የነገ ታህሳስ 3 ቀጠሮና የትግላችን የወደፊት አቅጣጫ!

የነገ ታህሳስ 3 ቀጠሮና የትግላችን የወደፊት አቅጣጫ!
ረቡእ ታህሳስ 2/2006

በማዕከላዊ ከህግ አግባብ ውጪ ለወራት ኢሰብዓዊ የሆነ ስቃይና ቶርቸር ሲፈጸምባቸው በቆዩት ኮሚቴዎቻችን ላይ የተከፈተውን የሀሰት ክስ በማየት ላይ ያለው ችሎት የዐቃቤ ህግ ምስክሮችንና መረጃዎችን ከተመለከተ በኋላ ‹‹ተከሳሾቹ ከክሱ ነጻ ናቸው ወይስ መከራከር ይጠበቅባቸዋል›› የሚለውን ብይን ለማሰማት የሰጠውን የህዳር ቀጠሮ ኢመደበኛ በሆነ መልኩ አዛውሮ ለነገ ታህሳስ 3/2006 ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ ‹‹የሚፈረደው በኮሚቴዎች ላይ ሳይሆን በእኛ ነው! በእነሱ መታሰር ታስረናልና ችሎቱ እደህዝብ የሚፈርድብንን እንጠብቃለን›› እያለ ይገኛል፡፡

መንግስት በእፎይታው ጊዜ ሲፈጽም የቆያቸው ተግባራት ሙስሊሙ ህብተሰብ የመንግስት ፍላጎት ምን እንደሆነ ቁልጭ አድርጎ እንዲያይ ያስቻለው ሲሆን ቀጣይ የትግሉ አቅጣጫ ምን መምሰል እንዳለበትም ያመላከተ ነበር፡፡ የእፎይታው ወቅት እንቅስቃሴው እጁን አጣጥፎ ከመንግስት የሚመጣን መፍትሄ ብቻ ሲጠብቅ የነበረበት ሳይሆን ራሱንም ቆም ብሎ የገመገመበት፣ መንግስት በተገቢው መንገድ ምላሽ ባይሰጥ ቀጣይ የትግሉ አቅጣጫ ምን መሆን እንዳለበት አማራጮችን የፈተሸበት ነበር፡፡ በድምጻችን ይሰማ አማካኝነት በተደረገው የህዝብ አስተያየት ስበሰባ በርካታ ጠቃሚ አቅጣጫዎች የተጠቆሙ ሲሆን በእነዚሁ አቅጣጫዎች ላይ ሰፊና ጥልቅ ውይይቶች የተደረጉ ሲሆን የተለያዩ አማራጭ አቅጣጫዎችና ማስፈጸሚያ ስልቶችም ጭምር ተዘጋጅተው እየተጠናቀቁ ይገኛል፡፡ 

ያለጥርጥር የዚህን ህዝባዊ እንቅስቃሴ የወደፊት አቅጣጫ የሚወስኑ በርካታ ጉዳዮች አሉ፡፡ መንግስት በእፎይታው ጊዜ ከተከተለው መንገድ በተጨማሪ ነገ ታህሳስ 3 በመሪዎቻችን ላይ የሚሰጠው ብይን ደግሞ ለዚህ ትልቅ ግብዓት ይሆናል፡፡ መንግስት የእስከዛሬውን ግትር አቋሙን ገፍቶ እየቀጠለ መሆን አለመሆኑንም በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል፡፡ ሙስሊሙ ህብረተሰብም ቢሆን ኮሚቴዎቻችንን በሙሉ በነጻ ከማሰናበት ውጭ ያለን ማንኛውም ውሳኔ አይቀበልም፡፡ እንደተለመደው ኮሚቴዎቻችንን በማን አለብኝነት በቀጠሮ ማጉላላት ወይም ጥፋተኛ ብሎ መወሰን መንግስት እየተከተለ ያለውን ፀረ-ኢስላም ፖሊሲ ገፍቶ መቀጠሉን በድጋሚ የሚያረጋግጥ ተግባር ስለሚሆን ይኸው ውሳኔ እንቅስቃሴያችን የወደፊት ጉዞውን አስመልክቶ ካስቀመጣቸው አማራጭ አቅጣጫዎች የመምረጥ ሂደት ላይ ጉልህ ሚና ይኖረዋል!!!

ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!