ኢትዮጵያ : ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣቸውን ይፈትሹ፤ድክመታቸው ሲነገራቸው ለጥንካሬያቸው ስለሚበጅ በእጅጉ ያስቡበት፡፡

 
በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡
ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንፈልጋለን ስንል አንዱ መገለጫው የተለያዩ ሐሳቦች የሚንሸራሸሩበት ሥርዓት እውን ማድረግ ነው፡፡ ለአገር የሚጠቅም የተሻለ ሐሳብ አለን የሚሉ ኃይሎች የሚሰባሰቡበትና የሚደራጁበት የፖለቲካ ፓርቲ መፍጠርና ሥልጣን ለመያዝ መወዳደር መብት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሥርዓት እውን ማድረግ ማለት ነው፡፡
ስለሆነም የፖለቲካ ፓርቲዎች መኖር ለአንድ አገር ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆን ወሳኝ ነው፡፡ ሐሳቦች እርስ በርስ ይወዳደራሉ፤ ይታገላሉ፡፡ ሕዝቡም የተሻለውን ሐሳብ ይመርጣል፡፡ በሕዝብ ድምፅ የተመረጠውም አገሪቱን እንዲመራ ኃላፊነት ይሰጠዋል ማለት ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ሕዝብም፣ መንግሥትም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሥነ ሐሳብ ደረጃ ልዩነት የላቸውም፡፡ ሕዝብ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ኖረው ይወዳደሩ ብሎ ያምናል፡፡

በተግባር ግን የጠንካራ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ትግል፣ ፉክክርና ውድድር ማየት አልቻልንም፡፡ ጠንካራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆነው ጠንካራ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በተግባር በኢትዮጵያ እውን መሆን አልቻለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ መሆን ያልቻልነው ገዥው ፓርቲ እንዳንጠናከር ስላደረገን ነው የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ይህንን በተመለከተ ተቃዋሚዎች እንዳይጠናከሩ ከውስጣዊ ሰርጎ ገብነት ጀምሮ እስከ አደባባይ አፈና እና እስር እንግልት ይፈጽምባቸዋል ይህ የማይካድ ሃቅ ነው።፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠናከሩበት ምክንያት በራሳቸው ድክመት፣ ጉድለትና የብቃት ማነስ ነው ማለትም ይቻላል ፡ ከማንም በፊት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ላለመኖሩ ተጠያቂ የምናደርገው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ራሳቸውን ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ፣ ግልጽና፣ ይፋ የሆነ አማራጭ ሐሳብ ለሕዝብ አላቀረቡም፡፡ ጠንካራ ሐሳብ አለመኖር ብቻ ሳይሆን ጠንካራ አደረጃጀትና ጠንካራ እንቅስቀሴም አያሳዩም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙና እንዲከበሩ አማራጭ ሐሳብ ማቅረብ አለባቸው፡፡

ገዥው ፓርቲ ትክክልም ይሁንለት ስህተት ለእያንዳንዱ ጉዳይ በፖለቲካ መስመር፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ዘርፎች ዕቅዶች አሉት፡፡ ግብርናን፣ ኢንዱስትሪን፣ ትራስፖርትን፣ ዲፕሎማሲን፣ መገናኛ ብዙኅንን፣ ምርጫን፣ ዲሞክራሲን፣ ልማትን፣ ወዘተ እንዲህ አደርጋለሁ፤ ዕቅዴን እንዲህ እፈጽመዋለሁ፤ በዚህ ዓመት ይህ ይከናወናል ብሎ በግልጽ አቅርቧል፡፡የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የለም እኛ ሥልጣን ብንይዝ በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በፕሬስ፣ በዲሞክራሲ፣ በዲፕሎማሲ፣ ወዘተ እንዲህ እናደርጋለን፤ ይህንን ፖሊሲ እንከተላለን፤ አፈጻጸሙም እንዲህ ይሆናል፤ ውጤቱም እንዲህ እንዲሆን እንታገላለን ማለት ነበረባቸው፡፡

ስለዚህ አንዱና ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት አማራጭ ሐሳብ፣ አማራጭ ፕሮግራምና አማራጭ ስትራቴጂ በግልጽ ለሕዝቡ አለማቅረባቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ድክመታቸው አማራጭ አደረጃጀትና የእንቅስቃሴ ጥንካሬ አለማሳየታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ምን ያህል ይሆናሉ? ለመሆኑ ዓመታዊ ጉባዔ ያካሂዳሉ ወይ? ለመሆኑ በፓርቲያቸው ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫና ግምገማ ይካሄዳል ወይ? የውስጥ ኦዲት ይደረጋል ወይ? ግልጽነት አለ ወይ? ፓርቲውን ሁሌም የሚመራው አንድ ዓይነት ኃይል ነው? ወዘተ የሚለው መታየት አለበት፡፡

ሌላው ትልቁ ድክመት ይህ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው ጥንካሬ አይታይም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሕይወት አይንፀባረቅም፡፡ ይህ የሚያሳየን አማራጭ ሐሳብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ ሐሳብ ተይዞም ወደ ድርጅታዊ እንቅስቃሴና ጥንካሬ ካልተቀየረ በሲዲና በወረቀት ብቻ ማሳየት አቅም አለመኖሩን ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ጥንካሬ ሲባል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን በግራም በቀኝም ሲያይ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለማያገኝ፣ ኢሕአዴግን የሚተካ ኃይል ይኖራል ብሎ መተማመን አልቻለም፡፡ ምን ተቃዋሚ አለና እያለ ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላ ወገን ሳያሳብቡ መጀመሪያ ውስጣቸውን ይፈትሹ፤ ድክመታቸውን ይመኑ፡፡ ብቁ ተቃዋሚ ለመሆን ይጣሩ፡፡ ድክመታቸው ሲነገራቸው ለጥንካሬያቸው ስለሚበጅ በእጅጉ ያስቡበት፡፡ የብቁ ተቃዋሚ የጥበብ መጀመሪያም አማራጭ ሐሳብና አማራጭ ጥንካሬ ለሕዝብ ማቅረብ ነው፡፡