የየካቲት አብዮትን ልዩ አስተዋጽኦ ክዶ ‹ኢትዮጵያዊነት›ን መላበስ አይቻልም፡፡

Image ምኒልክ ሳልሳዊ ብሎግ

የዘውዱ መንግሥት ከውስጡ በስብሶ የሚገፋው ብቻ እንደሚያሻው ሁሉም የለውጥ ወገኖች ባወቁበት ወቅት፣ ከተማሪውና ከምሁራኑ መካከል ቀርቶ ከታጠቀው ወታደር በኩል እንደሚታወቀው ለጊዜው መፍትሔ ተገኘ፡፡ ንጉሡ ከዙፋናቸው ተባረው፣ መሳፍንቱ ከየመንበራቸው ተወርውረው፣ ቀጥሎም ባለርስቱ ከንብረቱ ተላቆ አገሪቱ ወደ ሌላ ደረጃ ተሸጋገረች፡፡ ሕዝቡ የሚመኛቸውና ታጋዮች በየአቅጣጫው ሲጣጣሩላቸው የነበሩት ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ ባይፈቱም አገሪቱ ከዘውድና ከባላባታዊ ሥርዓት ተላቀቀች፡፡

የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ እጅጉን ሊጠናና ሊመረመር የሚገባው መሆኑ የማያከራክር ቢሆንም፣ በመጪው የካቲት 2006 ላይ 40ኛ ዓመቱን የሚሞላው አብዮት በተመለከተ ግን በታላቅ ክብረ በዓል ልንቀበለው የሚገባ ነው፡፡ በተለይ ውድ ሕይወታቸውን ሳያቅማሙ ላበረከቱት ወገኖች፣ ተሰውተውም ቢሆን በሕይወት ተርፈው ባሉበት ሁኔታ፣ ይህ ታሪካዊ ዕለት የራሳቸው የግል የሕይወት ምዕራፍ ተደርጐ ሊታሰብላቸው ይገባል፡፡ በሕይወት ያሉትም ሆኑ ተወላጆቻቸው እንዲሁም ወጣቱ ትውልድ በአጠቃላይ የራሱን ወገን መብት፣ ክብርና ህልውና በአዲስ መልክ ማዋቀሪያና ማቀፊያ ሆኖ የተነሳውን የካቲት 1966ን መልሶ ሊዘክረው፣ ሊያውቀውና ሊያቅፈው ይገባል፡፡

አብዮት የከበደ፣ መራርና በደም የተለወሰ ማኅበራዊ ነውጥ ነው፡፡ ጥቂቶች ተመልሶ የማይገኝ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ደረጃቸውን ያጣሉ፡፡ ብዙኃኑ ግን እግር ተወርች ተጠፍረው ከሚኖሩበት ሥርዓትና ሕይወት ተላቀው ወደ አዲስ ጐዳና ይገባሉ፡፡ ለውጡ ወዲያውኑ ለብዙኃኑ ሕዝብ ገነትን አይፈጥርም፡፡ ይህ ዓይነት አካሄድና ሁኔታ የመጀመሪያው ሕዝባዊ አብዮት በተካሄደባት በሃይቲም፣ ከዚያ በቀጠለው በፈረንሳይም፣ በሜክሲኮም፣ በሩሲያም፣ በካሜሩንም ታይቷል፡፡ የየካቲት የኢትዮጵያ አብዮት ከእነዚህ ሁሉ በአነሳሱም ሆነ ባቀፋቸው ኃይሎች ስብጥር በጣም የሚለይባቸው ምክንያቶች ስለነበሩ በሒደቱም በውጤቱም እንደዚያው ነበር፡፡

አንዳንዶች የየካቲት አብዮትን ሲያነሱ ያንገፈግፋቸዋል፡፡ በዜና ማሰራጫዎች በተለይ የማጥላላት ዘመቻ ሲካሄድ ውሎ አድሯል፡፡ የየካቲት አብዮትን ከደርግ አስተዳደር ጋር በማምታታት ይመስላል አንዳንዶች ይህ የሚሰማቸው፡፡ ነገር ግን የዛሬዋ ኢትዮጵያ መሠረት የተጣለው የየካቲት አብዮት ባስገኛቸው ድሎች ወይም በፈጠራቸው አማራጭ የለሽ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መዋቅሮች ላይ ነው፡፡ ደርግ ተገዶ የየካቲትን አብዮትን ቃላትና አልባሳት ተውሶ የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄዎች በከፊል መልሶ በአምባገነንነት አገሪቱን በጦርነትና በደም ቢያጥባትም የየካቲት አብዮት ጥፋት አይደለም፡፡ የሕዝብ ወገኖች ነን ባዮች ኃይላቸውን አስተባብረው አብዮቱን እንዳነሳሱ  ሁሉ ወደ ግቡ ሳያደርሱት ቢቀሩ ተጠያቂው ያው አብዮት ሊሆን አይችልም፡፡ በተለይ ደግሞ ደርግን በመደገፍና በመቃወም ዙሪያ የተከሰተው መተላለቅ ያንኑ አብዮት በተከሳሽነት አያስመድበውም፡፡

ለማንኛውም የየካቲት 1966 ዓ.ም 40ኛ ዓመት ይከበር ሲባል ከደርግ ጭፍጨፋ በፊት ገና ደርግ የሚባል ነገር ባልታሰበበት ወቅት የተከሰተውን ሰማይ ሰበር ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ትርዒት ነው፡፡ በወቅቱ በሕይወት የነበሩም ሆኑ ገና ያልተወለዱ ይህን የአገራችንን የታሪክ ጉልላት መለስ ብለው ሊያስታውሱት፣ ሊያስቡት፣ ሊመረምሩትና ሊያወድሱት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የራሳቸውን ማንነት የገነባውን ታላቅ ታሪካዊ ምዕራፍ እንዳልነበረ ወይም የጥፋትና የእልቂት ምልክት አድርጐ በአንዳንድ ወገኖች የሚነፋውን የውሸት ትረካ ማመን የለባቸውም፡፡ እውነተኛው መንገድ የአገሪቱን የገነገነ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሥርዓት ከሥሩ እንዲነቀል ያስቻለውን ታሪካዊ ዕልልታ መቀበልና ማወደስ፣ ድክመቱንና ጥንካሬውን መርምሮ ትምህርት መቅሰም ነው፡፡

ነገር ግን ይህንን የፈጠጠና በታሪክ መዝገብ የሰፈረ ትርዒት ተረግጠው ዘለው ሄደው፣ ያልነበረ የውሸት ሀተታ እየበዘበዙ የ1966 አብዮትን እንዳልነበረ ከአዕምሯቸው አውጥተው ጥለው፣ የአገሪቱ ወጣት ትውልድም ማንነቱን እንዳያውቅ ማድረግ ምሕረት የማይሰጠው ጥፋት ይሆናል፡፡ የየካቲት አብዮትን ልዩ አስተዋጽኦ ክዶ ነገር ግን ባዶነትን ሸፋፍኖ ‹ኢትዮጵያዊነት›ን መላበስ አይቻልም፡፡ ምን ላይ ተቁሞ የራስን ታሪክ በተውሶ ታሪክ፣ የራስን ባህል በተቀዳ ባዕድ ባህል ለመተካት ለሚሹ ምርጫቸውን መተቸት አይቻል ይሆናል፡፡ ሆኖም አገሬና እናቴ እያሉ ለሚዘፍኑ፣ ለሚቀኙ፣ ለሚሟገቱ፣ ትንታኔ ለሚያቀርቡና በየመድረኩ ለሚፎክሩ ሁሉ የወቅቱ አንድ ትልቅ ፈተና ይኸውና እፊታችሁ ተደቅኗል እንላቸዋለን፡፡ የየካቲት 1966ም 40ኛ ዓመት በዓል ለማክበር መነሳሳት፡፡

በዓሉን ለማክበር የሚሹ ሁሉ በየፊናቸው መደራጀት ይችላሉ፡፡ ሁሉም በአንድ አዳራሽ፣ በአንድ መድረክ፣ በአንድ አገር መሆን የለበትም በዓሉን ለማክበር፡፡ ዋናው ነገር ማክበሩ ነው፡፡ በየዘርፎችና በየመገናኛ ብዙኃኑም እንደዚሁ ለየብቻቸው ወይም በተባበረ መልክ ማክበር ይችላሉ፡፡ ሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ጋዜጦች፣ ቴአትር ቤቶች፣ ወዘተ ወቅቱን ተንተርሰው የየራሳቸው ዝግጅት ማድረጋቸው የማይቀር ነው፡፡ ለበዓሉ ዝግጅት የሚነሱትንና በተግባር የሚሠለፉትን ሁሉ ይበል፣ እሰይ እንላቸዋለን::
 የየካቲት 1966 አብዮት 40ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በተመለከተ  ምኒልክ ሳልሳዊ  ብሎግ ለሚነሱ አስተያየቶች ጸሐፊውን አስፋ አሰፋ አንደሻው በኢሜይል አድራሻቸው etfeb74@gmail.com ማግኘት ይቻላል፡፡