አሜሪካን የበጀት ቀውስ ውስጥ የከተተው ከአሜሪካ ሕዝብ ይልቅ በፓርቲ ፖለቲካ ሽኩቻሁለት ሚሊዮን የመንግሥት ሠራተኞች ባሉባትና በዓለም ላይ ከፍተኛ የቱሪስቶች መዳረሻ በሆነችው አሜሪካ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይዘጋሉ ብሎ ለማሰብ ያዳግታል፡፡

ሆኖም ከማሰብም ባለፈ በአሜሪካ ይህ እውን ሆኗል፡፡ በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ ያሉት ዴሞክራቶችና ሪፐብሊካኖች ሰሞኑን የቀረበውን የበጀት ሰነድ ማፅደቅ ላይ ባለመስማማታቸው፣ አገሪቷን ከ17 ዓመታት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግሥት በጀት ቀውስ ውስጥ ከተዋታል፡፡ 

አሜሪካን የበጀት ቀውስ ውስጥ የከተተው የፖለቲከኞች ውሳኔ

ለመንግሥት መሠረታዊ አገልግሎቶች አዲስ በጀት ለማፅደቅ የተቀመጡት የዲሞክራቱና የሪፐብሊካኑ ኮንግረስ አባላት ባለመስማማታቸው ሳቢያ፣ ማክሰኞ መስከረም 21 ቀን 2006 ዓ.ም. 800,000 የአገሪቱ የመንግሥት ሠራተኞች ቤታቸው ያለ ሥራ ቁጭ እንዲሉ ተገደዋል፡፡

ቢቢሲ እንደዘገበው ከማክሰኞ ጀምሮ ቤታቸው እንዲቀመጡ የተነገራቸው የመንግሥት ሠራተኞች ከሥራ ለቀሩባቸው ቀናት የኋላ ክፍያ የማሰቡ ነገርም የሞተ ነው፡፡ የአሜሪካ ውሳኔ ሰጪ ፖለቲከኞች ልዩነታቸውን ማጥበብ ባለመቻላቸውም የመንግሥት ሠራተኞች ያለዋስትና ቀርተዋል፡፡ በአሜሪካ ምክር ቤት ከፍተኛ መቀመጫ ያላቸው ሪፐብሊካኖችና በሴኔቱ ከፍተኛ መቀመጫ ያላቸው ዲሞክራቶች አንዱ የአንዱን ድምፅ በመጣልና ለመደራደሪያ በማቅረብ ከአሜሪካ ሕዝብ ይልቅ በፓርቲ ፖለቲካ ሽኩቻ በመጠመዳቸው፣ ሁለት ሚሊዮን የሚደርሱ የመንግሥት ተቀጣሪዎችን አደጋ ላይ ጥለዋል፡፡ 

የአሜሪካ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ለቀጣዩ ሦስት ሳምንታት በከፊል መዘጋት በመንግሥት ሠራተኞች ላይ ከሚፈጥረው የኑሮ ቀውስ በተጨማሪ፣ የአገሪቱን ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ኢኮኖሚ) በተያዘው ሩብ ዓመት ብቻ በ0.9 በመቶ እንደሚቀንሰው ጎልድማን ሳክስ ገምቷል፡፡

ጤናና ትምህርትን ለመሳሰሉ መሠረታዊ አገልግሎቶች የተቀመጠውን አዲስ በጀት ሪፐብሊካኑ ላለማፅደቅ በወሰኑበትና ከዲሞክራቶቹ ጋር መግባባት ባልቻሉበት መሠረታዊ የመንግሥት አገልግሎቶች በጀት ምክንያት፣ የዋይት ኃውስ በጀት ቢሮ የመንግሥት ኤጀንሲዎች ቢሮዎቻቸውን በከፊል እንዲዘጉ አዟል፡፡ 

ይህንን ተከትሎ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በትዊተር ገጻቸው ‹‹በምክር ቤቱ ውስጥ የሚገኙት የሪፐብሊካን ቡድኖች ትክክለኛውንና ዋናውን በጀት ከማፅደቅ ይልቅ፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲዘጉ ጫና አድርገዋል፤›› ሲሉ አስፍረዋል፡፡

የአሜሪካ ምክር ቤት የሪፐብሊካን አፈ ጉባዔ ጆን ቦህነር ሴኔቱ በአዲሱ በጀት ላይ ከስምምነት እንደሚደርስ ተስፋ እንዳላቸው በመግለጽ፣ ‹‹የአሜሪካውያን ችግር ይፈታል፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሜሪካውያን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲዘጉ አይፈልጉም፡፡ እኔም አልፈልግም፡፡ ሆኖም አዲሱ የጤና ኢንሹራንስ ሕግ የሚፈጥረው ተፅዕኖ አዋጭ አይደለም፡፡ መስተካከል ያለበት ጉዳይ አለ፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡ 

የቢቢሲ ዋሽንግተን ዘጋቢ ማርክ ማርዴል በአሜሪካ የተከሰተውን የመንግሥት በጀት ቀውስ አስመልክቶ፣ ‹‹የአሜሪካ ፖለቲከኞች ጥላቻ ውስጥ መግባት መንግሥት ሥራውን በአግባቡ እንዳይሠራ እስከመድረስ ተካሯል፤›› ሲል ተናግሯል፡፡ 

የአሜሪካ ሴኔት አባላት አዲሱን የመሠረታዊ አገልግሎት በጀት ማፅደቅ ባለመቻላቸው 19 ያህል ሙዚየሞች፣ ጋለሪዎች፣ ብሔራዊ የእንስሳት መጠለያዎችና ፓርኮች ተዘግተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ከመከላከያ ክፍል 400,000፣ ከንግድ ክፍል 30,000፣ ከኃይል ክፍል 12,700፣ ከትራንስፖርት ክፍል 18,481 ሠራተኞች ተጐጂ ሆነዋል፡፡ 

የአየር ትራፊክ ቁጥጥር፣ ብሔራዊ ደኅንነትና የኑክሌር ጦር መሣርያና ኃይልን ሳይጨምር ሁለት ሚሊዮን ሠራተኞችን ያቀፉትን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፊል መዘጋት አሜሪካና አሜሪካውያንን ዋጋ ያስከፍላል ተብሏል፡፡ 

የአዲሱ በጀት አለመፅደቅ የትምህርት ክፍሉ ለመንግሥት ትምህርት ቤቶች የያዘውን 22 ቢሊዮን ዶላር በቀጣይ ለማከፋፈል ቢያስችለውም፣ ሠራተኞችን ግን በከፋ ደረጃ ተጐጂ ያደርጋቸዋል፡፡ የፖስታ አገልግሎት እንደነበረ ቢቀጥልም፣ የጡረታ ክፍያና የባለሙያዎች ጥቅማ ጥቅም ይዘገያል ተብሏል፡፡ የፓስፖርትና የቪዛ ማመልከቻዎች ደግሞ አይስተናገዱም፡፡

በጀቱ ባለመፅደቁ ሪፐብሊካኖች እየተወቀሱ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ የሴኔቱ አባላት ‹‹እንደ ሦስት ዓመት ሕፃናት ስብስብ ይቆጠራሉ›› ሲል አንድ የኬንታኪ ነዋሪ ተናግሯል፡፡

አሜሪካውያንና ባለሥልጣኖቻቸው በሰላም ተንፍሰው ለመንቀሳቀስ የወታደራዊ ክፍሉን ጨምሮ የመንግሥት ሠራተኞች ሚና ከፍተኛ ቢሆንም፣ ‹‹ፖለቲከኞቹ በጀቱን አለማፅደቃቸው የሚያበሳጭ ነው፤›› ብሏል፡፡ 

የኦባማ የጤና ኢንሹራንስ ሕግ ተፈጻሚ እንዳይሆን የሚፈልጉ የሪፐብሊካን ሴኔት አባላት ለመሠረታዊ አገልግሎቶች የተያዘውን የመንግሥት በጀት ባለማፅደቅ እንደመደራደሪያ መያዛቸውም እያስተቻቸው ነው፡፡ 

ፕሬዚዳንት ኦባማም ‹‹የጤና ኢንሹራንስ በጀት አለ፡፡ ይህንን ማስቆም አትችሉም፡፡ እናንተ የማትፈልጉት ሕግ ስላለ ብቻ የምታሳልፉት ያልተገባ ውሳኔ አያሸልማችሁም፤›› ብለዋል፡፡ 

እ.ኤ.አ. በ1995 በተመሳሳይ 96 ያህል የአሜሪካ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች በከፊል ለ21 ቀናት በመዘጋታቸው፣ ሪፐብሊካኑ በምርጫ የአሜሪካን ሕዝብ ድምፅ እንዲያጡ ማድረጉን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡