የወያኔ ካድሬዎች- በምላሱ የሚተዳደር ሰው በዕውቀት ያልተደገፈ ድፍረት፣ የህሊና ማጣት ምርኩዝ ነው፡፡

ማህታማ ጋንዲ እንግሊዝን “በመጨረሻ ባዶህን ትወጣታለህ!” ማለቱን አንርሳ፡፡  

Minilik Salsawi

ለሀገራችን ጐታቿም አጥፊዋም፣ “አሾክሿኪው” ነው፡፡ ከታሪክ መማር ዕርም በሆነባት አገር ቀለሙን እየለዋወጠ አድር - ባይ ሁሉ እየመጣ፤ “እንቅፋት በመታው ቁጥር ቲዎሪ ድረሽ” (ያውም ዕውነተኛ ቲዎሪ ካለው) እያለ፤ “መንገድ ባስቸገረው ቁጥር” መመሪያ ማሪኝ” እያለ ህሊናውን እየሸጠ ይኖራል፡፡ ልባም አይደለምና አፍ ያወጣል፡፡ ምላሱ እየረዘመ፣ አንጐሉ እየጨለመ ይሄዳል፡፡ አበው “ከመሃይም ምላስ ይሰውረን” የሚሉት ለዚህ ነው፡፡
የጌቶች አስተሳሰብ ምን እንደሚመስል ተገዢ ወዳጆች ማወቅ አለባቸው፡፡ ሎሌነቱንም በቅጥ በቅጥ አለመያዝ፣
የመጨረሻውን ቀን ከማፋጠን አያልፍም፡፡ “የምጣዱ እያለ የእንቅቡ ተንጣጣ የሚለውን ተረት፤ በአፉ የሚንጣጣ
ሁሉ በጊዜ ሊገነዘብ ይገባል፡፡ መጨረሻው፤ “ያመኑት ፈረስ፣ ይጥል በደንደስ” ነውና፡፡ “እናቴን ያገባ ሁሉም
አባቴ ነው” ለሚሉ የዋሀን ሁልጊዜ ፋሲካ ሊመስላቸው ቢችልም፤ ለሁሉም ጊዜ አለውና “ምነው ምላሴን
በቆረጠው” የሚያሰኝ የፍርድ ቀን እንደሚኖር አሌ አይባልም፡፡
“እንብላም ካላችሁ እንብላ፤ አንብላም ካላችሁ እንብላ” በሚል ጅባማ ፍልስፍና ውስጥ መበላላት መሪ መርሀ -
ግብር መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡
“ለጋማማ አህያም ጋማ አላት
አያስጥልም እንጂ ጅብ ሲዘነጥላት” ሲባል የከረመው ያለ ነገር አይደለም፡፡
“እነሆ ብዙ ዘመን አለፍን፡፡ ከሁሉም የተረፈን ብዙ ምላሶችና እጅግ ጥቂት ልቦች ናቸው” ይላል ሲ ጆርጅ
የተባለ ፀሐፊ፡፡ በሀገራችን በቅንነት ሃሳብ የሚሰጡና በሎሌነት ሃሳብ የሚሰጡ መለየት አለባቸው፡፡ “ውሸት
አለምን ዞሮ ሊጨርስ ሲቃረብ ዕውነት ገና ቦት ጫማውን እያጠለቀ ነው” መባሉ በምክን እንጂ በአቦ - ሰጡኝ
አይደለም፡፡
በየአገሩ፤ የንጉሥ አጫዋቾች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ የጋራ ባህሪ ግን አላቸው - ንጉሱ ሲያስነጥሱ
ማስነጠስ፡፡ አድር ባይነት፡፡ በመካያው ራሱ አድርባዩ ማንነቱ ይጠፋበትና “የዘሬን ብለቅ ያንዘርዝረኝ” ማለት
እንኳን ይሳነዋል፡፡ “ነገር አንጓች፤ እንኳን ለጌታው ለራሱም አይመች” ነውና ፍፃሜው አጓጉል መሆኑ ዕሙን
ነው፡፡የትዕዛዝ ሁሉ ጉልላት ለህሊና መታዘዝ ነው፡፡ ማንም ቢሆን ማን፤ ህሊናውን ሲክድ አታላይ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ ብልጥ ለማኝ፤ “ጌታዬ ጌታዬ አምና የሰጡኝን ልብስ አምስት ዓመት ለበስኩት”እያለ ይኖራል፡፡
በዕውቀት ያልተደገፈ ድፍረት፣ የህሊና ማጣት ምርኩዝ ነው፡፡” ወትሮም፤ “መራዡ ተኳሹ” ሲል
የኖረ፣ “በራዡ ከላሹ” ማለት ከጀመረ ሁለተዜ ጥፋት ነው፡፡ ሀገራችን አያሌ አድር - ባይ አይታለች፡፡
ማህታማ ጋንዲ እንግሊዝን “በመጨረሻ ባዶህን ትወጣታለህ!” ማለቱን አንርሳ፡፡ “ቅዳሴው ሲያልቅበት ቀረርቶ አከለበት” እንዲሉ በምላሱ የሚተዳደር ሰው ውሸት ማብዛቱ ግዱ ነው፡፡ ዕውቀተ-ቢስ መሠረቱ ለዕውነት ረሃብ ያጋልጠዋልና! addisadmassnews.com አዲስ አድማስ።