ሕዝብን በማስቀደምና በማሳተፍ ካልተንቀሳቀሱ አደጋ አለ፡፡

አገራችን ጥቂቶች የዝሆን ጥርስ ማማ ላይ የሚቀመጡባት፣ብዙሃን መንገድ ላይ የሚያኩባት አገር እየሆነች ነው፡፡
Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)
አገራችን ጠንካራ ተቃዋሚ ያስፈልጋታል፡፡ ሕዝብ አማራጭ ይፈልጋል፡፡ ተቃዋሚዎች ግን አማራጭ ማቅረብም መሆንም አልቻሉም፡፡ የኢኮኖሚ ራዕይ የለም፡፡ የፖለቲካ ራዕይ የለም፡፡ በኪሳቸው ወይም በሆዳቸው አለ ይሉን ይሆናል፡፡ ለሕዝብ በአደባባይ ጠረጴዛ ላይ የተቀመጠ ራዕይ ግን የለም፡፡ ችግሮች አጋጠሙ ሲባል በእነሱ ዙሪያ መጮህ ብቻ ነው የሚታየው፣ የሚደመጠው፡፡ በጉዳዮች ላይ ዜናን እየተከታተሉ መግለጫ ማውጣት እንጂ ራዕይ ይዞ ፖለቲካው እንዲህ መሆን አለበት ሲባል አይሰማም፡፡ ኢኮኖሚው እንዲህ መደረግ አለበት የሚል ራዕይ አይታይም፡፡ አደረጃጀትም እምነትም የለም፡፡ በውጭ ያሉ ተቃዋሚዎች እንቅስቃሴያቸው በሙሉ አሳፋሪና አሳዛኝ ሆኗል፡፡ፖለቲካን የትርፍ ጊዜ ማትረፍያ ስራ እንጂ የሙሉ ጊዜ ሕዝባዊ መቆርቆሪያነት ተደርጎ እየተሰራበት አይደለም ። ተቃዋሚዎች የሙሉ ጊዜ ፖለቲከኛ ያስፈልጋቸዋል። በሕዝብ መሃል ዘልቆ መንቀሳቀስ ደሞ ሌላው ስራ ነው፡፤ ገዢውን ፓርቲ ድባቅ ለመምታት ጠንካራ መዋቅር በሕዝብ ውስጥ መገንባት አስፈላጊ ነው።

በአጠቃላይ ሲታይ ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አሳሳቢና አስጊ ስለሆነ ደጋፊው ጤነኛ ተቃዋሚው አሸባሪ የሚለው መንግሥት አሊያም ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎች ችግሩን ዓይተው መፍትሔ ካላስቀመጡ፣ አገርንና የሀገራችን አንድ ዋና ችግር የ"ፍትሕ" መታጣትና የሙስና ቤት ደጁን ማጣበብ ነው፡፡ ገንዘብ ተበድረንም ተለቅተንም፣ ሱሪ ባንገት አስወልቀንም ሰብስበን ማን እንደሚቦጠቡጠው ሳይታወቅ ይባክናሉ፡፡ ትላንት እዚህ ግባ የማይባል ሀብት የሌለው ሰው ድንገት በአንድ ጀንበር ሚሊዮኔር ይሆናል፡፡ ወይ አልሮጠ፣ ወይ አልዘፈነ፣ ወይ አበባ አልተከለ፣ ወይ ኤክስፖርት አላረገ ወይ ነዳጅ አላወጣ…እጁን አጣጥፎ ምላሱን ዘርግፎ ድንገት ወርቅ በወርቅ መሆን አስገራሚ ነው!! አገራችን ጥቂቶች የዝሆን ጥርስ ማማ ላይ የሚቀመጡባት፣ ብዙሃን መንገድ ላይ የሚያኩባት አገር እየሆነች ነው፡፡

ከበረሃ እስከ ከተማ ተሞተላት፣ ተሰዋባት የተባለችው አገርና ይመጣል የተባለው ለውጥ አምርተን አምርተን ኑሮ ውድነት ላይ የምናርፍ ከሆነ፣ ተምረን ተምረን ሥራ አጥነት ጥላ ሥር የምንጠለል ከሆነ፣ በብሔረሰብ ጀምረን ሃይማኖት ውስብስብ ውስጥ የምንገባ ከሆነ፣ ከዘፋኙ ጋር “የመጣነው መንገድ ያሳዝናል” ማለት ብቻ ሳይሆን “የምንሄደው መንገድም ያሳዝናል” ልንል እንገደዳለን! ሕዝብን በማስቀደምና በማሳተፍ ካልተንቀሳቀሱ አደጋ አለ፡፡