው ጋር መመሳሰሉ አያደናግረን፡፡ ኢሱስ ተከታዮቹ ሰውን ዛፍ ላይ ሰቅሎ በመግደል መስዋእትነት ስርዓት ያከብሩ ነበር (ስቅላት አይደለም) እንዲህ የሚያደርጉት ከዘለዘሉት በኋላ ነው፡፡ ኢሱስ (አንዳንዴ ከሜርኩሪ እና ማርስ ጋር የሚያያዝ ሲሆን) ሞቱን በተመለከተ ምንም ታሪክ የለም፡፡ ዳዮኒሰስ፡ ታይታነስ ሲሞት ያየነው በታይታኖቹ ሕጻን እያለ ተበልቶ ነው፡፡ ኢንድራ፡ በአንድ ታሪክ ኢንድራ ቭሪትራ በተባለ በእባብ ከነሕይወቱ ሲዋጥ የሚነገር ይገኛል፣ በኋላ ላይ በሌሎች አማልክት ትእዛዝ ተፍቶታል፡፡ በመዳኑም ሞት የሚባል ነገር አልተመዘገበም፣ ስቅላት ይቅርና፡፡ ፕሮሚትየስ፡ ፕሮሚትየስ[97] በዜኡስ ከተቀጣ በኋላ ተራራ ላይ ታስሮ ንስር በየቀኑ እየመጣ ጉበቱን እንዲበላ ነው የፈረደበት የሚባለው፡፡ ፕሮሚትየስ ከስቃዩ በሄርኩለስ ነጻ ይወጣል ይባላል፡፡ ሚትራስ፡ ከላይ እንዳየነው ሚትራስ ሞቷል የሚል ማስረጃ የለም እንዲያውም በሰረገላ ወደ ገነት ሂዷል ከነሕይወቱ ነው የሚለው፡፡ ኩኢሪነስ፡ ኩኢሪነስ[98] ሞተ የሚል ማስረጃ የለም፡፡ ከሮሙለስ ጋርም አጣምሮ ሊታይ በሚሞከርበት ጊዜም ቢሆን የሞት ነገር የለም፣ ሮሙለስ[99] ከነሕይወቱ እያለ ወደ ገነት ተወስዷል ስለሚል፡፡ መጥፋቱን ለማብራራት ሰኔቱ ነው የገደለው ብለው ብዙዎች ከሰዋል፡፡ ሆኖም ግን ስቅላት የሚል ነገር አልተነሳም፡፡ ቤል፡ ከዜኡስ ጋር የሚያያይዙት ሲሆን፣ ያቢሎኑ ቤል[100] ሞትን ቀመሰ የሚል አንድም ማስረጃ የለም፡፡ ባሊ / ማሃባሊ፡ ባሊ[101] የቪሽኑ አቫታር በሆነ ቫማና[102] ከተታለለ በኋላ ከነአካሉ ተይዞ በጉልበት ወደ ታችኛው ዓለም እንደተወሰደ ነው የሚናገረው ታሪኩ፡፡ አንዳንድ ታሪኮች ላይ ባሊ ተለቆ ንግስናን ሊያገኝ ችሏል ይላል፡፡ በሁለቱም ቢኬድ ስቅላት ብሎ ነገር የለም፡፡ ኦርፊየስ፡ ኦርፊየስ[103] በተበሳጩ የዳዮኒሰስ ማኤናዶች እንደተገደለ ነው የሚነገረው፣ ከአፖሎ በቀር ሌላ አማልክት አላመልክም ስላለ፡፡ ኢአኦ እና ዊቶባ፡ ስህተት ላለመፈጸም እነዚህ ሁለት አማልክትን በተመለከተ ስለ አሟሟታቸው ምንም አይነት ዋና ማስረጃ ስላላገኘሁ አስተያየት ከመስጠት ልቆጠብ፡፡ ስለነዚህ ሞት የሚያስረዳ ዋና ጽሑፍ አንባቢው የሚጠቁም ከሆነ እናየዋለን፡፡ እስከዛ ግን ምንጮችን ከማጣቀስ እንቆጠባለን፡፡ መደምደምያ ምንም እንኳ ሌሎች ጸሐፊዎች የበለጠ በዝርዝር በጉዳዩ ላይ የሚጽፉ ቢሆንም በዚህ ጽሑፍ ግን አንባቢው እውነትን ከፈጠራ እንዲለይ ባጭሩ ለማቅረብ የተደረገ ሙከራ ነው፡፡ አንባቢው ዋና ጽሑፎችን ማገላበጥ ሲጀምሩ መጀመርያውኑ እንዲህ ያለ ወሬ እንዴት እንደተጀመረ መጠየቅ ይጀምራሉ፡፡ ሃያስያኑ ለዚህ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ አስተዋጽኦ ከማድረጋቸው በፊት ዋና ጽሁፎችን ቢፈትሹ፣ እንዲህ ያለውን ፕሮፖጋዳ መመከት ይቻላቸው ነበር፡፡ በኢየሱስ እና ሌሎች አካሎች መሃከል አንዳንድ የሚያመሳስሉ ንጽጽሮች ቢኖሩ የመሆን እድል ኖሯቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ ከዘመናዊ ታሪክ ምሳሌ ብንወስድ[104] በሁለት የአሜሪካ ፕሬዚደንቶች፣ ኬነዲ እና ሊንከን መሃከል ያለው ንጽጽር አንዳቸው የፈጠራ ወይም የኩረጃ ናቸው ይባ ነበር፡ ሊንከን ለምክር ቤት የተመረጠው በ1846 ነበር፣ ኬነዲ ደግሞ በ1946 ነበር ለምክርቤት የተመረጠው (ኬነዲ በሕግ ማውጣት እና ፖሊሲ ትግበራዎች ቀልጣፋ ስኬት ቢያገኝም ሊንከን ግን ብዙ ሽንፈቶችን ቀምሷል)፡፡ ሊንከን ለፕሬዚደንትነትነት የተመረጠው በ1860 ሲሆን ኬነዲ ደግሞ ለፕሬዚደንትነት የተመረጠው በ1960 ነበር፡፡ (ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በአራት ዓመት አንዴ የሚደረግ እንደመሆኑ በማህናቸው ባለው መቶ ዓመት ይህ የመሆን እድሉ 1/20ኛ ነው፡፡) ሊንከንና ኬነዲ የሚሌት ስሞች በእንግሊዘኛ ሆህያት ሲቆጠሩ እኩል ሰባት ይሆናሉ፡፡ (የመጀመርያ ስማቸውን ከጨመርን ይህን ንጽጽር ያፋልሰዋል)፡፡ በሲቪል (ሕዝባዊ) መብት በተመለከተ ሰፊ ለውጥ በተደረገበት ዘመን ነበር ሁለቱም መሪዎች የነበሩት (ተኪዎቻቸውምና ሌሎችም ቢሆኑ እንዲሁ ነበሩ)፡፡ ሁለቱም ፕሬዚደንቶች በእለተ ዓርብ በነብሰ ገዳይ ጥይት ነው የሞቱት (ይህ ከሰባት አንድኛ የመሆን እድል የያዘ ነው)፡፡ ሁለቱም ነብሰ ገዳዮች በሶስት ስሞች የሚታወቁ ሲሆኑ 15 ሆህያት አላቸው (እያንዳንዳቸውም በሶስቱም ስማቸው አልነበረም የሚታወቁት፣ ሦስቱም ስሞቻቸው የታወቁት ከግድያው በኋላ ነው)፡፡ ሁለቱም ነብሰ ገዳዮች ለፍርድ ብይን ከመድረሳቸው በፊት ነበር ተገደሉት (ቡዝ እንደተያዘ ሲሆን የተገደለው ኦስዋልድ ደግሞ ከታሰረ ከእለታት በኋላ ነበር የተገደለው)፡፡ ሁለቱንም ፕሬዚደንቶች የተኳቸው ሰዎች የቤተሰብ ስማቸው ጆንሰን የሚል ነው፣ (በነጭ ወንዶች መሃከል ጆንሰን የሚለው ሥም ባለው ተወዳጅነት ምክንያት፣ ሁለት መሀመድ የሚል ስም ያላቸው ሙስሊም ወንዶች የማግኘት ያህል የሚቆጠር ነው)፡፡ መጀመርያ ላይ እኚህ ንጽጽሮች የሚደንቁ ሊመስሉ ይችላሉ፡፡ ከ 2,000 ዓመታት በኋላ ታሪክ ፀሐፊዎች ወደ ኋላ ተመልክተው ኬነዲ ምናባዊ ፈጠራ ወይም ከሊንከን ሕይወት ተኮረጀ ነው ብለው ይወቅሷቸው ይሆን? በአስደናቂው የአብርሃም ሊንከን ክንውኖች ተደምመው የእርሱ ነጸብራቅ የሆነውን አሜሪካዊ ጀግና የፈጠርን ይመስላቸው ይሆን? የራሱን ምርምር ለማድረግና ለመፈተሽ ተነሳሽነት ያለው አስተዋይ አንባቢ በእንደዚህ ዓይነት ፕሮፖጋንዳ የተሸፈነውን እውነት በቀላሉ ያገኘዋል፡፡ ማስታወሻዎችና ዋቢ ጽሑፎች [1] ይህ ጽሑፍ “Alleged Similarities Between Jesus and Other Deities” ከሚል የተወሰደ ነው፡፡ [2] ስራዎቹ በምሁራን የሐሰት ስለመሆናቸው የተረጋገጡ ቢሆንም አሁንም ብዙዎች ስራዎቹን ያጣቅሳሉ፣ ምንም እንኳ በቀላሉ መጸሐፍ ቅዱስንና ሂንዱ ጽሑፎችን በማነጻጸን ስህተቶቹን ማሳየት የሚቻል ቢሆንም፡፡ ስራዎቹ በወቅቱ ወድያውኑ በሬቨረንድ ታይለር ፔሪ ስህተታቸውን አሳይተው ነበር፡፡ ግሬቭስ የተጠቀመባቸው ምንጮች በጠቅላላ ነጻ-ሃሳባውያን ከሚባሉት ጸሐፍያን ሲሆን፣ እኚህም በበኩላቸው በትክክል ያልተገነዘቧቸው፣ በሚገባ ያላጠኗቸው ሃሳቦችን በሚያሳስት መንገድ ያቀረቡ ናቸው፡፡ ግሬቭስ ከዚህ ተነስቶ ሃይማኖት ቄሶች የፈጠሩት ተረት ነው የሚል ንድፈ ሃሳብ ገነባ፡፡ ይህ ሃሳብ /እምነት ከሮያል አርች ፍሪሜሶኖች የቤተ ክርስትያንን አስተምህሮ በግኖስቲሳውያን ለመቀየር የሚደረገው እንቅስቃሴዎች ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ግሬቭስ ከእርሱ ሃሳብ ጋር እንዲገጥም መረጃዎችን ያጠማዝዝ ነበር፣ መረጃ በሌለበት ደግሞ የራሱን ይፈጥራል፡፡ የኢየሱስ ታሪክ ተረት ነው የሚሉ ሰዎች እንኳ የዚህ ሰው መጽሐፍ ትክክለኛ እንዳልሆነ ይቀበላሉ፡፡ በአሁኑ ዘመን ስህተት መሆኑ ከተጋለጠም በኋላ ጽሑፎቹን የሚያጣቅሱ /የሚጠቀሙባቸው አልጠፉም በሌላ ጽሑፍ ያጋለጥናት አካርያ ኤስ. (የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ) በስፋት ታጣቅሰዋለች፣ The Christ Conspiracy ለሚለው መጽሐፏ ዋና ምንጭዋ ነው፡፡ ጽሑፎቹ ዳ ቪንቺ ኮድ ላይም ታይተዋል፡፡ ሌሎችም ተጠቅመውታል፡፡ (http://www.reference.com/browse/wiki/Kersey_Graves) [3] “ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል፤ እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።” ትንቢተ ኢሳይያስ 7፣14፡፡ [4] Mahabharata Bk 12, XLVIII [5] Bhagavata, Bk 4, XXII:7 [6] እርሱም ተነሥቶ ሕፃኑንና እናቱን በሌሊት ያዘና ከጌታ ዘንድ በነቢይ። ልጄን ከግብፅ ጠራሁት የተባለው እንዲፈጸም ወደ ግብፅ ሄደ፥ ሄሮድስም እስኪሞት ድረስ በዚያ ኖረ። ማቴ. 2፣ 14-15፡፡ [7] Bhagavata, Bk 4, I:4-5 [8] Bhagavata, Bk 8, I, pg 743 [9] Mahabharata, Book 16, 4 [10] Mahabharata, Book 16, 4 [11] “ኢየሱስም ቀረበና እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴ. 28፣ 18-20፡፡ [12] ሉቃስ 22፣ 7-23፤ ማቴ. 26፣ 17-30 ይመልከቱ፡፡ [13] በአንተና በሴቲቱ መካከል፥ በዘርህና በዘርዋም መካከል ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፥ አንተም ሰኰናውን ትቀጠቅጣለህ። ዘፍ. 3፣15፡፡ [14] Mahabharata, Bk 7, LXXXI እና Mahabharata Book 8, XC ይመልከቱ፡፡ [15] Krishna Janmaashtami [16] ማቴ. 17፣ 20፡፡ [17] Puranas (400-1000 A.D.), Bhagavata (400-1000 A.D.), Harivamsa, (100-1000 A.D.) እዚህ የሰፈረው ዓ.ም እጅግ የተለጠጠውና ሰፊው ግምት ነው፡፡ [18] Buddha [19] The Acts of the Buddha [20] http://www.sacred-texts.com/bud/sbe19/sbe1903.htm [21] Buddha Karita 1:18 [22] ማቴ. 2፣ 1-11 [23] Jataka I:55,57 [24] Buddha-Karita 1:54,62,74 [25] “ወደ ቤትም ገብተው ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት፥ ወድቀውም ሰገዱለት፥ ሣጥኖቻቸውንም ከፍተው እጅ መንሻ ወርቅና ዕጣን ከርቤም አቀረቡለት።” ማቴ. 2፣ 11፡፡ [26] Buddha Karita 1:27,36,38,40 [27] Marks of the Buddha [28] Jataka 1:56 [29] Buddha Karita 1:35,37,5465 [30] http://www.reference.com/browse/wiki/Vesak [31] http://en.wikipedia.org/wiki/Suddhodana [32] Jataka 1:57 [33] http://www.mahidol.ac.th/budsir/life_02.htm [34] http://www.sacred-texts.com/bud/btg/btg98.htm [35] http://www.mahidol.ac.th/budsir/life_10.htm [36] http://www.sacred-texts.com/bud/btg/btg98.htm [37] http://www.reference.com/browse/columbia/nirvana [38] http://www.reference.com/browse/wiki/Bodhi_tree [39] “ብልና ዝገት በሚያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በሚሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በምድር ላይ መዝገብ አትሰብስቡ፤ ነገር ግን ብልም ዝገትም በማያጠፉት ሌቦችም ቆፍረው በማይሰርቁት ዘንድ ለእናንተ በሰማይ መዝገብ ሰብስቡ፤ መዝገብህ ባለበት ልብህ ደግሞ በዛ ይሆናልና፡፡ የሰውነት መብራት አይን ናት ዓይንህ እንግዲህ ጤናማ ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ ብሩህ ይሆናል፤ ዓይንህ ግን ታማሚ ብትሆን፣ ሰውነትህ ሁሉ የጨለመ ይሆናል፡፡ እንግዲህ በአንተ ያለው ብርሃን ጨለማ ከሆነ፣ ጨለማውስ እንዴት ይበረታ! ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላል ሁለተኛውንም ይወዳል፤ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል፤ ለእግዚአብሔር እና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም፡፡” ማቴ. 6፣ 19-24፡፡ [40] http://www.pantheon.org/articles/h/horus.html [41] http://www.pantheon.org/articles/r/re.html [42] http://www.pantheon.org/articles/h/hathor.html [43] http://www.pantheon.org/articles/i/isis.html [44] http://www.pantheon.org/articles/o/osiris.html [45] "I, Hathor of Thebes, mistress of the goddesses, to grant to him a coming forth into the presence [of the god]... Hathor of Thebes, who was incarnate in the form of a cow and a woman." http://www.sacred-texts.com/egy/tut/tut05.htm እና http://www.pantheon.org/articles/h/hathor.html [46] "[Isis] made to rise up the helpless members [penis] of him whose heart was at rest, she drew from him his essence [sperm], and she made therefrom an heir [Horus]." http://www.sacred-texts.com/egy/leg/leg22.htm እና http://www.pantheon.org/articles/i/isis.html [47] http://www.sacred-texts.com/egy/leg/leg08.htm [48] “እኔም አባት እሆነዋለሁ፣ እርሱም ልጅ ይሆነኛል፤ ካንተ አስቀድሞ እንደነበረው እንዳልራቅሁ፣ ምህረቴንም ከእርሱ አላርቅም፡፡ በቤቴ እና በመንግስቴም ለዘልአለም አቆመዋለሁ፤ ዙፋኑም ለዘልአለም ይጸናል፡፡” 1ኛ ዜና መዋእል 17፣ 13-14 [49] http://www.sacred-texts.com/egy/pyt/pyt54.htm http://www.pantheon.org/articles/o/osiris.html [50] http://www.sacred-texts.com/egy/eml/eml05.htm [51] http://www.digitalegypt.ucl.ac.uk/ideology/khoiak.html [52] በዚህ ላይ ተጨማሪ ለማንበብ፡ የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ ይመልከቱ፡፡ [53] የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ [54] ማቴ. 4፣ 1-11 [55] http://www.sacred-texts.com/egy/pyt/pyt37.htm http://www.sacred-texts.com/egy/ebod/ebod18.htm http://www.sacred-texts.com/egy/eml/eml05.htm [56] http://en.wikipedia.org/wiki/Set_%28mythology%29#Desert_god http://en.wikipedia.org/wiki/Satan [57] http://www.bartleby.com/65/zo/Zoroaste.html [58] http://www.bartleby.com/65/hy/Hystaspe.html [59] http://www.reference.com/browse/wiki/Avesta [60] http://www.avesta.org/fragment/vytsbe.htm [61] http://www.avesta.org/denkard/dk5.html [62] http://www.pantheon.org/articles/a/ahura_mazda.html [63] http://www.pantheon.org/articles/h/haoma.html [64] http://www.avesta.org/vendidad/vd19sbe.htm#section1 [65] http://www.avesta.org/znames.htm http://www.cais-soas.com/CAIS/Religions/iranian/Zarathushtrian/zoroaster_name.htm [66] http://www.pantheon.org/articles/h/haoma.html [67] http://en.wikipedia.org/wiki/Gathas [68] http://www.reference.com/browse/wiki/Mithraism [69] http://thedevineevidence.com/prophecy_jesus.html [70] http://83.1911encyclopedia.org/M/MI/MITHRAS.htm [71] የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ [72] እዚህ የቀረበው የስእሉ መስመር ስለተበላሸ ይሆናል ያልኩትን በእረኞች ተከበበ ለሚሉት ማስረጃቸው የሚያቀርቡት አስቂኝ ስእልን ከስሩ አድርገነዋል፡፡ ከ1-4ኛ ክ.ዘመን ባለው ግዜ ስለሚትራስ የተጻፈ አንድም ታሪካዊ ማስረጃ የለም፡፡ ከክርስትና በኋላ በተጨመሩት ጽሑፎች ምክንያት ደግሞ ማን ከማን ቀዳ የሚል ክርክር ውስጥ መግባት አያስፈልግምም ነበር፡፡ [73] የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ [74] http://en.wikipedia.org/wiki/Messiah [75] http://www.reference.com/browse/columbia/Attis [76] http://www.pantheon.org/articles/a/agdistis.html [77] http://www.pantheon.org/articles/z/zeus.html [78] http://en.wikipedia.org/wiki/Sangarius [79] http://en.wikipedia.org/wiki/Nana_%28mythology%29 [80] http://www.pantheon.org/articles/g/great_mother.html [81] http://www.pantheon.org/articles/c/cybele.html [82] http://www.pantheon.org/articles/d/dionysus.html [83] የከሰረው የፀሃይ አምልኮን እና ክርስትናን የማገናኘት ሙከራ፡ ለአካርያ ኤስ. መጽሐፍ የተሰጠ መልስ [84] http://www.reference.com/browse/columbia/Semele [85] http://www.reference.com/browse/columbia/Hera [86] http://www.pantheon.org/articles/s/semele.html [87] http://www.pantheon.org/articles/p/persephone.html [88] http://www.pantheon.org/articles/d/dionysus.html [89] http://en.wikipedia.org/wiki/Titans [90] http://www.reference.com/browse/columbia/maenads [91] http://www.reference.com/browse/columbia/satyr [92] “ውርንጫውን በወይን ግንድ ያስራል፣ የአህያይቱንም ግልገል በወይን አረግ፤ ልብሱን በወይን ያጥባል፣ መጎናጸፊያውንም በወይን ደም፡፡ ዓይኑም ከወይን ይቀላል፤ ጥርሱም ከወተት ነጭ ይሆናል፡፡” ዘፍ. 49፣ 11፡፡ [93] http://en.wikipedia.org/wiki/King_Midas [94] http://www.pantheon.org/articles/a/anius.html [95] http://www.reference.com/browse/columbia/Tammuz [96] http://www.reference.com/browse/wiki/Esus [97] http://www.pantheon.org/articles/p/prometheus.html [98] http://www.pantheon.org/articles/q/quirinus.html [99] http://www.reference.com/browse/columbia/Romulus [100] http://www.pantheon.org/articles/b/bel.html [101] http://www.pantheon.org/articles/b/bali.html [102] http://www.pantheon.org/articles/v/vamana.html [103] http://www.pantheon.org/articles/o/orpheus.html [104] http://www.snopes.com/history/american/linckenn.htm