የነቀዘው ስርዓት ‹‹ህሊናዎች›› ……………

Getachew Shiferaw.
 ህወሓት/ኢህአዴግ ስለአንዳንድ ግለሰቦችን ብቻ ንቅዘት ቢያወራም የፓርቲውንና ስርዓቱን መበስበስ ግን ከህዝብ የተደበቀ አይደለም፡፡ እናም አንድ ቀን ከአክሱሙ ዘረፋ ጀምሮ በተመዘበረ የህዝብ ገንዘብ የተቋቋሙትን የፓርቲ ድርጅቶች ህዝብ ማስመለሱ አይቀርም፡፡ ከሞሶቦ እስከ ዳሸን፣ ከመስፍን ኢንጅነሪን እስከ ጥቁር አባይ፣ ትራንስ፣ ወጋገን፣ ……….ለህዝብ ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አስርት አመታት ስራ የሚገኘው በብቃት ሳይሆን በዝምድና፣ በጓድነት፣ በብሄር ትስስር፣ በታማኝነት፣ በፓርቲ አባልነት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ እነዚህን ሰራተኞች ይቆጣጠራል ተብሎ የተቋቋመው ደግሞ የሲቪል ሰርቪስ ሚንስትር ነው፡፡

ፍትህም ቢሆን በዝምድና፣ በጓድነት፣ በብሄር ትስስር፣ በታማኝነት፣ በፓርቲ አባልነት እንደተመሰረተ ቀጥሏል፡፡ የፍትህ ስርዓቱ በበላይነት ሊቆጣጠር ተብሎ የተቋቋመው የፍትህ ሚንስትር ፍትህን ባለመሳሪያዎች እንደፈለጋቸው የሚያደርጉት፣ በገንዘብ የሚገዛ፣ የስልጣን መጠቀሚያ ከመሆን አላዳነውም፡፡ የአገሪቱ የውጭ ንግድ እና ሌሎች ገቢዎችን ለመቆጣጠር የተቋቋመው ጉምሩክም ቢሆን ከላይ እስከታች የነቀዘ ስለመሆኑ ከመላኩ ፈንታ መታሰር በፊት ህዝብ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡

ታዲያ እነዚህ የነቀዙ ተቋማት ‹‹ስፖንሰር›› ያደረጉት ‹‹የነቀዙ ህሊናዎች›› የሚል ዶክመንተሪን ተመለከትኩ፡፡ እንደ ኢህአዴግ ባለ የነቀዘ ስርዓት ውስጥ ስለ ጥቂት የነቀዙ ህሊናዎች ማውራት እንዴት ይቻላል? ከወራት በፊት ታዋቂው ‹‹the richest.org›› ድህረ ገጽ አቶ መለስ ባለፉት 22 አመታት 54 ቢሊዮን ያህል የኢትዮጵያ ብር ማካበታቸውን ይፋ አድርጓል፡፡ ይህ ገንዘብ በዚህ አመት ሁሉም ክልሎች ከተመደበላቸው አጠቃላይ በጀት በ11 ቢሊዮን ብር ይበልጣል፡፡

በተመሳሳይ ወቅት የአቶ መለስ ልጅ ለንደን ውስጥ ከ5 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ እንዳላት ተዘግቧል፡፡ የአባትና ልጁ ገንዘብ በዚህ አመት ሙስናው የሚበላውን ጨምሮ ለ90 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ከተመደበለት በጀት ጋር ተመጣጣኝ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ኢሳት ‹‹the mystery of Eyasu Berhe's death›› በሚል እንደሰራው ዶክመንተሪ ከሆነ በአገራችን ወደ ውጭ ማስደወል የጀመሩት እነ ወይዘሮ አዜም መስፍን ናቸው፡፡ እነ እያሱና አዜም በአንድ ወቅት ብቻ እንኳን ከ500 በላይ ዲሾችን አስገብተው ከሙስናው ያልራቀውን ቴሌን በሚጎዳ መልኩ ሲያስደውሉ ኖረዋል፡፡ ከፍተኛ ጀኔራሎች፣ ባለስልጣናት፣ ዘመድ አዝማዶቻቸው፣ ኢህአዴግን የተጠጉ ባለሀብቶች፣ ካድሬዎችና ሌሎች የስርዓቱ አካላት በርካታ ካርታዎች፣ ቤቶችና ገንዘብ ባለቤቶች ናቸው፡፡ በትንሹ ባለፉት 20 አመታት አገራችን የሚችሉትን ያህል ጠብተዋታል፡፡ ህዝብ ደግሞ የማይችለው የድህነት አዘቅጥት ገብቷል፡፡

ከ1983 ጀምሮ ከተራ ታጋይ ጀምሮ የህንጻ፣ የመኪናና ሌሎች ንብረቶች ባለቤቶች ሆነዋል፡፡ አንዳንዴ ይህን ያህል እየተዘረፍን በርሃብ ከምድረ ገጽ አለመጥፋታችንም ያስደንቀኛል፡፡ ኢትዮጵያ ግን ምኑን ቻለችው? ይህ በሆነበት ነው እንግዲህ ጥቂት ህሊናቸው የነቀዙ ግለሰቦችን የሚያቀርቡልን፡፡ ኢህአዴግ ውስጥ ማን ነው ያልነቀዘው? ከአናቱ የገማው ስርዓት ውስጥ ስለጥቂቶቹ መለስተኛ ጥፋት ማውራት ሽፍኑን ለሌላ ንቅዘት ከመጠቀም ውጭ ምን ሊባል ይቻላል?

የነቀዘ ስርዓት ህሊና አይኖረውም፡፡ አለው እንኳን ከተባለ ያው የነዘቀዘ ነው፡፡ ታምራት ላይኔን፣ ስዬ አብርሃን፣ መላኩ ፈንታን የነቀዙ መሆናቸው የሚያከራክር አይደለም፡፡ ችግሩ የእነዚህ ግለሰቦች ንቅዘት ግን ከእነ መለስ፣ አባዱላ፣ አዲሱ፣ በረከት፣ ሽፈራው ሽጉጤ………(ስንቱ ይጠቀሳል?) ቢያንስ እንጅ የሚበልጥ አለመሆኑ ነው፡፡ ቢያንስ እነዚህ ሰዎች ቀድመው ታስረዋል፡፡ ሌሎቹ ግን አሁንም እየዘረፉን ቀጥለዋል፡፡ ከአምስትና ስድትስ አመት በላይ ስልጣን ላይ የቆየው ታምራት የተከሰሰው ልዩነት በፈጠረባቸው ጥቂት ወራት ውስጥ ‹‹ሰረቀው›› በተባለው ብቻ ነው፡፡ በአራትና አምስት ወር በሚሊዮኖች ከሰረቀ በስድስት አመት ውስጥ ስንት ዘርፎን ይሆን?

ህወሓት ለመጀመሪያ ጊዜ ገንዘብና መሳሪያ ያገኘበት ዘመቻ ‹‹የአክሱም ዘመቻ›› ይባላል፡፡ መሳሪያና ሌላውን ቁሳቁስ ትተን በዚህ ዘመቻ በገንዘብ እንኳ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 175 ሺህ ብር ዘርፏል፡፡ ይህ በአሁኑ የጸረ ሽብር ዘመቻ በሽብርተኝነት ያስፈርጃል፡፡ ከዚህ ዘመቻ በኋላ ከሻዕቢያ ጋር በጋራ በተደረጉ ዘረፋዎችም ህወሓት የድርሻውን ሲወስድ ቆይቷል፡፡ ደርግ እየተሸነፈ በሄደበት ወቅት ደግሞ ለኢህዴንና ለኦህዴድ ለቅምሻ ብቻ እያካፈለ በርካታ ገንዘብ አካብቷል፡፡ በስተመጨረሻም ኢፈርትንና ሌሎች የፓርቲ ተቋማት አቋቁሟል፡፡ ብአዴን፣ ኦህዴድ፣ ደኢህዴን…… እና ሌሎችም ህወሓት ከፍሎ ከሰጣቸው የየራሳቸውን የፓርቲ ድርጅቶች አቋቁመዋል፡፡ እነዚህ ኦዲት የማይደረጉና በቢሊዮኖች የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች ለፓርቲውና ለፖለቲከኞቹ ካልሆነ ለህዝብ የረባ ጥቅም እየሰጡ አይደለም፡፡

ምንም እንኳ ህወሓት/ኢህአዴግ ስለአንዳንድ ግለሰቦችን ብቻ ንቅዘት ቢያወራም የፓርቲውንና ስርዓቱን መበስበስ ግን ከህዝብ የተደበቀ አይደለም፡፡ እናም አንድ ቀን ከአክሱሙ ዘረፋ ጀምሮ በተመዘበረ የህዝብ ገንዘብ የተቋቋሙትን የፓርቲ ድርጅቶች ህዝብ ማስመለሱ አይቀርም፡፡ ከሞሶቦ እስከ ዳሸን፣ ከመስፍን ኢንጅነሪን እስከ ጥቁር አባይ፣ ትራንስ፣ ወጋገን፣ ……….ለህዝብ ሊመለሱ ይገባቸዋል፡፡