ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡

Minilik Salsawi  - አለማወቅና ስግብግብነት ሲቀናጁ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እየጣሉን እንደሆነ ማየት ተስኖናል፡፡
: የጭብጨባ ባህል! የፓርቲ አባል ያጨበጭባል፡፡ የድርጅት አባል ያጨበጭባል፡፡ የጎሣ አባል ያጨበጭባል፡፡ ጓደኛና ቲፎዞ ያጨበጭባል፡፡ የተማረው ያጨበጭባል! ያልተማረው ያጨበጭባል! አዋቂው ያጨበጭባል! አላዋቂው ያጨበጭባል! ሃይማኖተኛው ያጨበጭባል! ሃይማኖት - አልባው ያጨበጭባል! የኪነ-ጥበቡ ሰው እያጨበጨበ ጭብጨባ ይቀላውጣል!... ከዚህ የጭብጨባ ባህል ማን ይገላግለን ይሆን? ለጭብጨባም የአየር ሰዓት የሚጠየቅበት ወቅት እየመጣ ነው፡፡

ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡በየግል መድረኩ፤ በየመሸታ ቤቱ፣ በየሻይ ቤቱ፣ በየሬስቶራንቱ ወዘተ… በዕውቀት መከራከር ከቀረ ውሎ አድሯል፡፡ የተማረ የማይከበርበት፣ ያልተማረ ዘራፍ ሲል የሚደመጥበት ሁኔታ እየበረከተ የመጣበት ዘመን ነው፡፡ በመናገርና አውቆ በመናገር መካከል ልዩነቱ ከመከነ ሰንብቷል! አገሩን፤ “እኔ ምን ቸገረኝ ያባቴ ዶሮ አደለች!” ብሎ በምንግዴ የሚያየው ዜጋ በሚያስገርም ሁኔታ እንደባክቴሪያ የሚራባበት አየር እየተፈጠረ ነው፡፡ አገርን መሰረት አድርጎ ፖለቲካን፣ ኢኮኖሚን አሊያም ባህልን ማየት የተነወረበት ጊዜ እየመጣ ይመስላል፡፡ አለማወቅና ስግብግብነት ሲቀናጁ ምን ዓይነት አደጋ ላይ እየጣሉን እንደሆነ ማየት ተስኖናል፡፡

ወዳጁንም ጠላቱንም፣ አብሮ መጥረግ ነው በቀልህ??” ሊባል የሚችል ጣጣ ውስጥ እየገባን እንደሆነ ማስተዋል ደግ ነው::ካፒታሊዝም፤ “ለሰላምታም ለጭብጨባም ቫት የሚከፈልበት መሆኑን በአክብሮት እንገልፃለን” ሊያሰኘን የሚችል ምስጥም ዐይን - አውጣም ስርዓት መሆኑን አንዘንጋ፡፡ በአሁኑ ሰዓት ዕውቀት የሚያቀጭጭ ክፉ ባህል ጭበጨባ ነው! አደጋም ነው! ባመኑበትም ባላመኑበትም ማጨብጨብ፣ ባወቁትም ባላወቁትም ማጨብጨብ እርግማን ነው፡፡ ምክንያት የማይገዛው ማህበረሰብ ለገደል ቅርብ ነው ይላሉ ጸሀፍት፡፡

ከማቴሪያል ሙስና ወደ ህሊና ሙስና እየተሸጋገርን ይመስላል! የድንቁርና ሙስናና የዕውቅና ሙስና ምን ያህል እንደሚተጋገዙ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም፡፡ያገራችን ነገረ በተመለደና ባልተለወጠ ነገረ - ሥራ መጯጯህ መሆኑ ያሳዝናል! ልማዳዊ አካሄዳችን አልለወጥ የሚለው ለውጥ ስለሌለ ይሆን? ሁሉ ነገር የልማድ፣ የወግ፣ የወረት ተገዢ የሆነ መምሰሉ ይገርማል፡፡ የእገሌ ራዕይ፣ ራዕይ፣ ራዕይ … እንደጀመርን … እንደጀመርን … (አንዴ ከገባንበት ስሜት ዓይነት ጭምር)… እንዳጋመስን … እንዳጋመስን … ስንጨርስስ? … እንደጨረስን… እንጨርሰዋለን … እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ከዘፈን ወደ መፈክር መሄድ፣ ከዘፈን ወደ ዘፈን ከመሄድ የተሻለ ነው ወይ? የሚለውን ለማረጋገጥ መሞከር ብልህነት ነው፡፡