የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር እጦት ወያኔ የያዘውን ስልጣን ላለመነጠቅ የሚሰራው ፖለቲካዊ ደባ

Minilik Salsawi

ለዘላቂ ልማት እንሰራለን በሚል ስርኣት ውስጥ የመሰረታዊ የዲሞክራሲ መብቶች በጊዜያዊነት መኖር እና እንደመነገጃ መጠቀም ህዝብን አገለግላለሁ ሳይሆን አጭበረብራለሁ እንደማለት ይቆጠራል:: የወያኔ ስርኣት ባለስልጣናት በፍርሃት ተውጠው በጠበንጃ ሃይል በሚኖሩባት በዚች ኢትዮጵያችን የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ አሁንም እጅግ መልስ የሚያሻቸው ጉዳዮች ናቸው::ዜጎች በሃገራቸው እንዳይኮሩ በመኖር ደህንነታቸው ላይ ጥርጣሬ እንዲያሳድሩ እየተደረገ ስለሆነ ይህ ደሞ ወያኔ የያዘውን ስልጣን ላለመነጠቅ የሚሰራው ፖለቲካዊ ደባ ውጤት መሆኑ እሙን ነው::
ፍትህን እና መልካም አስተዳደርን ወደ እውነት ያመጡ ህጎች በኢትዮጵያ አሉ የሚለው ወያኔ ህዝቦች ግን በተግባር ተጠቃሚ ሲሆኑ አላየንም::ህጎቹ በተግባር ይዋሉ ይህንን ህጎች በመመሪያ በደብዳቤ እና በስልክ የሚቀይሩ የሚደፈጥጡ በጥቅም የሚሸጡ የሚረጋግጡ የሚለውጡ ከየወንበራቸው ተሽቀንጥረው ይጣሉ:: የቀን ተቀን የፍትህ እና የመልካም አስተዳደር ሂደት ውስጥ እጃቸውን እያጠለቁ ፍትህን የሚያዛቡ አስተዳደራዊ በደሎችን የሚፈጽሙ ባለስልጣናት የህዝብን ማህበራዊ ህይወቶች ከማፋለሳቸውም በላይ ከቀድሞው በባሰ መልኩ ፖለቲካው እንዲጭበረበር ኢኮኖሚው እንዲደቅ ሃገር በብድር እንድትዘፈቅ ህዝብ እንዲደኽይ ከባዱን ሚና እየተጫወቱ ነው::
ህዝቦች ህግ እየጸደ ህግ እየተሽሞነሞነ እና እየተብለጨለጨ ቢቀመጥ ምንም የሚጠቅማቸው ነገር እንደሌለ መታወቅ ያለበት ሲሆ አንድ ህዝብ ባላረቀቀ ባልተወያየበት እና ባላጸደቀው ህግ እየተገዛ ፍትህን እና መልካም አስተዳደርን እንዴት ማስፈን ይቻላል??? መተማመን እና የዜግነት ኩራቱን በሚሰብሩ ባለስልጣናት እየተሰበረበት ያለ ህዝብ ፍትህን እና አስተዳደራዊ እንዲሁም አገልግሎቶችን በተግባል ለማየት እና ለመጨበጥ አልቻለም:: ለተበደለና ፍትሕ ላጣ ዜጋ፣ መልካም አስተዳደር አጥቶ ለሚንገላታ ዜጋ ፍትሕና መልካም አስተዳደር እንዲኖር በአንቀጽ ተደንግጓል እያልን ብናወራ ዋጋ የለውም::
ህዝብ ባለው ስርኣት ላይ እምነት የለውም:; ይህ ደግሞ ራሱ ስርኣቱ ያረጋገጠው ነገር ነው የስርኣቱ ታጣቂ ሃይሎች በሌሎች ወገኖቻቸው ላይ የሚያደርሱትን የሰብኣዊ መብት ጥሰት እያዩ በሃገሪቱ ህግ የለም እኔም ነገ እደበደባለሁ እታሰራለሁ ንብረቴን እነጠቃለሁ መብቴን እነፍርጋለሁ እጠቃልሁ እገደዳለሁ እሰደዳለሁ እገደላለሁ በሚል በስርኣቱ ላይ ያላቸው እምነት የተሟጠጠ ከመሆኑም በላይ ከትንሽ እስከ ትልቅ ከሃገር የመውጣት ንብረትን እና ሃብትን የማሸሽ ተግባር ላይ በመሰማራት በዜግነት አለመተማመን እንዲፈጠር በሩን በርግዶ ከፍቷል ይህ ደሞ ህጎች በተግባር ህዝብን አለማገልገላቸው እና በባለስልጣናት የመደፍጠጣቸው ውጤት ነው::
በተግባር ፍትህን እና መልካም አስተዳደርን እውን ለማድረግ በቁርጠኝነት የተነሳ ማንም የለም::ስርኣቱም በጥቅመኞች የሚመራ ህዝቡም ላላወጣው ህግ በዝምታ ደንታቢስነቱን እየገለጸ ነው; ፍትህን እና መልካም አስተዳደርን የሚጥስና የሚያደናቅፍ የስርኣቱ ባለሥልጣን፣ ዜጋም ሆነ ግለሰብ፣ በማስረጃ ሲታይና ሲረጋገጥ ዕርምጃ ለመውሰድ ሕግ ፊት ለማቅረብ ምንም አይነት የተሰራ ስራ ካለመኖሩም በላይ በባሰ መልኩ በይፋ ህጎች ሲደፈጠጡ እያየን ነው:: ባለሥልጣንም ሆነ ባለ ሀብት፣ ታዋቂም ይሁን ተራ ዜጋ፣ ከፈለገው ብሔር ብሔረሰብ ይምጣ፣ የፈለገውን ሃይማኖት የሚከተል ይሁን፣ የጾታና የዕድሜ ልዩነት ሳይኖር ተቃዋሚም ይሁን ደጋፊ ሁሉም ሕግ ፊት፣ ፍትሕ ፊት፣ መልካም አስተዳደር ፊት እኩል መሆኑን አምነን በተግባር ለማዋል ቁርጠኝነት በፍጹም የለም:: ፍትህ እና መልካም አስተዳደር እንዴት ሊረጋገጡ ይችላሉ በዚህ ሁኔታ ውስጥ እየተጓዝን ነው ጥያቄያችን ;ስለዚህ ህዝብ ለውጥ ይፈልጋል::የወደደ ይውደድ የጠላ ይጥላ እትዮጵያ ውስጥ ወያኔን ጨምሮ ሁሉም የፖለቲካ ጎራ ጥያቄው የስልጣን እና የአገዛዝ ሩጫ ነው::የእኛ የዜጎች ጥያቄ ግን ፍትህ መልካም አስተዳደር የአገልግሎት አቅርቦት እና ሰላም ነው::ይህንን ለማግኘት በጃችን ያለውን ነጻነት ለመቀዳጀት ከትግሉ ያልተቀላቀላችሁ እንድትቀላቀሉ ያስፈልጋል።