እንደ ኢህአዴግ ፈሪ ፓርቲ ከወደየት አለ?

እንደ ኢህአዴግ ፈሪ ፓርቲ ከወደየት አለ? ጌታቸው ሺፈራው

beዚህ ጽሁፍ መግለጽ የምፈለግው የኢህአዴግን መጠነሰፊ ፍርሃት ያሳያሉ ያልኳቸውንጥቂት ምሳሌዎች ነው፡፡ እስካሁን እንደ ኢህአዴግ ፈሪ ፓርቲ አጋጥሞኝ ስለማያውቅም እንደ ኢህአዴግ ፈሪ ድርጅት ከወደየት አለ? ብሎ መጠየቁ አግባብ መስሎ ታይቶኛል፡፡ ፈሪው ድርጅት ‹‹የለም ከእኛ በላይ ፈሪ ድርጅቶች እዚህ እዚህ…አገር ይገኛሉ›› የማለት መብቱ የተጠበቀ ነው፡፡ እንዲያውም እስካሁን የነበረበትን ከፍርሃት የመነጨ ድብቅነት በጥቂቱም ቢሆን እንደቀነሰ እንረዳለታለን፡፡ በድፍኑ ‹‹አይ እኛ ፈርተን አናውቅም!›› ቢል ግን ያው የተለመደ ስለሆነ የሚያምነው አያገኝም፡፡ ደግሞስ እየፈሩ ‹‹አልፈራንም›› ማለት ምን ማለት ነው? ‹‹አልፈራንምንስ ምን አመጣው? ኢህአዴግ የሚፈራውን ከመዘርዘር ይልቅ ራሱ የማይፈራቸው ነገሮች ካሉ ቢነግረን የተሻለ ነበር፡፡ እኔ ግን ከሚፈሯቸው ነገሮች መካከል በጣም ጥቂቶቹን ብቻ በመጥቀስ የፍርሃቱን መጠን ለማሰየት እሞክራለሁ፡፡ ህገ መንግስቱን ለብሄር ብሄረሰቦች መብት መከታ ነው የሚባለው የወቅቱ ህገ መንግስት የአቶ መለስና ለንጮ ለታ የፖለቲካ ማህተም ያረፈበት እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ ይህ ህገ መንግስት እንደ አንቀጽ 39ን ያሉትን ጨምሮ ስለ የመሬት ፖሊሲ፣ አንድነትና ሌሎች ጉዳዮች ያለው ህጸጽ እንዳለ ሆኖ ከነ ድክመቱም ቢሆን ቢተገበር አሁን ካለንበት ብልሹ ፖለቲካ የተሻለ ስርዓት ሊመሰርት እንደሚችል ይታመንበታል፡፡ በተለይ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የአመለካከትና ሌሎች ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶችን ከዳር ዳር ከማጨቅ ውጭ ተግባራዊ ሲሆኑ አይታዩም፡፡

Image

ከተግባራዊነቱ ይልቅ ለይስሙላህነቱ እንዲውል ተደርጓል፡፡ ይህም የሆነው ህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት አብዛኛዎቹ መርሆች ተግባራዊ ቢሆኑ የገዥውን ፓርቲ ስልጣን የሚያሳጡ መስለው ስለሚሰሙት ነው፡፡ እናም ኢህአዴግ ‹‹ባለ ራዕዩ›› መሪ በበላይነት መርጠው ያጸደቁትን ህገ መንግስቱንም ቢሆን ለመተግበር ይፈራዋል፡፡ ስለሆነም በተቻለ መጠን ህገ መንግስቱ ላይ ያሉት መርሆች ተግባራዊ የማይሆኑበትን አጋጣሚ ሁሉ ይጠቀማል፡፡ ለዚህ አተገባበሩ የዳኝነት ሰርዓቱን ጨምሮ በጉዳዩ ተያያዥነት ያላቸውን አካላት የገዥውን ፖሊሲ የሚያቀነቅኑ እንዲሆኑ ጥሯል፡፡ ይህ ግን በቂ አልነበረም፡፡ በተለይ በ1997 በኋላ ኢህአዴግ እንደ አንዳች ነገር የሚፈራቸው ወሳኝ የህገ መንግስቱ መርሆች በጸረ ህገ መንግስት አዋጆች ታጥረው ተቀምጠዋል፡፡ የጸረ ሽብር፣ የሶቪክ ማህበራት፣ የፓርቲዎች የስነ ምግባር፣ የሚዲያ…..አዋጆች ህዝብን ብቻ ሳይሆን ህገ መንግስቱን አሽገው ለህዝብ እንዳይቆም ያደረጉ አዋጆች ናቸው፡፡ ተወዳዳሪ ፓርቲን ኢህአዴግ መድብለ ፓርቲን መርህን እቀበላለሁ እያለ የጠንካራ ፓርቲዎችን መኖር ግን በእጅጉ ይፈራል፡፡ ለዚህም ሲባል ከፓርቲዎች ጋር አብሮ ከመስራት ይልቅ ተገንጣዮችን በመፈልፈል የኢትዮጵያን ፓርቲዎች ከ80 በላይ አድርሷቸዋል፡፡ በእርግጥ ይህ የጠንካራ ፓርቲ ‹‹ፎብያ›› የጀመረው ህገ መንግስቱ ላይ ‹‹የበድብለ ፓርቲ›› በስምም ቢሆን ከተፈቀደ በኋላ አይደለም፡፡ ህወሓት በዱር እያለም ፓርቲዎችን ከዚህም በላይ ይፈራቸው እንደነበር ታሪኩ ያስረዳል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ኢህአፓ ከህወሓት ጎን ለጎን አብሮ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ ይሁንና የኢህአፓ ህብረ ብሄርነት ህወሓት የቆመለትን የመገንጠል ፖሊሲ አደጋ ላይ በመጣሉ ህወሓት ‹‹ከትግራይ መሬት ውጡልን ይህ የትግራይ ህዝብ መሬት ነው›› ብሎ አባረረው፡፡ የትግራይ አርነት ግንባርን (TLF)ንም የትግራይ ህዝብ ከአንድ በላይ ፖለቲካ ፓርቲ መሸከም አይችልም ብሎ አጥፍቶታል፡፡ እንዲያውም የትግራይ አርነት ግንባር አባላት ከህወሓት ጋር ለመደራደር ከተስማሙ በኋላ በተኙበት በህወሓት መጨፍጨፋቸውንና ይህን ዘግናኝ የጭፍጨፋ ሂደት አንዳንድ የህወሓት አባላት ለህዝብ ይፋ አድርገዋል፡፡ እንደራደር ብሎ የመጡትን ፖለቲከኞች መጨፍጨፍ መቼም ጀግንነት፣ ድፍረት ሊሆን አይችል፡፡ ኢህአዴግም እየተጠቀመበት የሚገኘው ይህን የህወሓትን የፍርሃት ልምድ ነው፡፡ ገና ስልጣን እንደያዘ ጠንካራ ከሚባሉት ኦነግ፣ ኦብነግና ሌሎች የብሄር ድርጅቶችን ጋር ከጥርጣሬም አልፎ አለመግባባት ውስጥ ገባ፡፡ በምትካቸው ደግሞ እንደ ኦህዴድ፣ ሶዴፓ ያሉ ደካማ ፓርቲዎችን ተገን ማድረግ ጀመረ፡፡ ለጠንካራ ፓርቲዎች በርካታ ደካማ ተገን ፓርቲዎችን የሚፈጥረው ኢህአዴግ ከመቼውም በላይ ስለፈራ 80 ያህል ደካማ ፓርቲዎች አገሪቱን ተፍልፍለዋል፡፡ ኢህአዴግ ተቃዋሚዎቹን ብቻ ሳይሆን አብረውት እየሰሩ የሚገኙትንም ቢሆን ‹‹በአጋር ፓርቲነት›› ስም ብቻ ፖለቲካውን ከእርቀት እንዲመለከቱ እያደረገ ነው፡፡ በአገሪቱ የረባ የፖለቲካ ተሳትፎ የሌላቸውን እነዚህ ፓርቲዎች ያፈነግጡብኛልበማለትም የህወሓት/ኢህአዴግን አማካሪዎች በተቆጣጠሪነት ከማስቀመጥ ጀምሮ መረዎቻቸውን በተለያየ መንገድ ማግለል የተለመደ የፖለቲካው እቃ እቃ ጨዋታ ሆኗል፡፡ የሶማሊ፣ ጋንቤላና ቤንሻንጉልን ህዝቦች ስም ‹‹አጋር›› የሆኑት እነዚህ ፓርቲዎች መሪዎቻቸው ከአዲስ አበባ በተላከ ትዕዛዝ በተደጋጋሚ ገለል የሚደረጉት ያፈነግጡብኛል ብሎ ስለሚፈራቸው ነው፡፡ የአገር አንድነትን ኢህአዴግ የአንድነት ፍርሃት የሚጀምረው እስካሁንም ድረስ የትግራይን ህዝብ ነጻ ለማውጣት የቆምኩ ነኝ የሚለውን ስሙን ለመቀየር ከሚፈራው ህወሓት ነው፡፡ የህወሓት የተገንጣይ ስምም ቢሆን እስካሁን የማይቀየረው አንድነት ይቅርና ፌደራሊዝሙም ላይ ፍራቻ ሳላለው ይመስላል፡፡ ከዚህ ውጭ የትኛውም አንድነትን የሚወክል ወይንም የሚያንጸባርቅ ነገር ለህወሓት/ኢሀአዴግ ያስበረግገዋል፡፡ ልክ እንደ ህወሓት/ ኢህአዴግ ሁሉ የኢትዮጵያ አንድነትን የሚጠላው ሻዕቢያ መጀመሪያ የተረባረበው የአንድነት ዋነኛው መገለጫ የሆነው ሰንደቅ አላማው ላይ ነበር፡፡ ሻዕቢያ ባልታጣ መቋጠሪያ የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ዋነኛው የዱቄት መቋጠሪያው አድርጎ ተጠቅሞበታል፡፡ በለስ (ቁልቋል) ሳይቀር የሚሸመጥጡት በኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ እንደነበር ይነገራል፡፡ ህወሓት በተለይ መጀመሪያ አካባቢ ትጥቅም ሆነ ስንቅ (ዱቄት) ይቀበል የነበረው ከሻዕቢያ ነውና ከሻዕቢያ የተለየ ተግባር ሊፈጽም እንደማይችል መገመት ቀላል ነው፡፡ አቶ መለስ ስልጣን ከያዙ በኋላ ስንደቅ አላማውን ጨርቅ ያሉት ከሻዕቢያ በወረሱት የአንድነት ፍርሃት መሆኑን እንረዳለን፡፡ ሁለቱም ድርጅቶች ይህ በደል የፈጸሙት ከሰንደቅ አላማው በስተጀርባ ያለውን አንድነት በእጅጉ ስለሚፈሩት ነው፡፡ ኢህአዴግ ለዚህ የረዥም ጊዜ ፍርሃት መሃል ላይ ያስቀመጠው ኮከብም ፍርሃቱን ሊያስወግድለት አይቻለም፡፡ አቶ መለስ ከመሞታቸው ከወራት ቀደም ብለው ሰንደቅ አላማውን የዘቀዘቁት አሁን ባለው ቅርጹም ቢሆን ስለሚፈሩት ይመስለኛል፡፡ ዛሬም ቢሆን ኢህአዴግ ራሱ መጥኖ በጠራው ጉዳይ ካልሆነ በስተቀርሰ ህዝብ በስፋት ባለኮከቡን ሰንደቅ አላማ በክብር ሲያነሳም ብርክ ይይዘዋል፡፡ አማራጭ ሚዲያን ኢትዮጵያ በሚዲያ ወደኋላ ከቀሩት አገራት መካከል የመጀመሪያዋ ናት፡፡ ለ90 ሚሊዮን ህዝብ ያለን አንድ ፕሮፖጋንዳ የሚሰራጭበት ቴሊቪዝን ጣቢያ ብቻ ነው፡፡ በአንጻሩ 6 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ላኦስ፣ ሁለት ሚሊዮን ህዝብ ያላት ጃማይካ፣ አንድ ሚሊዮን ህዝብ ያላት ትሪንዳድና ቴቪጎ እያንዳንዳቸው የግልን ጨምሮ ባለ ሰባት ጣቢያዎች ናቸው፡፡ 400 ሺህ ህዝብ ያላት ማልታ 8፣ 36 ሺህ ህዝብ ያላት ሞናኮ 5 ጣቢያዎች ለህዝባቸው አማራጭ መረጃ ያስተላልፋሉ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር የሚነጻጸር ህዝብ ያላቸው አገራት ደግሞ በርካታ ጣቢያዎች ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ ለአብነት ያህል ከኢትዮጵያ ጋር በአባይ በኩል የምትተሳሰረው ግብጽ 98 ያህል ጣቢያዎች ባለቤት ነች፡፡ ከኢትዮጵያ ህዝብ ከግማሽ ያነሰ ህዝብ ያላት ጎረቤት ኬንያ እንዲሁም 34 ሚሊዮን ህዝብ ያላት ዩጋንዳ እያንዳንዳቸው 8 ጣቢያ ያላቸው ሲሆን አብዛኛዎቹ የግል ሚዲያዎች ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ሚዲያ ይህን ያህል ከአገሪቱ ታሪክም ይሁን ህዝብ ጋር የሚቃረን የሆነው ኢህአዴግ በእጅጉ ስለሚፈራው ነው፡፡ ሚዲያ ህዝብን ያነቃል፣ ሙስናንና ሚስጥርን ያጋልጣል፣ አንድነትን ያጠናክራል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሲቪክ ማህበራት አማራጭ ሀሰብ ህዝብ ዘንድ እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ይህ የነቃ ማህበረሰብ የሚፈጥረው ሚዲያ ደግሞ ለአንድ ፓርቲና ግለሰብ የበላይነት ጸር ነው፡፡ ለህዝብ ልዓላዊነት እንጅ ለ‹‹አውራ ፓርቲ›› አያመችም፡፡ ስለሆነም ኢህአዴግን ከምንም በላይ ያስፈራዋል፡፡ ለዚህም ነው 90 ሚሊዮን ህዝብ አሰልች ፕሮፖጋንዳ በሚነዙ የመንግስት (ፓርቲ ሚዲያዎች) ብቻ የተወሰነው፡፡ በፍርሃቱ ምክንያትም የህትመት ሚዲያው አሳሩን ሊበላ የግድ ሆኖበታል፡፡ ህገ መንግስቱም ሆነ አዋጁ አማራጭ (የግል) ሚዲያን አይከለክልም፡፡ እንዲያውም በአዋጁ የብሮድካስት ሚዲያም በግል እንደሚፈቀድ ሁሉ አስቀምጧል፡፡ ይህ በሆነበት ግን አንድም የግል ቴሊቪዥን ጣቢያ የለንም፡፡ ሚዲያ ህዝብን እንደሚያነቃ የሚያውቀውና ይህንን የሚፈራው ኢህአዴግ ኢሳትን ጨምሮ በርካታ ሚዲያዎችን ለመዝጋት አገሪቱን ከፍተኛ ገንዘብ በማባከን ላይ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አልጀዚራም ጭምር የታገደበት አጋጣሚ ተፈጥሯል፡፡ አማራጭ ሀሳብ የሚተላለፍበትን ሚዲያ እንዲህ የሚጠላው ‹‹አብዮታዊ›› ፓርቲ ፌስ ቡክን እንኳ ንቆ አልተወውም፡፡ በርካታ ፌስ ቡክ ላይ የሚጽፉ አካላት ጽሁፋቸው አገር ውስጥ እንዳነበብ ይደረጋል፡፡ እስክንድር ከታሰረባቸው ምክንያቶች ቀዳሚው ፌስ ቡክ ላይ በሚጽፋቸው ትንታኔዎቹ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ልክ የቻይና እና የኢራን አምባገነን ፓርቲዎች በአንድ ወቅት እንዳደረጉት ፌስ ቡክን ሊዘጋ እንደሚችል እየተነገረ ነው፡፡ ሰላማዊ ሰልፍና የአደባባይ ሰልፍ በኢህአዴግ ዘንድ የሚፈራ ብቻ ሳይሆን የሚጠላም ተግባር ለመሆን ደርሷል፡፡ ታይቶ ከጠፋው የ1997 ምርጫ በኋላ ለአለፉት 8 አመታት ከድጋፍ ሰልፍ ውጭ የህዝብ ሮሮ የሚሰማባቸው ሰላማዊ ሰልፎች በግልጽም ሆነ በተዘዋዋሪ ታግደው ቆይተዋል፡፡ ባለፉት ስድስትና ሰባት ወራት የሰላማዊ ሰልፍ መብት እንደገና ተመልሶ የነበር ቢሆንም አሁን ግን እንደገና ታግዷል፡፡ ኢህአዴግ ሰላማዊ ሰልፍን ብቻ ሳይሆን አደባባዮችንና ጎዳናዎችን ኢትዮጵያዊ ታህሪር እንዳይሆኑ አብዛቶ ፈርቷል፡፡ ለአብነት ያህል 97ት ላይ ክፉኛ የደነገጠበት መስቀል አደባባይ ለድጋፍ ሰልፍ እንጅ ለሰላማዊ ሰልፍ ክልክል ሆኗል፡፡ ከዚህ አለፍ ሲልም ኢትዮጵያውያን ኳስ እንዳያዩበት ሁሉ እየተደረገ ነው፡፡ የናይጀሪያንና የኢትዮጵያን ጨዋታ መስቀል አደባባይ ላይ ለመመልከት ሰንደቅ አላማ ለብሰው የጎረፉ ኢትዮጵያውያን ደጋፊዎች ተደብድበው ተመልሰዋል፡፡ ሀይማኖት፣ ግለሰባዊነት፣ ነጻ ተቋም… ብቻ ኢህአዴግ የማያስፈራውን ነገር ቢናገር ይሻል ነበር፡፡ በእርግጥ አቶ ሀይለማሪያም ደሳለኝ ‹‹አንፈራም!ፓርቲው እንደማይፈራ ታሪኩ ይናገራል፡፡›› ብለውናል፡፡ እዚህ ላይ አቶ ሃይለማሪያም እንደተለመደው ተሳስተው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም እሳቸው አይፈራም ብለው ለመከራከር የፈለጉት አርሳቸው ያልነበሩበትን የኢህአዴግን የጠብመንጃ ታሪክ ነው፡፡ መሳሪያ ያነሳ ሁሉ ግን ደፋርም ጀግናም አይደለም፡፡ እንዲያውም ፈሪ ዱላው፣ ጠብ መንጃው፣ መሳሪያው፣ መሰሪነቱም ከልክ በላይ በርካታዎች ናቸው፡፡ ከእነ ተረቱም ቢሆን የፈሪ ዱላ ይባላል እኮ፡፡ ፈሪ ይህን ያህል ጉዳት ሊያደርስበት የማይችለውን አካል ሁሉ ያለ አቅሙ ይደበድባል፡፡ በራሱ አይተማመንምና እንደገና እንዳያስፈራራው ያወድመዋል፡፡ አይደለም አንዳች የሚንቀሳቀስን አካል ይቅርና ጥላውን እንኳ አያምንም፡፡ የመዋጋት፤ የማሰር፣ የመፈረጅ ታሪክ ከዚሁ ከፈሪነት ባህሪው የመነጩ ናቸው፡፡ በአንጻሩ ደፋር ለመርህ ይታገላል፡፡ ለአቆመው ህግና ስርዓት ራሱንም የሚሰዋ ታማኝ ነው፡፡ ያቆመውን ስርዓት፣ አብሮት የሚኖረውን አካልና ራሱን ያምናል፡፡ በህዝብና በአገሩ ስለሚያምን፣ በራሱ ስለሚተማመን ህዝብን በፍቅር ያቀርባል፣ ተቀናቃኙን በፍቅር ይስባል እንጅ በግድ ወደኔ ካልመጣህ ብሎ ለማጥፋት ከሆነ አንዳች ነገር ፈርቷል ማለት ነው፡፡ ያኔ ፈርቷል፣ ተፍረክርኳል፣……ይባላል፡፡ ልክ እንደ ኢህአዴግ!