በገዛ ሃገራችን በአሸባሪነት የሚፈርጀንን የወንበዴ አገዛዝ ታግለን ለማስወገድ ተባብረን እንነሳ።

ወያኔ የሕዝብን ጥያቄ ከማድመጥ ይልቅ ንቆ በመተው ለማዳፈን በመሞከር በሕዝብ ተቀባይነትንና አመኔታን ወዳገኙ ግለሰቦችና ፓርቲዎች ላይ ለማመካኘት እየሞከረ ነው፡፡ 
 
Minilik Salsawi


ወገኖቻችን ለኢኮኖሚና ማሕበራዊ ችግሮች ከመጋለጥ አልፈው ከባድ አደገኛ አጣብቂኝ ውስጥ ናቸው ፡፡ ለሕዝቡና ለሀገሪቱ ጥቅም የሚቆም ብቃት ያለው አስተዳደር የለም፡፡ ህግ አለ ህገ መንግስት አለ ቢባልም ተገቢ ያልሆኑና ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጣረሱ አፋኝ አስደንጋጭ እና ኢሰብአዊ ሕጐችና ደንቦች በተከታታይ ይወጣሉ፡፡ እነኚህም ሕዝቡን በተደራራቢነት እያስጨነቁት ይገኛሉ፡፡ ህጐችና ደንቦች ሲወጡ ሕዝብ መወያየትና መምከር ሲገባው ውይይት ሳይደረግባቸው በዘፈቀደ እና ባልሰለጠኑ አስፈጻሚዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ይታያል፡፡ የወጡና የፀደቁ ሕጐች ላይም ሆነ በአፈፃፀም ላይ ችግሮች ሲፈጠሩ ማየት የሚኖርበት ፍርድ ቤት ነበር፤ነገር ግን በሚወጡ ሕጐች የፍ/ቤት ሥልጣን ተነጥቆ ለኤጀንሲዎችና ለባለስልጣናት እንዲሁም ለሌሎች ባልበሰሉ ካድሬዎች ለተሞሉ መስሪያ ቤቶች እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ ስናይ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት በሀገራችን አለ ወይ? የሚል ጥያቄን አስነስቶ አስነስቶ ከመሰላቸታችን የተነሳ በኢትዮጵያ ሕግና መንግስት እንደሌለ ደምድመናል።
የፖለቲካው ሁኔታ ደግሞ እጅግ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ነው ያለው፡፡ዜጐች ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው በመገፈፉ አቤቱታ ሲያቀርቡ የሚሰማ አስተዳደር ባለመኖሩ፤የሕዝቡ ብሶት እንዲሰማና ጥያቄያቸው መልስ እንዲያገኝ እንቅስቃሴ ሲያደርጉ “ሀገሪቱ ላይ ሁከትና ሽብር ልትፈጥሩ ነው” እየተባለ በተለይ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና አባላት፣ጋዜጠኞችና ወጣቶች እየታሰሩ ናቸው፡፡ ላለፉት 7 አመታት ብቻ እጅግ ብዙ ኢትዮጵያውያን በነጻ ሃሳባቸውን በማስተላለፋቸው ብቻ በ “ፀረ ሽብርተኝነት” ስም እየታሰሩ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወቅታዊው የሀገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ምህዳሩ ጠቦ ጠቦ አሁን ካለበት እና ግመልን ከማያሾልክ የመርፌ ቀዳዳ ላይ መድረሱ ምስክር አያስፈልገውም።
ኢህአዴግ የሕዝብን ጥያቄ መመለስ ስላልቻለ፣ በዕቅዱ መሠረት ቢያንስ ለ50 ዓመት ሀገሪቱን የመምራት ዓላማ ስለነበረው እንደማይሳካለት ሲያውቅና ከሕዝቡ አመኔታና ተቀባይነትን ስላጣ ፈርቶ የራሱን ስህተት ለመሸፈን ዳግም ስህተት እየፈፀመ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የሕዝብን ጥያቄ ከማድመጥ ይልቅ ንቆ በመተው ለማዳፈን በመሞከር በሕዝብ ተቀባይነትንና አመኔታን ወዳገኙ ግለሰቦችና ፓርቲዎች ላይ ለማመካኘት እየሞከረ ነው፡፡ በተለይ የተቃዋሚ አመራሮች እና ጋዜጠኞች ከሽብር ወንጀል ጋር ማያያዙ ከፍርሃት የመነጨ የከሰረ ፕሮፖጋንዳ ነው፡፡ከላይ በግርድፉ የተጠቀሱትን ጉዳዮች ለመፍታት የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር አንድ እና አንድ ነው ። መፍትሄው ወያኔን ከስልጣን አስወግዶ ሕዝባዊ መንግስት መመስረት አማራጭ የማይገኝለት ጉዳይ መሆኑ እሙን ስለሆነ ኢትዮጵያውያን በአጠቃላይ በአንድነት በመተባበር ይህንን የበሰበሰ አስከፊ ስርአት መንግሎ ለመጣል በሚደረገው ትግል ውስጥ በመሳተፍ የዜግነት ድርሻችንን መወጣት ይጠበቅብናል። ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬