ፍትሕ የሚያስፈልጋቸው የሕገወጥ ስደት ሰለባዎች


(ምንሊክ ሳልሳዊ)

በአሁኑ ጊዜ ሳዑዲ ዓረቢያ በስደት የነበሩ ከ100 ሺሕ በላይ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን አገራቸው ለመግባት በቅተዋል፡፡ አሁንም በርካታ ወገኖች የመሄጃ ጊዜያቸውን በማጎሪያ ጣቢያዎች ወይም በቤታቸው ሆነው እየተጠባበቁ ነው፡፡
ሰሞኑንም የሳዑዲ መንግሥት ኢትዮጵያዊያኑን ‹‹ለጊዜው ማቆያ ቦታዎቻችን ከመጠን በላይ ስለተጨናነቁና ሁላችሁንም ልናስተናግድ ስለማንችል በየቤታችሁ ሆናችሁ ድጋሚ ጥሪ እስክናደርግ ተጠባበቁ፤›› የሚል መልዕክት ‹‹ወደ አገራችን አሳፍሩን›› ለሚሉት ኢትዮጵያዊያን እያስተላለፈ ነው፡፡ በዜና ዘገባዎች ላይ የተጠቀሰው ቁጥር እነዚህን በቤታቸው ሆነው የሚጠባበቁትንም ያጠቃልል እንደሆነ ወይም እንዳልሆነ የተረጋገጠ መረጃ ማግኘት አልቻልንም፡፡
ይሁንና ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ሲታይ፣ የተጠቀሰው ቁጥር አሁንም ገና የሚቀረው ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ በቅርቡ በጅዳ አካባቢ ማረፊያ ጣቢያዎች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያዊን ቁጥር በጥቂቱ ከ20,000 በላይ እንደሆነ ተገምቷል፡፡ ከሃምሳ በሚበልጡ የተለያዩ ማጎሪያ ቤቶች ውስጥ የተሰበሰበው ሕዝብ ደግሞ ቢያንስ 20,000 ይሆናል፡፡ በየቤቱ የሳዑዲ መንግሥትን ዳግም ጥሪ የሚጠባበቀው በሪያድ፣ በጅዳ፣ በመካ፣ በደማምና በሌሎች ከተሞች የሚኖረውን ኢትዮጵያዊ ደግሞ ለመቁጠር እጅግ የሚያስቸግር ነው፡፡
ከላይ የዘረዘርኩት እንግዲህ ይተልቅም ይነስም በከተሞች አካባቢ የሚኖረው መሆኑ ነው፡፡ በሌላው በኩል ደግሞ በየበረሃው በበግ፣ በፍየልና በግመል ጥበቃ ወይም በሌሎች ሥራዎች የተሰማራውና ለመገናኛ ብዙኃን ቅርበት የሌለው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ ምን ያህል እንደሆነ ለማወቅ አይቻልም፡፡ ሁሉም ለማለት ይቻላል፤ የየመንን ድንበሮች በመከራና በስቃይ ሕይወታቸውን፣ አካላቸውን፣ ሴትነታቸውንና ሰብዓዊ ክብራቸውን እየገበሩ፣ ካንዱ ቦታ የሚቀጥለው ቦታ የሚያደርሳቸውን የኮንትሮባንድ ትራንስፖርት ገንዘብ እስኪያሟሉ ይቆዩና ወደ ሚቀጥለው መዳረሻቸው ጉዞ የሚጀምሩ እንዳሉ በደንብ ይታወቃል፡፡ በሳዑዲ እንደሚታወቀው አንድ ሰው ከየመን ከምትዋሰነው የሳዑዲ ድንበር ከተማ ጀዛን አንስቶ በቀጥታ ሪያድ ወይንም ጅዳ ለመግባት ቢያንስ 1,000 የአሜሪካ ዶላር ስለሚፈጅ፣ በድንብር ከተሞች ያለው ፍተሻም ከረር ያለ በመሆኑ ማንም ስደተኛ በድንበር ከተሞች መቆየት አይፈልግም፡፡
(ምንሊክ ሳልሳዊ)
በዋና ዋና ከተሞች የሚኖር ሌላ አጋዥ ኢትዮጵያዊ ወገን ከሌለው ሁሉም አቆራርጦ መድረስ ነው የሚፈልገው፡፡ ይህም ከድንበር ከተማዋ ጀዛን ወደ ዋና ከተሞች ለመድረስ የሚፈጀውን ገንዘብ ለማሟላት ጉዞውን እያቆራረጡ ማድረግ የግድ ይላል፡፡ ለምሳሌ ከጀዛን ሪያድ ርቀቱ ወደ 1,800 ኪሎ ሜትር ገደማ ነው፡፡ ስለዚህ በዋና ከተሞች ወጪውን የሚሸፍንለት ወገን የሌለው ስደተኛ ይህንን 1,800 ኪሎ ሜትር ለመሸፈን ቢያንስ ቢያንስ ከስምንት ወር እስከ አንድ ዓመት ይፈጅበታል፡፡ አንድ ቦታ አንድ ወር ይሠራና ባገኘው ገንዘብ የተወሰኑ መቶ ኪሎ ሜትሮችን ይቀንስና ገንዘቡ ባደረሰው ቦታ ሌላ የእረኝነት ሥራ ይጀምራል፡፡ ከዚያም እንደመጀመሪያው እያደረገና እያቆራረጠ ዋና ከተሞች ይደርሳል፡፡
ስደተኞች ዋና ከተሞችን የሚመርጡበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የተሻለ ክፍያ ፍለጋ፤ አነስተኛ ፍተሻና በርከት ያለ አቅርቦት ስላለ ነው፡፡ ለምሳሌ በጀዛን አካባቢ መንደሮች ለአንድ የጉልበት ሠራተኛ እረኛ የሚከፈለው ገንዘብ ከ100 ዶላር በታች ሲሆን፣ በሪያድ አካባቢ ደግሞ ላንድ ሙያ ለሌለው የጉልበት ሠራተኛ የሚከፈለው 500 ዶላር ይደርሳል፡፡ ታዲያ ጉዞውን ከጀዛን ከዓመት ወይም ከስድስት ወር በፊት የጀመረው ስደተኛ አሁንም መንገድ ላይ ነው ማለት ነው፡፡ እንዲያውም ባለፉት አሥራ ሁለት ወራት ባብዛኛው ለሥርዓት አልበኞች ጥቃት አብልጦ ሲጋለጥ የነበረው ስደተኛ እንዲህ ዓይነቱ ነበር፡፡ ካለፈው ዓመት አንስቶ በኢትዮጵያዊያን ላይ ሲሰነዘር የተስተዋለውና በየማኀበራዊ ድረ ገጾች ሲለቀቅ የነበረው ፎቶና ቪዲዮም ላይ የተመለከትናቸው ኢትዮጵያዊያን የመከራ ገፈት ቀማሾች እኚሁ መንገደኞች ናቸው፡፡
ምንም እንኳን በመንግሥታችን በኩል እየተደረገ ያለው ወገኖችን ወደ አገራቸው የማስገባት ጥረት የሚበረታታና የሚያስደስት ቢሆንም፣ ተደራሽነቱ አሁንም ለኔ እጅግ በጣም አጠያያቂ ነው፡፡ እንደ አገር ያሉትን ወገኖች በተቻለ መጠን ጠቅልለን እስካላወጣን ድረስ መሞታቸውን እንኳን የማናውቃቸው ኢትዮጵያዊያን ቁጥር እየጨመረ እንደሚሄድ የሚያውቀው አገር ቤት ያለው ቤተሰባቸው ብቻ ነው የሚሆነው፡፡
ለመሆኑ ይኼን ያህል ኢትዮጵያዊ ወገን በሕገወጥ መንገድ ከአገር ሲወጣ ለምን ተመልካች አልነበረም? በአፋር በረሃዎች ለግመል እረኞች የዒላማ መለማመጃ ሆኖ ሕይወቱ ያለፈውን፣ በጂቡቲ በረሃዎችና የባህር ዳርቻዎች በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ቱጃሮች ወንድና ሴት ሳይለይ ጾታዊና አካላዊ ጉዳት እየደረሰባቸው፣ የሚላስና የሚቀመስ እያጡ በረሃ ወድቀው የቀሩት፣ በሶማሊላንድ በረሃዎች እስከ ቦሳሶ ወደብ ድረስ እየተደበደቡ፣ እየተዘረፉ፣ እየተደፈሩና ክብራቸው እየተዋረደ ሕይወታቸው ያለፈው፣ ቀይ ባህር ሰጥመው ለአሳነባሪ እራት የሆነው፣ ዕድል ቀንቶአቸው የመን ደርሰው በየመን ሕገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪዎች ከባህር ጀምሮ እንደ ሽቀጥ ካንዱ አዘዋዋሪ ወደሚቀጥለው አዘዋዋሪ ሲቸበቸቡ፣ በሳዑዲ ከተሞች የሚኖር አንድ ወገን በችግር ሠርቶ ያጠራቀመውን ገንዘብ ከፍሎ አለዚያም አገር ቤት የሚኖር ቤተሰብ መሬቱን ሸጦ ወይንም አከራይቶ በሚልከው ገንዘብ ነፍሱ ያልተዋጀችለትና በሚነድ ፌስታል ተለብልቦ፣ በሚስማር ተቸነካክሮ፣ በስለት ተተልትሎ፣ በብረት በትር እንደ እባብ ተቀጥቅጦ፣ በፕላስቲክ ገመድ ደሙ እስኪቆም ድረስ ብልቱና የዘር ፍሬውን ታስሮ እየተንጠለጠለና እጆቹን የፊጥኝ ተጠፍሮ፣ በጥይት አረር አሮ፣ ያውም በገዛ ወገኖቹ ኢትዮጵያዊያን ከየመን በረሃዎች እስከ መንፊሃና ነሲም በተዘረጋው የደም ንግድ ደሙ ደመ ከልብ የሆነበትን ኢትዮጵያዊ ከቶ ማን ሊቆጥረው ይችላል? በጀማ እየተደፈሩ ሕይወታቸው ያለፈ ኢትዮጵያዊያት እህቶችንስ ማን ይቆጥራቸዋል?
መቼም አንዱን ካንዱ ማበላለጥ ቢያስቸግርም እንደ ከብት ኢትዮጵያዊያን የተቸበቸቡባቸውና የታረዱባቸው የስደተኛ ንግድ ሸሪኮች ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ማወቅ ደግሞ ሐዘኑን የከፋ ያደርገዋል፡፡ ከየመን በረሃዎች አንስቶ በሳዑዲ ዋና ዋና ከተሞች ድረስ የተዘረጋው የግፍ ንግድ ምንም እንኳን በየመናውያኑና በሳዑዲያውያኑ ቢመራም በየመን በረሃዎች ውስጥ የነበሩት ገራፊዎችና በየከተሞቹ የሚገኙት ገንዘብ አቀባባዮች ግን በሙሉ ኢትዮጵያዊያን ነበሩ፡፡
ምን ይኼ ብቻ? በኢትዮጵያ ካሉ ከተሞችና የገጠር ቀበሌዎችስ እነኚህን ተስፈኞች እየደለሉና እያባበሉ ወደ ሞት የነዷቸውስ እነማን ነበሩ? ‹‹የሌላ አገር ዜጋ ኢትዮጵያ ውስጥ በየመንደሩ ገብቶ ዜጎችን ለስደት መለመለ›› ብሎ የሚከራከር ያለ አይመስለኝም፡፡ በዚህ የምልመላ ሥራ ላይ ለመሳተፍ ደግሞ የግድ ባይሆንም የተመልማዩ ወገን አካባቢ ነዋሪ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ በአዲስ አበባ ዋና ዋና መንገዶች ለዘመናት ተለጥፈው ስናነባቸው የከረምናቸው ‹‹ወደ ዓረብ አገር በነፃ እንልካለን›› የሚሉት ማስታወቂያዎች እማኞች ናቸው፡፡
በዚህ ጹሑፌ ትኩረት ላደርግበት የፈለግኩት እነዚህን የዚህን ሁሉ ኢትዮጵያዊ ነፍስ የበሉትንና ለዚሁ ሁሉ መከራ የዳረጉትን ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ነው፡፡ እንዲያውም ከወር በፊት አዲስ አበባ ሄጄ የታዘብኩት ነገር ቢኖር፣ አንዳንድ ኤጀንሲዎች ቢሯቸውን ወደ ካርቱም ማዛወራቸውን ነው፡፡ ዜጎችን በመመርያ ወደ ካርቱም ከዚያም ወደ ዓረብ አገር ኤክስፖርት ለማድረግ!
አይግረማችሁና በሳዑዲ የዚህ የብዙዎችን ሕይወት የቀጠፈውንና ስንቶችን የአካል ጉዳተኛና የአዕምሮ በሽተኛ ያደረገው ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ገንዘብ አስተላላፊዎች፣ ሱቆቻቸውን እየዘጉና ሚኒባሶቻቸውን እያቆሙ ከነዚሁ መከረኞች ጋር ወደ አዲስ አበባ እየተሳፈሩና የመሳፈሪያ ጊዜያቸውን እየጠበቁ ነው፡፡ በየመንም ያሉት ኢትዮጵያዊያኑን ሲያሰቃዩ የነበሩት ኢትዮጵያዊያንም እንዲሁ፡፡ አገር ቤት ያሉት ደላሎችና ኤጀንሲዎች ባለ በርካታ ፎቆችና መኪኖች ባለቤት መሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡
ታዲያ እነዚህን ሁሉ ወንጀለኞች እያወቅናቸውና በመካከላችን አቅፈናቸው እየኖርን፣ ወገንን ለባርነትና እንደ መኪና መለዋለጫ አካላቸውን እየተተለተሉ በመቸብቸብ ንግድ ሀብትና ንብረት ያለማንም ከልካይ አፍርተው በእነዚህ ተበዳዮች አገር ሲንፈላሰሱ እያስተዋልን ‹‹ይኼ ነገር ገነ አይቀጥልም›› ብለን የምናስብ ከሆነ መቼም ምን እንደምንባል አላውቅም፡፡ እስኪ ለመሆኑ የትኛው ደላላ ወይም ኤጀንሲ ነው ለኮፍ ለኮፍ ሳይሆን ለተከሰተው የሕይወት መጥፋት፣ ያአካል መጉደልና ያአዕምሮ መታወክ ተመጣጣኝ ቅጣት የተቀጣና ተመጣጣኝ ካሳ የካሰ?
ተበዳዮች ደማቸውንና የሚያስመልስላቸውና በደላቸውን የበላይ አካል በጠፋ ጊዜ ራሳቸው በራሳቸው ፍትሕ ማግኘታቸውን ትናንት ወይም ዛሬ የተጀመረ ሀቅ አይደለም፡፡ ለዘመናት የኖረና አሁንም የሚኖር ነው፡፡ ዘመናችን በከሰተው በዚህ የባሪያ ፍንገላና የሰው ልጅን ለዕርድ የማቅረብ አሰቃቂ ወንጀል በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ግንኙነት ያላቸውና በዚሁ ኢሰብዓዊ ወንጀል እጃቸውን በንፁኃን ደም ያጠቡ ደላሎች፣ የሕክምና ተቋማት፣ ኤጀንሲዎች፣ በየመን የነበሩ አሰቃዮችና በሳዑዲ የነበሩና የሚገኙ ገንዘብ አስተላላፊ ግለሰቦች ከያሉበት ታድነው የሚገባቸውን ፍርድ እስካላገኙና ወደፊትም በዚህ ዓይነቱ አሰቃቂ የደም ንግድ ለመግባት ላሰቡ ሰዎች መቀጣጫ የሚሆንና በቂ ቅጣት ካልተቀጡ በቀር፣ አሁን ያየነው ዓይነት አሰቃቂ ክስተት ላለመከሰቱ ምንም ዓይነት ዋስትና የለም፡፡ እዚህ ላይ በቅርቡ አሜሪካ ውስጥ ኢትዮጵያዊቷን ልጅ እስርበው ለሞት አብቅተዋታል በሚል ወንጀል የተከሰሱት አሜሪካውያን ባልና ሚስት፣ ሦስት ሴቶችን ለዓመታት እቤቱ አግቶ የወሲብ ጥቃት ሲፈጽም ነበረ የተባለው አሜሪካዊ ላይ የተበየኑትን ብይኖች ስናስታውስ ‹‹መቼ ይሆን በኛስ አገር ተበዳይ ፍትሕ የሚያገኘው?›› ብዬ እንድጠይቅ ብቻ እገደዳለሁ፡፡
 ጸሐፊው ነዋሪነታቸው በሳዑዲ ዓረቢያ ሪያድ ከተማ  ነው፡፡ (ምንሊክ ሳልሳዊ)