የቤተሰብ ‹‹ጆሮ ጠቢነት››...ባልና ሚስትን በ1ለ5 …… ‹‹ደህንነትን›› በ1ለ5 ....

Imageካድሬ በሁሉም ስርዓቶች ቢኖሩም ‹‹ጥርነፋው›› ግን የግራና ግራ ዘመም ፓርቲዎች መለያ ነው፡፡ አንድ ግለሰብ፣ ወይንም የማዕከላዊ ኮሚቴና ፓርቲ የሚመራው ዕዝ ስርዓትም የኢህአዴግ አንዱ መገለጫ ነው፡፡ ይህ የእዝ ካድሬያዊ ስርዓት በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተጠናከረ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ ይሰራበት ከነበረው ካድሬያዊ የዕዝ ስርዓት ባሻገር በቅርቡ የግራ ዘመሙ ዘመን ላይ በፖለቲካው ተሳታፊ ያልነበሩት አቶ ሀይለማሪያም አማካሪ በነበሩበት ወቅት 1ለ5 ተብሎ የሚጠራውን አዲስ የጥርነፋ ስርዓት ለፓርቲያቸው አበረከቱ፡፡ ይህ ‹‹አደረጃጀት›› የተለያዩ ማህበረሰቦችን ለመያዝ በሙያና በእድሜ ሳይቀር ትግበራ ላይ ውሏል፡፡ አርሶ አደሮች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች ሰራተኞች ድረስ የገባው 1 ለ5 አሁን ደግሞ ቤተሰብ ድረስ ወርዷል፡፡ ባልና ሚስትም ድረስ!

‹‹ደህንነትን›› በ1ለ5 …… … ……… … በግብርናው፣ በትምህርት ቤቱና በሌሎች ተቋማት ሰዎች አምስት አምስት እየሆኑ እንዲደራጁ እየተደረገ ነው፡፡ ይህ ኢህአዴግ ውጤታማ ነው የሚለውን አደረጃጀት ተከትሎም ሰዎች 10 ሆኑ ከዚያ በላይ አሊያም ከዚህ ቁጥር በታች ብቻ የአደረጃጀት አይነቱ አቶ ሀይለማሪያም ባስጀመሩት በ1ለ5 መጠራቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ምክንያቱም ከቁጥሩ ውጭ ሌላው አሰራሩ በ1ለ5 ላይ ከሚሰራበት ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ነው፡፡ ከወራት በፊት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን “አገራዊ የማሕበረሰብ አቀፍ ፖሊሳዊ አገልግሎት” ረቂቅ ህግ አዘጋጅቶ ተቃዋሚዎችን ጨምሮ ለይስሙላህ አወያይቶ ነበር፡፡ የረቂቁ አላማ ወንጀልን ለመከላከል ማህበረሰቡን ማሳተፍ የሚል ሲሆን ለዚህም ከላይ እስከታች በ1 ለ5 አደረጃጀት ማዋቀር አለበት፡፡ ለዚህም ሲባል ህዝብን በቀበሌ፣ በብሎክ፣ በጎጥ፣ በመንደር እንደ አመችነቱና በየ አቅራቢያው ማደራጀትን ይጠይቃል፡፡

ይህ ረቂቅ ህግ ጸድቋ ተግባር ላይ ውሏል፡፡ ፖሊሶች በተለያዩ የከተማይቱ ክፍሎች በር እያንኳኩ የመደራጃውን ቅጽ ከአደሉ ሰነባብተዋል፡፡ ባለ አንድ ቅጽ ወረቀቱም ‹‹የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ፕሮጀክት የቤተሰብ ፖሊስ ተጠሪ ማቋቋሚያ ቅጽ›› የሚል ‹‹ርዕስ›› ተሰጥቶታል፡፡ ቅጹ የ10 ያህል ቤተሰቦች ስምና ፊርማ ዝርዝር እንደሚቀመጥበት አድርጎ ያስቀመጠ ሲሆን አንድ ተወካይ ስምና ፊርማም አስፈላጊ ነው፡፡

በመግለጫውም ‹‹ይህ የቤተሰብ ፖሊስ (ተወካይ) ማቋቋም ያስፈለገበት ዋና አላማ በቤተሰብዎ መካከል ለሚፈጠር ጸጥታ ችግሮች ማለትም አለመግባባቶች የተለያዩ ማህበራዊ ግጭቶች ወዘተ የመሳሰሉት ሲፈጠሩ እርስዎ የቤተሰብዎ ወኪል እንደ ፖሊስ ሆኖ በቅርበት ከፖሊስ ጋር እየተወያየ/የች የማስታረቅ የማስማማት ስራ እንዲሰራ እና ችግሩን እየተከታተለ በቅርበት መፍትሄ እንዲሰጥና መፍታት ያልተቻለውን ነገር በአካባቢው ከተመደቡት የፖሊስ አባላት ጋር ለመፍታት ታስቦ ነው፡፡›› ይላል፡፡

ፖሊስ አስታራቂ ወይስ…? በአዲሱ ህግ መሰረት አንድ ግቢ ውስጥ የሚኖሩ ባልና ሚስት በ1ለ5 አደረጃጀት መሰረት ይጠረነፋሉ፡፡ ባልና ሚስት እየተቀያየሩ የኮሚሽነርነትን ስልጣን ይወስዳሉ፡፡ በየትኛውም ባልና ሚስት መካከል የሚፈጠር አለመግባባት በእነዚህ ሁለቱ መካከል ሲፈጠርም የወቅቱ የቤተሰብ ‹‹ኮሚሽነር›› ከፖሊስ ጋር ‹‹እየተወያየ በሁለቱ መካከል ያለውን እሰጣ ገባ ለመፍታት›› ይጥራል፡፡ ባል ወይንም ሚስት ራሱን ወክሎ ብቻ አንዱ አንዱን ከፖሊስ ጋር ሲያማ እንደመዋል ማለት ነው፡፡ የሁለቱ ችግር በዚህ ሁኔታ ካልተፈታ ደግሞ ጉዳዩ ወደ ፖሊስ እንዲያመራ ይደረጋል፡፡ ከባልና ከሚስት መካከል ጊዜያዊ ስልጣን ባገኘው ውሳኔ!

በባልና ሚስት መካከል ከአስቤዛ፣ ከድሮ የፍቅር ግንኙነትና ሌሎች ለልጆችና ለጎረቤትም የማይነገሩትን የግጭት ምክንያቶች የሚነሱ አለመግባባቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህ የዘወትር ጭቅጭቆች አንድም በስካር አሊያም በሌላ ገፊ ምክንያት ወደ ባሰ አለመግባባት ቢያመሩ ችግሩ የሚፈታው ባል ወይንም ሚስት ራሷን/ራሱን ወክለው ከፖሊስ ጋር በሚያደርጉት ውይይት ነው፡፡ ጎረቤት፣ ዘመድ አዝማድ፣ ለጉዳዩ ሽምግልና ከመግባቱ በፊት የሚደርሰው ለፖሊስ ነው፡፡ ችግሩ ቢብስ እንኳ ለፍርድ ቤትም ሆነ ለዘመድ አዝማድ የሚመራው ተወካዩ መሰረት ‹‹ሪፖርት›› የተደረገለት ፖሊስ መሆኑ ነው፡፡ ምክንያቱም አዲሱ አሰራር ይፈጠራል ብሎ ለሰጋው ችግር ይወያያል፣ ይከታተላል፣ ይፈታል የሚለው ፖሊስን በመሆኑ ነው፡፡

የቤተሰብ ‹‹ጆሮ ጠቢነት›› …… እስከ ቤተሰብ የወረደው ፖሊስ መር ጥርነፋ ‹‹ለህዝብ ደህንነትን ማስጠበቅ›› የሚል አላማ ተሰጥቶታል፡፡ ጥርነፋው የቤተሰቡን አባል ባህርይ፣ ማን ከማን ጋር እንደሚኖር፣ ማን ‹‹ከጸባዩ›› እንደታረመ፣ ማን እንዳልታረመና ሌሎች ቀስ በቀስ ፖሊስ ከወኪሎቹ የሚያገኘውን መረጃም ለመስጠት የሚያስችል አዲስ ስልት ነው፡፡ የቤተሰቡ አባላት ከማን ጋር እንደሚውሉ፣ ፖለቲካዊ አመለካከታቸው፣ እምነታቸው፣ የኢኮኖሚ ምንጭና ሌሎቹም ጭምር የሚያመላክቱ መረጃዎች ይሰበሰብበታል፡፡ ምን አልባትም በቅርቡ በሚንስትር ደረጃ ከተቋቋመው የደህንነት መስሪያ ቤት ይልቅ የእያንዳንዳንዱን ዜጋ ዝርዝር መረጃ ለመሰብሰብ ይጠቅማቸዋል፡፡ ቤተሰብን የወከለው አካል በየደረጃው ‹‹ደህንነትን መከላከል፣ ከህገወጦች መራቅ፣ ህገወጦችን ከማህበረሰቡ ማግለል›› በሚሉና በመሳሰሉት የተለያዩ ውይይቶችን ያደርጋሉ፡፡ በምርጫ ሰሞንም ቢሆን ይህ ቤተሰባዊ አደረጃጀት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡