ሃራባና ቆቦ ሆኖ የትግል ጥሪ ማቅረብ ህዝብን መሃል ሰፋሪ አድርጎ ለወያኔ ሴራ መንገድ ይከፍታል::


 


ወይ ተባበሩ አሊያም ተሰባበሩ ======= አንድ እንጨት ብቻውን አይነድም!!!

ምንልክ  ሳልሳዊ :- ይህ አባባል ከቀድሞው ጊዜ ጀምሮ ተቃዋሚ ናቸው ለሚባሉ ዚግዛግ ድርጅቶች እና ግለሰቦች አየር በአየር በጥቅም ላይ የዋለች ጥቅስ አይሏት ምክር; አረፍተ ነገር አይሏት የፖለቲካ ምቀኝነት እኔም ዛሬ አነሳኋት:: እንዲህ አይሏት እንዲህ ..ያልኩት ይህን ስትነግራቸው ተቃዋሚ ነን ባዮች ጆሮዋቸው ለመስማት ያዳግተዋል:: ወይ ተባበሩ ወይ ተሰባበሩ እያልናቸው እስካሁን ባረጀ ፖለቲካ ሊታገሉ እና ሊያታግሉ የሚዳዳቸውን እነ በየነ ጴጥሮስን አይመለከትም :: ለምን ያመጡት ወይንም የፈየዱት ነገር የለምና ተሰባብረው ቁጭ ብለዋል::ስለዚ መልካሙን እየተመኙ ሳይጃጁ የፖለቲካ ፈውስ እንዲያገኙ እንጸልይላቸዋለን ወደ ሌኒን ::

አዎ ይህች እስከዛሬ ምንነቷ ያለየላት ቃላት ለመጠቀም የፈለኩት እየተዋወቁ ወደ ወያኔ ያሾሉትን ጥርሳቸውን እርስ በእርስ እንዳይነካከሱበት ለፈራሁላቸው ለአንድነት እና ለሰማያዊ ፓርቲ ነው:: ትንሽ አንድነት ፓርቲ አዛውንቶቹ ፖለቲካውን እያወላገዱት ቢሆንም ወጣቶቹ መልካም ጅማሮ አላቸው ድጋፋችንን እየሰጠን ሲሆን ሰማያዊ ፓርቲም ገና በፖለቲካ ምድጃ ላይ ከመጣዱ ጉዞውን በመልካም እየሄደ ያለ ነበልባል ሰራዊታችን በመሆኑ ሁለቱንም እናከብራለን::

አንድነት እና ሰማያዊ ፓርቲ ወቅታዊውን ሁኔታ አገናዝበው በጋራ የሚሰሩበት ጊዜ መሆኑን ለመናገር እወዳለሁ:: እንደእኔ ተዋሃዱ ወይንም ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ሳይሆን ለመናገር የወደድኩት በአሁን ሰኣት በሁለቱም ፓርቲዎች የተጀመረው የነጻነት እንቅስቃሴ በአንድ ወጥ በሆነ መልኩ በጋራ መካሄድ አለበት የሚል ምክራዊ አቋም አለኝ:: በዚህን ወቅት የጋራ የሆነ አገራዊ የነጻነት አጀንዳ ተይዞ ትግሉ መለኮስ አለበት:: ገና ሊለኮስ ክብሪቱ እና ማንደጃው ከነማገዶው የተዘጋጀውን የሃገር ቤት ትግል በጋራ ሆኖ ለኳኩሶ ማንደድ ግዴታ አለባችሁ:: ይህ ህዝብም አንድ አድርጎ የሚያቀናጀው መሪ ድርጅት ነው እንጂ ያጣው ሌላ ወኔ አላጣም:: መድረክ እያለ ራሱን የካበው ያረጁ የፈጁ ፖለቲከኞችን በጉያው የሚያባብለው ፓርቲ በመንገድ ግንባታ ሰበብ ወያኔ ከጨዋታው ውጪ አድርጎታል::

ውዶቼ ሰማያዊ ፓርቲ እና አንድነት ይህንን ለየብቻ ጎራ እየተለየ የሚሰራው የፖለቲካ ግራ መጋባት በህዝቡ ላይ እንዳይፈጥር በጋራ ሆናቹ ተነጋግራችሁ በጋራ ህዝብን ምሩት ካልሆነ የናንተ ሃራባና ቆቦ ሆኖ የትግል ጥሪ ማቅረብ ተባባሪውን ህዝብ መሃል ሰፋሪ አድርጎ ለወያኔ ሴራ መንገድ ይከፍታል:: ለየብቻ የምታደርጉት ጥረት መንገድ ቢይዝም አይሳካም አንድነት ሃይል ስለሆነ በጀመራችሁት ትግል ላይ አንድ ሁኑ::ራሳችንን ነጻ የምናወጣው እና የሃገራችንን እጣ ፋንታ የምንወስነው እናንተ ስትስማሙ የህዝብ ድምጽ የሚስተጋባው እናንተ በጋራ ስትሰሩ ሲሆን አንድ እንጨት ብቻውን ስለማይነድ እባካችሁ በነጻነት ጥያቄው ላይ ተባበሩ ,መርሃ ግብራችሁን ሳይሆን ህዝቡን አንድ አድርጉት:: ካልሆነ የፖለቲካ መደናበር ስለሚፈጠር ትሰባበራላችሁ::