ሊበሏት ያሰቧትን....የአዲስ አበባ መስተዳደር እና አዲሱ ጥቃት ህገመንግስቱን እና ሌሎች አዋጆችን አፈር የሚያበላቸው ማነው? 
ምንሊክ ሳልሳዊ
የአዲስ አበባ ጎረምሳው መስተዳደር ተግባራዊ አደርገዋለሁ በሚለው መሪ እቅዱ በግንባርቀደምትነት ጡንቻውን አጠንክሮ ለተቃዋሚዎች ትብብር ያደርጋሉ በሙስና ተጨማልቀዋል የሚላቸውን አመራሮቹን እና ህገመንግስታዊ ስርኣቱን ለመናድ አሰፍስፈዋል ያላቸውን ተቃዋሚዎች በማስጠንቀቅ አምርሮ ወቅሷል::

መስተዳደሩ መጀመሪያ ደረጃ ስርኣቱ ከአናቱ በሙስና የተጨማለቀ እና የገማ መሆኑን እየታወቅ አባቴ ሲበላ እኔም አብሬ ልብላ የሚሉ ከፍተኛ እና መካከለጫ አመራሮች በሙስና ቢዘፈቁ አይደንቅም:: ይህ በአደባባይ በመሬት ሽያጭ ስራዎች እንዲሁም በጉዳይ ማስፈጸም በህገወጥ ንግዶች እንዲሁም በአፈና ዙሪያ ከፍተኛ ወንጀሎች እንደሚታዩ የታወቀው ዛሬ አይደለም ይህ የተለመደ እና የታወቀ ጉዳይ ነው:: ማስፈራራቱ ለምን አስፈለገ በርቱልን ነው:: የስርኣቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ እስካልተለወጠ ድረስ በታማኝነት እና በካድረነት የሚቀጥሩ ሰዎች የማስጠንቀቂያው ሰለባ አይሆኑም :: የዚህ ሰላባ እና ተጠቂ የሚሆኑት አስተሳሰባቸው እና አመለካከታቸው በፖለቲካው ለየት ያሉ ሰዎችን ተቃዋሚዎችን ይተባበራሉ ተብለው የሚጠረጠሩትን አጥምዶ በሙስና ስም ወህኒ ለመወርወር የታቀደ እንጂ የሙስና ጉዳይ እኮ አዲስ ነገር አይደለም::

በአዲስ አበባ ውስጥ የሚያሳስቡ ህዝባዊ ጉዳዮች በስፋት እያሉ በፖለቲካው መስክ ሊደረጉ በታቀዱ አፈናዎች እና ቁጥጥሮች ዙሪያ አጥብቆ የሚወተውተው የመስተዳደሩ ሰነድ ከፍተኛ አመራሩን በተመለከተ ሲተነትን፣ ሥራን በቁርጠኝነት ከመሥራት ይልቅ ያዝ ለቀቅ የሚታይበት በመሆኑ ሥራው በሚፈለገው ጥራትና መጠን እየተፈጸመ ነው ለማለት እንደማይቻል ገልጾ፣... አመራሩ በሥራው የመሰላቸትና በተወሰኑ ሥራዎች የመርካት ዝንባሌዎች ይታዩበታል ይላል፡፡ ይህ ማለት ከፍተኛ አመራሩ በስርኣቱ ላይ ተስፋ መቁረጡን ያመለክታል:: ስርኣቱ የለውጥ ሳይሆን የፖለቲካ ማጭበርበር እንዲሁም በበላይነት የሚመሩ ሰዎች በሙስና መዘፈቃቸው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት እና ተመሳሳይ ጉዳዮችን ሲመለከት የወያኔ ኢዲሞክራሲያዊ የውስጥ አሰራሮች ተጨማምረው ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሩ ለስርኣቱ ያላቸው አመለካከት መሞቱን እና ተስፋቸው መሟጠጡን ያመለክታል::
ያልገባን ኪራ ሰብሳቢነት ኪራይ ሰብሳቢነት የሚሉት አባዜ ነው:: ራሳቸው የሚያዩበትን መስታውት ማየት ሲገባቸው ህዝቡ እና ተቃዋሚው አይደለም እኮ ኪራይ ሰብሳቢ እና ሙሰኛ ...እነዚህን ቃላቶች ለሚዲያ ፍጆታ ከማዋል እና በአስተሳሰብ የተለዩ የውስጥ ለውጥ ፈላጊዎችን ወደ እስር ቤት ለማጋዝ ከመጠቀም ውጪ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም::

የመጀመርያው ችግር የሥነ ምግባርና የኪራይ ሰብሳቢነት ነው የሚለው ሰነዱ፣ የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር የሚታይባቸው መካከለኛ አመራሮች ቁጥር ቀላል አይደለም ይላል፡፡ይህን ከማውራት ለኛ ሰብስቦ ለፍርድ ማቅረብ የተሻለ ነው:ሰነዱ በሌላ አነጋገር አርፋችሁ ብሉ ተቃዋሚዎችን አትደግፉ ካልሆነ ዋ አይነት ማስፈራሪያ የሚሰነዝር ይመስላል:: የመሬት ወረራ፣ ሕገወጥ ግንባታና፣ ሕገወጥ ንግድ በየአካባቢያቸው ሲስፋፉ አይተው እንዳላዩ የሚያልፉ፣ አልፎ ተርፎም ከሕገወጦች ጋር የሚደራደሩ ሽፋን የሚሰጡ፣ በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚደለሉ በመርህ ላይ ተመሥርተው ከመታገል ይልቅ በኔትወርክና በቡድንተኝነት ላይ የተመሠረተ መጠቃቃት የጎላ ችግር መሆኑ የታወቀው ዛሬ ሳይሆን ስር የሰደደ ጉዳይ ነው::

አዲስ አበባ እና ተቃዋሚዎች

ሰነዱ በምን መስፈርት ተቃዋሚዎችን እንዳስቀመጠ እና በየትናው የፖለቲካ ሞራሉ እንደተቸ የሚገርም ነው ይህ የመስተዳደሩ ሰነድ በተቃዋሚዎች ላይ የሰነዘረው ሃሳብ ህገመንግስቱን ከለምንም ጥያቄ ደፍጥጦታል:: በህጉ መሰረት እውቅና አግኝተው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ተቋማት ተቃዋሚ ብቻ በመሆናቸው በነገር እየዘለዘሉ ለማስፈራራት መሞከር ተጠያቂነቱ የበረታ መሆኑን መስተዳደሩ አላወቀውም:;እንዲህ አይነት አጓጉል ውንጀላ ይሰራል ለተባለውም ልማት ከፍተኛ እንቅፋት ነው::

ያለው ስርኣት ህገመንግስታዊ ስርኣት ለመሆኑ በቂ ማረጋገጫ ስርኣቱ ራሱ ሊያቀርብ አይችልም:: ስርኣቱ በራሱ በዘፈቀደ አርቅቆ እና አጽድቆ የሚያወጣቸውን ህጎች በማክበር እየኖሩ የሚገኙት ተቃዋሚዎች እና ህዝቡ እንጂ የገዢው ፓርቲ ካድሬዎች እና አጋሮቻቸው እንደፈለጉ በህጉ ላይ ሲፈነጩ እያየን ነው::እንዲሁም ከህዝብ በሚሰበሰብ ግብር ደሞዝ የሚከፈለው ፖለስ እና ወታደር እንኳን ሳይቀር ማፊያዊ ተግባራትን በህዝብ ላይ እየፈጸመ ነው:;

በመጀመሪያ ደረጃ የመስተዳደሩ ከንቲባ እና ካቢኔ የተሾሙት ህዝብን ለማገልገል ነው ወይንስ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶችን የትግል ስልት እየተከተሉ ለመዋጋት...ሳይታሰብ በደፈናው ለአፈና ብቻ ተብሎ የተጻፈ ሰነድ መሆኑ በግልጽ ያስታውቃል:ተቃዋሚውን ለመጉዳት ህገመንግስትን ሽፋን አድርጎ የሰላማዊ ሰልፍ እና የስብሰባ ፕሮግራሞችን ለማገድ መንቀሳቀስ በራሱ ስርኣቱ ለህገመንግስቱ ያለውን ንቀት ያሳያል::በሃይማኖት ሽፋን ምናምን መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ አይገባም ተደጋጋሚ ኢሕኣዴጋዊ ቃላቶች ህዝቡን ሰልችተውታል::እባካችሁ ማሰብ ጀምሩ ውሸት ሲደራረብ ውነት ይሆናል የሚለው በህዝቡ ዘንድ ስለተነቃባችሁ በሚቻላቹ መጠን የተቃዋሚዎችን ስልት ለማኮላሸት ከመሮጥ ይልቅ ራሳችሁ አዲስ ስልት ለራሳችሁ ቀይሱ::


ወደ ተግባር ለመለወጥ የታቀደው ይህ አፋኝ ሰነድ የኑሮ ውድነትን የመልካም አስተዳደርና ሌሎች ብሶት ይቀሰቅሳሉ ብለው ያሰቧቸውን ችግሮች በማራገብ፣ ሕዝብን ለማነሳሳትና የተለያዩ ሰላማዊ ሠልፎችን እያካሄዱ ነው::... አዎ ታዲያ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ያነሱ ሰዎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይል በመናድ የህዳሴ ጉዟችንን ማደናቀፍ ነው፤ በማለት ወደ ወህኒ ለመወርወር አሰፍስፏል:: ህዝባዊ ጥያቄዎችን አንግቦ ለውጥ መፈለግ ጸረ ሰላም እና ጸረ ህገመንግስት አያስብልም ::ለህዝባዊ ጥያቄዎች ምላሽ ላለመስጠን መንደፋደፍ ምን አመጣው? የጥፋት ሴራ ስርኣቱ እንጂ ህዝባዊ ጥያቄዎች ይመለሱ የሚሉ ህዝቦች አይደሉም::