የመብት ህጎች እና ድንጋጌዎች የተቆለሉባት ግን የቤት ስራዋ የደቆሳት ሃገር

ምንሊክ ሳልሳዊ

ታዋቂነታችን በድርቅ በድህነት ብሎም በጭፍጨፋ ደሞ በሰብኣዊ መብት ጥሰት
የሕወሓት መራሹ ጁንታ ወደ ስልጣን በጠበንጃ ሃይል ከመጣ ጀምሮ በአለም አቀፍ ደረጃ የተደነገጉ የሰባዊ መብት ህጎችን ካለምንም ማርቅርቅ እና ድካም ከሌሎች በመገልበጥ በወረቀት ላይ ከማስፈሩም በተጨማሪ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት በአለም ላይ የሰው አገር ህግን እና አለማቀፍ ድንጋጌን ከሃገራችን ሁኔታ ጋር ሳይገናዘቡ በስፋት በደመነፍስ ለፍጆታ የተጻፈበት ሃገር ኢትዮጵያ ብቻ ሲሆን በየትኛውም አለም ሃገራት ያልተከሰተ የአለም አቀፍ ህጎችን ግልባጭ በከፊል በህገመንግስት እንዲሁም የገዢ ፓርቲን የፖለቲካ ፕሮግራም በከፊል ደባልቆ በጋር እንደ አውራ ህግ የወጣባት ሃገር ብትኖር ኢትዮጵያ ብቻ ናት::ኢትዮጵያ በታሪኳ ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ የመብቶች ሕጋዊነት በተጨበጨበለት ሁኔታ እና ይህ በማይባል ደረጃ የተደነገጉባት አገር ነች፡፡ እንግዲህ ይህ ሆኖ እያለ ነው በአገሪቱ የመብቶች ጥሰት ጉዳይ ከአገሪቱ ብሔራዊ አነታራኪ ፖለቲካዊ አጀንዳነት አልፎ ዓለም አቀፍ አጀንዳ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የቀድሞ መንግስትን ሽንፈት ተከትሎ በኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች የፍፃሜ ምዕራፍ ይሆናል ተብሎ ተስፋ ተደርጎ ነበር፡፡ ነገር ግን ጭራሽ ብሶበት ቁጭ አለ፡፡ የሕወሓት ወንበሩን መቆጣጠር ተንተርሶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተለይም ሒዩማን ራይት ዎችና አምነስቲ ኢንተርናሽናል የወያኔን ጁንታ በሰብዓዊ መብት ጥሰት በማብጠልጠል ነበር የተቀበሉት፡፡ ባለፉት ሃያ ሁለት ዓመታት የሰብኣዊ መብት ጥያቄዎች አቤቱታ ማሰማታቸውን አላቆሙም፡፡ ጋዜጠኞችን የሃሳብ ነጻነት ከሚገድብ ጥቃት በመከላከል ላይ የተሰማሩ የመብት አስከባሪ ድርጅቶችም ወያኔ በሚፈጥረው ከባድ የሰብኣዊ መብት ጥሰት በየጊዜው መክሰስ ሥራቸው ሆኗል::የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት በየጊዜው በሚያወጣው ዓመታዊ መግለጫው ወያኔን በሰብዓዊ መብት ጥሰትና የፖለቲካ መብቶችን ማፈን ይከሰዋል፡፡ ባሁን ወቅትየእነኚህን አካላት መግለጫዎች የታወቁ ዓለም አቀፍ መገናኛ ድርጅቶች በመቀባበል ኢትዮጵያ የዜጎቿን መብቶች በመጣስና በማፈን ወደር የሌላት አገር እንደሆነች ዓለም እንዲረዳው እያደረጉ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በአስከፊ ድርቅና ረሃብ ለመታወቅ እንደበቃችው ሁሉ ወያኔ የዜጎችን መብቶች በመጣስና በማፈን እንዲሁም በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጽመው ወንጀል በዓለም ላይ ታዋቂነትን እያተረፈ ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም;ወያኔ የፖለቲካ ተቀናቃኞችን መብቶች ለመጣስ ስለሚጠቀምባቸው ዘደዎች የሚቀርቡ ማስረጃዎች እና ማብራሪዎች እጅግ ዘግናኝ ናቸው፡፡የወያኔ መሪዎች የፖለቲካ ተቀናቃኖችን ለማዳከም ሲሉ ንፁኃንን ወንጀለኛ የሚያደርግ ዘዴዎችን ሥራ ላይ እንደሚያውሉ በተለያዩ ይፋዊ ሪፖርቶች ላይ ሁሉ ከነማስረጃው እየተነገረ ይገኛል::

የህ የሰብኣዊ መብጥ ጥሰት እየተባባሰ የሚሄድበት ምክንያት ወይኔ በአብዛኛው ካድሬዎች ዘንድ በስፋት ሰርጾ እንዲገባ ያደረገው የተቃዋሚዎች ጥላቻ እና እንዲሁም የተቃዋሚው ቡድን የትግል አቅጣጫው በተመሳሳይ መልኩ በጥላቻ ላይ የተመረኮዘ መሆኑ ነው::ተቃዋሚዎች የታጠቁ ሃይላት ባለመሆናቸው የመርሃቸው እንቅስቃሴ የተገደበ እና ለፖለቲካ እና ለሚዲያ ፍጆታ የዋለ ተዳፍኖ ይርሚገኝ ሲሆን የወያኔው ግን በታጠቁ የጸጥታ ሃይሎች እና በፖለቲካ ማጭበርበሮች ላይ ስለተመረኮዘ ካድሬዎቹ በተሰጣቸው የጥላቻ ተግዳሮት እና ወያኔያዊ ስልቶች የፈጠሩትን ጥቅማጥቅሞች ጠብቀው ለማቆየት ሲባል ጥላቻ በፈጠረው ፍርሃት ብቻ የሃገሪቱን ህጎች ዜጎች ለመጥለፍ እያዋሉት ነው::

ይህ ፍርሃት እና ጥላቻ በወያኔ ከትልቅ እስከ ትንሽ ካድሬዎች አናት ውስጥ ስር ለስር በመስደድ የፈጠረው ነገር ቢኖር ማንኛውም ዜጋ ተቃውሞ ካሰማ በወንጀለኛነት በመፈረጅ በማሳደድ በማጥፋት እረፍት ለማግኘት እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲራወጡ የህዝብን የበላይነት አፈር ከተውታል::ማእከላዊ የወያኔ ጁንታ በዲሞክራሲ ባለመወቀጣቸው የህጎችን የበላይነት ማረጋገጥ ካለመቻሉም በተጨማሪ በህዝብ እና በዲሞክራሲ ላይ በደሎችን የሚያደርሱ ባለስልጣናት የሚጠየቁት በሃገሪቱ የበላይ ህጎች ሳይሆን በወያኔያዊ የፓርቲ መመሪያዎች በመሆኑ በጥቅም መተሳሰር በፈጠርው ዝግ መንገድ የሰብኣዊ መብት ጥሰቶች እየተብራከቱም ከመሆኑ አልፎ የእለት ተእለት ተግባራት አካል ሆነዋል::
— at Minilik Salsawi.