ለትግል ጽናት ቃላችንን እናጥብቅ::ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በራስ መተማመን አንድነትን ማጠንከር በጋራ መቆም ነው፡፡

ቃል ስንገባ በስሜታዊነት አይሁን! ቃል ስንገባ በአድር-ባይነት አይሁን! ቃል ስንገባ ለይስሙላ አይሁን! ቃል ስንገባ በእርግጥ አደርገዋለሁ ወይ? ብለን ከልባችን ጠይቀን፣ በአዎንታዊነት እራሳችንን አሳምነን፣ በቁርጠኝነታችን ተማምነን እንጂ እንደው በሞቅ ሞቅና በሰሞነኛ መንገኝነት ተገፋፍተን እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቃል የምንገባበትን ጉዳይ ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ደጋግመን መፈክር ስላሰገርንና፣ ደጋግመን በቃል ቃል ስለገባን ግባችንን በተግባር እንመታለን ማለት አይደለም፡፡ የምንጓዘው ዓላማችንን አንጥረንና አነጣጥረን መሆን አለበት፡፡ ተግባሩን እንጂ ተደጋጋሚ ወሬውን እንተው፡፡

ለትግል ጽናት በራስ ለመተማመን ቢያንስ በሌሎች መፈራት ሳይሆን መወደድ፣ መጠርጠር ሳይሆን መከበር፤ ይቆይብኛል ብሎ መስጋት ሳይሆን ይሄድብኛል ብሎ መጨነቅ የሚፈጥር መሪ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በራስ ለመተማመን ለሁሉም የሀገራችን ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት መፍጨርጨር ሳይሆን ሌሎች የሚሰጧቸውን አማራጮች ለማዳመጥ መትጋትም ግድ ይላል።ይህ የሚከሰተው ከአለማወቅ ወይም ግንዛቤ ከማጣት ሊሆን ይችላል፡፡የአገሪቱ አምባገነን ገዢዎች ያሉት ሁሉ ልክ ነው ከሚል የሎሌያዊነት አመለካከት ሊሆን ይችላል፡፡ ጎረቤቴ ካደረገው ልክ ቢሆን ነው ብሎ ከማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆነ ብሎ ስህተትም ቢሆን ልከተለውና ገደል ሲገባ ልየው ከሚል እኩይ ሀሳብም ሊሆን ይችላል፡፡ የድርጅትንም ኢ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ቆም ብሎ መቃኘትም ያስፈልጋል።መንገኝነት ወረተኝነት በራስ አለመተማመንን ይፈጥራል።

አላዋቂ እጅ መውደቅ እርግማን ነው፡፡ ነብሴ በእጅህ ናት ብሎ የአላዋቂ ተገዢ መሆን የከፋ መርገምት ነው፡፡ አንዱ ስላረገው ብቻ ሌላው የሚከተልበት፣ እንደ መንጋ ተከታትሎ የሚነዱበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል፡፡ ቆም ብሎ የምሄድበት መንገድ ትክክል ነወይ? ከተለመደው መንገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አጥቼ ነወይ? ማሰብ ያስፈልጋል ። እንደ መንጋ ተከታትሎ የሚነዱበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል፡፡ ለመንገኝነት አስተሳሰብ ወይም ለወረተኝነት አካሄድ ወይም እንደ አዲስ የትግል ስትራቴጂ፣ ዕቅድ፣ መመሪያ፣ ሲወጣ እንደፋሽን መከተልና ሳይመረምሩ መቀበል፣ ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ለመጠፋፋት ጊዜ የማይፈጅብን፤ ለመፋቀር ረዥም ዘመን የማይበቃን አያሌ ነን፡፡ ቀድሞም ሆነ ዛሬ እርስ በርስ፣ በፖለቲካ ድርጅትና ድርጅት ውስጥ ያለውን መናቆር፤ ትላንት ገዢዎች ያደርጉ ከነበረው ፍትጊያ ተነስቶ ማየት ቀላል ነው፡፡በኢትዮጵያ ወቅታዊ ምህዳሮች ውስጥ ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፤ በማህበራዊም መልኩ በራስ መተማመን አንድነትን ማጥበቅ በጋራ መቆም ነው፡፡ለትግል ጽናት ቃላችንን እናጥብቅ::ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በራስ መተማመን አንድነትን ማጠንከር በጋራ መቆም ነው፡፡ ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬