“በግንባር” እና በ“ውህደት” መካከል የሚዋልለው የኢንጂነሩ ሹመትና የዶ/ሩ ሽኝት

 የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) ከተመሠረተ በኋላ ሦስተኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ሰሞኑን አካሂዷል። ፓርቲው “የቅንጅት ወራሽ” በሚል መርህ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን ሊቀመንበር በማድረግ ጉዞውን ከጀመረ በኋላ በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፏል። በ2002ቱ ሀገር አቀፍ ምርጫ ዋዜማ የቀድሞው የሕወሓት ከፍተኛ አመራርና የመከላከያ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስዬ አብርሃንና የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን በአመራር አሳትፎ ጉዞውን ቀጥሏል።
ፓርቲው ሁለቱን ታዋቂ ግለሰቦች በአመራር ደረጃ ካሳተፈ በኋላ ፓርቲው ለሁለት የመከፈል አደጋውን በመቀነስ ህልውናውን አስጠብቆ ዘልቋል። ምንም እንኳ በወቅቱ “መርህ ይከበር” ብለው በፓርቲው መጠነኛ የፕሮግራም ለውጥ ላይ ጥያቄ ያነሱ አካላት በዚህ ወቅት “ሰማያዊ” በሚል መጠሪያ ፓርቲ መመስረታቸውም የሚታይ ሐቅ ነው። በዛን ጊዜ የተቀሰቀሰው የፖለቲካ አለመግባባት አሁን በተጨባጭ ሁለት ፓርቲ እንዲኖር ማድረጉም መሬት የረገጠ እውነታ ነው።
በአንድነት የውጣ ውረድ የፖለቲካ ሂደት ውስጥ በምርጫ 2002 ዓ.ም ዋዜማ “መድረክ” መፈጠሩም ይታወቃል። አንዳንድ የአንድነት ፓርቲ አባላት መድረክ የአንድነት የጦስ ዶሮ አድርገው ያዩታል። ያም ሆኖ ኢህአዴግ 99.6 በመቶ ውጤት እንዳገኘ በገለፀበት “ምርጫ 2002” መድረክ የተሻለ ተፎካካሪ እንደነበር አይዘነጋም።
ብዙዎች “ባልተጠናቀቀ ፕሮግራም” ወደ ምርጫ ገብቷል፤ የብሔርና ሕብረብሔር በአንድ አጣምሯል፣ በመሬት ፖሊሲ፣ በፌዴራሊዝምና በሃገሪቱ ሌሎች ወሳኝ ጥያቄዎች ላይ የጋራ መግባባት አልደረሰም በማለት የሰላ ትችት ቢያቀርቡበትም ባለፉት ሁለት ዓመታት መድረክ ግን ከተራ ቅንጅት ወደ ግንባር ለማደግ ችሏል። ይሁን እንጂ መድረክ ወደ “ግንባር” ማደጉ ያላጠገባቸው በርካታዎች ናቸው።
ከሰሞኑ በአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ ከተነሱ አጀንዳዎች መካከልም የመድረክ በተለይም የፓርቲ የውህደት ጉዳይ አንዱ ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በምርጫ ዋዜማ ስለ ውህደት የማሰባቸው ጉዳይ የተለመደ ነው። በዚህ አሁን ባለንበት ጊዜም የ2007ቱ የምርጫ ዋዜማ የውህደት ድምጾች ከየአቅጣጫው እየተደመጡ ነው።
በአንድነት ጠቅላላ ጉባኤ የፓርቲው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው የበርካታ ፓርቲዎችን ስም በመጥራት “የእንዋሃድ” ጥሪ አሰምተዋል። ከሁሉም በላይ ቀደም ሲል አቶ ልደቱ አያሌው ሲመሩት የነበሩትን ኢዴፓ እና ውህደት አስፈላጊ ነው ብሎ ለማያምነው ሰማያዊ ፓርቲ ጭምር ጥሪ አድርገዋል። ይህ ጥሪ ለአንዳንዶች “እንዳያማህ ጥራው እንዳይበላህ ግፋው” ቢመስልም ኢንጂነር ግዛቸው ግን የውህደት ሃዋርያ ሆነው ቀርበዋል።
ውህደትን በተመለከተ የአንድነት ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በሦስት ወራት ውስጥ እልባት እንዲሰጠው መወሰኑም ታውቋል። አሁን በውህደት ጠረጴዛ ላይ የተቀመጡ በርካታ የውህደት ሰነዶች አሉ። የውህደት ሰነዶቹ በአፋጣኝ ተግባራዊ እንዲሆኑ “አዲሱ” የአንድነት ሊቀመንበር እጅ ላይ ወድቀዋል።
አንድነት ፓርቲ ባዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅድ መሠረት ፓርቲዎችን ማሰባሰብ አንዱ አላማው ነው። “ማሰባሰብ” የሚለው ቃል በግልፅ “ማዋሃድ” የሚለውን ባይተካም ፓርቲው የተበታተኑ ፓርቲዎችን በአንድ ላይ እንዲሆኑ ማድረጉ ጤናማ አካሄድ እንደሆነ የሚስማሙ ብዙዎች ናቸው። በዚህም መነሻ ባለፉት ወራት ውስጥ በርካታ የውህደት ጥያቄዎች ወደ አንድነት ፓርቲ እያመሩ ነው።
ከሁለት ዓመት በፊት በዲአፍሪክ ሆቴል በተካሄደው የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ “የፖለቲካ ኃይሌ ተሟጦ አልቋል” በማለት ከፖለቲካው መድረክ የተገለሉት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው ውስብስቡን የውህደት ማመልከቻ የመመርመር ታሪካዊ ኃላፊነት የወደቀባቸው ይመስላል። ኢንጂነር ግዛቸው የወጣቶች ሚና መጉላት እንዳለበት ደጋግመው ቢገልፁም፤ የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ ፓርቲው በእጃቸው ላይ እንዲወድቅ ሆኗል። አንድነት ፓርቲን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች የኢንጂነር ግዛቸውን በድጋሚ ወደ አመራር መምጣት ከተገነዘቡ በኋላ “ፓርቲው ወደ ፊት ተራመደ ወይስ ወደኋላ” ብለው እንዲጠይቁም አድርጓቸዋል። አንዳንዶች ደግሞ የኢንጂነሩን መመረጥ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ካምፕ የአመራር ንጥፈት ማሳያ አድርገውታል።
በሌላ በኩል የኢህአዴግ ፋሽን የሆነው “መተካካት” በተቃዋሚው ጎራ ውጤታማ እንዳልሆነም የሚገልፁ አልጠፉም። በተመሳሳይ መንገድ የእነ አቶ አዲሱ ለገሰን ወደ አመራር መመለስ በማየት በገዢውም ሆነ በተቃዋሚ ጎራ “መተካካት” ሳይሆን በስልጣን “መመላለስ” አድርገው የተገነዘቡም ይመስላል።
የሀገሪቱን ፖለቲካ በትውልድ መነፅር የሚለኩ ወገኖች ዛሬም ቢሆን “የ60ዎቹ ትውልድ” የሀገሪቱን የፖለቲካና ኢኮኖሚ ተቆጣጥሯል የሚል ቅሬታ እየተደመጠ ነው። አንድነትም ቢሆን የወጣት አመራር በማጣቱና በመቸገሩ በኢንጂነር ግዛቸው ስር መጠለሉን እንደመረጠና አማራጭም እንዳጣ በመግለፅ በማሳያነት የሚያቀርቡ አሉ።
በሌላ በኩል አንድነት ፓርቲ ኢንጂነር ግዛቸውን በሊቀመንበርነት ቢመረጡም ፓርቲውን በበላይነት በሚመራው የስራ አስፈፃሚ አባላት (ካቢኔ) መካከል 60 በመቶ ወጣቶች እንዲሆኑ መወሰኑ አሁንም የአንድነት ፓርቲ በወጣቶች የሚመራ ፓርቲ ነው ወደሚል ስሜት የሚያደሉ ወገኖች እንዲበራከቱ መንገድ ጠርጓል።
በአጠቃላይ ፓርቲው በወጣቶች ከመመራቱም ጋር በተያያዘ “ቅንጅትና ግንባር” እያሉ ትግሉን ከማስታመም ባለፈ የተበታተነውን የፓርቲዎች ኃይል በውህደት አማካኝነት ለማሰባሰብ ከፍተኛ ወኔ የተንፀባረቀበት ጉባዔ ነበር።
ይሁን እንጂ የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ግን የውህደት ሂደት ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ከጉባኤው በኋላ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደተናገሩት በአንድነት ፓርቲ የሁለት ዓመት የሊቀመንበርነት ዘመናቸው አልሰራሁም ብለው ከሚቆጫቸው ጉዳዮች መካከል የመድረክና የአንድነት ግንኙነት አለመጠናከር አንዱ ነው። ዶ/ር ነጋሶ በፓርቲው የአመራር ዘመናቸው መድረክ ወደ “ግንባር” ማደጉ ተስፋ የሰጣቸውና ተገቢም የፖለቲካ እርምጃ እንደነበር ይገልፃሉ። ውህደቱ ግን ገና ነው።
በአንፃሩ የሰሞኑ የአንድነት ጉባኤን ተከትሎ ለፓርቲዎቹ የተደረገው የውህደት ጥሪ በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ያለው ጥሪ ቢሆንም ከተቀመጠው ጊዜና ካሉት አስቸጋሪ ሁኔታዎች አንፃር ተግባራዊነቱ ላይ ጥርጣሬ እንዳላቸው ነው ዶ/ር ነጋሶ የገለፁት። አዲሱ የአንድነት ሊቀመንበር ኢዴፓን ጨምሮ ለሁሉም ፓርቲዎች የውህደት ጥሪ ያስተላለፉበት መነሻ “ጊዜ አጠፋን” ከሚል ስሜት እንደሆነ የሚጠቅሱት ዶ/ር ነጋሶ “የእኔ አቋም ከአራቱ የፓርቲዎች የትብብር አይነቶች “ውህደት” የሚለው ላይ ጥያቄ አለኝ። በተለይ የመድረክና የአንድነት ግንኙነት ላይ ለጊዜው የሚያዋጣው መድረክ “ግንባር” ነው ብለዋል።
“ከፓርቲዎች ጋር የተለያዩ ሕብረቶች መፍጠር ይቻላል። በተለይም በምርጫ በሰብአዊ መብት፣ በሕግ የበላይነት ትብብር መፍጠር ያስኬዳል። ከዚህ አለፍ ሲሉ ጠንካራ መዋቅራዊ ግንኙነት በማድረግ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን እንደ ኢህአዴግ ግንባር ፈጥረው መሄድ ይችላሉ። ይህንን ደረጃ ካለፉ ደግሞ ወደ ውህደት ይሄዳሉ” ብለዋል።
ከዚህ አንፃር ባለፉት ሁለት ዓመታት የእሳቸው አመራር በሁለት መንገድ ውጤታማ እንዳልነበረ አምነዋል። አንደኛውና ዋነኛው የመድረክ/አንድነት ግንኙነት ላይ ከልብ ሆኖ ያለመስራት ችግር ነው። በዚህ ረገድ አንድነት ጨምሮ የመድረክ አባል ፓርቲዎች በተናጠል ከራሳቸው ፕሮግራም ባለፈ የጋራ ፕሮግራም ለሆነው የመድረክ ፕሮግራም በኩል ጠንካራ ስራ አልተሰራም ብለዋል። ከዚህ አኳያ ብዙ ጭቅጭቆች ስለነበሩ ውጤታማ እንዳልሆኑም ገልፀዋል።
በዶ/ር ነጋሶ እምነት የመድረክና የአንድነት ፕሮግራምን በማስፈፀም በኩል መንታ ኀሳብ መኖሩ ውጤማ እንዳይኮን መሰናክል መፍጠሩን ነው የገለፁት፤ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱን የሚወስደው “የእገሌ ድርጅት ነው” ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ ነው የሚገልፁት። “በአንዳንድ ድርጅቶች አንድነትን ጨምሮ የጋራውን ፕሮግራም በአግባቡ አልተሰራም። ሌሎቹም በዚያው መጠን የመድረክ ፕሮግራም በቆራጥነት አላስፈፀሙም” ብለዋል።
በሁለተኛ ደረጃ ውጤታማ ያልሆኑበት የስራ አፈፃፀም ፓርቲው ባዘጋጀው የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ሰነድ መሠረት በህዝብ ግንኙነት በኩል በርካታ ስራዎች ቢሰሩም የምርጫ ማኒፌስቶ በማዘጋጀት በኩል ብዙ ርቀት አለመኬዱን እንዲሁም በስትራቴጂክ እቅዱ መሠረት ሻዶ ካቢኔ እና ፓርላማ እናቋቁማለን የሚል እቅድ ብንይዝም አልተሳካልንም ብለዋል። በውጤት ረገድ ፓርቲው አዲስ እይታ እንዲኖረው በማድረግና “የሚሊዮኖች ድምፅ ለነፃነት” የሚለው የሕዝብ ንቅናቄ አርኪ ተግባር እንደሆነም ሳይገልፁ አላለፉም።
የአንድነትና መድረክ ግንኙነት በተመለከተም በስልጣን ዘመናቸው ግንኙነቱ በሙሉ ልብ ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ያልተቆጠበ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበር ገልፀዋል። በፓርቲውም ውስጥ ከመድረክ ጋር በገባነው የቃል ኪዳን ውል መሠረት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ሲወተውቱ ቢቆዩም በኢንጂነር ግዛቸው በኩል ጉልህ ሆኖ የወጣው “ግንባር አንፈልግም” የሚለው ጉዳይ የእሳቸው ውትወታ የተሳካ እንዳልነበር፣ የጠቆመ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
“እኔ ወደ አንድነት የመጣሁት በመድረክ ምክንያት ነው። አንድነት መድረክ ውስጥ ስገባ ፕሮግራሙ ከተስማማኝ በአንድነት በኩል መድረክን ለማገልገል ነው። አሁን ግን ኢንጂነር ግዛቸው ውህደት ብለዋል። በእኔ እምነት ቃል በገባነው መሠረት መድረክ በግንባር ካልቀጠለ እኔ ከአንድነት ጋር የለሁም” የሚሉት ዶ/ር ነጋሶ የ“ግንባር” አደረጃጀት በአሁኑ ወቅት ለሁሉም ፓርቲዎች ጠቃሚ ነው። ውህደት በችኮላ ሳይሆን በሂደት የሚመጣ ነው ብለዋል።
ሌላው ዶ/ር ነጋሶ የአንድነት ፓርቲ ሆነው በተመረጡት ወቅት “አንድነት ፓርቲን ወደ ኦሮምያ ክልል ያሰርፃሉ” የሚለው አስተያየት በመጀመሪያ በአስተያየቱ እንደማይስማሙ የገለፁት ዶ/ር ነጋሶ፤ እሳቸው ሲሰሩ የነበሩት በሁሉም ክልሎች እንደነበር አስረድተዋል። በእሳቸው የአመራር ቆይታም እሳቸው የኦሮሞ ተወላጅ ስለሆኑ ወደ አንድነት አመራር የመጡት የኦሮሞን ሕዝብ ለመሳብ ነው የሚለው አመለካከት የተሳሳተ ነው ብለዋል።
በእሳቸው የአመራር ዘመን ከገዢው ፓርቲ ጋር ድርድር አለመደረጉን በተመለከተም የሚያስቆጫቸው ጉዳይ እንዳለ ዶ/ር ነጋሶ ተጠይቀው፤ የኢህአዴግ አቋም አስቸጋሪ መሆኑን፣ የፖለቲካ ተፈጥሮአዊ ባህሪ መወያየት ቢሆንም የውይይት በሩ መዘጋቱ እንደሚያሳዝናቸው ገልፀዋል። “እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ፓርቲ መነጋገር መርሃችን ነበር። ጭብጨባ የሚያምረው በሁለት እጅ ነው። በአንድ እጅ ማጨብጨብ አይቻልም። አሁንም ሆነ ወደፊት በዚህች ሀገር ዴሞክራሲያዊ ሂደት እንዲጎለብት የውይይት መድረክ ክፍት መሆን አለበት። ይሁን እንጂ ኢህአዴግ ለድርድር ዝግጁ አለመሆኑ ያሳዝናል። ይህንንም በተመለከተ አንድ ሰው ሊቀመንበር ስለሆነ ብቻ አያሳካውም። ጥረቱ የጋራ ስለሆነ ኢህአዴግ ድርድርን ባለመቀበሉ ባዝንም በግሌ ግን የሚቆጨኝ የለም” ብለዋል።
በመጨረሻም በመድረክና በአንድነት መካከል ያለው ግንኙነት “ግንባር” የማይሆን ከሆነና እሳቸው ከአንድነት ጋር የሚለያዩ ከሆነ ያሳለፉት ጊዜ እንደባከነ ይቆጠር ይሆን ወይ? ለሚለው ጥያቄም “የሚቆጨኝ ነገር የለም። ጉዳዩ የትግል ጉዳይ ነው። ህሊናን የማይነካ፣ በመርህ ጉዳይና በእምነት ጉዳይ ልዩነት እስከሌለ አብሮ መስራት ይቻላል። የእምነትና ህሊናን የሚነኩ ጉዳዮች ከተቻለ ለማሳመን ካልሆነ በሰላም መለያየት ነው። ይህንን በምልበት ጊዜ ለምን “ውህደት” የሚል አቋም ያዙ ብዬ ሰዎችን መውቀስ አልፈልግም። በተፈጥሮዬም የሰዎችን አቋም አከብራለሁ። የራሴን አመለካከት ለማስረፅ የምሄደውን ርቀት ያህል የሌሎችን አቋም አልጋፋም” ሲሉ ዶ/ር ነጋሶ መልሰዋል።
    እንደሚጠበቀው ከአንድነት ፓርቲ ጋር የኀሳብ ልዩነት ከተፈጠረ ቀሪው ህይወታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል የተጠየቁት ዶ/ር ነጋሶ በማናቸውም ጉዳይ ላይ እስከህይወት ፍፃሜአቸው ኀሳባቸውን በመስጠት፣ በሀገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲጎለብትና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትና ማኅበራዊ ፍትህ ላይ በማናቸውም መልኩ ድምፄን እያሰማሁ እቀጥላለሁ ብለዋል። “ነገር ግን በአንድ ፓርቲ ፕሮግራም ወይም ሕገ-ደንብ ተግባር ውስጥ ገብቼ የፓርቲ ፖለቲካን ለማራመድ ፍላጎት የለኝም። በቀጣይም ሁሉም ፓርቲዎች ሁሉን በሚያይ ዓይን እቀጥላለሁ” ሲሉ አጠቃለዋል።