ኢህአዴግና ደርግ የፈጠሯቸው አስደንጋጭ ስብዕናዎች


የደርግን ዘመነ ግዛት ከእልቂትና ከጭፍጨፋ፣ከሰቆቃና ዋይታ ነጥሎ ማየት እጅጉን ከባድ ነው፡፡የኢህአዴግን የማጠልሸት ዘመቻንም ልብ ይሏል፡፡በ20ኛው ክ/ዘመን ውስጥ እንደ ሐይማኖት ብቅ ያለው ኮምዩኒዝም በሶቭየት ዩኒየን፣በቻይና፣በኢንዶቻይና እና በተለያዩ የአፍሪካ አገራት ከአንድ መቶ ሐያ ሚሊዬን ህዝብ በላይ ጨፍጭፏል፡፡ የመንግስቱ ኃ/ማርያም መንግስትም አገራችን አንድ ትውልድ እንድታጣ አድርጓል፡፡ የደርግ ዘመንን ዛሬ ላይ ሆኘ ሳስበው ከጭፍጨፋውና ከዋይታው በላይ ደርግ የፈጠረው ስብዕና ኢትዮጵያን ላትቃና ተስፋዋን ዘልሶባታል እላለሁ፡፡ደርግ በወኔው የላሸቀ፣ለውጥን ከአፈሙዝ ለይቶ የማያይ፤ ስለ ፍትህ መጮህን በነጭ ሽብር ሒሳብ አስልቶ የቀይ ሽብርን አፀፋዊ ድምር ውጤት በህሌናው የሚየሰላስል፣ወኔው የተሰለበ ትውልድ በመፍጠር ለተረኛው ባለ ቀምበር ደርግ የማነቆን ሚና ተጫውቶለታል፡፡እናም ደርግ የተሸማቀቀ፣ ፓለቲካን፣መብት መጠየቅን አብዝቶ የሚፈራ የፍርሐት ዛር በኢትዮጵያውያን ላይ ተክሎ ህዝቦቹን ለወያኔ አሳልፎ ሰጥቶ በመሸሽ የፍርሐት አብዮቱን እራሱ መንግሰቱ ኃ/ማርያም ጀመረውና ሐበሻ የአሉላ፣የበላይ፣የቴዎድሮስ የባልቻ ሳፎ የትላንት ወኔው፣ ጀግንነቱ ከድቶት በአባቶቹ ጀግንነት እራሱን እያሰላ በፍርሐት ድባብ መኖሩ እውነት ሆኗል፡፡
ሌላው ደርግ ፈጥሮት የነበረውና ዛሬም ድረስ የዘለቀው ስብዕና “አብዬት ጠባቂነት” ነው፡፡ቀደምት አባቶች እንኳንስ የአበሻ ሰው ወንዝ ያፈራላቸውን ይቅርና የውጭ አገር እንግዳቸውን እንኳን አሳልፈው አይሰጡም ነበር፡፡ድህነት የጎዳው ስነ-ልቦናቸውን ሊፈተታን የሚችል የረብጣ ብር ስጦታ እንኳን ቢሆን ለእውነታቸውና ለእምነታቸው የሚሰውም ነበሩ (ማንዴላን በገንዘብ እንዲገድሉ ተጠይቀው አሻፈረኝ ያሉትን ጀግና ያስቡ)፡፡ይህ ያማረ ማንነት ግን ደርግ በዘራው የክህደት ዘር ከምድረ ኢትዮጵያ ላይመለስ እንደጉም ተንኖ ጠፍቷል፡፡ ደርግ አበሻን እፍኝ በማትሞላ ሲሳይ፣እንደ ውሻ በአጥንት እያስሰየ አበሻ እርስ በእርሱ ይባላ ዘንድ “አብዮት ጠባቂነት” የተሰኘ ተውሳክ አውርሶታል፡፡ የቀበሌ ሙገሳን አሳቦ የጎረቢቱን ልጅ በቀይ ሽብር ሽፋን ያስደፋውን፣ ከአስራ ሰባት አመት ላልዘለለ ሹመት የእህት የወንድሙን፣የአብሮ አደግ እድርተኛውን ልጅ በደርግ አብዬት ያስበላውን፣ ከአንደበቱ በታች ላላሰረገው የሶሻሊዝም ኮምዩኒዝም ርዕዬት ፅንሰሐሳብ ሲል የአበሻን እናቶች ቅስም የሰበረውን…እዳ! ተወኝ እባክህ! ሁሉንም ቤት ይቁጠረው!! ከዚህ የባሰ ውድቀት ምን አለ? በእፍኝ ስንዴ ወገንን አፍር ከማስቃም በላይ ከቶ ዝቅጠትስ ይገኝ ይሆን? ሆዱ ከቂጣና ሽሮ ያልዘለለ ወጣትን በጥይት አሳርሮ የጥይት ዋጋ ከመጠየቅ የዘለለ ግፍስ ከቶ ከየት ይገኝ ይሆን? እንጃ!! በእርግጥ የኮሚንዩዝም ስሪቱ ከሰው ደም ይሆን? የዚህ ፅሁፍ ኣላማ ደርግ የሰራውን ግፍ መዘከር አይደለም ከዚሁ ጋር የሚገናኝ ገጠመኝን ማካፈል እንጅ!!
አቢዮት አደባባይ የሚገኘውን “የቀይሽብር ሰማዕታት” ለመጎብኘት አስበው ገና ሲገቡ ጀምሮ “ሞት ሞት” ወደ ሚሸተው አዳራሽ ገብተው የአገርዎን ቅሌት እየጎበኙ ነው እንበል፡፡መቼም እዚያ አዳራሽ ገብተው ከጎበኙ ትላንትናና ዛሬ ይደባለቅበዎታል፡፡ደርግ ይጠቀምባቸው የነበሩ የማሰቃያ መሳሪያዎች የሴቶችን ጡት ያጣብቁበት የነበረው ጉጠት፣ ወፌላላ የተባለው ገልብጦ መግረፊያ፣ የእግርና እጅ ጥፍር መንቀያ ሜንጦ… የቀረ የለም “ደርግ ግፍ ሲፈፅምባቸው የነበሩ መሳሪያዎች” ተብለው ተሰድረውልዎታል፡፡ ቅሉ በምስል ቀይ ሽብር ሰማዕታት አዳራሽ በአካል ግን ማዕከላዊ በተባለው ቦታ! አሁንም መሳሪያዎቹ ስራ ባይፈቱም!! ብቻ ትላንትን ከዛሬ ለመለየት እየሞከሩና አልሆንልዎት እያለ ብቻዎትን ለመግባት የሚፈሩበት ክፍል ከፊት ለፊትዎ በደርግ አቢዮት ጠባቂዎች ተረሽነው አፅማቸው የተጠራቀመበት ክፍል አስፈሪና ለአይን ያዝ የሚያደርግ ጨለማ ክፍል ያገኛሉ፡፡ ወደ ውስጥ ዘልቆ ለመግባት ከፍርሐተዎ ጋር መታገልዎ አልቀረም… ግዴልም ይቅርብዎት! የሆነውን እኔ ራሴ እነግርዎታለሁ፡፡ አንዲት የሥራ ባልደረባዬ ከባለቤቷ ጋር በመጎብኘት ላይ ሳለች ወደ አስፈሪው ክፍል የባለቤቷን እጅ ይዛ ስትገባ ሁለት “በህይዎት ያሉ” ወጣቶች ተመለከተች ዙርያቸውን በአፅም ተከበዋል፤ ጥርሳቸው ያገጠጠ፣ ፀጉራቸው ከነጩ የራስ ቅላቸው ላይ የጨገሰ የራስ ቅሎች ከስራቸው የተሰባበሩ የክንድ፣የጎን አጥንት፣ የጉልበት አጥንቶቻቸውን አድርገው “እንዴት የተገደልን ይመስልሻል?” ፣ “እኛ የተሰዋነው ለዚህ ነበር?” ፣ “ህዝባችን የጠማውን ፍትህ ጠጥቶ ይሆን?” ፣” በእውኑ ደመ ከልብ ሆነን ቀርን ማለት ነው?”፣ ” በአፅማችንም ትነግዱብን ጀመር?”… የመሳሰሉ አናት የሚበረቅሱ ጥያቄዎችን የሚሰነዝሩ ይመስል ፀጥ-ረጭ ብለው አፋጠው በሚታዘቡበት ክፍል ኢህአዴግ የፈጠረው ስብዕና ግን ይህን ሁሉ አጽም ረግጦ፣ ሞትን ንቆ ምናልባትም እዚያ ለቅርስ የተቀመጡት አፅሞች ብሔራቸውን ተመልክተው እንደሁ አይታወቅም የኢህአዴግ ውጤት የሁኑት ወጣቶች ግን አፍ ለአፍ ተጣብቀው እየተሳሳሙ ነበር፡፡አዎ! ይህ ልቦለድ አይደለም አውነተኛ አጋጣሚ እንጅ! ባልደረባዬ ከአፅሙ ይልቅ በወጣቶቹ መዘኗን ነግራኛለች፡፡
በግፍ የተገደሉት ሰማዕቶች ለፍትህ ትጮህ ዘንዳ ወኔ ይሰንቁልሃል! “ ግን ለምን?” ብለህ አራስህን እንድትጠይቅ ጉልበት ይሆኑሃል! እናማ ሞተው እንኳን የህዝብን አደራ ያስታውሱሃል! ደርግ እለታቸውን ቢቀማቸውም ዛሬም ስለ ፍትህ ይጮሃሉ! እነዚህኞቹ ግን የኢህአዴግ ስብዕናዎች ግን ከከንፈር ያለፈ ሳይኖሩ ይሞታሉ፡፡ስለ ከንፈር እያለመ በፍርሃትና በንቅዘት ውስጥ የሚኖር፣ ቆሞ የማይፈይድ ሞቶም ወግ ሆኖ እንጅ የማያቆጭ ስብዕና ኢህአዴግ ፈጥሯል፡፡ በእርግጥ ይህ ስብዕና አንድ ሙሉ ትውልድን ባይወክልም የዚህ ትውልድ ናሙና መሆኑ ግን አሌ አይባልም፡፡ይህ አጋጣሚ ልቦናውን ለከንፈርና፣ለሱስ፣ለጭፈራና ዳንኪራ ያተጋው፤ለእውነትና ለቁም ነገር ግን ያዳተው ትውልድ ማሳያ ነው፡፡ ከዚህ ጀርባ ደግሞ በአንድ ወገን ፓለቲካን ሞት፣መብት መጠየቅን ድንቁርናና ቂልነት አልፎም “የአደጋ ቀጠና” ነው ብሎ እንዲያስብ የፍርሃት ዘር የዘሩት የደርግ አመራሮችና የኢህአዴግ ትውልድ ገዳይ “ዳንኪረኛ!” ባለስልጣኖች የረቀቀ ስርዓት ውጤት ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ “ዋልጌነትና ዳንኪራን፣ጭፈራና እልቆቢስ ሱስን” ለአዲሱ ትውልድ የሚመጥን “ስልጣኔያዊ ገፀ-በረከት” ያደረገው የኢህአዴግ “የዴሞክራሲ” ለምድን ያጠለቀ “አስተኝቶ የመጋለብ” ፓለቲካ ውጤት ነው፡፡ እሺ ነገስ? ምን ይሻላል? ወገን መተኛት ዝንብ አያስቀዋም ብላችሁ ነው? አበቃሁ፡፡
 
ልጅ ተይሚያህ አል-ሐበሽይ Miniliksalsaw.iblogspot.com