ዜጎችን ሊታደጉ የማይችሉ የሃይማኖት መሪዎች ሊወገዱ ይገባል።


ዜጎችን መታደግ የማይችሉ በአስቸኳይ ቆባቸውን አውልቀው ከተራው ሕዝብ የመቀላቀል ግዴታ አለባቸው።
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)

ቤተክርስቲያን እና መንግስት በኢትዮጵያ ውስጥ እጅና ጓንት ሆነው በኢትዮጵያውያን ላይ የማያባራ ጭቆና ማካሄድ ከጀመሩ ረዥም ዘመናት ተቆጥረዋል። ይብልጡኑ የመንግስቶች ጎህ ከቀደደ ጀምሮ በተለይ የተዋህዶ ሃይማኖት መሪዎች  አስፈሪ እና አስደንጋጭ እንዲሁም አሳዛኝ ደግሞም አሳፋሪ ቃላቶችን በመጠቀም ስጋዊ እና ምድራዊ ስልጣኖችን ለገዢዎች ለማደላደል ይህ ነው የማይባል ግፍ በምእመናኖቻቸው እን በሌሎች አማኞች ላይ ፈጽመዋል አስፈጽመዋል፤ እየፈጸሙ ነው፤ እያስፈጸሙ ነው። ይህ የማይዋጥለት አሊያም የሚክድ ካለ እውነት የማይደላው ብቻ ነው።

የኢትዮጵያ ጨቋኝ መንግስታት የሆኑ ከጥንት እስከ ዛሬ የተንሰራፉ በህዝብ ላይ የሚያደርጉት ጭቆና እና በደል ታሪክ የማይሽረው ጠባሳ በሰው ልጆች የትውልድ ሂደት ላይ መፍጠሩ እንደተጠበቀ ሆኖ የሃይማኖቶች ሚና ግን እጅግ በሚያሳዝን መልኩ ዜጎች በግፍ በጨቋኝ መንግስቶች ሲታረዱ በመባረክ የመንግስታቱን እድሜ አስረዝመዋል አሁንም እያስረዘሙ ነው። የመንግስት እና የሃይማኖት ቁርኝት የሚፈለገው ስልጣንን አደላድሎ ለመያዝ እና ህዝብን ረግጦ ለመግዛት ካለ ምኞት እንጅ ለዜጎች ከመቆርቆር የመነጨ አይደለም። የሃይማኖት አባቶች በሃይማኖታዊ የመንፈስ ጥኡም ሰበካና ዜማ ጋር በማጣፈጥ የጨቋኞችን የበላይነት በመስበክ ማስፈራራት እና ማሸማቀቅ የጳጳሳት እና የሼህዎች አብይ ተግባር ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ተገዝተው አሊያም አድርባይ ሆነው  በመስራት ላይ ያሉ የሁሉም ሃይማኖት መሪዎች እጅግ ጥንቃቄ በጎደለው ሁኔታ በዜጎች ላይ የሚደርሱ ግድያዎች ድብደባዎች እስሮች እና መንገላታቶችን እንደ አንድ መንፈሳዊ የሃይማኖት መሪ እንደ ሰብአዊ ተፈጥሮ አሊያም መጽሃፋቸው እንደሚያዛቸው ለዚጎች ሲደራደሩ ሲከራከሩ ሲዋያዩ ሲሆንም አንተም ተው አንተም ተው ሲሉ አልታዩም ከዚህ በከፋ መልኩ በልማታዊ ዲሞክራሲ የፖለቲካ ፉጨት ስር ተደብቀው በለው በሚል አብዮታዊ ዜማ ዜጎችን እያስፈጁ ይገኛሉ።

አንድ የሃይማኖት አባት የታመመ ሲጠይቅ፤ የሞተ ሲቀብር ፤የተቸገር ሲረዳ ፤የታሰረ ዞሮ በመጎብኘት ሲያጽናና እንጂ ሲፖተልክ አሊያም ሲወሸክት ማየት ያማል። በሃገራችን ምእመናንን እንምራለን የሚሉ ሕዝብን መንፈስ እንመግባለን የሚሉ የለሊት ወፍ የሆኑ የክርስትና እና እስልምና የሃይማኖት መሪዎች ዜጎችን መታደግ የማይችሉ ከሆነ በአስቸኳይ ቆባቸውን አውልቀው ከተራው ሕዝብ መቀላቀል ግዴታ አለባቸው። ይህ ጉዳይ የብዙሃኑ የዜጎች ጉዳይ ስለሆነ ክርስቲያን እስላም የሚባልበት ሳይሆን የኢትዮጵያውያን የጋራ ጉዳይ ነው።በሃገሪቱ ዜጎች በአለም ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በነጻነት በመጻፋቸው የእኩልነት እና የነጻነት ጥይቄ በማንሳታቸው ብቻ አሸባሪ ተብለው እስር ቤት በታጎሩባት ኢትዮጵያ ጉዳዩን እስኪ ላስጠናው ላጥናው ያለ የሃይማኖት መሪም ይሁን የሃይማኖት ሃራጥቃ የለም። እንዲሁም በታሰሩ ሰዎች እና በአሳሪዎች መካከል እርቀ ሰላም እንዲወርድ ለወደፊቱ ስህተቶች ካሉ እንዳይደገሙ ነገሮችን ለማግባባት እና ለማቻቻል የፈቀደ አንድም የሃይማኖት መሪ የለም። ይብስኑ የሃይማኖት መሪዎቹ በየስብሰባው እና በየጭብጨባው ዜጎች የመንግስታዊ ሽብር ዱላ ሰለባ እንዲሆኑ እያበረታቱ ይገኛሉ ።

የዜጎች ሁኔታ ያሳሰባቸው የሃይማኖት መሪዎች በከፍተኛ ዛቻ እና ማስፈራራት እንዲሁም በጥቅም በማሰር እንዳይንቀሳቀሱ አሊያም በተዘዋዋሪ ባልሰሩት ወንጀል ለማጥመድ ሴራ በመጎንጎን እያስፈራሩ የህዝቦችን የሰብ አዊ መብት ጥያቄዎች እንዳያነሱ በማስደንገጥ እንዲሁም በጥቅማ ጥቅም እና በገንዘብ በመደለል አባትነታቸውን ለስጋዊ ባለስልጣናት እንዲሸጡ እና የፖለቲካ ምንዝር እንዲፍጽሙ እየተደረገ ሲገኝ ይህንን የምንዝር ጌጥ ከመለማመዳቸው የመጣ የሃይማኖት አባቶች ከጨቋኞች ብሰው በሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደል እንዲፈስም ከባዱን ሚና እየተቻውቱ ይገኛሉ ።

የሃይማኖት አባቶች ሰጥ ለጥ ብለው ስለልማት ብቻ እንዲሰብኩ የእስላሙንም ሆነ የክርስቲያኑን ጥያቄዎች በተገኙበት እንድያስተጋቡ ማስጠንቀቂያ ከተሰጣቸው አባቶች መካከል አቡነ ማትያስ አቡነ ሉቃስ እና ሌሎችም ተጠቃሾች ናቸው እንዲሁም የወያኔ መንግስት በቅርቡ ለሾማቸው የእስልምና ምክር ቢት ሼሆችን ከፍተኛ የሆነ ምክር አዘል ማስጠንቀቂያ አስተላልፏል። እኔ ስጨፈጭፍ እናንተ አጨብጭቡ የሚለው አሸባሪው የወያኒ መንግስት ሃይማኖቶችን በራሱ አይዲኦሎጂ በመቀጽ ቀሚሳቸውን ያንዥረገጉ ሰላዮችን እና የሃይማኖት ነቅእዞችን በመመደብ ዜጎችን በተመለከተ የሚደርሱ በደሎች እና ገፈፋዎች ጠያቂ እንዳያገኙ አስታራቂ እንዳይሹ አድርጓል። ፓትርያርኩ ተንገላተው ከተለቀቁ በኋላ በማህበራዊ ድህረገጾች ላይ ብዕራቸው ለምን ታቀበ? ከፋሲካ ክብረ በአል በኋላ በትዊተር ላይ እንዳልተገኙ የሚነገርላቸው ፓትርያርኩ ራሳቸውን ከማንኛውም አንደፋዳፊ ንግግር በመቆጠብ በተረጋጋ መልኩ አንገታቸውን እንዲሰብሩ እና በቅርባቸው ለተመደቡላቸው የመንግስት ደህንነቶች /አማካሪዎች ተገዢ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ዜጎቹን የማይታደግ የሃይማኖት መሪ ቆቡን አውልቆ ከፖለቲካው ጎላ ልኢቀላቀል አሊያም ገለልተኛ ሰው ሆኖ እንዲቀመጥ ለመምከር እንፈልጋለን ። በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ሃይምኖቶች ለመንግስታዊ ሽብር ተገዢ እና ታዛዥ እንዲሁም የሽብር ሰባኪ ሆነው ዜጎችን በአደባባይ እያስግደሉ ዜጎች ከሞቱ በኋላ በሃይማኖታቸው ስር አት እና ደንብ እንዳይቀበሩ ተጽእኖ በማድረግ ለምድራዊው የጨቋኝ ምደብ ተባባሪ እና አስተባባሪ በመሆን ከባድ ወንጀል እየፈጸሙ ይገኛሉ። ስለዚህ በዜጎች ላይ የሚደርሱ በደሎች የማይቆረቁራቸው የሃይማኖት አባቶች ሊወገዱ ይገባል።

ማሳሰቢያ ፦ በዛሬው እለት በኦርቶዶክስ በእስልምና በካቶሊክ እና ከመካነ እየሱስ ቤተክርስቲያን የተዘዋወረው የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ቡድን ያሰባሰበውን ጉድ የያዘ መረጃ በቅርቡ በይፋ እናወጣዋለን ይጠብቁን።