በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌዴሬሽን (ESFNA) ላይ የተጋረጠው አደጋ


በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌዴሬሽን Ethiopian Sports Federation in North America (ESFNA) 
ላይ የተጋረጠው አደጋ

እንደሚታወቀው እስከ ዛሬ 3 ዓመት ድረስ የሼህ አላሙዲን የቀኝ እጅ በሆነው በአብነት ገ/መስቀል መሪነት የተወሰኑ ግለሰቦች ፌዴሬሽኑን በገንዘብ ሃይል ለመቆጣጠር ያደረጉት የተቀነባበረ እንቅስቃሴ በጠንካራ ኢትዮጵያውያን ከሽፎ እና እነሱም የእኛ ገንዘብ ካልተጨመረበት ፌዴሬሽኑ መክሰሩ አይቀርም በማለት ተንጋግተው ሌላ ፌዴሬሽን ለመመስረት መሄዳቸው ይታወሳል::
ይህንን ኢትዮጵያውያንን አንገት የማስደፋት ሴራ በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የነገሮችን አካሄድ ተመልክተው ወልደው አሳድገው ለጉልምስና ያበቁትን ፌዴሬሽን ለመታደግ እና እንዲሁም ጥንካሬውን ለማየት ከፌዴሬሽኑ ጎነ በመቆም በ2012 በዳላስ፣ በ2013 በሜሪላንድ ሁለት የተሳካ ውድድር በማኪያሄድ አክሽፈውታል;; በሌላ ጎን የቆሙት ደግሞ የህዝብ ፍርድ ደርሶባቸው ባዶ ስቲዲየም ታቅፈው እንደቀሩ አይተናል::
አዲስ ፌዴሬሽን በማቌቌም በህዝብ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የማይቻል መሆኑን የተረዱት የሁልጊዜም የፌዴሬሽኑ ተጻራሪዎች አማራጭ ብለው ያሰቡትን ሁለተኛ እቅድ ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ ከጀመሩ አንድ አመት አልፏቸዋል:: ይሄ ካልተቆጣጠርነው እናፈርሰዋለን ወይም እንዳይሰራ እናደርገዋለን የሚለውን ወያኔያዊ አካሄድ ለዚሁ ስራ አድብተው እንዲቀመጡ ባደረጓቸው እንዲሁም ከጊዜ በሁዋላ በመለመሏቸው የተወሰኑ የፌዴሬሽኑ የቡድን ተወካዮች እና በየቡድኖች ውስጥ በተሰገሰጉ ተላላኪዎች አማካኝነት አንገታቸውን ብቅ አድርገው በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛሉ:: በተለይም ያለፈው አመት የሜሪላንድ ውድድር እንዳይሳካ
በስቴድየም ፣በሆቴልና በተለያዩ ዝግጅቶ ች ላይ የሞከሩት የማሰናከል ጥረት ፌዴፌሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ተስፋዬ እና በሌሎች ጠንካራ የስራ አስፈጻሚና የቦርድ አባላት ድካም ከሽፏል::
ሁሉም ኢትዮጵያዊያን እንደሚያውቁት እኛ የማንመራው ወይም የማንቆጣጠረው ምንም አይነት ማህበራዊ እንቅስቃሴ አይኖርም፤ ብሎ የሚያምነው በኢትዮጵያ ስልጣን ላይ የተቆናጠጠው ቡድን እንደባለፈው ሁሉ በፌዴሬሽኑ ውስጥ በግልጽ ይህንን ለማድረግ ቢቸገረም ያዋጣኛል ባለው ስውር መንገድ መሞከሩ አልቀረም:: ይሄንንም በሐይማኖት ተቋማት፣ኮሚኒቲዎችና በሌሎች የኢትዮጵያውያን ማህበራት ላይ ከዚህ በፊትም ያየነው፣ አሁንም ተጠናክሮ እያየነው የሚገኝ ተግባር ነው:: ለዚህም ነው ለሴራቸው መሰናክል ብለው ያሰቧቸውን እነዚህን ጠንካራና የማይገዙ መሪዎች ለማስወገድ የተቀነባበረ ሙከራ ለድርጊቱ በተባበራቸው ሚዲያ አማካኝነት ማፋፋም የጀመሩት::
የነገሩን አመጣጥ ቀድመው በተረዱ ቁርጠኞች እስካሁን ይህንን አካሄድ ለመመከት ተችሏል:: የአሁኑ ስጋት ከበፊቱ የሚለየው ውሻ ራሱ ነክሶ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው የዛሬዎቹ ተላላኪዎች በነጻ ሃገር እየኖሩ ራሳቸው ለአምባገነን ስርአት በትጋት እየሰሩ የፌዴሬሽኑን አመራሮች አምባገነኖች ብለው መክሰሳቸው ነው:: በሌላ በኩል ሃላፊነት የሚሰማቸው የፌዴሬሽኑ አመራሮች በተቻለ መጠን በአደባባይ ከሚደረግ እሰጣ ገባ ተቆጥበው ነገሮችን በጥንቃቄና በአስተዋይነት ሲያስተናግዱ ቆይተዋል:: ሆኖም ግን እነዚህ ጨዋታታሪና ታማኝ ኢትዮጵያውያን ካለምንም ክፍያ ጊዜና ገንዘባቸውን ሰውተው ወገናቸውን በማገልገላቸው የሚደርስባቸውን ውርጅብኝ ለፌዴሬሽኑ ሰላም እና አንድነት ሲሉ በዝምታ ለማሳለፍ መርጠዋል:: በተለይ በፕሬዝዳንቱ አቶ ጌታቸው ተስፋዬና ቤተሰባቸው ላይ የደረሰውን ለማስረጃ ማስቀመጥ ይቻላል:: ይሄ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የሚሳሱለት ፌዴሬሽን ከፊቱ ጠላቶች ተጋርጠውበታል:: እነዚህ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ ያላቸው የወያኔ ኢህአዴግና የአላሙዲ_ አብነት ጥምረት ይሄንን ፌዴሬሽን ለማዳከም የሚደረጉ ሴራዎች በሙሉ ከእነዚህ ከሁለቱ ሀይሎች የሚሰነዘር ለመሆኑ ማንም ከህጻንንነት እድሜ ላለፈ ኢትዮጵያዊ ለመረዳት የሚያዳግት አይደለም ::
ለዚህ ም ጥቃት በመሳሪያነት በማገልገል ላይ የሚገኙት ከዚህ የሚከተሉትን ቡድኖች በመወከል በቦርድ አባልነት የሚገኙት ናቸው:: ቶሮንቶ፣ካልጋሪ፣ሲያትል ዳሽን፣ሎሳንጀለስ ስታር፣ሳንዲያጎ፣አትላንታ፣ዋሽንግተን ዲሲ ስታር፣ ዲሲ ዩኒቲ ሚነሶታና ኦሃዮ:: ከነዚህ ቡድን ተወካዮች የተወሰኑት የእኛ ነው ላሉትና ለማገልገል ቆርጠው ለተነሱበት የፖለቲካ ድርጅት/ ወያኔ/ ቀን ከሌሊት በትጋት ሲሰሩ የተቀሩት ደግሞ በተለያየ ጥቅም ተገዝተው ወይም በኢትዮጵያ ባፈሰሱት ንብረት እስረኛ ሆነው የማደናቀፍ ድርጊት ተሳትፈው ይገኛሉ ::
ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ESFNA ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ የሚታወቁ ቡድኖች በየጊዜው ፌዴሬሽኑ ላይ ለሚደርሰው ጥቃት መሳሪያ በመሆን ማገልገላቸው ነው፡፡ በሸዊት ወ/ሚካኤል የሚዘወረው ዋሽንግተን ዲሲ ከዚህ በፊትም በእያያ አረጋና ሰብስቤ አሰፋ ጊዜ የፌዴሬሽኑ የጎን ውጋት ሆኖ እንደቆየው ዛሬም ከዚያ በማይለይ መልኩ ፌዴሬሽኑን ለማመስ እይሰራ ይገኛል፡፡ የአላሙዲን ሰዎች የተሰገሰጉበት ሎሳንጀለስ ስታርም በተደጋጋሚ እንደታየው ውስጡን ሳያጠራ ፌዴሬሽኑን ለመጉዳት መሳሪያ ሆኖ ቀጥሏል::
ጥሪ ለተጫዋቾች፡ለቡድን አባላትና ደጋፊዎች
የወያኔ አላሙዲንን ፌዴሬሽን አንቀላቀልም ብላችሁ ከፌዴሬሽኑ ጎን የቆማችሁ በሙሉ በዳላሰና በሜሪላንድ ሊደግፋችሁ የመጣውን ህዝብ በማሰብ ዛሬ በመሃላችሁ ተሰግስገው ተሳስተው ሊያሳስቷችሁ ደፋ ቀና የሚሉ ጥቂት አውቆ አጥፊ ግለሰቦችን በቃችሁ የምትሉበት ጊዜ አሁን ነው:: እናንተ ሳታውቁት ሳንሆዜ አንሄድም ከሚል ጀምሮ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨትና ሌሎችንም ጎጂ ተግባራት የሚፈጸሙትን የቡድን ተወካዮች የሚከተሉትን አደገኛ አዝማሚያ በመመከት እንዲሁም ማን ከማን ጎን እንደቆመ በንቃት በመከታተል እነኝህን የወያኔ ተላላኪዎች አስወግዳችሁ በምትካቸው ለፌዴሬሽኑ አንድነት የሚሰሩ በስነምግባራቸው የተመሰከረላቸውን ሀቀኛ ኢትዮጵያንን በመወከል ይህንን ሴራ ማክሸፍ ይጠበቅባችሁዋል፡፡ ይህን በብዙ ልፋትና ጥረት እዚህ የደረሰውን በዘር በሃይማኖት እና በሌላው ሁሉ መልኩ ሊከፋፍሉት የሚሞክሩትን ህዝብ አንድ አድርጎ ኢትዮጵያዊነትን አጉልቶ የሚያሳየውን ፌዴሬሽናችንን እንታደግ፡፡ በዜጎቻችን ስቃይ ትርፍ ለማግኘት የሚሩሯሯጡትንና ድንበር ተሻግረው ባህር አቋርጠው ፌዴሬሽኑንና አመታዊ ውድድራችንን የፕሮፖጋንዳቸው መንዣ ሊያደርጉት ያቀነባበሩትን ሴራ ተባብረን እንመክት፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የዚህ ተንኮል መሳሪያ የሆናችሁ ግለሰቦች ከዚህ ድርጊታችሁ ልትታረሙ ይገባል፡፡ ይህንን ማሳሰቢያ በመናቅ ለጨቋኞች መሳሪያ ለመሆን መርጣችሁ የምትንቀሳቀሱ ግን የህዝብ ፍርድ አንደሚከተላችሁ እርግጠኛ መሆን ይገባችኋል፡፡ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የስም ዝርዝራችሁን ይፋ በማውጣት ፌዴሬሽኑን ሊደርስበት ከሚችል አደጋ የመጠበቀ ሃላፊነትን መወጣት ግድ መሆኑን ልትገነዘቡ ይገባል፡፡
በመጨረሻም የዚህን ጽሁፍ መውጣት ተከትሎ እነዚህ የወያኔ ወዳጆች በከፍተኛ ሁኔታ መንጫጫታቸው አይቀርም፡፡ ሆኖም ግን በነዚህ እኩዮች ሳንደናገርና ግራ የማጋባት ሙከራቸውን ቸል በማለት ያለፉትን ሁለት ዝግጅቶች እንዲሳካ ካደረጉት የፌዴሬሽኑ ቁርጠኛ መሪዎች ጎን እንቁም። የሳንሆዜው ውድድር እንዳይሳካ ከፍተኛ የቅስቀሳና የአሻጥር ስራ በወያኔ ወኪሎች እየተሰራ መሆኑን ግምት ውስጥ በማስገባት የሰሜን አሜሪካ ኢትዮጵያውያን እንዳለፉት አመታት ሁሉ ወደ ሳንሆዜ በመጉረፍ ውውድሩን የተሳካ በማድረግ አጋርነታችንን ልናሳይ ይገባል::ኢትዮጵያ ሪቪው