የሰላም ዘቦች እሥር እና ግልብ “ፀረ-አክራሪነት” -የሁከት ናፍቆት

‘እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል’ - ልንዋጋው የሚገባ አህያዊ ብሂል!
- By Nasrudin Ousman

በኢሕአዴግ የሚመራው መንግሥት በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች መካከል የእርስ በርስ ጥርጣሬና ጥላቻ ለመፍጠር፣ ከተሳካም የሃይማኖት ግጭት ለመቀስቀስ በተለያዩ አቅጣጫዎች በጣም አደገኛና መርዘኛ የሆነ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ከፍቷል፡፡ “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” በሚል አህያዊ ብሂል ላይ የተመሠረተውን ይህንን እርኩስ ዘመቻ፣ ለዚህች አገር ህዝቦች ሰላምና ፍቅርን የሚመኝ ኢትዮጵያዊ በሙሉ አጥብቆ ሊዋጋው ይገባል፡፡ …

እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ያነሳናቸውና ተገቢ ምላሽ ያገኙ ዘንድ በሰላማዊ መንገድ የምንታገልላቸው ጥያቄዎች፣ መንግሥት በሃይማኖታችን ላይ የቃጣውን ዓይን ያወጣ ጣልቃ ገብነት መነሻ አድርገው የተነሱ እንጂ ድንገት ከመሬት ላይ የበቀሉ አይደሉም፡፡ [ከቶውኑ ድንገት ከመሬት ላይ የበቀሉ ጥያቄዎች የድፍን አገሪቱን ሙስሊሞች በአንድ መንፈስ በጋራ ሊያነቃንቁ ይቻላቸዋልን? ይህ የማይመስል ነገር ነው፡፡]

… መንግሥት ከ1987 አጋማሽ አንስቶ በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ላይ ያሻውን ሰው ሲሾም እና ተቋሙን በካድሬዎቹ ሲያሽከረከር እየታዘብን በዝምታ አሳልፈናል፡፡ ጠቅላይ ምክር ቤቱ ለህዝበ ሙስሊሙ ምንም የረባ መንፈሳዊም ሆነ ማኅበራዊ አገልግሎት የመስጠት ብቃት እንደሌለው፣ በህዝበ ሙስሊሙ ስም በተቋሙ የሚንቀሳቀስ የህዝብ እና የአገር ሀብት በአሳፋሪ ሁኔታ በግለሰቦች ሲመዘበር፣ በሐጅና ዑምራ ጉዞ በህዝበ ሙስሊሙ ላይ ከፍተኛ ብዝበዛ (ዝርፊያ) ሲፈፀም፣ የአርባ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ተቋም የሠፈር ዕድር እንኳ ለመምራት በማይበቁ መደዴ ግለሰቦች ሲመራ … ልባችን በሐዘን እየደማም ብዙ ዓመታትን በዝምታ አሳልፈናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲኾን፣ ከዚህ የተቋማችን አሳዛኝ ገፅታ ጀርባ የኢሕአዴግ እጅ እንዳለ ሳናውቅ ቀርተን አልነበረም፡፡ … መንግሥትን “በቃህ!” ለማለት የተገደድንበት ሁኔታ የተከሰተው ኢሕአዴግ ይህንኑ ተቋማችንን መሣርያ በማድረግ በአዲስ አስተምህሮ ሊያጠምቀን መጠነ ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረግ ከጀመረበት ከሐምሌ 2003 ወዲህ ነው፡፡ [… ይህ በስፋት የሚታወቅ በመሆኑ እዚያ ላይ ሀተታ አላበዛም፡፡]

የሰላም ዘቦች እሥር እና ግልብ “ፀረ-አክራሪነት”

እኛ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ባይኖረን ኖሮ፣ እንደ ተቋም አልባነታችን ከዓመታት በፊት ወደ አስከፊ የጥፋት መንገዶች ለመነዳት በተዳረግን ነበር፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መሪ አልባ ሁነው በቆዩባቸው ባለፉት አሥራ ዘጠኝ ዓመታት የሃይማኖት ጽንፈኝነት እና ነውጠኝነት ሊስፋፉ የሚችሉባቸው ብዙ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ እነዚህን ክፍተቶች የደፈናቸው የነቀዘው መጅሊስ ሳይሆን፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ውስጥ የበቀሉ በሳል አንጋፋና ወጣት የሃይማኖቱ ምሁራን ናቸው፡፡ በተለያዩ መድረኮች፣ እንዲሁም የትምህርትና መረጃ ማሰራጫ አውታሮች (መጻሕፍት፣ መጽሔት፣ ሲዲ፣ ወዘተ.) በሃይማኖት መቻቻልና ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር አብሮ በመኗኗር፣ የጎረቤትን ሐቅ (መብት) በመጠበቅ አስፈላጊነት፣ የጽንፈኛ አስተምህሮቶችን ጉድፍ እና አሉታዊ ገፅታ በማጋለጥ እነዚህ ወጣት እና አንጋፋ ምሁራን ሙስሊሙን ማኅበረሰብ በትጋት አስተምረዋል፡፡ እነዚህ አንጋፋና ወጣት የሃይማኖቱ ምሁራን በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 27 የተደነገገውን “የሃይማኖት፣ የእምነትና የአስተሳሰብ ነፃነት” በመጠቀም ለኢትዮጵያ ሙስሊም ማኅበረሰብ መንፈሳዊና ማኅበራዊ ህይወት መበልፀግ፣ እንዲሁም ህዝበ ሙስሊሙ ከሌሎች ሃይማኖት ተከታዮች ጋር በሰላም፣ በፍቅር እና በመከባበር የመኖር እሴትን በጥልቀት ተገንዝቦ ይህን እሴቱን እንዲንከባከብ በማስተማር ባይተጉ ኖሮ ኢትዮጵያዊው ሙስሊም በተለያዩ ኃይሎች ተፅዕኖ ውሉ በማይታወቅ አቅጣጫ የዕውር ድንብር በተጓዘና በተጋለበ ነበር፡፡ በእርግጥም የኢሕአዴግ መንግሥት ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ በኩል የሃይማኖት ጽንፈኝነት የሚያሰጋው ቢሆን ኖሮ፣ በኢትዮጵያዊው ሙስሊም ማኅበረሰብ ውስጥ የሰላምንና የአብሮ መኖር እሴቶችን ያሰረፁትን እነዚህን ድንቅ የማኅበረሰቡ አባላት (የሃይማኖት ምሁራን) በአጋርነት በማሰለፍ ስጋቱን በአስተማማኝ ሁኔታ የሚያስወግድ ውጤታማ ሥራ መሥራት በቻለ ነበር፡፡

የሁከት ናፍቆት

እጅግ የሚያሳዝነውና በአሁኑ ወቅት በገሃድ የሚታየው ግን፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ፍላጎት በአገሪቱ ላይ ሰላምንና የህዝቦች አንድነትን ማስፈን አለመሆኑ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የአገር ሰላምን እና የህዝቦችን በሰላም አብሮ የመኖር ትሩፋት በጽናት ሲሰብኩ የኖሩ የሙስሊሙ ማኅበረሰብ ወጣትና አንጋፋ የሃይማኖት ምሁራንን ዘብጥያ የወረወረው ከሰላም ፍፁም ተቃራኒ የሆነ እኩይ አጀንዳ በማንገቡ መሆኑ አሁን ግልፅ ሆኗል፡፡ ፍላጎቱ ሰላም ባለመሆኑም ነው፣ አልሳካልህ ያለውን ጽንፈኝነት ለመፈብረክ ነጋ ጠባ የሚደክመው፡፡ የህዝቦች ተፈቃቅሮ እና ተከባብሮ መኖር አልዋጥልህ ቢለው ነው ጽንፈኝነትን እና ሽብርን በዶኩመንታሪ ፊልም ለማቀናበር አለቅጥ ደፋ ቀና የሚለው፡፡ … የህዝቦች በሰላም መኖር፣ ሰላም ቢነሳው ነው በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች እና ክርስቲያኖች መካከል ጥላቻን ለመዝራት፣ ሁከትና የእርስ በርስ ግጭትን ለመጋበዝ ያለ አንዳች ኃፍረት በዘመቻ መልክ መንቀሳቀስ የጀመረው፡፡ …

… ዛሬ አመሻሽ ላይ አንድ ወንድሜ “ኢትዮጵያን ዳያስፖራ” የተሰኘ አሜሪካ ውስጥ የሚሰራጭ የራዲዮ ጣቢያ በቅርቡ ካሰራጫቸው ዝግጅቶች የቀዳቸውን የተወሰኑ ድምፆች ልኮልኝ ሳደምጥ የተረዳሁት ይህንን እና ይህንን ሐቅ ብቻ ነው፡፡ የኢሕአዴግ መንግሥት እና አጫፋሪዎቹ ለዚህች አገር እና ለህዝቧ ምን እየደገሱለት እንደሆነ ማሰብ በጣም ይዘገንናል፡፡ ምን ያህል አቅላቸውን ቢስቱ ይህንን ለማድረግ እንደወሰኑ ለእኔ ፈጽሞ ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ምን ያህል አዕምሯቸው ማሰብ ቢሳነው ነው የዚህ ተግባራቸውን ውጤት አስከፊነት ለመገመት ያልቻሉት ለሚለው ጥያቄዬ ፈጽሞ መልስ ላገኝለት አልቻልኩም፡፡ ሃይማኖትን በመሰለ ለሰዎች ስሜት እጅግ ቅርብ በሆነ ጉዳይ ላይ እንዲህ ያለ መርዘኛ የጥላቻ እና የግጭት ቅስቀሳ ያውም በራዲዮና በድረ ገፅ ማሰራጨት እንደምን ለአገር ሰላም አሳቢ ሊያሰኝ እንደሚችል አላውቅም፡፡ ከዓመታት በፊት በአንድ የአገሪቱ አካባቢ በተፈጠረ ሃይማኖት ነክ ሁከት ላይ ‹‹እንዲህ እና እንዲያ አደረጉን›› የሚሉ የሰዎችን ስሜት በመጥፎ መልኩ የሚኮረኩሩ መልዕክቶችን ማሰራጨት እውን ለአገር ሰላም ከማሰብ የመነጨ ነውን? … የመንግሥት ሥልጣን ከስኳር እንደሚጥም ቢያንስ መገመት አያቅተኝም፡፡ ፖለቲከኞች ከጠላት ጋር የሚደረግ ጦርነትን ለሥልጣን ዕድሜ ማራዘሚያነት እንደሚጠቀሙባትም አውቃለሁ፡፡ ነገር ግን በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲባል ለረዥም ጊዜ ሊገዙት የሚሹትን የራስን አገር ህዝብ በሃይማኖት ለማጋጨት ታጥቆ መነሳት፣ ፖለቲካዊ ጥበብ ሳይሆን “እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል” ያለችውን አህያን መሆን ይመስለኛል፡፡ አላህ ከአህያነት ይጠብቀን!!

ኢሕአዴግ ህዝበ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ ጋር ለማጋጨት ታጥቆ በተነሳበት በአሁኑ ወቅት ከወደ አሜሪካ እንዲህ ያለ መርዘኛ ፕሮፖጋንዳ በራዲዮና በድረ ገፅ መሰራጨቱ፣ አገራችን እና ህዝቧ ምን ያህል ከባድ አደጋ እንደተደቀነባቸው በግልፅ ያሳያል፡፡ ምንም እንኳ እንዲከሰት የሚናፍቁት የህዝቦች የእርስ በርስ ግጭት ቢከሰት (በአክራሪ እና በጽንፈኛ ዲስኩራቸው) ሙስሊሙን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚንደረደሩ ግልፅ ቢሆንም፣ አደጋው ግን በሙስሊሙ ላይ ብቻ የተደቀነ አለመሆኑን መላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ክርስቲያኑም ጭምር በውል ሊገነዘበው ይገባል፡፡ በዚህ ግንዛቤ ላይ በመመሥረትም፣ ይህን በእኛ በኢትዮጵያውያን ላይ የተደቀነ ወቅታዊ አደጋ ወይም ፈተና፣ የረዥም ዘመናት አብሮ መኖር ባስተማረን ትዕግስት፣ ብልሀትና ጥበብ በአሸናፊነት ለመወጣት የየድርሻችንን ኃላፊነት እንወጣ እላለሁ፡፡ ይህንንም ለማድረግ የኃያሉን ፈጣሪያችንን እገዛ እማፀናለሁ፡፡ …

ላለፉት ሁለት ዓመታት እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም፣ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩ የእምነት ወንድምና እህቶቼ ጋር ለሃይማኖት ነፃነቴ መከበር በሰላማዊ መንገድ እየታገልኩኝ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ነገር ግን የሃይማኖት ነፃነቴ መከበር ከሚያስጨንቀኝ ባላነሰ፣ ምናልባትም በበለጠ የኢሕአዴግ መንግሥት ህዝበ ክርስቲያኑን ከሙስሊሙ የማጋጨት ዕኩይ ሤራ ያስጨንቀኛል፡፡ እናም በአላህ ፈቃድ እና እገዛ ይህንን ዕኩይ ሤራ እስከ መጨረሻው አምርሬ እታገላለሁ፡፡ ለእኔ ከዚህ በላይ ኢትዮጵያዊነት የለም፡፡

… ቅኑን መንገድ በተከተሉ ሁሉ ላይ ሰላም ይስፈን፡፡ የዓለማት ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ከክፋት ኃይሎች ክፋት ይጠብቅልን፡፡ አሚን፡፡
_______________________
*መልዕክቴን ከተጋራችሁት፣ በሰሌዳችሁ ላይ ለሌሎች ብታጋሩት ደስ ይለኛል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡