የሚያስፈልገን ቆራጥነት ነው! ተግባር እንጂ የወሬ ነፋስ የትም፣ መቼም አይበጀንም፡፡

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) - ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ሲጮህ የማናይባት አገር ታስፈልገናለች! ራሱ ሰርቆ አፋልጉኝ ይላል እንደተባለው አይን-አውጣ ሌባ እያየን ዝም የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! የምናስባቸውንም የምንጠረጥራቸውንም ጉዳዮች ሁሉ አስቀድመን በተግባር እናረጋግጥ፡፡ በማናቸውም መልኩ በወሬ አንፈታ! ከመፎከርም ከማውራትም በተግባር ምን እናድርግ? ማለት ተመራጭ ነው!! መረጃ መስጠት እንዳለ ሁሉ አሳሳች መረጃ መስጠትም አለ፤ አስቦ መጓዝ ይሄኔ ነው!በሁሉም ወገን የወሬ ናዳ አለ፡፡ ያ ወሬ እውነትም ይሁን ውሸት ህዝቡን ይፈታዋል፡፡ 

የማይወራ ወሬ፣ የማይሰደብ ስድብ፣ የማይቀርብ ሃሳብ የለም፡፡ ችግሩ ግን ወሬ የትም አያደርሰንም፡፡ እፎይ ያሰኘናል - ከምን? ከትግል! በወሬ ወጣልና! ልክ ልካቸውን ነገራቸው! ብለን ለጥ ብለን እንተኛለና! ይሄ አንድ እርግማን ነው! በወሬ መፈታት ማለት ይሄ ነው! ተግባር እንጂ የወሬ ነፋስ የትም፣ መቼም አይበጀንም፡፡ 

ሕግ ለሁሉም እኩል የሚሰራባት አገር ታስፈልገናለች! ድካማችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ሟርት የማይበዛባት አገር ታስፈልገናለች! በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ አገር ይለወጣል ከሚል አስተሳሰብ የፀዳች አገር ታስፈልገናለች! ባንድ በኩል የራሳችንን ድምፅ ብቻ መልሰን ለማዳመጥ ዝግጁ ከሆን፣ በሌላ በኩል እኔ ያልኩትን ብቻ አዳምጡ ካልን፤ የትላንትናን ዜማ ብቻ የምንደግም ከሆነ፤...........ዲሞክራሲን፤ ፍትሐዊነትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ እውነተኛ ምርጫን፣ እኩልነትትን፣ ዲፕሎማሲን፣ ለማግኘት አያሌ አመታትን አሳልፈናል፡፡ እንደ አፍ እንደማይቀልም፣ አውቀናል፡፡ ተገንዝበናል፡፡ አንድም የራሳችንን የሽኩቻ ባህላዊ አሽክላ በቀላሉ ለመላቀቅ ባለመቻል፤ አንድም ደሞ ከውጪ የሚመጣብንን ጫና ለመመከት ባለመታደል፣ ጠንክረን ዳር የመድረስ ነገር የህልም ሩጫ ሲሆንብን ከርሟል፡፡

ደጋግመን በመሳደብ፣ ደጋግመን በማማት ምንም አላፈራን! መሬት ላይ ያለው ችግር አሁንም መሬት ላይ ነው፡፡ ደጋግመን ብናወራ፤ ደጋግመን ብንቋሰል፤ ደጋግመን እዬዬ ብንል ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! ብንገማገም፣ ስብሰባ ብናበዛ ለሀገራችን ጠብ የሚል ነገር የለም! የሚያስፈልገን ልብ ነው! የሚያስፈልገን ቆራጥነት ነው! በቆራጥነት ጉዳያችንን መወያየትና ልባም መፍትሄ መስጠት ነው፡፡